Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልዒድ አል አድሓ/ ዓረፋ

ዒድ አል አድሓ/ ዓረፋ

ቀን:

እስላማዊው ቅዱስ ቀን ዓረፋ፣ በዓመተ ሒጅራ መሠረት በሐሳበ ጨረቃ በ12ኛው ወር ዙልሂጃ 10ኛ ቀን – ዘንድሮ በፀሐይ ሐምሌ 2 ቀን 2014-  ላይ ይውላል፡፡ ዒድ አል አድሓ የመስዋዕት በዓል ተብሎ ይከበራል፡፡ ይሄም ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እስማኤልን ለመስዋዕት ሲያዘጋጁ በምትኩ በግ የቀረበበት መሆኑ ያመላታል ይላሉ ድርሳናት፡፡

‹‹ዓረፋ እና ዒድ አል አድሓ›› በሚል በተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ እንደተመለከተው፣ ዒድ አል አድሓ በመታዘዝ የተገኘ የድኅነት መገለጫ ነው፡፡ እነዚህ ቀናት አደምና ሐዋን ከጥፋት በዓረፋ ጊዜ ያገናኘ፣ ነቢዩላህ ኢብራሂምም መሥዋዕትነት በፈጣሪ መዳኑን ያረጋገጡላቸው ተምሳሌቶች ናቸው፡፡

የዒድ አል አድሓ ቀናት ዳግም ከፈጣሪ ጋር መታመንን የሚያስገኙ ኢስላማዊ አስተምህሮ በዓላት ናቸው፡፡ የዓረፋ በዓል የሐጂ ሥነ ሥርዓት የሚከናወንበት በዘጠነኛው ቀን ነው፡፡ በ10ኛው ቀን ደግሞ ዒድ አል አድሓ የስግደት እና የሶላት በዓል ነው፡፡ ዓረፋ ማለት ቀኑ ነው፡፡ አደም እና ሐዋ በጀነት ሲኖሩ እንዳይነኩ የተከለከሉትን በዲያብሎስ አማካይነት ስተው ወደ ምድር በተሰደዱበት ጊዜ ሁለቱም ተለያይተው ነበር፡፡ ለበርካታ ዓመታት ተለያይተው ከኖሩ በኋላ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ዓረፋት በሚባል ቦታ የተገናኙበትም ነው ይላል አስተምሮቱ፡፡

- Advertisement -

‹‹ሁለቱም ‘አረፍ’ ተባባሉ፡፡ አረፍ ማለት ‘አወቅከኝ? አወቅሽኝ?’ ማለት ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ መላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በዚህ በ9ኛው ቀን በቦታው በመዋል ከፍተኛ መንፈሳዊ ጸጋን መጎናጸፍ እንደሆነ ያምናል፡፡ የሒጅራ ጉዞ ከእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮዎች አንዱ ነው፡፡ ተከታዮችም ወደእነዚህ ቅዱስ ቦታዎች በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ እንዲሄዱ ያዝዛል፡፡ በሐጂ ሥነ ሥርዓት ‘ረብ’ የሚባሉ ጠጠሮችን ይወረወራል፤ የጌታ ሰው ነቢዩ ኢብራሂም ለአምላካቸው ያላቸውን ታዛዥነት ለመገምገም ሰይጣን ፈትኗቸው ነበር፡፡ በዚህ ተራራ ላይ በመሆን ክፋቱን ጠጠር በመወርወር አባሮታል፡፡ ይህን ለማስታወስ አሁንም ጠጠር ይወረወራል፡፡ ሐጂ ሐዋና አደምን ያገናኘበት ወቅት መዘከሪያ ነው፡፡

‹‹ዓረፋ›› እና ‹‹ዒድ አል አድሓ›› በሚል ርዕስ  አፈንዲ ሙተቂ እንደጻፉት፣ የዒድ አል-አድሓ ታሪካዊ ዳራ ደግሞ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለአላህ ለመሰዋት ያደረጉት ቁርጠኝነት የተመላበት ውሳኔና ለመስዋዕትነት የቀረበው ልጅ ያሳየው የተለየ ጽናት ነው፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም የበኩር ልጃቸው የሆነውን ኢስማኢልን ያገኙት በእርጅና ዘመናቸው ነው፡፡ ታላቅ ሚስታቸው ሳራ ለፍሬ ባለመብቃቷ ‹‹ያ አላህ ያለ ዘር አታስቀረኝ፤ እኔን የሚተካ ሷሊህ የሆነ ልጅ ስጠኝ›› በማለት ዱዓ አደረጉ፡፡

በዚሁ መሠረት በሳራ ፈቃደኝነት ሐጀራ የምትባለውን የቤት ሠራተኛቸውን አገቡ፡፡ ሐጀራም ኢስማኢል የተባለ ልጃቸውን ወለደችላቸው፡፡ ይህ ልጅ በአላህ ፈቃድ በመካ ከተማ እንዲያድግ የተወሰነ ስለነበረ ኢብራሂም ሐጀራን እና ኢስማኢልን ወደ ዓረቢያ ከተማ ወሰዷቸው፡፡  

ኢስማኢል ካደገ በኋላ ደግሞ አላህ ‹‹ልጅህን እንድትሰዋ ታዘሃል›› የሚል ትዕይንት በህልማቸው አሳያቸው፡፡ የነቢያት ህልም ደግሞ ከራዕይ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ ኢብራሂም በህልማቸው ያዩትን በዝምታ አላለፉትም፡፡ በወቅቱ የሆነውን ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይተርካል፡፡ ‹‹ከርሱ ጋር ለሥራ በደረሰ ጊዜም ‹ልጄ ሆይ! እኔ በህልሜ የማርድህ ሆኜ አይቻለሁ፤ (እስቲ አንተም ነገሩን) ተመልከት፤ ምን ይታይሃል አለው፡፡ (ልጁም) ‹‹አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ፈጽም፤ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ አለ፤››

‹‹የዙልሂጃ ወር በገባ የሚኖሩት የመጀመርያዎቹ አሥር ቀናት በጾም በጸሎት ያልፋሉ፡፡ ይህ ጾም ግን እንደ ረመዳን ጾም ግዴታ አይደለም፡፡ ነገር ግን በፈጣሪ ዘንድ ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል፡፡ ጾሙ ሲገባደድ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ይደምቃል፡፡ የዕርድ በዓል በመባል ለሚታወቀው የዓረፋ በዓል ከተገኘ በግ፣ ፍየል፣ በሬ የመሳሰሉትን ማረድ ግድ ይላል፡፡ አቅሙ ለሌላቸው ደግሞ ሰደቃ መስጠት ኢስላማዊ ግዴታ ነው፡፡

ስለ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ማኅበራዊ ተቋማት አትቶ በመጻፍ የሚታወቀው አፈንዲ ሙተቂ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደሚያብራራው፣ ሐጅ በሚባለው አምስተኛው የእስልምና ማዕዘን (አርካን) ውስጥ ከሚፈጸሙት መንፈሳዊ ሥርዓቶች መካከል በዙልሒጃ ወር ዘጠነኛ ቀን የሚከናወነው ‹‹አል-ዉቁፍ ቢዐረፋት›› (በዐረፋ ቆሞ ጸሎት ማድረግ) ቀዳሚው መሠረቱ ከነቢዩ አደም ጋር የተገናኘው ታሪኩ ነው፡፡

ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ሐጃጆች ብሔር፣ ጾታ፣ ቀለም፣ አህጉር፣ ሀገር፣ ክፍለ ሀገር፣ መደብ፣ ሥልጣን፣ የሥራ መደብ፣ ወዘተ ሳይገድባቸው በአንድ ቦታ ቆመው የአዳም ልጆች መሆናቸውን ያስመሰክራሉ፡፡

‹‹ታዲያ በዚሁ ቀን ሁለት ትልቅ ድርጊቶች ተከናውነዋል፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) በታሪክ ገጾች The Masterpiece Sermon of Prophet Mohammed እየተባለ የሚጠራውን ታላቅ ዲስኩራቸውን ያሰሙበት ዕለት መሆኑ ነው፡፡ ነቢዩ ንግግራቸውን የጀመሩት ‹ሰዎች ሆይ! ከዚህ በኋላ በናንተ መካከል ላልገኝ እችላለሁ፤ ስለዚህ ልብ ብላችሁ አድምጡኝ› በሚል ዓረፍተ ነገር ነው፡፡ በርግጥም ነቢዩ ከዚህ የመሰናበቻ ንግግራቸው በኋላ በሕይወት ብዙም አልቆዩም፡፡ ቢሆንም ከነቢዩ ንግግሮች መካከል በደንብ የተመዘገበው ይህ ንግግራቸው ነው፡፡ በሐዲስ ምሁራን ዘንድ የቃላትና የሐረጋት ልዩነት ሳይደረግበትና በእውነተኛነቱ ላይ ጥርጣሬ ሳይጣልበት (‹‹ሰሒሕ›› እና ‹‹ደዒፍ›› ሳይባል) ተቀባይነትን ያገኘው ይህ የሐጀቱል ወዳዕ ንግግራቸው ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ንግግሩ በመቶ ሺህ ሕዝብ የተሰማ መሆኑ ነው፡፡

‹‹ይህ ቀን የሚታወስበት ሁለተኛው ታላቅ ክስተት የቅዱስ ቁርአን የመጨረሻው አያህ (አንቀጽ) የወረደበት ዕለት መሆኑ ነው፡፡ አዎን!! ‹ኢቅራእ› በሚለው መለኮታዊ ቃል የጀመረው መጽሐፍ በዚህ ዕለት በሱረቱል ማኢዳ ውስጥ በሚገኘው ሦስተኛው አንቀጽ ተጠናቅቋል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ውስጥ እስላማዊውን ርዕዮት ለዓለም የማዳረሱ ተልዕኮ በከፍተኛ ስኬት መጠናቀቁን የሚገልጸው ዐረፍተ ነገር ይገኛል፡፡ እንዲህም ይላል፡- ‹ዛሬ ለናንተ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፤ ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ፤ እስልምናንም በሃይማኖትነት ወደድኩላችሁ›፡፡››

ዓረፋ ሲከበር

በኢትዮጵያ በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ደቡብ ወሎ ይገኝበታል፡፡ የደቡብ ወሎ ምዕመናን የበዓሉ ዕለት ማልደው በመነሳት ገላቸውን ታጥበው ለበዓሉ የገዙትን አዲስ ወይም የታጠበ ልብስ ለብሰው የሚሰግዱበትን አነስተኛ ምንጣፍ መስገጃ አንጠልጥለው በጀመዓ (በኅብረት) ወደ ሚሰግዱበት ስታዲየም ያመራሉ፡፡ ከመስገጃው ቦታ እስኪደርሱ  ተክቢራ  (ፈጣሪን ማወደስ) ይላሉ፡፡ ከቦታው ወንዶች ለብቻ ሴቶች ለብቻ ሆነው በጀመአ ይሰግዳሉ፡፡

  በደቡቡ የአገሪቱ ክፍል በሚገኘው የስልጤ ዞን ስላለው የዓረፋ በዓል አከባበር የመስክ ጥናት ያደረገው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡ የኢንታንጀብል (የማይዳሰሱ) ባህላዊ ቅርሶች ምዝገባ (ኢንቬንተሪ) ብሎ ባሳተመው ድርሳን የሚከተለውን አስፍሯል፡፡

በስልጤ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረው ትልቅ በዓል ዓረፋ ነው፡፡
ዓረፋ ገና ከመድረሱ ቀደም ብሎ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ከፍተኛ ዝግጅት ይጀመራል፡፡ ሴቶች ቅቤ፣ ቅመማ ቅመምና ቆጮ ያዘጋጃሉ፣ አባወራዎች ለእርድ የሚሆን ሠንጋና የማገዶ እንጨት ያቀርባሉ፡፡ ልጃገረዶች ቤቶቹን በተለያዩ የማስዋቢያ ቀለማት በመጠቀም ይቀባሉ፣ ግቢን ያፀዳሉ፡፡ በበዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ለወላጆቻቸው ስጦታ በመያዝ ወደየአካባቢያቸው ይገባሉ፡፡ በዓረፋ ወደ ቤተሰቡ ያልመጣ በሕይወት እንደሌለ ይቆጠራል፡፡ ቤተሰብንም ሥጋት ላይ ይጥላል፡፡

 በበዓሉ ሰሞን የሚጀመረው የልጃገረዶች ጭፈራ ተጠቃሽ ነው፡፡ በየመንገዱ ያሉ ልጃገረዶች ከአካባቢያቸው ራቅ ብለው በመሄድ በነፃነት የሚጫወቱበትና የሚጨፍሩበት ወንዶች ወጣቶችም በመሄድ አብረው ሲጫወቱ የትዳር አጋራቸውን ያጩበታል፡፡ በዚህም የዓረፋ በዓል በአብዛኛው የመተጫጫ የጋብቻ ወቅት ነው፡፡

በበዓሉ ዋዜማ የሚከበረው የሴቶች ዓረፋ ሲሆን የወንዶች ደግሞ የበዓሉ ስግደት በሚከናወንበት ዕለት ነው፡፡ በሴቶች ዓረፋ ክልፋን (የተከተፈ ጐመን) አተካና (ቡላ፣ አይብና ቅቤ) የተለመዱ ባህላዊ ምግቦች ናቸው፡፡ እርዱ የሚከናወነው በበዓሉ ዕለት በሽማግሌ ከተመረቀ በኋላ ነው፡፡

  • ቅንብር በሔኖክ ያሬድ
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...