Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየግብርና ምርቶች መለያ ትግበራ

የግብርና ምርቶች መለያ ትግበራ

ቀን:

ለግብርና ምርቶች መለያ (ብራንድ) መስጠት ለአምራችና ለሸማች አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተለይም የምርት መለያ አምራቾች በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የተዛቡ የገበያ ሰንሰለቶችን ለመቅረፍ እንዲችሉ ያግዛል፡፡

በምርት ግብይት ማዕቀፍ ውስጥ ከመወዳደርያ አቅም መለኪያዎች አንዱ የሆነውን የምርት መለያ ኢትዮጵያ ለቡና ግብይቷ የምትጠቀመው ሲሆን አሁን ደግሞ ለድንችና ለሌሎችም ጥቅም ላይ ማዋል ጀምራለች፡፡

በኢትዮጵያ በበርካታ ቦታዎች ድንች የሚመረት ሲሆን፣ በተለይም በአማራ ክልል ምርቱ እየጨመረ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአማራ ክልል በአዊ ዞን፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም በስፋት እንደሚመረትም የክልሉ የግብርና ጥናት ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአዊ ድንች

በክልሉ በ2013 ዓ.ም. ከ33 ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ ከ16 ሺሕ በላይ ሔክታር አዊ ዞን ውስጥ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በዓመቱ ከተመረተው ከ5 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ውስጥ ከ1.5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ከዚሁ ዞን የተገኘ ነው፡፡

አቶ መዝገቡ አያሌው አዊ ዞን ጓኩሳሽ ኩዳድ ወረዳ ወንጀላ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡

ለበርካታ ዓመታት በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያግዙ ያስረዳሉ፡፡

በአነስተኛ ማሳቸው የአበባ ድንች የተሰኘውን ዝርያ የሚያመርቱ መሆኑን፣ ምርቱን ከዕለት ጉርሻ በተጨማሪ በርካሽ ዋጋ ለጎረቤቶቻቸው እንደሚሸጡ ይገልጻሉ፡፡

በወዳረው አቶ መዝገቡን ጨምሮ በርካታ አርሶ አደሮች ድንች የሚያመርቱ ቢሆንም፣ የግብይት ትስስር ችግር በመኖሩ ኑሯቸውን ሊለውጡ አልቻሉም፡፡

በወረዳው ከሚስተዋለው ገበያ ትስስር ችግር በተጨማሪ የድንች ምርታማነት አለማደግ፣ የመጋዘንና የገበያ መሠረተ ልማት አለመኖር እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ አናሳ መሆኑን አቶ መዝገቡ ተናግረዋል፡፡

የጓኩሳሽ ኩዳድ ወረዳ አርሶ አደር እንደተናገሩት፣ ብዙ የለፉበትን የድንች ምርት የሚሸጡት ነጋዴዎችን ለምነው ነው፡፡ በመሆኑም በምርታቸው ላይ ዋጋ የመተመን መብት የላቸውም፡፡ ይህም ልፋታቸውን መና እያስቀረ ይገኛል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ የተለያዩ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ሲሆን ከእነዚህ አንዱ ለምርቶች መለያ (ብራንድ) መስጠት ነው፡፡  

የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ወልደተንሳይ መኮንን እንዳሉት፣ 23,269 ኅብረት ሥራ ማኅበራትና 72 ዩኒየኖች ይገኛሉ፡፡

ኅብረት ሥራ ማኅበራቱ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ገበያ የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ከሚቀርቡት ውስጥም በአሥር ዓመት የስትራቴጂክ ዕቅድ ውስጥ አሥር ምርቶችን መለያ ለመስጠት ታቅዷል፡፡

ከአሥሩ የተለያዩ ምርቶች መካከል የአዊ ድንች፣ የአርባ ምርጭ ሙዝና የጨንቻ አፕል መለያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ምርቶቹ በገበያው ተፈላጊና ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በዘንገና አትክልትና ፍራፍሬ ኅብረት ሥራ ዩኒየን አማካይነት ለገበያ እንደሚቀርቡም ገልጸዋል፡፡

በአዊ ዞን በአነስተኛ ማሳ የተሰማሩ 69,948 አርሶ አደሮች በ10,332 ሔክታር የእርሻ መሬት ላይ የድንች ምርት እያመረቱ እንደሚገኙና በዞኑ የአየር ሁኔታው ድንችን ለማምረት አመቺ በመሆኑ ምርቱ በዓመት ሦስት ጊዜ እንደሚደርስ፣ አክለዋል፡፡

በምርምር ጣቢያ በሔክታር 400 ኩንታልና በአርሶ አደር መሬት ደግሞ በሔክታር ከ300 ኩንታል በላይ እንደሚመረት የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ቢያሳይም፣ የድንች ዝርያዎቹን አርሶ አደሩ ለበርካታ ዓመታት ሲጠቀምባቸው የቆየ በመሆኑ፣ በአሁኑ ሰዓት በአማካይ በአንድ ሔክታር 200 ኩንታል እያመረቱ መሆኑን አርሶ አደሮች ያስረዳሉ፡፡

የጨንቻ አፕል

በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን የጨንቻ ደጋ ፍራፍሬ ኅብረት ሥራ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አጌና እንደተናገሩት፣ የጨንቻ አፕል ዕውቅና ማግኘቱ፣ ከአገር ውስጥ በተጨማሪ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ያስችላቸዋል፡፡

በጨንቻና አካባቢዋ አፕል በስፋት የሚመረት ሲሆን፣ 66 ዝርያዎች አሉት፡፡ ካሉት ዝርያዎች 24ቱ ፍሬ መስጠት እንደጀመሩ፣ አንድ ዛፍ እስከ 100 ኩንታል እንደሚገኝበት ገልጸዋል፡፡ በሰፊው የሚመረተው የጨንቻ አፕል ቋሚ የግብይት ትስስር፣ ያልደረሱ ምርቶችን በመልቀም የአካባቢውን የምርት ጥራት ሊያጎድል የሚችል ግብይትን የሚከለክል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ ሕገወጥ ነጋዴዎች መበራከትና የመሠረተ ልማት ችግሮች በመኖራቸው የተፈለገውን ያህል ጥቅም እያስገኘ አለመሆኑን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡

አንድ ኪሎ አፕል በጨንቻና አካባቢዋ በ50 ብር እንደሚሸጥ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች የሚሸጠው ከ150 ብር እስከ 200 ብር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጨንቻ ወረዳ ከአነስተኛ ማሳ ላይ አፕልና ፍራፍሬን የሚያመርቱ 242,906 አርሶ አደሮች በ7,773 ሔክታር የእርሻ መሬት ላይ እያመረቱ እንደሚገኙም አክለዋል፡፡

ቀደም ሲል በጋሞ ዞን ጨንቻ ወረዳ ብቻ የአፕል ምርት እንደሚመረት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዞኑ የሚገኙ ሰባት ወረዳዎች ወደ ማምረት መግባታቸውን፣ በዞኑ ከ24 በላይ የአፕል ዝርያዎች እንደሚገኙ፣ ከፍተኛ ምርት የሚገኘውም ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ወራት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ሙዝ

አቶ ይልማ ቆንስል የደቡብ ክልል ጋሞ ዞን አትክልትና ፍራፍሬ ኅብረት ሥራ  ዩኒየን የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ በዞኑ በተለይም አርባ ምንጭ ዙሪያ በሙዝ ምርት የሚታወቅ ሲሆን፣ ከ142,355 በላይ አርሶ አደሮችም በዚሁ ሥራ ተሰማርተው እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡

አርሶ አደሮቹ በ37,841 ሔክታር ማሳ እንደሚያለሙ የገለጹት አቶ ይልማ፣ በሔክታር በአማካይ ከ144 ኩንታል እስከ 219 ኩንታል ሙዝ ያመርታሉ ብለዋል፡፡

በአርባ ምንጭና ዙሪያዋ ሙዝ በማምረትና በመነገድ የሚተዳደሩ ቢኖሩም፣ አርሶ አደሮች ባመረቱት ምርት ላይ ዋጋ መወሰን እንደማይችሉና ከፍተኛ የሆነ የደላላ ጣልቃ ገብነት መኖሩን አቶ ይልማ ይጠቁማሉ፡፡

የሆነ የገበያ ትስስር አለመኖር፣ የቴክኒክ ድጋፍ ውስንነት፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የመስኖ ቴክኖሎጂ አለመዘመንና ሌሎችም ችግሮች መኖራቸውንም ያክላሉ፡፡

የአርባ ምንጭ ሙዝ ለአገር ውስጥ ገበያ ብቻ እየቀረበ መሆኑን የገለጹት አቶ ይልማ፣ መለያ ማግኘቱ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አመቺ እንደሚያደርገው ያላቸውን ተስፋ አጋርተዋል፡፡

ሙዝ በሚመረትባቸው አካባቢዎች አንድ ኪሎ 20 ብር መሆኑን፣ በአዲስ አበባና በሌሎች ትልልቅ ከተሞች ዋጋው በእጥፍ እንደሆነ፣ ይህም የሆነው በገበያ ሰንሰለት ውስጥ ደላሎች በመግባታቸው መሆኑንና አሁን ላይ በቀጥታ ምርቱን ለሸማች ለማቅረብ በሒደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ሙዝ ሁለት ዓይነት ዝርያዎች እንዳሉትና አጭርና ረዥም ተብለው እንደሚለዩ፣ አንድ የሙዝ ዛፍ ከ60 ኪሎ ግራም እስከ 80 ብሎ ኪሎ ግራም ምርት እንደሚሰጥ፣ እንደ መሬቱ ዓይነት የሚሰጠውም ምርታማነት እንደሚለያይ ተናግረዋል፡፡

በጋሞ ዞን ቆላማ ቀበሌዎች ላይ ሙሉ በሙሉ ሙዝ የሚያመርቱ መኖራቸውን፣ በተለይም አርባ ምንጭና ምዕራብ አባይ በይበልጥ እንደሚመረት ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አምራያ ሲራጅ እንደተናገሩት፣ ክልሉ አትክልትና ፍራፍሬ የማምረት ከፍተኛ አቅም አለው፡፡

በክልሉ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች የሚመረቱ ቢሆንም፣ በተለይም የአርባ ምንጭ ሙዝና የጨንቻ አፕል የጋሞ ዞን መለያ ከመሆናቸውም በላይ ለበርካታ አርሶ አደሮች የኑሮ መሠረት መሆናቸውን ወ/ሮ አምራያ ተናግረዋል፡፡

ሙዝና አፕል በሚመረትባቸው አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ምርቶቹን ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም 5,860 አርሶ አደሮች፣ በ30 ማኅበራትና በአንድ ዩኒየን በማደራጀት ምርትማነታቸውን ለማሳደግና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እንደተናገሩት፣ ዘርፉ በርካታ ችግሮች ያሉበት ሲሆን፣ አርሶ አደሮችም ላመረቱት ምርት ተገቢውን ዋጋ አያገኙም፡፡

በደላላ መዋከብ፣ የሚዛን ማጭበርበርና አርሶ አደሮች ባመረቱት ምርት ዋጋ መተመን እንዳይችሉ ማድረግ የተለመደ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ለምርቶቹ መለያ መስጠት ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ለግብርና ምርቶች የመለያ መስጠት ደቡብ ክልልን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ መገኛ መሆኑን ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በዓይነታቸው የተለዩ የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የአዊ ድንችና የጨንቻ አፕል መለያ (ብራንድ) መስጠት አስፈላጊ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል አገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መንደፏን አስታውሰው፣ በፖሊሲው መሠረት የአሥር ዓመት የስትራቴጂ ዕቅድም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር በአሥር ዓመት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረጉ አሥር ፕሮግራሞች ወደ ሥራ መገባታቸውን፣ ካሉት አሥር መርሐ ግብሮች የበጋ መስኖ ስንዴ አንዱ ማሳያ መሆኑን፣ ሌሎቹም በተለይ በአሥር ዓመት ውስጥ የሚተገበሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የግብይት ሰንሰለቱ ችግሮች እንዳሉበት የገለጹት ሶፊያ (ዶ/ር) ጥቂት ነጋዴዎችና እሴት የማይጨምሩ ሕገወጦች ብቻ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የተዛባ የግብይት ሥርዓት በመኖሩ፣ አምራቹና ሸማቹ በፍትሐዊነት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረጉን፣ ለገበያ የሚቀርቡት ደረጃ ወጥቶላቸውና የሚታወቁበት የመለያ ብራንድ ባለመኖሩ፣ በገበያ ተወዳዳሪነት እየተፈተኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከእነዚህ ችግሮች በመነሳት የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ምርቶቹ በሚገኙበት ክልሎች ማኅበራቱን በማጠናከርና ምርታማነትን በማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የግብርና ምርቶች ጥራትና ምርታማነትን መሠረት ያደረገ ብራንድ በማውጣት ለገበያ ለማቅረብ የሙዝ፣ አፕልና የድንች ምርትን በብዛትና በጥራት በማምረት የተዛባ የገበያ ሥርዓትን ለማስተካከል መለያው እንደሚረ አክለዋል፡፡

የምርት መለያ በግብይት ሥርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን እንደሚቀርፉና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እንደሚያግዝም አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኀብረት ሥራ ኮሚሽን አነሳሽነት በዓይነታቸው የተለዩ በኀብረት ሥራ ማኅበራት አባላት የሚመረቱ ‹‹የአርባ ምንጭ ሙዝ››፣ ‹‹የአዊ ድንች›› እና ‹‹የጨንቻ አፕል›› ምርቶች ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም.  በስካይ ላይት ሆቴል አዳዲስ መለያ ወይም ስያሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በተመሳሳይ በቀጣይ በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች በቅደም ተከተል የሚገኙትን የፍየል፣ ማንጎና ቀይ ሽንኩርት ምርቶች ብራንድ ለማድረግ የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...