Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየወንድሞቻችንና የእህቶቻችን ጠባቂ ማነው?

የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን ጠባቂ ማነው?

ቀን:

በዋካንዳ ኢትዮጵያ

በአገራችን ነባራዊ ሀቅ ክልሎች የተዋቀሩት በአብዛኛው ቋንቋንና ባህልን መሠረት አድርጎ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እያንዳንዱ ክልል የራሱ ሕገ መንግሥት፣ አስተዳደር፣ የተደራጀ ፖሊስ፣ ሚሊሻና ልዩ ኃይል አለው። ሁላችንም እንደምናውቀው እንዲህ ዓይነት የፌዴራል ሥርዓት በአገራችን ውስጥ የተተገበረው፣ ደርግን በትጥቅ ትግል ከሥልጣን በማስወገዱ ሒደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ የነበረው “ሕወሓት” ከሚያምንበትና ከታገለለት የፖለቲካ አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ ስለሆነ ነው።

ነገር ግን ራሳቸውን በአዲስ መልክ ከተደራጀው ክልል ሳይፈርጁ እንደ ቀደመው ልማድ “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉ፣ አገራቸው በካርታ ላይ የምናያት ኢትዮጵያ የምትባለው አገር መሆኗን የሚናገሩ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም ቦታ መኖር ሕገ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን፣ ለሰው ልጆች ሁሉ የታደለ መለኮታዊ ስጦታ እንደሆነ የሚያምኑ፣ ከቋንቋና ከባህል በፊት ሰው መሆን ይቅደም የሚሉ፣ ከደርግ ውድቀት በኋላ “የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል ድረስ” የሚለው ዕሳቤና ይህንን ገቢራዊ ለማድረግ የተፈጠረው የፌዴራል ሥርዓት በላያቸው ላይ በግዳጅ የተጫነባቸው እንደሆነ አምርረው የሚናገሩ፣ ነገር ግን የተለያየ ቋንቋና ባህል ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ምርጫ 97 ይህንን ዝም ብሎ የቆየን ኃይል አሳይቶን አልፏል።

ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች “ትምክህተኞች” ተብለው “በኢሕአዴግ” በመፈረጃቸው የደፈሩ ለዓላማቸው መስዋዕትነት ሲከፍሉ፣ አብዛኞቹ፣

አምባሰል አግድሞ የጁን ደግፎታል፣

የቆመውን አውሬ የተኛው በልቶታል፣

የቆመውን አውሬ የተኛው መብላቱ፣

ሥፍራው ቢደላው ነው በመመቻቸቱ፣

ብሎ የወሎ ገበሬ እንደ ገጠመው በቁጭት “ክፉውን” ጊዜ አሳልፈዋል።

አንዳንድ “የኢሕአዴግ” ባለሥልጣናትና ካድሬዎች፣ በመገናኛ ብዙኃን ብቅ እያሉ፣ “ትምክህተኞች” የሚሏቸውን “አርባ ሞፈር ቁልቁል ቆፍረው እንደ ቀበሯቸው” በከፍተኛ የመተማመን መንፈስ ይናገሩ ነበር። ነገር ግን ያ የምቾት ጊዜ ሲያልፍ ሞቷል የተባለው “ኢትዮጵያዊ” ማኅበረሰብ ከያለበት ብቅ አለ። በተለይ  ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተወካዮች ምክር ቤት የመጀመርያ ንግግራቸውን ሲያደርጉ ኢትዮጵያውያንን “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” ማለታቸው፣ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ለሚለው ለዚህ ማኅበረሰብ ትልቅ ተስፋ ይዞ ብቅ ብሎ ነበር። አብላጫ ድምፅ እንዳለውም አመላክቶ ነበር።

እርግጥ ነው በእነ  ዓብይ (ዶ/ር) የተመራው ለውጥ ከመጣ በኋላ፣ “ኢትዮጵያዊ ነን” በሚሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የነበረው “ትምክህተኞች” የሚለው ፍረጃ ቀርቷል። ነገር ግን በብሔር ጭቆና ሰበብ ዘረኝነትን በሚያቀነቅኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች በቀሰቀሷቸው ግጭቶች ሰለባ መሆናቸው አልቀረላቸውም። ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንጂ ክልል ስለሌላቸው እነሱን የሚጠብቃቸው በአጠገባቸው ያለ ልዩ ኃይልና ፖሊስ ወይም ሚሊሻ የላቸውም። ስለዚህ በቀላሉ ለጥቃት ተጋልጠዋል።

ማንም ግለሰብ የእንጀራ ገመዱ ወደ ሳበው ሥፍራ ያለ ሥጋት ለመኖር ዋስትናዎቹ ጎረቤቱ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሕግና ሥርዓት፣ ይህንንም የሚያስፈጽመው መንግሥት ነው። በአገራችን ግን እነዚህ አካላት በቸልተኛነት ይሁን አቅም አጥተው ወይም ፈርተው ከለላ ሊሆኑላቸው ባለመቻላቸው፣ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ ንብረታቸው ወድሟል፣ መንፈሳዊና ሥነ ልቦናዊ ስብራት ገጥሟቸዋል፣ ሕይወታቸው ተቀጥፏል። ነገር ግን የዚህ ሁሉ ችግር ዋነኛ መንስዔ በኢትዮጵያ ውስጥ “ሕወሓት/ኢሕአዴግ” የዘረጋው ሥርዓት መሆኑን መርሳት የለብንም።

የማኅበራዊ ሳይንስ አዋቂዎች እንደሚሉት ከሆነ የትኛውም የፌዴራል ሥርዓት አደጋ አለው። በተለይ የፌዴራል ሥርዓቱ የተዋቀረው በሃይማኖት፣ በጎሳ፣ በቋንቋና በባህል ከሆነ በብሔራዊ ስሜትና የሕግ የበላይነት ሊመራ ይገባዋል። አለበለዚያ ግን እኩይ ዓላማ ላላቸው የፖለቲካ ልሂቃን መጠቀሚያ በመሆን በእነዚህ ማኅበረሰቦች መካከል ዕልቂት ያስከትላል።

“ሕወሓት/ኢሕአዴግ” በአገራችን ውስጥ የዘረጋው የፌዴራል ሥርዓት “ሶሻሊስታዊ ፌዴራሊዝም” የተባለው ነው። የእዚህ ሥርዓት አመንጪዎቹ ኮሙዩኒስቶቹ ቭላድሚር ሌኒንና ጆሴፍ ስታሊን ናቸው። የሌኒንና የስታሊን መፍትሔ እንኳን ለኢትዮጵያ ለራሳቸው አገር ለሶቭየት ኅብረትም አልሠራላትም፡፡ ምክንያቱም በመጀመርያ ሌኒንም ሆነ ስታሊን “የራስን ዕድል በራስ መወሰን”ን የተጠቀሙበት በጊዜው ለተነሳው የብሔር ጥያቄ ጊዚያዊ ማስተንፈሻ እንዲሆን እንጂ፣ ከካርል ማርክስ የኮሙዩኒዝም ፍልስፍና ጋር ስለሚጣጣም አይደለም፡፡

ቀጥሎም መፍትሔ ተብየው ተግባር ላይ የዋለው ሁሉም መክረውበትና ተስማምተውበት ሳይሆን በኮሙዩኒስት ፓርቲው የበላይ አመራር ተቀነባብሮ በግድ የተጫነ ነበር። የኮሙዩኒስት ፓርቲው የብሔር ጥያቄን ላነሱት ሕዝቦች “የራስን ዕድል በራስ መወሰን”ን እንደ “መፍትሔ” አቅርቦ “በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት” አሠራር ሁሉንም በመፍቀድ፣ ሶቭየት ኅብረትን ለ74 ዓመታት በአምባገነንነት ገዝቷል።

ነገር ግን እ.ኤ.አ. በ1991 አምባገነኑ የኮሙዩኒዝም ሥርዓት ሲፈርስ የሶቭየት ኅብረትም ግብዓተ መሬት ተፈጸመ፡፡ መለያየት ጉርብትናን አያስቀርም። ጎረቤቱን የማያከብርና የማይወድ በሰላም መኖር አይችልም። ስለዚህ ዛሬ በሩሲያና በዩክሬን መካከል ያለው ጦርነት ምንጩ በከፊል ይኸው የከሸፈው ሥርዓት ነው።

እንግዲህ ይህንን ሥርዓትና አሠራር ነው “ሕወሓት/ኢሕአዴግ” እንደ ልዩና ህያው ጥበብ ቆጥሮ በከሸፈ በማግሥቱ ኢትዮጵያ ላይ የሞከረው። ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ በሶቭየት ኅብረት፣ በቼኮዝላቫኪያና በዩጎዝላቪያ ተሞክሮ አገርን ወደ መበታተን ያደረሰውን፣ እንዲሁም በአገራችን ኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት ሥራ ላይ ውሎ “የብሔር ብሔረሰቦችን መብት” በተግባር ማስከበር ያልቻለውን ሥርዓትና አሠራር እንዲቀጥል የሚጮኹ የፖለቲካ ልሂቃንና ድርጅቶች በአገራችን አሁንም መኖራቸው ነው። ሞተን ካላየን ሞት መኖሩን አናምንም እያሉ ይመስላል።

ጋዜጠኛ ዓለምነህ ዋሴ በልጅነቱ ወቅት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን አንድ ዓይነ ሥውር አህያን ከገደል ላይ እንዲወረወር በማድረግ ሲፈጠፈጥ ለማየት ያደረጉትን ሙከራ፣ በአንድ ቃለ ምልልስ ላይ ሲናገር አዳምጫለሁ። የሚያስገርመው ዓይነ ሥውሩ አህያ ሜዳ ሜዳውን እነ ዓለምነህ ዋሴ በመሩት መንገድ ሲሄድ፣ ገደል አፋፍ ላይ ሲደርስ ግን አልታዘዝም አላቸው። ግምት የማንሰጠው ዓይነ ሥውሩ አህያ ገደል ግባ ሲባል እንቢ ካለ እኛ የሰው ልጆችማ እንዴት አብልጠን እምቢ ማለት ይነሰን? ሌሎች ገደል ገብተው እያየን እኛም እንግባ ካልን ከእንስሳው ማነሳችን አይደለምን? እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከፈለግን አይቀር ተነጋግረን መግባባት ይኖርብናል። ምክንያቱም የሥርዓት ግንባታ ስኬት ሚስጥሩ የሩቁን ዓይቶ በምክር የተሠራ መሆኑ ነውና።

እንከን ቢኖርበትም በዓለማችን ላይ ተሞክሮ የተሳካው የፌዴራል ሥርዓት “ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም” የተባለው ነው። የስኬቱም ምክንያት በአገር ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች ውይይት አድርገው ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረሳቸው ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ጎራ የተሠለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ምልዓተ ሕዝቡ ተቀራርበው መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ተመካክረው መግባባት ላይ እንዲደርሱ ለማስቻል፣ “አገራዊ የምክክር ኮሚሽን” ተቋቁሟል። የእኔ ምኞት በዚህ መድረክ ላይ መሳተፍ የሚገባቸው ሁሉ ሐሳባቸውን በግልጽነት ለማስረዳት፣ የሌላውንም ለመስማት፣ ከዚያም ሁላችንንም የሚያግባባ የጋራ አቋም ላይ ለመድረስ ይገኛሉ ነው።

በተለይ “ፌዴራሊስት” ነን የሚሉ ሁሉ በዓለም ላይ ተሞክሮ የሠራን እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲኖር ከፈለጉ፣ በዚህ መድረክ ላይ መሳተፍ የሚኖርባቸው ይመስለኛል። እገሌ ካልተካፈለ ብሎ ራስን ከማግለል በምክክር ውስጥ እየተሳተፉ፣ በምክክሩ እንዳይገኙ ተገልለዋል ለሚሏቸው መጮህና መታገል ጨዋነት ነው። በአገሩ ጉዳይ ሁሉም ያገባዋልና የሚገለል መኖር የለበትም።

ስለዚህ ከላይ ያነሳኋቸውን “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉትን የማኅበረሰብ ክፍሎች በዚህ መድረክ ላይ እንዲሳተፉ መጋበዝ ያስፈልጋል። “ኢትዮጵያዊ ነን” ማለት (በግድ ካልፈረጅነው በስተቀር) የማንነት መገለጫ እንጂ፣ በአንድ ማኅበረሰብ የተወሰነ ወይም የፖለቲካ አመለካከት ስላይደለ በፖለቲካ ፓርቲዎች ሊወከል አይችልም። ትናንት “ሕወሓት/ኢሕአዴግ” ይህንን ማኅበረሰብ “ትምክህተኛ” ብሎ አግልሎ ትልቅ ስህተት ሠርቷል። ዛሬም ያንኑ ስህተት እንዳንደግም ከወዲሁ አሳስባለሁ።

 “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉ ሰዎች የተለያዩ ቋንቋና ባህል ካላቸው ማኅበረሰቦች ጋር አብሮ ለመኖር ራሳቸውን ያዘጋጁ ስለሆኑ፣ ሁላችንም ተግባብተን በጋራ ለምንገነባት አገር ጠቃሚ ናቸው። ለእነዚህ ሰዎች የተከለለ ክልል፣ የራሳቸው ሕገ መንግሥትና አስተዳደር፣ የሚጠብቃቸው ፖሊስ፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ያለ ሥጋት በየትኛውም የአገራችን ክፍል የሚኖሩበት ድባብና ድምፃቸው የሚሰማበት መድረክ ሊኖራቸው ይገባል። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን የመኖር “ደመነፍሳቸው” አስገድዷቸው ወደሚመስላቸው በመጠጋት የአገራችን ችግሮች የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ ተጨማሪ ችግር ይሆናሉ። ሥር ሳይሰድ ቅድሚያ ተሰጥቶ ወጥ ዕርምጃ መወሰዱን ቢያዩ፣ አገራቸው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ስለሚወዱ ዛሬ ከሚያስተጋቡት ቁጣና ምሬት ምልስ ይላሉ።

ቃየን ወንድሙን አቤልን አድብቶ ከገደለው በኋላ ፈጣሪ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” ብሎ ሲጠይቀው፣ “አላውቅም፣ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” ብሎ መለሰለት። ሁሉን የሚያውቀው አምላክ ይህንን ጥያቄ የጠየቀው ቃየን ኃላፊነትን ወስዶና በክፉ ሥራው ተፀፅቶ በንስሐ እንዲመለስ ነበር። ዛሬም በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች ንፁኃንን በግፍ ሲገደሉ ኃላፊነቱን እንኳ የሚወስድ የለም። ድርጊቱን ከማውገዝ ይልቅ ለፖለቲካ ትርፍ ከየአቅጣጫው የሚሰማው ጬኸት በተግባር “የወንድማችን ጠባቂ” ከመሆን በላይ እጅጉን ጎልቶ ታይቷል። የሟች ቤተሰቦች አማራ ሞተ፣ ኦሮሞ ሞተ፣ ትግሬ ሞተ፣ አፋር ሞተ፣ አኝዋክ ሞተ፣ ኢትዮጵያዊ ሞተ፣ ወዘተ ብለው አያለቅሱም። አባቴ አባቴ፣ እናቴ እናቴ፣ ወንድሜ ወንድሜ፣ እህቴ እህቴ፣ ልጄ ልጄ፣ ወዘተ ብለው ነው የሚያለቅሱት። የጠባቂነት ፍሬ ከኋላ ለቅሶና ፀፀት ይበልጣል።

ስለዚህ ሁላችንም የንፁኃን ወገኖቻችን ደም እንዳይፈስ፣ “የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን ጠባቂ” የመሆን ሞራላዊ ግዴታ እንዳለብን አውቀን የፀጥታ አካላት ዓይንና ጆሮ መሆን ይገባናል። እንደ ቃየን ወንድሙን አድብቶ የሚገድልን ፈጽሞ ማቆም ባይቻልም በትብብር ግን መቀነስ ይቻላል። ተባብሮ አገራችንን መታደግ እንጂ ሁሉን ነገር አንድ ሰው ላይ መደፍደፍ ፋይዳ የለውም። የክልል አስተዳደሮችና የፀጥታ አካላት በክልሎቻቸው የሚኖሩትን ዜጎች ሁሉ እኩል የመጠበቅ፣ እኩል የሕግ ከለላ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። ይህንን ካላደረጉ ደግሞ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብቶ የዜጎችን በነፃነት የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብት ያስከብራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለመቶ ሚሊዮን ሕዝብ መቶ ሚሊዮን ወታደር ጠባቂ ማድረግ አይቻልም ብለው ተናግረዋል። ማንም መንግሥት ይህንን ማድረግ አይችልም፣ ሕዝብም ይህንን ከመንግሥት አይጠብቅም። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት 11 ሚሊዮን አባላት ያለው ብልፅግና ፓርቲ አለ። ይህ ማለት ከኢትዮጵያ ሕዝብ አሥር በመቶ የብልፅግና ፓርቲ አባል ነው። ከአገራችን የቤተሰብ ብዛት አንፃር አንድ የብልፅግና ፓርቲ አባል በአማካይ ሁለት የቤተሰብ አባላት ይኖረዋል ብንል፣ 33 ሚሊዮን ሰው ከብልፅግና ፓርቲ ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግንኙነት አለው ብለን መደምደም እንችላለን።

እንግዲህ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 33 በመቶ የሚያክል ተከታይ ያለው ፓርቲ ከላይ እስከ ታች ለሰላምና ለሕግ የበላይነት በትጋትና በቁርጠኝነት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ቢሠራ፣ “የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን ጠባቂ” መሆን የሚያስችል አቅም አለውና ይጠቀሙበት። ከፓርቲውና ከሠራዊት ብዛት በላይ እስካሁን ከስንት መዓት ያወጣን ፈጣሪ እርሱ ይጨመርበት። ውዶቻቸውን በሞት ላጡት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ቤተሰቦች የርህራሔ አባት የመፅናናትም ሁሉ አምላክ ዕንባቸውን ያብስላቸው። አድብተው “የወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን” ሕይወት የሚያጠፉትን ማስተዋል ይስጥልን። የተቀረነውንም የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን ጠባቂዎች ያድርገን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...