Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለታሸገ ውኃ በዓመት ይከፈል የነበረው የ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንዲቆም ተወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የታሸገ ውኃ አምራቾች በዓመት ወጪ ያደርጉ የነበረው 100 ሚሊዮን ዶላርን የሚያስቀር ማስተርባች የተሰኘ ምርት መጠቀም እንዲያቆሙ መወሰኑን የኢትዮጵያ ውኃ፣ ለስላሳ መጠጦች፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ማኅበር ገለጸ።

የታሸገ ውኃ አምራቾች በተለይም በጥሬ ዕቃ እጥረት ለማምረት ሲቸገሩ መቆየታቸውንና ለዚህም እንደ መፍትሔ ከተወሰዱት ጉዳዮች መካከል ተጨማሪ ግብዓቶችን መጠቀም ማቆም መሆኑን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ መርዕድ ገልጸዋል።

በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ከዚህ በፊት ከ20 በላይ የታሸገ ውኃ አምራቾች መዘጋታቸው የሚታወስ ሲሆን አሁንም እነዚህ አምራቾች ወደ ምርት እንዳልተመለሱ አቶ አሸናፊ ገልጸዋል። ሌሎችም ተጨማሪ ድርጅቶች ማምረት ያቆሙ መኖራቸውን አክለዋል።

ማስተር ባች የተሰኘው የውኃ ፕላስቲክ ግብዓት በዋናነት ፕላስቲኩ ውኃ ሰማያዊ ቀለም እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት አቶ አሸናፊ ይህም በምርቱ ላይ ምንም ተጨማሪ ጥቅም የማያስገኝ በመሆኑ አምራቾቹ መጠቀም እንዲያቆሙ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. መወሰኑን ተናግረዋል። ይህም ባለፉት አንድ ዓመት ተኩል ጥናት ሲደረግበት የቆየና ከአካባቢ፣ ከጤና እና ከኢኮኖሚ አንፃር ያለው ጥቅም ግምት ውስት የገባ መሆኑን አብራርተዋል። ‹‹ከዚህ በፊት ምርቱን መጠቀም አስገዳጅ ባይሆንም፣ አምራቾች በራሳቸው ፍላጎት እየተጠቀሙ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የፕላስቲክ ውኃ አምራቾች ማስተር ባች የተባለውን ግብዓት ለማስመጣት በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያደርጉ ገልጸው ግብዓቱ ጥቅም ላይ እንዳይውል መደረጉ ከፍተኛ ወጪ የሚቆጥብ መሆኑን ገልጸዋል። አምራቾቹ ከመጪው ጥቅምት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ምርቱን ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንዲያቆሙ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ውሳኔ መተላለፉንና ጊዜው እስኪደርስ ያላቸውን ምርት ተጠቅመው እንዲጨርሱ ጊዜ እንደተጣቸው አቶ አሸናፊ አብራርተዋል።

በውኃ ፕላስቲክ ምርቶች ውስጥ እንደ ተጨማሪ ግብዓት የሚያገለግለው ማስተር ባች ጥቅም ላይ የዋሉ የውኃ ፕላስቲኮችን መልሶ ለመጠቀም እንደማያስችል ገልጸው ይህም መቅረቱ ፕላስቲኮቹን ወደ ውጭ ለመላክና ለሌሎች ምርቶች ግብዓትነት ለማዋል ይጠቅማል ብለዋል። ለምርቱ የሚወጣው ገንዘብ ሲቀንስ አሁን ካለው የፕላስቲክ ውኃ ዋጋ ላይ ቅናሽ ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች