Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ናዕት (እያመመው መጣ ቁጥር- ፪) በግላዊ ምልከታ ላይ የተመሠረተ ሙያዊ ዳሰሳ

በመዝገበቃል አየለ ገላጋይ     

ዕንቁውና ብርቅዬው የጥበብ ፈርጥ ከያኒ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ ሰሞኑን የአያሌ ኢትዮጵያውያንንና ኢትዮጵያውያትን የልብ ሰቆቃ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይና ወቅታዊውን የአገራችን የሐዘን ድባብ በተገቢ ሁኔታ ያገናዘበ፣ እንዲሁም በጠንካራ ጭብጥ የበለፀገ አንድ ነጠላ ዜማ እንካችሁ ብሎናል፡፡

ይኼን ጽሑፍ ከማዘጋጀቴ በፊት፣ በተለያዩ የርዕሰ መዲናዋ አካባቢያዊ ክፍሎች ተንቀሳቅሼ፣ ይኼ ነጠላ ዜማ በሰዎች ላይ እያሳደረው ያለውን የስሜት ተፅዕኖና ተደማጭነቱን ስታዘብ፣ አንዳች ጩኸት የተሸከመ ቁጣ አዘል ዝምታን ተከናንቦ ከትንሽ እስከ ትልቅ በጥልቅ ስሜት ሁሉም እያደመጠው መሆኑን በትክክል መገንዘብ ችያለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ ይኼንን ጥልቅ ሕዝባዊ ዝምታ ስታዘብ፣ እጅግ በጣም የሚያስፈራ ስሜት አልፎ አልፎ ውስጤን ውርር እንዳደረገኝ መካድ የምችልበት ምንም ዓይነት አቅም ማግኘት አልችልም፡፡

ወቅታዊውን የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ የሚረዳበት አቅመ ልዕልናው ያቀነጨረ ካልሆነና ሰዋዊ የኪነ ጥበብን ብርታት ለመገንዘብ የሚያስችለው ጤነኛ ስሜቱ ወደ ጥልቁ ዝቅጠት የወደቀ፣ አልያም ለሆነ ጊዜ ወለድ ጎራ አፈንዳጅ አጎብዳጅ ካልሆነ በስተቀር፣ በዚህ ነጠላ ዜማ ጭብጥ እንደ ሰው ልቡ የማይነካ ይኖራል ብየ አላስብም፡፡ ብቻ ከያኒ ቴዎድሮስ ካሳሁን ቴዎድሮስ ነው፡፡ በሚወዳት አገሩ ዙፋነ ሰብዕና ላይ፣ የጥበብንና በሕዝብ ዘንድ ተወዶ የመከበር ዘውድን የተቀዳጀ ልበ-ገብና ጆሮ-ገብ የኪነ ጥበብ ንጉሥ፡፡

የተከበራችሁ አንባብያንና አንባብያት፣ እንደ አንድ የኪነ ጥበብ ባለሙያ፣ ወቅታዊው የአገራችን ጉዳይ ባለቤትነት፣ በዚህ ነጠላ ዜማ ጭብጥና ኪናዊ ሐሴት ልባቸው በሐዘን አንዳንዴም በደሴ ስሜት ከተመለዘጉት የኪነ ጥበብ ቤተሰቦች መካከል አንዱ በመሆኔ፣ የዚህን ነጠላ ዜማ ግጥማዊ ጭብጥ ብቻ መሠረት አድርጌ፣ የሙያ ምልከታየንና ግላዊ አረዳዴን እንደሚከተለው በመተንተን፣ በግጥሙ ውስጥ የተነሱትን ዓበይት ሐሳቦች ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

አንድ የኪነ ጥበብ ባለሙያ፣ ስለአንድ የኪነ ጥበብ ሥራ ግላዊ ምልከታውን ወይም ሙያን መሠረት ያደረገ ሒሳዊ ዳሰሳውን ሲያቀርብ፣ ከሁሉም በፊት አስቀድሞ እንደ መግቢያ ከያኒው ከዚህ በፊት የሠራቸውን ኪናዊ ሥራዎች ዘርዘር አድርጎ በመጥቀስና ተገቢውን ምሥጋና በማቅረብ፣ አሁን ወደ ሚያተኩርበት የከያኒው ኪናዊ ዓውድ መሸጋገሩ የተለመደ ሙያዊ ይትበሃል መሆኑ ባይዘነጋም፣ እኔ ግን የከያኒ ቴዎድሮስ ካሣሁንን (ቴዲ አፍሮን) ቀደምት ሥራዎች እንደ መግቢያ መጥቀሱ፣ ለአንባብያንና ለአንባብያት ለቀባሪ እንደ ማርዳት መስሎ ስለተሰማኝ፣ ያን ማድረጉን ትቼ፣ በቀጥታ በዚህ አዲስ ነጠላ ዜማ ግጥማዊ ጭብጥና ይዘት ላይ ብቻ በማተኮር፣ ግላዊ ምልከታየን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

የነጠላ ዜማው ርእስ፣ ናዕት (እያመመው ቁጥር-፪) የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ዜማው ለተቀነቀነበት ወቅታዊ ሁኔታና ለአጠቃላዩ የግጥሙ ጭብጣዊ ይዘት፣ በትክክል ተገቢነትን የተላበሰ ርዕስ ነው በማለት መመስከር እችላለሁ፡፡ አገራችንና ሕዝቦቿ መንስዔው አደገኛ በሆነ ፖለቲካዊ ቫይረስ በሽታ ተይዘን የታመምንና በዚህ ሕመማችን ምክንያትም ብሔራዊ ቁዘማ ውስጥ የገባን መሆናችን አሌ የማይባል የገመናችን ሀቅ ነው፡፡

ከያኒውም፣ ይኼን የሁላችንንም እውነታ በሰላ ምልከታው የበለጠ በጥልቀት ተገንዝቦ ነው፣ ለዚህ ነጠላ ዜማው እያመመው የሚል ስያሜ የሰጠው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሁሉም በላይ ልቤን የጎተተውና የከያኒውን የረቀቁ የኪነት ዓይኖች ተገንዝቤ እንድደመም ያደረገኝ፣ ተደራቢ ርዕስ ሆኖ የቀረበውና ‹‹ናዕት›› የሚለው ቃል ነው፡፡ አንባብያንና አንባብያት ይኼን ቃል ሲሰሙ ወይም ሲያነብቡ፣ ስለቃሉ የት መጣነት ጥያቄ ማንሳታቸው እንደማይቀር አልጠራጠርም፡፡

‹‹ናዕት›› የሚለው ቃል ‹‹ነዐተ›› ጋገረ ከሚል የግዕዝ ቋንቋ ሥርወ ቃል ወይም ቀዳማይ አንቀጽ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ቂጣ›› ማለት ነው፡፡ ሒደቱን በጠበቀ መልኩ ተስተካክሎ ሳይቦካ፣ ለጊዜያዊ የረሃብ ማስታገሻነት ብቻ በድረስ ድረስ የሚጋገር አፍለኛ ቂጣ ማለት ነው፡፡ ራያዎችና የጁዎች ‹‹መንገሌ›› ዋድላ፣ ደላንታና ዳውንቶች ደግሞ ‹‹ደንገሎ›› እንደሚሉት የምግብ ዓይነት፡፡

ከያኒው ይኼን ቃል በተደራቢ ርዕስነት ለምን መረጠው? ብየ ራሴን ስጠይቅ ወደ አዕምሮየ የመጣው መልስ፣ ደመ ነፍሳዊነት ጎልቶ ወደሚታይበትና ብስለትና ስክነት ወደ ጎደለው፣ እንዲሁም ራሳቸውን ሳይክዱ የበግ ለምድ በማጥለቅ የሕዝባችንን መስቀል እንሸከማለን የሚሉ የአገራችን የፖለቲካ ሐዋርያት ወደ ከተሙበት ገንዳ በምናቤ ጎራ እንድል አስገድዶኛል፡፡  ከያኒው፣ በዚህ ነጠላ ዜማው ውስጥ በአማራጭ ርዕስነት ያቀረበው ‹‹ናዕት›› የሚለው ቃል፣ ‹‹ሆዴ ይሙላ፣ ደረቴ ይቅላ፣ ተሹሜ ሳልሻር በዚህ ጊዜ ልብላ›› በሚል መፈክር የታሰሩት እነዚህ አካላት፣ ፖለቲካዊ አቅመ ሰብዕናቸው የተሠራበት ቅንጣጢት ከ‹‹ናዕት›› የተለየ ትርጉም እንደሌለው በማነፃፀር፣ ስሜታችንን እየኮረኮረ ልንገፋው የማንችለውን እውነታ ይነግረናል፡፡

ይኼም ድርጊት፣ አገራችንና ሕዝቦቿ ዓይነተ ብዙ የሆነ የመከራ ዶፍ እንዲወርድብን አስተዋጽኦ ካበረከቱት አሉታዊ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ በመሆን የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይኼ መቋጫ ያልተገኘለት ሕዝባዊ ሰቆቃ፣ በሸካራ ሞረዱ ስሜቱን የፈገፈገው ከያኒውም ከወዲሁ ዜማውን ‹‹ዶፍ…ዶፍ›› በማለት ይጀምራል፡፡ የዘመናችን አስከፊነትና የትውልዳችን ያለመታደል በረከተ መርገም፣ የህልውናችንን መቅረዝ እያደበዘዘ፣ አገራችን በተቃራኒ ጎራ የተሠለፉ የአልቃሾችና የዳንኪረኞች ጉሮኖ ከሆነች ሰነባበተች፡፡ እኛ ሕዝቦቿም የተስፋ ጭላንጭላችን እየከዳን፣ አምነንና አጨብጭበን የተቀበልነው ዙፋኑን እንደተቆናጠጠ በሸፍጥ ጀርባውን ሲሰጠንና በመፀፀት ለቁጭት ሲዳርገን፣ ያለንበትን ገልቱ የጎግ ማጎግ ዘመን አስከፊነት፣ እንደ ከያኒው ዜማ ኡኡታየ በማለት ካልሆነ በስተቀር በምን ሊገለጽ ይችላል? ለዚህ ነው ከያኒውም በዚህ አዲስ ነጠላ ዜማው፡-

‹‹ግርም ያለ ጊዜ ሆነ ሰዓቱ፣

በዳንኪራው ደምቆ በምቱ፣

ለደቂቃም አይቆይ በስልቱ፣

ቦግ እልም እያለ መብራቱ፡፡

ኡ ኡ ሬጌ ናዕት ሬጌ ናዕት›› በማለት ሮሮውን ለመግለጽ የተገደደው፡፡

በአባቶቻችንና በእናቶቻችን አርቆ አሳቢነትና ለትውልድ ሲባል በከፈሉት ብርቱ የሕይወት ክፍያ፣ ነፃነቷን የተቀዳጀችውና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ያበረከተችው የነፃነት አርዓያነቷ ከፍ ወዳለው የክብር ሠገነት መጥቆ የነበረችው አገራችን ኢትዮጵያ፣ ዛሬ በእኛ ትውልድ ደረመን ካጠለቀው ሕዝባዊ የውርደት መዳፍ ላይ ከወደቀች ሰነባበተች፡፡

በትውልዳችንና በአገራችን መፃኢ ዕጣ ፈንታ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ፣ ኃላፊነቱን ከሕዝብ መዳፍ ላይ የተረከቡት የፖለቲካ ልሂቃንም፣ የጎረሰው እውነት ያነቀው ፖለቲካዊ ገመናችንን አምነው ይፋ በማድረግ፣ ፍቱን መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ የርዕሰ መዲናዋን አደባባዮች ቀለም በመቀባት ዕይታን በማንሸዋረር ተግባር ላይ ተጠምደዋል፡፡ ይኼ ነው እንግዲህ ‹‹ናዕት›› ማለት፡፡ ከዚህ እውነት ጎን በተቃራኒው ቆመው የነበሩ ጥቂት አካላት ቢኖሩም፣ በተለያዩ ማማለያዎች ብዕራቸው እንዲነጥፍና አንደበታቸው እስከወዲያኛው እንዲሸጎብ ተደርገዋል፡፡

በተቃራኒው፣ ከዚህ ብሔራዊ አዙሪታችን ለመውጣትና ከሞተከዳ በላይ ከሚጎፈንን አገራዊ የውስጥ ግማታችን ለመንፃት፣ የመጀመርያው ነገር ራሳችንን መፈተሽና ማፅዳት ነው የሚሉ፣ በጣም ጥቂት የ‹‹ሞራል›› ባለፀጋዎች ግን፣ የማማለያ ‹‹ጆከር›› ካርዶች በፊታቸው ቢቅለሰለሱም፣ ጣቶቻቸውን ልከው ለመምዘዝ እንደተጸየፏቸው፣ እንደ ሰው መረዳት አይገደንም፡፡ ከእነዚህ የ‹‹ሞራል›› ባለፀጋዎች መካከል አንዱ ከያኒው ነው፡፡ እሱም ለእንደዚህ ዓይነቱ ጊዜያዊ ሆድ አደርነት ያለውን የመጸየፍ ደረጃ ምን ያህል እንደሆነ፣ በዚህ አዲስ ነጠላ ዜማው ውስጥ፣

‹‹ብልጭልጭ ቢሆን ዳሱ፣

ማን ሊታደም ከድግሱ፡፡

ብልጭልጭ ቢሆን ድንኳን፣

አይለውጥ ጎግ የእውነት መልኳን›› በሚሉት ስንኞቹ፣ ደርዝ ባለው ገለጻው ያረጋግጥልናል፡፡

በአንድ መንፈሳዊ መጽሐፍ ገጾች ላይ አንብቤው ፈገግና ግርም ያደረገኝን አንድ ታሪክ ከዚህ ላይ ባነሳ፣ በሚቀጥሉት የነጠላ ዜማው ስንኞች ላይ ተመሥርቼ የማንፀባርቀውን ሐሳቤን፣ ከወዲሁ የበለጠ ያጎላልኛል ብየ አስባለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ከዕለታት በአንድ ቀን የእመቤታችን በዓል በሚታሰብበት ዕለት፣ መሪ ቀዳሽ ሆነው ‹‹ጎሥዓ›› የተሰኘውን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ቅዳሴ ይቀድሳሉ፡፡ ቅዳሴውን አጠናቀው ከቤተ መቅደሱ ከወጡ በኋላ፣ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ቄርሎስን፣ ‹‹አባታችን፣ ዛሬ እንዴት ነው ‹‹ጎሥዓ››ን ጥሩ አድርጌ ቀደስኳት?›› በማለት ይጠይቋቸዋል፡፡ ታላቁ አባት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስም፣ በወቅቱ በቤተ ክርስቲያኗም ሆነ በአገሪቱ እየተከናወነ ያለውን ጎሳዊ ሁኔታ ለመግለጽ የተጠየቁትን ጥያቄ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ ‹‹እንዴ አባታችን በደንብ አሳምረው ነዋ፡፡ ደግሞ ለጎሳ እርስዎን ማን ብሎዎት፤›› በማለት መለሱላቸው ይባላል፡፡

አሁን ላይ ባለው አገራዊ የፖለቲካ ምኅዳራችንም እየሆነ ያለው ነገር፣ ከቀድሞው ፓትርያርክ የልብ እውነታና የግል ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር፣ የተለየ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በጎጠኝነት ልባብ የተሸበበው ፖለቲካዊ አሠላለፍ፣ የተረኛነት ጋቢን የተከናነበ ዘውጋዊ ጎሰኝነት ከጅምሩ ስለተጠናወተው፣ ለዜጎች ህልውና ዋስትና ለመስጠት ገና በጧቱ ጎህ ሲቀድ መቅኒው ፈሷል፡፡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዜጎች፣ በጠራራ ፀሐይ በአደባባይ እንደ እባብ ጭንቅላታቸው እየተቀጠቀጠ ተገድለዋል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትም፣ ለፍተው ያጠራቀሙትን ሀብት ንብረታቸውን፣ በአንድ ጀምበር በግፈኞች ተዘርፈው አሰቃቂ በሆነ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ወለጋ መንግሥት እንደሌለባት ሥርዓት አልባ መደዴ አገር፣ በንፁኃን ደም ቀልታ አኬልዳማ ከሆነች ሰነባበተች፡፡ እልፍ አእላፍ የዘካርያስ ደሞች፣ አሁንም ወለጋ ላይ በጩኸት እያክላሉ ነው፡፡ በጥቅሉ አራዳነት ያልጎበኘውና ይሉኝታው የከዳው ሰገጤ ተረኝነት፣ አገሪቱን ወደ ጥልቁ የጥፋት ገደል እየወሰዳት ይገኛል፡፡ ለዚህ ነው ከያኒውም በዚህ ነጠላ ዜማው አብዝቶ ኡኡ በማለት ድምፁን እያሰማ ያለው፡፡

ሮጦ ሳይጨርስና ገና ሠርቶ ሳይጠግብ በለግላጋ ዕድሜው በጧቱ በግፈኞች ለተቀጠፈው ወንድማችን ለድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ፣ ባንዲራ ዝቅ አድርጋ የሰቀለች፣ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ያወጀችና የተለያዩ የመታሰቢያ ስያሜዎችን የሰየመች አገር፣ ወለጋ ላይ በግፍ ዘር የማጥፋት ድርጊት የተጨፈጨፉትና እየተጨፈጨፉ ያሉት በርካታ ሺሕ የአማራ ተወላጆች ዕልቂት ግን፣ ለአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የውይይት አጀንዳ ለመሆን እንኳን ሚዛን መድፋት አልቻለም፡፡ የዜጎች በሕይወት የመኖር መብት በነበር የቆመ ተረት ተረት እየሆነ ነው፡፡ ፖለቲከኞቻችን ኢትዮጵያዊነትን በመጸየፍ ዘውጌ ጎሰኝነትን እያገነኑ ለማንገሣቸው፣ ከዚህ በላይ ምስክር ይኖር አይመስለኝም፡፡ ከያኒውም ይኼን ውርደት አዘል ብሔራዊ የአደባባይ ምሥጢር በሰላ ትዝብቱ፡-

‹‹ቢጋርድ ሐሳብ አርጎ ሜዳን ገደል፣

እምአእላፍ ስቃይ ጭንቀት ቢደረደር፣

የነፍስ ህላዌ መሻት ዋዌ ሳይገባቸው፣

ስንቶች በዘር ተዘፍቀው ታዘብናቸው፡፡›› በማለት በኪናዊ ልሳኑ ሕዝባዊ ሙሾውን ያወርዳል፡፡

ከያኒው፣ በዚህ ብቻ አያቆምም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ በኢትዮጵያዊነት ባህሪያችን፣ ለሦስት ነገሮች ልባችን በቀላሉ ተሸናፊ ነው፡፡ በፈጣሪያችን፣ በአገራችንና በእናቶቻችን ስም በፍቅር ለሚመጣ ሁሉ ልባችን ስስ ነው፡፡ በቀላሉ ይላላል፡፡ ብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ ከምንም ነገር ጋር የማናነፃፅራቸው እነዚህ ሦስት የመሸነፊያ ድክመቶቻችን፣ በወቅቱ ፈጽመን ባመነው አንደበት አደባባይ ላይ ጎልተው ሲንቆላጰሱ አድምጠን አምነን ተሸነፍን፡፡ ልባችን በሀሴት ተሞልቶ ፈንጠዝያችን በረከተ፡፡ ከፍቅራችን ፅናት የተነሳ ገንዳዎቻችንን በስማቸው ሰየምን፡፡ አንደበቶቻችንና ብዕሮቻችን፣ ተስፋችን ውሎ ላያድር እነሱን በማንቆላጰስ ተግባር ተጠመዱ፡፡ ነገር ግን ይኼ ሁሉ ውሎ ሳያድር፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን፣ መንግሥታዊ ከለላ አጥተው ወለጋ ላይ በግፍ ሲጨፈጨፉ፣ ለኡኡታቸው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ ጸዐዳ ሸሚዝ አጥልቀው ችግኝ ሲተክሉ መዋላቸውን ተመልክተን፣ ደስታችን በሐዘን፣ ማመን መታመናችን በሚያሳቅቅና በሚያም ሁኔታ በመከዳት ተጠናቀቀ፡፡ እምነት የጣልንበት ቃል ኪዳንና መሃላ፣ ዘውጌነት ባካፋው የጎሰኝነት ጎርፍ ተጠርጎ ተወሰደ፡፡ ይኼ ማኅበራዊ በደል ልቡን ጠልቆ የወጋው ከያኒውም፡-

‹‹ዘውግ ያወረው ድንበር ማላውን የረሳ፣

ሣር ያለመልማል ዛሬም በእልፍ አእላፍ ሬሳ፡፡

እያረረ ሆዴ ብስቅ በማሽላ ዘዴ፣

ና ታደም ይለኛል ደግሞ በነ ኡኡ ሬጌ፡፡››

በሚሉት ስንኞቹ ውስጥ፣ የብዙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ልሳንነቱንና የቁርጥ ቀን የብሶታችን ተጋሪነቱን አሳይቶናል፡፡

ከላይ በጠቀስኳቸው የከያኒው አራት ስንኞች ውስጥ፣ የመጨረሻው ስንኝ ቤት መድፊያ የሆኑትንና ‹‹ኡኡ›› እና ‹‹ሬጌ›› የሚሉትን ሁለት ቃላት በተለየ ሁኔታ እንዳያቸው ተገድጃለሁ፡፡ በራሴ ዕይታና አረዳድ፣ ከያኒው እነዚህን ሁለት ቃላት፣ ከሒሳባዊ ቀመር ባልተናነሰ መልኩ ግዙፍ ውክልና እንድኖራቸው በማድረግ፣ አስቦበት በልክ የሰፋቸው ዓላማ አዘል የቃላት ዲጐች ሲሆኑ፣ ‹‹ኡኡ›› የግፍ ዋይታ ላነቃቸው ግፉአን ዜጎች ‹‹ሬጌ›› ደግሞ ዘመን ላነሳቸው የጊዜው ዳንኪረኞች መገለጫነት፣ ተሠርተው ጎን ለጎን የቆሙ ተቃራኒ የትዝብት ሐውልቶች ናቸው ብየ አስባለሁ፡፡

ከያኒው እስካሁን ከሆነውና እየሆነ ካለው በላይ የወደፊቱ የዜጎች ህልውና ያሠጋዋል፡፡ ከሰማያዊው ጌታ በስተቀር አድሮ ለመገኘት ተስፋ የሚጥልበት የሙሴ ጥግ የለውም፡፡ የመከራችን ባህር ከመከፈሉ በፊት፣ ሕዝባዊ በትረ ድህነታችን ተቀልጥሞ የተሰበረ ያህል ይሰማዋል፡፡ ካለፈው ተምሮና የአሁኑን ተገንዝቦ፣ መፃኢውን በብልኃት የሚያሻግረንና ከተጋረጠብን ብሔራዊ የህልውና አደጋ የሚታደገን ጠቢብ የሚያበቅሉ ማህፀኖች ነጠፉ ይላል፡፡ የት ይደርሳል የተባለው ወይፈናችን ልኳንዳ ቤት መገኘቱን ይጠቁመናል፡፡ ይኼን መሰል ዓይነተ ብዙ ሕዝባዊ ሰቀቀን እያየና እየሰማ ዝም ማለት ደግሞ፣ በራስ ላይ ጥፋት የማወጅ ያህል ይቆጥረዋል፡፡ ይኼን ህልውናችን በሥጋት የተከናነበውን ጥቁር ሸማ፡-

‹‹ተላላ ዝንጉ ሰብእ የሙታን ሸማ ደዋሪ፣

ምን አለ አይል ከፊት ሆኖ ቅርብ አዳሪ፡፡

ተናገር አፌ ደፍረህ ሳትናወጥ ከቶ፣

ዝም አይሆንም ሜዳ ተራራ ሞት መጥቶ፡፡›› እያለ ነው በዚህ አዲስ ነጠላ ዜማው የትውልዳችንን የልብ በር ደጋግሞ የሚቆረቁረው፡፡

ከያኒው፣ አሁን ከገባንበት ብሔራዊ የህልውና አደጋ ለመውጣት፣ መፍትሔው ከእኛው ከኢትዮጵውያንና ኢትዮጵያውያት ዘንድ ብቻ ነው ይለናል፡፡ ከሕዝባዊ አንድነታችን በስተቀር ከየትኛውም ሌላ አካል መፍትሔ አይጠብቅም፡፡ እንዲያውም መስሎን ያጨበጨብንለትንና የዘመርንለትን ምውት ተስፋ ይፀፀትበታል፡፡ ከመቼውም በላይ አንድነታችንን አጠናክረን የፍቅር ኅብረት እንመሥርት ይላል፡፡ ያን ጊዜ በወንድማማቾች ደም የራሳቸውን የግል ጥቅምና የሥልጣን መደላድል የሚያመቻቹትን፣ ውስጣዊና ውጫዊ ጠላቶቻችንን አሳፍረን፣ ብሔራዊ ህልውናችንን እናስቀጥላለን ይለናል፡፡ ለዚህ የከያኒው አስተሳሰብም፡-

‹‹ከበሮ ግም ሲል በእምቢ ነጎድጓድ ምቱ፣

ይናዳል የዘር ድንዛዜ ያ ድውይ ቤቱ፡፡

ገለልል በል ኤሳው ነፍሴን አንቀህ አታሳሳት፣

ብታገስ ባሰ ባንተ የልቤ እሳት፡፡››

የሚሉት የነጠላ ዜማው ስንኞች ምስክሮች ናቸው፡፡ ከያኒው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውንና ውስጡን እየጠዘጠዘው ያለውን ሕዝባዊ ግፍ መሠረት አድርጎ፣ በውስጣዊ ተብሰልስሎት በቁጣና በዝምታ ተገምዶ የተፈተለውን ሕዝባዊ ስሜት በመሻገር፣ የፖለቲካ ልሂቃኖቻችንን አዕምሮ ይበረብራል፡፡ በጣዕም አልባ በውሸት የታጀበውን ፈገግታቸውን አልፎ፣ መግደርደር አንቆ የያዘውን ያንጀት ውስጥ ልቅሷቸውን በትዝብት ያኝከዋል፡፡ ልክፍታችሁ ከመገንተሩ የተነሳ፣ የሐሳብ ደዌያችሁ እጅጉን እየናረ ነውና ለመሸፈን የምትጣጣሩለት ሕመማችሁ በሬሳ እንዳያጋልጣችሁ ተጠንቀቁ ይላል፡፡ ይኼን የከያኒውን አስተሳሰብ ፍንትው አድርገው የሚያሳዩን የነጠላ ዜማው የግጥም ስንኞችም፡-

‹‹እያመመው …እያመመው መጣ፤

ያዳፈነው እሳት ከሆዱ ሳይወጣ፡፡

ልቤ እንደ ካቻምናው እያመመው መጣ፡፡

የሚያዜም ይመስላል ሲያጣጥር ተጨንቆ፣

ውስጡን ሲሰብቅለት ኡ እያለ ማሲንቆ››፡፡ የሚሉት ናቸው፡፡

በዚህ የመጨረሻው ስንኝ ውስጥ ‹‹ኡ እያለ ማሲንቆ›› የሚለው ሐረግ፣ የሰሚ ያለህ በማለት ለሚጮሁ ግፉዓን ድምፆች የቆመ ውክልና መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ከያኒው፣ የተጋረጠብንን የህልውና አደጋና የትውልዳችንን የሰብዕና ህፀፅ፣ በመጠቆም ብቻ ዝም አይልም፡፡ የሰብዕናቸው ባህሪ ግለ ወጥነት ርቆት ግራ የሚያጋቡንንና በፖለቲካው ሜዳ ላይ እየተገለባበጡ ዘወትር የምላስ አክሮባት የሚሠሩትን አካላት፣ አማራጭ የሌለው ምክር አዘል የመፍትሔ አቅጣጫንም ‹‹ዘቦ እዝን ሰሚዐ ለይስማዕ-›› ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ – በማለት ይጠቁማል፡፡

‹‹ቂምን ሻረው እና ወይ ፍቅርን አንግሠው፣

ሁለት ሆኖ አያውቅም አንድ ነው አንድ ሰው፡፡

ከሀገር ይሰፋል ያ የፍቅር ገዳም፣

መጠሪያው ሰው እንጅ ዘር አይደለም አዳም፡፡››

በሚሉት የነጠላ ዜማው ስንኞች፣ አዳማዊ ሰውነትን ተላብሰን ከዘውጌ ጎሰኝነትና ጎጠኝነት ስሜት እንውጣ ሲል፣ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮሃል፡፡

ከያኒው፣ ዓለም ያወቃቸውንና ፀሐይ የሞቃቸውን በአገራችን ውስጥ በየቦታው የሚያክላሉትን ሕዝባዊ ሰቆቃዎች፣ የተለያዩ አጀንዳዎችን እየፈጠርን ሕዝብን በማደንዘዝ ለመሸፋፈን የምናደርገውን ጥረት አጥብቆ በመቃወም፣ በፅኑ ሁኔታ ያስጠነቅቃል፡፡ እስከ ሰንኮፉ ከወዲሁ ጎልጉለን ያላወጣነው ሞጀሊሳችን በአደገኛ ሁኔታ መልሶ እንደሚያመረቅዝም፡-

‹‹የተረገጠ እውነት በጊዜ ውስጥ እግር፣

ታፎኖ የቆየ በሆታ ግርግር፣

ትንሽ ጋብ እንዳለ የጭብጨባው ጩኸት፣

እረጭ ሲል ውሸት ይናገራል እውነት፡፡”

በሚሉት ስንኞቹ፣ ነጭ ነጩን እያሰመረ ቢመረንም ቢጣፍጠንም ልንፍቀው የማይችለውን እውነታ እንካችሁ ይለናል፡፡ ለጋራ ችግሮቻችን ከወዲሁ የጋራ መፍትሔ እናብጅ፣ ወሰን ድንበራችንም ፍቅር ብቻ ይሁን ይላል፡፡ ለከያኒው ፍቅር ዳር ድንበር የለውም፡፡ ፍቅር የዘር የሃይማኖት ስብራት አይጎበኘውም፡፡ ከጥንት ጀምሮ በአባቶቻችንና በእናቶቻችን ልብ ውስጥ ፀንቶ በቆየ በዚህ ቅዱስ እውነት፣ በጋራ ተጋምደን እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ ድረስ ለአንድነታችንና ለአገራችን ህልውና በጋራ ዘብ እንቁም ይላል፡፡

ከያኒው፣ በመጨረሻም ይኼን ነጠላ ዜማውን የሚቋጨው፣ ለሚወዳት፣ ብዙ ነገር ላየባትና ለሆነላት አገሩ፣ የመዝሙረኛውን የቅዱስ ዳዊትን አቻ ቋንቋ በመጠቀም ‹‹ኦ ኢትዮጵያ እመኒ ረሳእኩኪ ለትርስአኒ የማንየ፣ ወይጥእጋ ልሳንየ በጉርኤየ፡፡–ኢትየጵያ ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ምላሴም ከጉሮሮየ ትጣበቅ›› እያለ፣ የኪዳን ቃል በመግባት ነው፡፡

ከጠቢቡ ሰሎሞንም ጥበብን በመጋራት፣ ‹‹ኦ እምየ ኢትዮጵያ አነብረኪ ከመ ህልቀት ውስተ ልብየ-እናቴ ኢትዮጵያ ሆይ፣ እንደ ቀለበት በልቤ ጣት ላይ አስቀምጥሻለሁ፤›› በማለት ለእሷ ያለውን የፍቅር ጽንዓት ያረጋግጥላታል፡፡ ስንዱ እመቤት አገሩን፣ የባለቤቴ ውብ ፈገግታና ማራኪ ውበት፣ የልጆቼም ጣፋጭ የአንደበት ለዛ ከአንቺ አይበልጥም ይላታል፡፡ ይኼንን የልቡን እውነትም፣ ገና ከወዲሁ በሕይወት እያለ በዚህ ነጠላ ዜማው ውስጥ፡-

‹‹ዶፍ ቢዘንብ እሳት ሀገሬን ላልረሳት፣

ቃል አለኝ ኖሬ ሞቼም ልክሳት፡፡››

በሚሉት ስንኞቹ፣ የቃል ኪዳኑን ማኅተም ያረጋግጥልናል፡፡ ይኼም፣ እኔን ጨምሮ በማይሞቅ የኑሮ ‹‹ሼል›› ውስጥ ተኮርምተን ለምናንኮራፋ የኪነ ጥበብ ቀንድ አውጣዎች፣ ራሳችንን መመልከቻ መስታወት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ማጠቃለያ

ይኼ፣ የከያኒው አዲስ ነጠላ ዜማ፣ የበርካታ ጭብጦች ብዝኃነት የከተመበትና ወቅታዊ የአገራችንን መልክ አጉልቶ የሚያሳይ፣ ጉልህ መነጽር ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ከያኒው፣ የአገራችንና የሕዝባችንን ተለዋዋጭ የመከራ መልክ፣ በያይነቱ እየፈረጀ ያቀረበበት፣ የገመናችን ሙዳይ ልንለውም እንችላለን፡፡

በነጠላ ዜማው የግጥም ስንኞች ውስጥ የሚገኙት ቃላትና ሐረጋት፣ ያለምንም ተልዕኮ በረብ የለሽ አውደልዳይነት፣ ያለቦታቸው የተሸጎሩ አይደሉ፡፡ ለዚህ ጥበባዊ ሥራም የተዋጣለትና ማራኪ መሆን፣ ተገቢነትና ልክነት በሚታይበት አግባብ፣ የየራሳቸውን ድርሻ ያለምንም ማደናገር በተገቢ ሁኔታ ተወጥተዋል፡፡

የዚህ ነጠላ ዜማ አጠቃላይ ይዘት፣ ከያኒው አሁን ካለንበት አገራዊ ሁኔታ ላይ በመቆም፣ ኃላፍያቱን ወደ ኋላ ተመልሶ እየሰፈረ፣ መጻእያቱን ከወዲሁ አስቀድሞ የለካበት፣ የከያኒው የጥበብ ቀላድ ሲሆን፣ ኪነት፣ ውበት፣ እውነት፣ ምክርና ተግሳጽ ተባብረው ያገዘፉት፣ ጥበባዊ ሥራ መሆኑን ለመመስከር አንዳች የሚገደን ነገር የለም፡፡

ከያኒው፣ በዚህ አዲስ ነጠላ ዜማው ግጥም ውስጥ፣ ከመጀመርያው ስንኝ እስከ መጨረሻው ስንኝ ድረስ፣ ትክክለኛ ቦታ ተሰጥቷቸው የተሰደሩት ናዕት፣ እልፍ፣ አእላፍ፣ ድውይ፣ ህላዌ፣ ዋዌ፣ ዘውግ፣ ሰብእእቶን የሚሉት ቃላት፣ ሥርወ መነሻቸው የግእዝ ቋንቋ ሲሆን፣ ትርጉማቸውም በቅደም ተከተል፣ ቂጣ፣ አንድ ሺሕ፣ አሥር ሺሕ፣ ሕመምተኛ ወይም በሽተኛ፣ ባሕሪ-ኑሮ-አኗኗር፣ የውስጣዊ ስሜት ንረት፣ ጎሳ ወይም ዝርያ፣ ሰውከፍተኛ የግለት ቃጠሎ ያለው ምድጃ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ግእዝ ወለድ ቃላት፣ ለነጠላ ዜማው ግጥም ጥፍጥናም ሆነ በጭብጥ ደድሮ መገኘት ያበረከቱት አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

አንድ ከያኒ፣ የተዋጣለት ጥበባዊ ሥራ ለመሥራት፣ ግለ ሰብእናው በአራት ጥበባዊ የፈጠራ ሒደቶች፣ በትክክል የሚያልፍና በእነዚህ ጥበባዊ የፈጠራ ሒደቶችም የተገራ ማንነት ሊኖረው እንደሚገባ፣ በርካታ የዘርፉ ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡  እነዚህ አራት ቅደም ተከተላዊና ጥበባዊ የፈጠራ ሒደቶችም፣ አስተውሎትን የተላበሰ ጥልቅ ምልከታ (Observation)፣ አካባቢያዊ የሕይወት ክስተቶች ተጋሪነት (Sensitivity)፣ ከበርካታ የሕይወት ሁነቶች መካከል፣ ለጥበባዊ የፈጠራ ሥራ ጭብጥነት የሚያገለግል ዓብይ ርዕሰ ጉዳይን ነቅሶ የመለየት ብቃት (Selectivity) እና የመረጠውን ዓብይ ርዕሰ ጉዳይ መነሻ በማድረግ፣ ጥልቅ ወደ ሆነ ጥበባዊ ምናብ (Imagination) ውስጥ መግባት ሲሆኑ፣ በማንኛውም የኪነ ጥበብ ዘርፍ የተሳካለትና የተዋጣለት ጥበባዊ የፈጠራ ሥራን እንካችሁ ለማለት የታደለ ማንኛውም ከያኒ፣ ዓይነቱና መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ እነዚህን ጥበባዊ የፈጠራ ሒደት ቅደም ተከተሎች፣ በትክክል ሲተገብር ይስተዋላል፡፡ እነዚህን ጥበባዊ የፈጠራ ሒደቶች፣ አንድ ባንድ ሙያዊ ትርጓሜያቸውን ለአንባብያንና ለአንባብያት ግልጽ ለማድረግ ያህል፣ ትንሽ ማብራሪያ አጋርቶ ማለፍ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

አስተውሎት የተላበሰ ጥልቅ ምልከታ (Observation) ስንል፣ ከያኒው በሚኖርበት አካባቢ ወይም አገር፣ እየሆኑ ያሉትን አሉታዊና አዎንታዊ ማኅበራዊ ሁነቶችን፣ ደርዝ ባለው የንቃተ ህሊና አረዳድ በትክክል መገንዘብ መቻል ማለት ነው፡፡

አካባቢያዊ የሕይወት ክስተቶች ተጋሪነት (Sensitivity) ስንል ደግሞ፣ ከያኒው እየተገነዘበው ያለውን ማኅበራዊ ሐሴት ወይም ምስቅልቅሎሽ፣ በዜጎች ህልውና ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመረዳት፣ በሚኖርበት ማኅበረሰብ ጫማ ውስጥ ተረከዙን አስገብቶ በመቆም፣ የማኅበረሰቡን የደስታና የሐዘን ስሜት አብሮ መጋራት ማለት ነው፡፡

ሌላውና ሦስተኛው የጥበባዊ ሥራ የፈጠራ ሒደት፣ ለጥበባዊ የፈጠራ ሥራ ጭብጥነት የሚያገለግል ዓብይ ርዕሰ ጉዳይን ነቅሶ የመለየት ብቃት (Selectivity) የሚለው ሲሆን፣ ከያኒው ከተመለከታቸውና ከተገነዘባቸው በርካታ ማኅበራዊ ሁኔታዎች መካከል፣ የበለጠ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባውንና ስሜቱን የበለጠ ያስደሰተውን ወይም የቆጠቆጠውን በመለየት ለጥበባዊ ሥራው ዓውድነት መምረጥ መቻል ማለት ነው፡፡

አራተኛውና የመጨረሻው የጥበባዊ ሥራ የፈጠራ ሒደት ደግሞ፣ ጥልቅ ወደ ሆነ ጥበባዊ የምናብ ተብሰልስሎት (Imagination) ውስጥ መግባት የሚባለው ሲሆን፣ በታደልነው ወይም በተሠራንበት ጥበብን የመጠበብ አቅም ልክ፣ ከበርካታ የኪነ ጥበብ ዓይነቶች መካከል፣ ለውስጣችን የሚቀርበንን አንዱን በመከተል፣ ወደ ምናባዊው የየግላችን የፈጠራ ዓለም (Imaginative World) የመረጥነውን ዓብይ ርዕሰ ጉዳይ ይዞ በመጓዝ ፈጠራዊ ሥራችንን መሥራት ማለት ነው፡፡

የዚህን ነጠላ ዜማ ግጥም በኪነት፣ በውበት፣ በይዘትና በጭብጥ መበልፀግ መነሻ አድርጌ፣ በራሴ አረዳድ ልክ ከያኒውን ስገመግመው፣ አራቱንም የጥበባዊ ሥራ የፈጠራ ሒደቶች፣ በትክክል አሟልቶ አግኝቼዋለሁ፡፡

ከያኒው፣ አገሩ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከመገንዘብ በላይ፣ በትክክል እየኖረው ለመሆኑ፣ ይኼ ጥበባዊ ሥራው ምስክር ሲሆን፣ የሚሠራውን ወይም ምን መሥራት እንዳለበት ከወዲሁ ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑን ለመገንዘብም፣ ይኼ የጥበብ ሥራው፣ የቤት ሥራችንን የሚያቀልልን ዋቢ መሆን ይችላል፡፡

የግጥሙን ኪነተ ልዕልና ከፍ ለማድረግና የግጥሙን ስንኞች በመካከላቸው የሚያደናቅፍ እንቅፋት ሳይኖር በትክክል ለማሰናሰል የተጠቀመበት ሥልት እንዲሁም የግጥሙን ቀልብ የመሳብና ስሜትን ቆንጥጦ የመያዝ ጥበባዊ ብርታት ከፍ ለማድረግ፣ በግጥሙ ውስጥ የከለሳቸው ጥበባዊ ቅመማት (Artistic ingridients) የከያኒውን ምናብ ጥልቀትና ምጥቀት ፍንትው አድርገው ያሳዩናል፡፡

አንባብያንና አንባብያት፣ የከያኒው አገልግሎት እንደተቀደሱት የእግዚአብሔር ንዋያት፣ ያለጊዜውና ያለቦታው ለማሽቃበጥ አይገለጥም፡፡ ሰነፍ እንዳሰረው ነዶ በየሠፈሩ አለመዝረክረኩና የግላዊ ሰብእናው ቁጥብነትም ኪናዊ ውድነቱን አጉልተውለታል፡፡

በአጠቃላይ ከያኒው፣ እግዚአብሔር በቸርነቱ በዚህ ሰው በሚያሰኝ ሰው አልባ ዘመን፣ ለኢትዮጵያ የለገሳት ልዩ እና የተቀደሰ በረከት ነው በማለት ጽሑፌን እየቋጨሁ በመጨረሻም፣ የእናቴ ልጅ ወንድም ዓለሜ፣ ከያኒ ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ለዚህ ለለገስከን ኪናዊ የጥበብ እፍታ፣ ካለሁበት ባለህበት ምስጋናዬ ይድረስልኝ በማለት እሰናበታለሁ፡፡ ይቆየን፡፡ ያቆየንም!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በንጋት ኮርፖሬት የአምባሰል የንግድ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከፍተኛ የግብይት ጥናትና የማስታወቂያ መኰንን፣ እንዲሁም በልቀት የንግድ ሥራ አመራርና ኪነ ጥበባት ኮሌጅ የፊልም አሠራር ጥበብ መምህር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles