Friday, September 22, 2023

የኮቪድ-19 የሥርጭት ስፋትን እንዲያሳይ የታለመው የዳሰሳ ጥናት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኮቪድ-19 የሥርጭት ስፋትን ማሳየት ይችላል የተባለው የዳሰሳ ጥናት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

እንደ አገር ያለውን የኮቪድ-19 የሥርጭት አድማስ ማወቅና ቫይረሱን ለመከላከል እንዲሁም ለመቆጣጠር መረጃን መሠረት ያደረገ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ የዳሰሳ ጥናቱ ዋና አላማ እንደሆነ የኢንስቲትዩቱ የባክቴሪያ፣ ፓራሳይቲክና የእንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክተር ገረመው ጣሰው (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ የሚከናወነው ከኅብረተሰቡ የደም ናሙናዎች ተሰብስቦ በደማቸው ውስጥ ባለው አንቲቦዲ በማየት ከቫይረሱ ጋር የነበራቸውን ንኪኪ ማወቅ ሲሆን፣ ለዚህም ዘመናዊ የመመርመሪያ መሣሪያዎች እንደተዘጋጁ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደገለጸው፣ ከትግራይ ክልል ውጭ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚደረገው ይህ ጥናት ዕድሜያቸው ከ15 በላይ የሆኑ የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡

የደም ናሙና የሚሰጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ፈቃደኝነታቸው የሚጠየቅ ሲሆን፣ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 18 ዓመት ድረስ የሆኑ ሕፃናት ደግሞ የቤተሰብና የአሳዳጊዎች ፈቃድ ይጠየቃል፡፡

በዳሰሳው ዶክተሮች፣ የላቦራቶሪ ባለሙያዎች፣ ነርሶችና በየአካባቢው የተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሲሆን ለሁሉም በቂ ሥልጠና እንደተሰጣቸው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ በአገሪቱ የሚጀምረውና ለአንድ ወር ለሚቆየው የዳሰሳ ጥናት ኅብረተሰቡ መንገድ በማሳየት፣ ቋንቋ በመተርጐም፣ እና ለምርመራ ፈቃደኛ በመሆን ለሥራው ውጤታማነት የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡

አሁናዊው የኮቪድ-19 መረጃ

በሐምሌ ወር የመጀመርያዎቹ አራት ቀናት በተደረጉ የላቦራቶሪ ምርመራዎች  ሦት ሰዎች መሞታቸውንና 455 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የጤና ሚኒስቴር በተከታታይ ባሠራጫቸው መረጃዎች አስታውቋል፡፡

በአጠቃላይ እስከ ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 490,486 መድረሱ፣ ከበሽታው ያገገሙትም 466,895 ሰዎች መሆናቸው፣ እንዲሁም 42.9 ሚሊዮን ሰዎች መከተባቸውንም መረጃው ያሳያል፡፡

ኮቪድ-19 ባለው ተለዋዋጭ ባህሪ ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ከፍ ዝቅ እያለ የኅብረተሰቡን ጤና እየጎዳ እንደሚገኝ በመዘናጋትና የመከላከያ መንገዶች ትግበራን ኅብረተሰቡ በመቀነሱ ወረርሽኝ እንደገና እየጨመረ መሆኑን መገለጹም ይታወሳል፡፡

ዕድሜያቸው ከ12 በላይ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያዳረሰና የመከላከል አቅም የሚያጠናከር ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ ባለፈው ሰኔ ወር ተካሂዶ ከ22 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መከተባቸውም ተመልክቷል፡፡

ሚኒስቴሩ በኮቪድ-19 ተይዘው በፅኑ ሕክምና ክፍል ዕርዳታ እያገኙ ያሉ ወገኖች መኖራቸውን፣ ክረምቱን ተከትሎም ኮቪድ-19ን ጨምሮ በንፅህና ጉድለት ሊመጡ የሚችሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ኅብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንፅህና በአግባቡ መጠበቅ እንዳለበት ማሳሰቡም ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -