Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በሲሚንቶ ጉዳይ አገር እየተተረማመሰ እስከ መቼ ይቀጥላል?

የአገራችን የሲሚንቶ ገበያ ጉዳይ ዛሬም እንቆቅልሽ እንደሆነብን ነው፡፡ ከሲሚንቶ ግብይትና አጠቃላይ ገበያ ሒደቱ ከችግር ሳይፀዳ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህም የሲሚንቶ ጉዳይ የአገራችን የግብይት ሥርዓት ብልሽት አንድ ማሳያ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡

የሲሚንቶ ግብይትን ለማረጋጋት ሕጋዊ በሆነ አሠራር እዲጓዝና ግብይቱን  በአግባቡ ያስኬዳሉ የተባሉ በርካታ ውሳኔዎች ቢወሰኑም አንዱም ሊሠራ ያለመቻሉ ጉዳይ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡

የሲሚንቶ ገበያን ለማስተካከል በሚል ሲወሰዱ የነበሩት ዕርምጃዎች ከተጀመሩ ሁለት አሥርት ዓመታትን ተሻግረዋል፡፡ ምናልባትም ወደ 30 ዓመት የተጠጋ ጊዜ አለው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ሁሉ የሲሚንቶ ጉዳይ ችግር ሳይሆን የቀረበት ጊዜ የለም፡፡ በየዓመቱ የሲሚንቶ ችግርና እጥረት እንዲሁም የዋጋ መወደድ ይወራል ይመከርበታል፡፡ ‹‹አቅጣጫ ይሸጥበታል›› ይዛትበታል፡፡ ግን የተለወጠ ወይም የተጨበጠ ውጤት አላመጣም፡፡ ዛሬም ይህ የሲሚንቶ ችግር ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሷል፡፡ መፍትሔ የተባሉ ውሳኔዎች ያልሰመሩበት ቢወቅጡት እንቦጭ ሆኖ ተገልጋዮችን እያማረረ ነው፡፡ ከዛሬ ነገ መፍትሔ ይመጣል ተብሎ ቢጠበቅም መፍትሔ በመታጣቱ ዛሬ ጥቂት የማይባሉ ፕሮጀክቶች በሲሚንቶ ዕጦት ተደነቃቅፈው ቆመዋል፡፡ አንዳንዶችም ከዋጋ በላይ ገዝተው እየተጠቀሙ ኪሳራ እያሰፉ ነው፡፡ ነገር ግን ዋጋ ይወደድ እንጂ ገበያ ላይ ሲሚንቶ እንደ ልብ እየተሸጠ መሆኑን ግን መዘንጋት የለብንም፡፡ ከፋብሪካው የለም የተባለ ሲሚንቶ ዋጋው ተቆልሎ በየሲሚንቶ መሸጫ ሥፍራዎች ያለከልካይ እየተሸጠ ነው፡፡

ከፋብሪካ ከ500 ብር ባነሰ ዋጋ የሚወጣው ሲሚንቶ ገበያ ላይ 1,400 ብር የሚሸጥበት ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ባይኖርም እንደ ሕጋዊ ዋጋ ታይቶ ሲሸመት ያሳዝናል፡፡

ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የሲሚንቶ ግብይትን በተመለከተ በፌዴራል ደረጃ በተለይ በንግድና ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት በኩል ችግሩን ይፈታሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸው ውሳኔዎች አሁንም ውጤት ያልታየባቸው ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ እነዚህ ውሳኔዎች ሲወሰኑ የተሰጡት አማላይ ትንታኔዎች በሲሚንቶ ጉዳይ መፍትሔ ሊያገኝ ይችላል ብሎ ያላሰበ ጥቂት አልነበረም፡፡

በውሳኔው መሠረት ሲሚንቶ ከፋብሪካው ዋጋ ከአሥር በመቶ ያልበለጠ ጭማሪ ተደርጎበት ብቻ የሚሸጥ መሆኑ መገለጹ ደግሞ የበለጠ ተስፋ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከአሥር በመቶ ጭማሪው በላይ ሽያጭ ሲያከናውን የተገኘ አይቀጡ ቅጣት ይቀጣል የሚል ማስፈራሪያ የያዘው ነበርና ተስፋ ያደረጉ ሰዎች አይፈረድባቸውም ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን ነገሩን መሬት ላይ ስናየው የተባለው ነገር የለም፡፡ ጭራሽ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ 1,400 ብር ገብቶ አረፈው፡፡ አሁንም ከዚህ በላይ ዋጋ ቢያወጣ ጠያቂ የለም፡፡

ከሦስትና አራት ሳምንታት በፊት የኦሮሚያ ክልል በክልሉ ከሚገኙ አሥር የሲሚንቶ አምራቾች ጋር በመዋዋል ሲሚንቶ ቢቀረጥ ዋጋ እንደሚሸጥ ቢገልጽም ይህ ብዙ የተባለለት ውሳኔ በአዲስ አበባ ገበያ ላይ ሊታይ አልቻለም፡፡

በተመሳሳይ ከሁለት ሳምንት በፊት የንግድና ትስስር ሚኒስቴር የሲሚንቶ ገበያውን ያረጋጋል የተባለ አዲስ ውሳኔ መወሰኑን ቢያስቀምጥም ይህንንም ውሳኔ ሰምቶ የተገበረና ውሳውን ተከትሎ ያስፈጸመ የለም፡፡ ስለዚህ ችግሩ ቀጠለ፡፡ ሲሚንቶ ሁለት እጥፍ ትርፍ ተይዞበት ተቸበቸበ፡፡

በመሆኑም የሲሚንቶ ገበያን ለመቆጣጠር ያልተቻለበት ወይም ገበያውን ለማረጋጋት የተኬደባቸው ዕርምጃዎች ሁሉ ያለመሳካታቸው ሚስጥር ግራ ያጋባል፡፡

ይህ መላ ያጣ ጉዳይ ግን አንድ የሚነግረን እውነታ አለ፡፡ የሲሚንቶ ገበያው በአንድ ፍፁም ጉልበታም በሚባል አካል መያዙንና የሕገወጥ ግብይቱ እንዲስፋፋ ፍላጎት ያለው አካል አይነኬ የሚባል መሆኑን ነው፡፡

ካለበለዚያ ይህንን ችግር እንዴት መፍታት ያቅታል? እጥረት አለበት የሚባለውን የሲሚንቶ ምርት እንደፈለጉ እያወጡ በግልጽ ደርድረው የሚሸጡ አካላት ሲሚንቶውን ከየት አመጣችሁ? ብሎ የሚጠቅ ይጠፋል፡፡ ከተማ ውስጥስ ያለው ሕግ አስከባሪ ይህ ዓይታየውም፡፡

ከፋብሪካ 500 ብር ባልሞላ ዋጋ የወጣ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከሦስት እጥፍ በላይ ሲሸጥ እየታየ እንዴት ዝም ይባላል? ወዲህ ግን ሕጋዊ ዕርምጃ እንወስዳለን ይባላል፡፡

ስለዚህ የሲሚንቶ ጉዳይ እንዲሁ እየተተረማመሰ እስከ መቼ እንደሚቀጥል እንደሚፈለግ ግራ ያጋባል፡፡ በጥቂቶች ሸፍጥ አገር ጭምር እየተጎዳ እስከ መቼ ይቀጥላል? ያለውን ችግር ተገንዝቦ ትክክለኛ መፍትሔ ያልተበጀለትን ምክንያት ለማወቅ እንዴት ተሳነን? የሚሉት ጥያቄዎችን አሁንም እንጠይቃለን፡፡ ነገር ግን የሲሚንቶ የተጨመላለቀ አሠራር ያለበት ከፋብሪካ ጀምሮ እስከ አይነኬ ባለሥልጣናት ድረስ እጃቸውን ያስገቡበት ጉዳይ ነው ብለን ደፍረን ለመናገር የምንገደደውም በዚሁ ነው፡፡

ሕገወጥ ተግባር ሲፈጸም ማስተካከል ያልቻለ አካል በጉዳዩ እጁ እንደሌለበት እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?

ዛሬ በከተማችን ውስጥ በ1,400 ብር ደፍረው ሲሚንቶ የሚሸጡ ወገኖች ሲሚንቶውን ከየት እንዳመጡና ለምን በዚህ ዋጋ እንደሚሸጡ ጠይቆ ዕርምጃ መውሰድ የተሳነው አካል ነጋ ጠባ ቢዝት ዋጋ እንደሌለው መታወቅ ይኖርበታል፡፡

በዚህ መሀል ግን ሕዝብና አገር ድርብ ድርብርብ ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡ ሲሚንቶ እያስከፈለው ያለውን ዋጋ ስንደምረው ጉድ ሊያሰኙ የሚችሉ ብክነቶች ቢጠኑ አገር ምን ያህል እንደተበዘበዘች፣ ያለ አግባብ ምን ያህል ወጪ አወጣችሁ ያሳየን ነበር፡፡

በተያያዥነት ግን ለሕዝብ አገልግሎት ተብለው የተጀመሩ በርካታ መሠረተ ልማቶች በዚሁ ሲሚንቶ አጠረ በሚል ሰበሰብ በተደነቃቀፈ ቁጥር የሚያስከትለው ጉዳት ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ቀውስም ጭምር መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

መስተጓጎላቸው ደግሞ ሌላ ጣጣ አለው፡፡ በሲሚንቶ እጥረት የተጓተተ ፕሮጀክት ሁሉ መልሶ ሥራ ቢጀምር እንኳን የሚጠይቀው ተጨማሪ ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ጉዳቱ እንዲህ ቀላል አይሆንም፡፡  ስለዚህ መፍትሔ ለታጣለት ለዚህ ጉዳይ ምን ይደረግ ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጠን እንሻለን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት