በኦሮሚያ ክልል በወለጋ አካባቢ ባለፉት አራት ዓመታት የደረሱ ግድያዎች በርካታ ናቸው፡፡ በርካታ ዜጎች የዘር ተኮር ግድያና መፈናቀል ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም. መገባደጃ በወለጋ አካባቢ ተፈጽመዋል የተባሉና የበርካታ ዜጎችን ጭፍጨፋ ያስከተሉ አጋጣሚዎች ቢቆጠሩ የአካባቢው ቀውስ ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
በ2013 ዓ.ም. ጥቅምት ወር በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ወደ 300 ዜጎች ያለቁበት ጭፍጨፋ እጅግ ከፍተኛና አገር አቀፍ ሐዘን የፈጠረ አጋጣሚ ነበር፡፡ በመጋቢት 2013 ዓ.ም. ደግሞ ምዕራብ ወለጋ ባቦ ጋምቤል ወረዳ ከ150 በላይ ዜጎች ማለቃቸው ተነግሯል፡፡ ይህ ሁሉ በወለጋ ዞኖች በየአካባቢው ከደረሱና ከመቶ በታች ዜጎችን ግድያ ካስከተሉ በርካታ የጭፍጨፋ አጋጣሚዎች ጋር ተዳምሮ፣ በዓመቱ በዚሁ አካባቢ የደረሰውን የንፁኃን ዕልቂት ከፍተኛ እንደሚያደርገው ይገመታል፡፡
በተገባደደው 2014 ዓ.ም. ይኸው ጭፍጨፋ የቀጠለ ሲሆን፣ ዘንድሮም በርካቶች የተገደሉባቸው ሦስት አጋጣሚዎች ተከስተዋል፡፡ በጥር 2014 ዓ.ም. ቄለም ወለጋ ጊዳሚ ወረዳ ወደ 160 ዜጎች መጨፍጨፋቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በቅርቡ ሰኔ ወር መንግሥት 338 ዜጎች መጨፍጨፋቸውን ሲገልጽ በአንዳንዶች ግምት ከ1,000 በላይ ዜጎች የተጨፈጨፉበት አስደንጋጭ ክስተት በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ መድረሱ አይዘነጋም፡፡ ይህ የሐዘን ድባብ ገና ሳይበርድ ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ቄለም ወለጋ ሀዋ ገላን ወረዳ የ300 ዜጎችን ሕይወት የነጠቀ ጭፍጨፋ ተከሰተ መባሉ፣ የወለጋ አካባቢ አሳሳቢና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መውደቁን አመላካች ተደርጎ ነበር የተወሰደው፡፡
በእነዚህ አጋጣሚዎች ደርሰዋል የሚባሉ ዕልቂቶች አኃዞች ላይ መግባባት የለም፡፡ በዕልቂቱ ስያሜና ምንነት ላይም እስካሁን የሚያግባባ ነጥብ ላይ የተደረሰ አይመስልም፡፡ በዚህ መሀል ግን የወለጋ ጭፍጨፋ ክስተቱና ድግግሞሹ ሳይቋረጥ ቀጥሏል፡፡ የጭካኔው ዓይነትም አይሏል፡፡ በአካባቢው ለሚፈጸመው ጭፍጨፋ ኦነግ ሸኔ የሚባል ታጣቂ ኃይል ጥፈታኝነቱን ይወስዳል ቢባልም፣ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገርለት የኦሮሞ ነፃነት ጦር (OLA) የተባለው ቡድን ግን ኦነግ ሸኔ የሚባል ኃይል አለመኖሩን በመግለጽ ክዷል፡፡
በወለጋ በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ጭፍጨፋ በተመለከተ ዋናውን ተጠያቂነትና ኃላፊነት ሊወስድ የሚገባው አካል ማን ነው? የሚለው ጥያቄ እስካሁን ቁርጥ ያለ መልስ አላገኘም፡፡
ረቡዕ ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት ለዚህ ሁሉ ጭፍጨፋ ማን ኃላፊነት ይውሰድ? የሚለው ጥያቄ ከሁሉ ጎልቶ ተነስቶ ነበር፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ መስፍን ዳኜ ባቀረቡት ጥያቄ ተጠያቂነትን አጠንክረው አንስተዋል፡፡ ‹‹የዜጎችን ደኅንነት ማስከበር ያልቻሉ የፌዴራልና የክልል አመራሮች ተብሎ ተጠያቂነት ይቀመጥ፡፡ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራር ተብሎ ተጠያቂነት ይቀመጥ፡፡ በተናጠልና በዚህ ደረጃ ምክር ቤቱ መጠየቅ ካልቻለና ተጠያቂነት ካልሰፈነ ነገም ይህ ነገር መደገሙ ይቀጥላል፤›› በማለት ነበር የፓርላማ አባሉ ተጠያቂነት ሊሰፍን የሚገባበትን መንገድ ያስረዱት፡፡
የእናት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ያዬ አስማረ ተጠያቂነት የሚሰፍነው በፓርላማው አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን ኃይል ብቻ በመወንጀል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ተጠያቂነት ከዚያ አልፎ በሁሉም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ኃላፊዎችን መጠየቅን ይጨምራል፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡ ኦነግ ሸኔ ይህን አደረገ ማለት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ያሰመሩበት አቶ ያዬ፣ ‹‹እነሱማ ግብራቸው ታይቶ እኮ አሸባሪ ተብለዋል፡፡ እነሱ ጭፍጨፋውን ሲፈጽሙ ማስቆም ያልቻሉ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ከላይ እስከ ታች ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ናቸው መጠየቅ ያለባቸው፤›› ብለዋል፡፡
የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩትና አሁን በሕግ አማካሪነት እየሠሩ ያሉት አቶ ታረቀኝ አበራ፣ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የተጠያቂነትን አሠራር ለማስፈን ከባድ ፈተና ሆኖ መዝለቁን ይናገራሉ፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ጠንካራ የሪፎርም አመራር ነበሩ፤›› ሲሉ ያደነቋቸውን የቀድሞው የአቅም ግንባታ ሚኒስትር አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ በፍትሕ ተቋማት ውስጥ ለውጥ እንዲደረግ ጥረት ጀምረው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹በአሻጥርና በሴራ›› የተሞላ ባሉት ፖለቲካ ሥራው ተደናቅፎ በአጭር መቅረቱን ይናገራሉ፡፡
ለውጥ ከመጣ ወዲህም የፍትሕ ተቋማት ሪፎርም ይደረጉ ተብሎ በደቡብ ክልል በአጭር ጊዜ ብዙ በጎ ሥራዎች መከናወናቸውን የሚናገሩት አቶ ታረቀኝ፣ ልክ እንደ ቀድሞው ጊዜ ሁሉ ፖለቲካው ጣልቃ በመግባቱ ጥረቱ በአጭሩ መቀጨቱን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ካላስከበርክ ምኑን መንግሥት ነህ?›› በማለት ጠንካራ ጥያቄ ያነሱት የሕግ ባለሙያው፣ ‹‹የፀጥታ፣ የደኅንነትና የፖሊስ መዋቅሩም ሆነ እስከ ላይ ድረስ ያለው አመራር በየደረጃው ተጠያቂነትና ኃላፊነት ይወስዳሉ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የክልል መንግሥታት ሥልጣንና ኃላፊነት ይሰጠን ብለው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ወስደዋል፡፡ ሆኖም የዜጎች የመኖር መብት መረጋገጥ አልቻለም፡፡ በአንድ በኩል ሥልጣን እየጠየቁ በሌላ በኩል የዜጋን ሕይወት አለመጠበቃቸው ትልቅ ውድቀት ነው፤›› ያሉት አቶ ታረቀኝ፣ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ባሉ የመንግሥት ተቋማት በተለይ የፍትሕ ተቋማት፣ ‹‹በብሔር ፖለቲካ ተተብትበው የተፈጠሩ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ ታረቀኝ በየተዋረዱ ተጠያቂነት መስፈን አለበት እንዳሉት ሁሉ፣ ከሰሞኑ በወለጋ የተፈጠረውን ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ ተከትሎ ብዙ ወገኖች የተጠያቂነትን ጉዳይ በጉልህ እያነሱት ነው፡፡ ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እጅግ ብዙ ተመልካችን አትርፎ የከረመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ሀንጋሳ አህመድ ኢብራሂም በፌስቡክ ገጻቸው በቀጥታ ያሠራጩት ቪዲዮ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ማጠንጠኛውን ያደረገ ነበር፡፡ አቶ ሀንጋሳ በኦሮምኛና በአማርኛ ባስተላለፉት ቪዲዮ የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናትን ለቀውሱ ዋና ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
‹‹ዓብይ (ዶ/ር) መረጋጋት እንዲፈጠር የማልፈልገው እኔ ነኝ በለንና ገላግለን፡፡ ሰው እየሞተ ዝም የምትለው ለምንድነው? ወደ 78 ጊዜ እኮ ነው የሐዘን መግለጫ ብቻ እየወጣ የሰው ዕልቂት የታለፈው፡፡ የኦሮሚያ ክልልን የሚመራውን ተጠያቂ አድርገው፡፡ ከአብዲ ኢሌ ጋር አገናኘው፡፡ ከወራት በፊት ለዚህ ቀውስ ሁሉም ተጠያቂ ናቸው የሚለው የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናትን ነበር፡፡ አሁን ግን አንተን እያለ ነው፡፡ በጊዜ ሒደት ደግሞ ሁሉም ነገር አንተ ላይ ነው የሚደፈደፈው፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ሀንጋሳ፣ የተጠያቂነቱ ተዋረድ በሒደት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሄድ አመልክተዋል፡፡
የሕግ ባለሙያና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት አቶ ወንድሙ ኢብሳ፣ ከሰሞኑ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደተናገሩት፣ ተጠያቂነትን ማስፈን ከመንግሥት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡
‹‹የሕዝብ ደኅንነት ማስጠበቅ የመንግሥት ዝቅተኛ ግዴታ ነው፡፡ የጥፋት ተባባሪ የሆኑ አካላትን ከላይ እስከ ታች አጣርቶ ለሕግ ማቅረብና ተጠያቂነትን ማስፈን ከመንግሥት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፤›› በማለት መናገራቸው የተዘገበው አቶ ወንድሙ፣ የተጠያቂነቱ ኃላፊነት በዋናነት ማን ላይ እንደወደቀ አመልክተዋል፡፡
ሐሙስ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተነሱላቸው ጥያቄዎች አንዱ የተጠያቂነት ጉዳይ ይገኝበት ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ፣ ‹‹ትክክል ነው መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማስከበር ኃላፊነት አለበት፤›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሲናገሩ ግን መንግሥት አሸባሪ ተከላካይ እንጂ አሸባሪ አለመሆኑን በማመልከት፣ ‹‹ሕዝቡ መንግሥት የሚናገረውንም መስማትና ከመንግሥት ጋር መተባበር አለበት፤›› በማለት ነበር ተጠያቂነቱ የሚረጋገጥበትን መንገድ የተናገሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ከአሸባሪዎች ጋር የሚተባበሩ ሰርጎ ገቦች መሰግሰጋቸውን በግልጽ ያመኑ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል ከ5,000 በላይ አመራሮችን ማፅዳት መቻሉን አመልክተዋል፡፡
መንግሥታቸው ተጠያቂነትን በማስፈን በኩል ብዙ ጥረት እያደረገ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ ትግሉ ውስብስብና ፈተና የበዛው እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡ ከዚህ ውጪ ተጠያቂነት ካልሰፈነ በሚል አመራሩን መወንጀልና ጣት መቀሰር ትግሉን እንደማያግዝ በሰፊው ያብራሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን እየሰው የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የሚለፉ የፀጥታ አካላትንና አመራሮችን ጥረት አናደናቅፈው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በአመራሮች ላይ በተናጠልም ሆነ በጅምላ የሚካሄድ ውንጀላ ከዚህ ባለፈ የሥልጣን ፈላጊዎች ጩኸት ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ቢናገሩም፣ ከተቃዋሚዎች ወይም ከተቺዎች ብቻ ሳይሆን ከራሱ ከብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችም በድፍረት ወጥተው ተጠያቂነት ይስፈን የሚሉ ብቅ እያሉ ይገኛል፡፡ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታና የኦሮሚያ ብልፅግና ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ፣ ከሰሞኑ በፌስቡክ ገጻቸው ያሠራጩት መልዕክት ለዚህ ቀዳሚ ምሳሌ ሆኖ መቅረብ ይችላል፡፡
‹‹ተጠያቂነት ይስፈን›› በሚል ርዕስ አቶ ታዬ ያወጡት አጭር የፌስቡክ መልዕክት፣ የዜጎች ጭፍጨፋ መቀጠል ሊያስከትል የሚችለውን ከባድ አደጋም ይጠቁማል፡፡
‹‹በነገራችን ላይ ጥፋቱ የማን ነው? ጠያቂና ተጠያቂ ሊኖር የግድ ይላል፡፡ ተጠያቂነት ባለመኖሩ አንድ ችግር መቶ ጊዜ ራሱን ይደግማል፤›› ብለዋል አቶ ታዬ በጽሑፋቸው፡፡
በማሳረጊያቸው ደግሞ፣ ‹‹ለመሆኑ ሕዝብ በሌለበት ምድር ሥልጣን ለምን ይጠቅማል? አሁን ተጠያቂነትን በማስፈን እንቆቅልሹን መፍታት የህልውና ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከዚህ ካለፈ አደጋው ከቁጥጥር ይወጣል፤›› በማለት ነበር ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል የሥልጣን ፈላጊዎች ጩኸት ተብሎ የተተቸው ይህን መሰሉ ዓይነት አስተያየት ይሁን አይሁን አልታወቀም፡፡ ይሁን እንጂ የሰሞኑ ተከታታይ የወለጋ የዘር ተኮር ጭፍጨፋ የተጠያቂነትን ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ ጎልቶ እንዲነሳ አድርጎታል፡፡
ተቺዎች እንደሚሉት ከሆነ ግን የሰሞኑ ተጠያቂነት ይስፈን የሚል ጩኸት፣ ሌላ ዙር የመንግሥት ጩኸት መንጠቂያ ታክቲክ ነው በሚል እየገለጹ ይገኛል፡፡ ለአራት ተከታታይ ዓመታት የማያባራ የዘር ተኮር ጭፍጨፋና አሰቃቂ ዕልቂት ሲካሄድ ማስቆም ያልቻለው የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር፣ አሁንም ቢሆን ችግሩን ለመቅረፍ ያለውን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ተቺዎቹ ይጠራጠራሉ፡፡ አንዳንድ ወገኖች መንግሥት ተጠያቂነት ይስፈን የሚለው፣ አቅጣጫ ለማስቀየስና ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ ለማስመሰል ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ መንግሥት መጀመርያ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ግጭትና ግድያ የተስፋፋው ለውጡ ከቀድሞ መንግሥታት በተለየ ሰፊ ነፃነት በመፍቀዱና የዴሞክራሲ ምኅዳሩ በመከፈቱ ነው ይል ነበር፡፡ በሒደት ይህ የመንግሥት አመክንዮ የሕወሓት ተላላኪዎች ሴራ ነው ወደሚል መዞሩንም ተቺዎች ይናገራሉ፡፡
አሁን እንደሚታየው ደግሞ የሕወሓት ተላላኪ የሆኑ ኦነግ ሸኔና የመሳሰሉ ኃይሎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላና በኦሮሚያ ክልሎች ጭፍጨፋ ይፈጽማሉ የሚል ውንጀላ በመንግሥት ተደጋግሞ ይሰማል፡፡ ከሰሞኑ ዓብይ (ዶ/ር) በፓርላማ እንደተናገሩት ከሆነ ደግሞ፣ በአገሪቱ የሚታየው የፀጥታ ችግርና የንፁኃን ጭፍጨፋ አገሪቱን ለማፍረስ የተቀናጀ ዘመቻ በከፈቱ ኃይሎች የተፈጠረ ቀውስ ነው የሚል ማሳመኛ ቀርቦበታል፡፡
ይህ ያልተዋጠላቸው የመንግሥት ተችዎች ግን በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል ለነገሮች ውስብስብ አመክንዮ በማቅረብም ሆነ በሦስተኛ ወገን ላይ በመደፍደፍ ችግሩን መሻገር የሚችልበት አንዳችም ቀዳዳ እንደሌለ በመጥቀስ፣ ራሱን ተጠያቂ ያድርግ ሲሉ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ ታረቀኝ፣ ‹‹አሁን ባለው አለመረጋጋትም ሆነ በሰዎች ጭፍጨፋ ትልቁን ኃላፊነት የሚወስደው መንግሥት ነው፡፡ ይህን በማስተባበል ብቻ ማለፍ አይቻልም፤›› ሲሉ ነው የሚናገሩት፡፡ በደቡብ ክልልና በፌዴራል ደረጃ በፍትሕ አካላት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት የሠሩት አቶ ታረቀኝ፣ የክልል መንግሥታት ብሔር መርጠው ሕግ ማስክበር ሳይሆን ለሁሉም ዜጋ እኩል ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው ያሰምሩበታል፡፡
‹‹ይህ ነገር እስከ ስንት ጊዜ ይወገዛል? በአንድ ደቂቃ ፀሎት ወይም በወሬ ብቻ መታለፍ የለበትም፡፡ ወንጀሉ ልክ እንደ ዘር ማጥፋት ከፍ ያለ ቦታ ተሰጥቶት መታየትና በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ ኦነግ ሸኔ ይባላል፣ ነገር ግን የኦነግ ሸኔ ዋና መፈልፈያም ሆነ ምሽግ ማን እንደሆነ በግልጽ ይታወቃል፡፡ አገራችን የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤትንም ሆነ የአፍሪካ ሰብዓዊ መብቶች ወንጀል ፍርድ ቤት ስምምነቶችን ፈራሚ አገር አይደለችም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስጠየቅ ፈታኝ ነው፤›› ይላሉ፡፡ የናይጄሪያንና የህንድን የፌዴራላዊ ሥርዓት እንደ ምሳሌ ያነሱት አቶ ታረቀኝ፣ ‹‹እነዚህ አገሮች ጠንካራ የፌዴራል መንግሥት በመፍጠር ከመበተን ድነዋል፤›› በማለት፣ በኢትዮጵያም የፌዴራል መንግሥቱ ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲከተል አሳስበዋል፡፡
የእናት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት አቶ ያዬ፣ ‹‹መንግሥት ከደሙ ንፁህ ነኝ፣ የምችለውን እያደረኩ ነው፣ አትጠይቁኝ በማለት ብቻ ነገሩን ማለፍ አይችልም፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ አቶ ያዬ ሲቀጥሉም፣ የዜጎችን ሕይወት መታደግ ያልቻለ መንግሥት ‹‹ተጠያቂነት ያላሰፈነ ነውና አልቻልኩም ብሎ ሥልጣኑን አስረክቦ መውረድ ነው ያለበት፤›› ሲሉ ነው ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት፡፡