Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሲሪላንካ ተቃውሞ

የሲሪላንካ ተቃውሞ

ቀን:

የሲሪላንካ ፕሬዚዳንት ከቤታቸው ከወጡ ዛሬ አምስተኛ ቀን አስቆጥረዋል፡፡ እሳቸው ከመኖሪያቸው የወጡት በፈቃዳቸው፣ ለጉብኝት አሊያም ለሥራ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሲሪላንካውያን ፕሬዚዳንታቸውን ተቃውመው ወደ ቤታቸው በመትመማቸው ነው፡፡

የ73 ዓመቱ የሲሪላንካ ፕሬዚዳንት ጎታባያ ራጃ ፓክሳ የአገሪቱን 22 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ ለኢኮኖሚ ቀውስ ዳርገዋል ያሉት ተቃዋሚዎች፣ የፕሬዚዳንቱን ቤት ገርስሰው የገቡበት ሁኔታ ለፀጥታ ኃይሎች ፈታኝ ነበር ተብሏል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ደኅንነቱ ወደ ተጠበቀ ሥፍራ ሲወሰዱ፣ በእሳቸው ፈንታ መኖሪያቸውን የተቆጣጠሩት ተቃዋሚዎች ቤቱን እንዳሻቸው ሲዝናኑበት በተንቀሳቃሽ ምስልና በፎቶግራፍ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ታይተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ዓለምን ያነጋገረው የሲሪላንካ ክስተት በሕዝብ ማዕበል የታጀበ ተቃውሞ ብቻ አይደለም፡፡ ለተቃውሞ የመጡ ሰዎች በፕሬዚዳንቱ ቤት ሲዋኙ፣ ሲመገቡ፣ ሲተኙ፣ በጂም ውስጥ እስፖርት ሲሠሩና ሲዝናኑ መታየታቸውም ነው፡፡

ከተማ አቋርጠው ኮሎምቦ የገቡ ተቃዋሚዎችም የፕሬዚዳንቱ ቅንጡ መኖሪያ ትንግርት እንደሆነባቸው፣ እነሱ ልጆቻቸውን የሚመግቡት አጥተው ባለሥልጣናት ተንደላቀው መኖራቸውን መታዘባቸውን ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡ የተሻለ ኑሮ እንዲመጣ ያስችለናል ያሏቸውን ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

ተቃዋሚዎች በሲሪላንካ ዋና ከተማ ኮሎምቦ ከሚገኘው የፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ከገቡ በኋላ ከመኖሪያው ለመውጣት የተለያዩ ጥያቄዎች እንዲመለሱላቸው መጠየቃቸውንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1948 ጀምሮ ለከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ተጋልጠናል የሚሉት ሲሪላንካውያን፣ ፕሬዚዳንት ራጃ ፓክሳና ጠቅላይ ሚኒስትር ማኔል ዊክሪሚስንጌ አሁኑኑ ሥልጣን እንዲለቁ፣ ከዚህ በኋላም ለስድስት ወራት የሚቆይ ጊዜያዊ መንግሥት እንዲመሠረት ጠይቀዋል፡፡

የተቃውሞ መሪዎቹ የፕሬዚዳንት ራጃ ፓክሳ ፓርቲ ያለበት ‹‹ኦል ፓርቲ ገቨርመንት›› በጊዜያዊ መንግሥቱ እንዳይገባም አሳስበዋል፡፡

ተቃዋሚዎች በለቀቁት የድርጊት መርሐ ግብር መሠረት፣ የፖለቲካ ሽግግርን ሲያቀነቅን ከነበረው ‹‹ጃናታ አርጋላያ›› በተውጣጡ አካላት የሕዝብ ምክር ቤት ማቋቋም የተቃዋሚዎች ጥያቄዎች ውስጥ ከጠየቋቸው ይገኙበታል፡፡

በዓመት ውስጥ አዲስ ሕገ መንግሥት እንዲዘጋጅ፣ የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን እንዲቀንስና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲጠናከሩ፣ አዲስ ሕገ መንግሥት እስኪረቀቅ ድረስ ጊዜያዊ መንግሥቱ እነዚህን እንዲያስፈጽም የሚሉ ሐሳቦችም ይገኙበታል፡፡

በአብዛኛው ወጣቶች የተሳተፉበት ተቃውሞን እመራለሁ ብሎ በመወከል የወጣ የፖለቲካ ድርጅት እንደሌለ የዘገበው አልጀዚራ፣ የግራ ክንፍ ሶሻሊስት ፓርቲ አቀንቃኞች የሆኑት፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረትና የሶሻሊስት ወጣቶች ኅብረት በ‹‹ጃናታ አርጋላያ›› ውስጥ የመሪነት ሚና እንደሚጫወቱም አስታውሷል፡፡

ከሶሻሊስት ወጣቶች ኅብረት ኢራኛ ጉናሳካራን ጠቅሶ አልጀዚራ እንዳሰፈረው፣ ጊዜያዊ መንግሥቱ መሠረታዊ የመዋቅር ማሻሻያ በማድረግ አዲሱ ትውልድ ወደ ሥልጣን እንዲመጣና በአጠቃላይ በምርጫ እንዲሳተፍ ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል፡፡

የሲሪላንካ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን እንደሚለቁ ያስታወቁ ሲሆን፣ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት የፓርላማው አፈ ጉባዔ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑን ይይዛል፡፡ የአሁኑ አፈ ጉባዔ ማሂዳን ያፖ የፕሬዚዳንቱ ዘመድ ቢሆኑም፣ ተቃዋሚዎች ለጊዜው ሕገ መንግሥቱ ላይ ያለውን ከመቀበል ውጭ ምርጫ የለም ብለዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ እስኪሻሻል ድረስ ምንም የተሻለ አማራጭ እንደሌለም አስታውቀዋል፡፡

ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንቱ ቤት ገብተው ባለሥልጣናት ሥራ እንዲለቁ ከመጠየቅ ባለፈ በተደራጀ መልኩ የሚፈልጉትን የሚያስፈጽም አካል የላቸውም፡፡ ሁሉም በየፊናው የተለያየ ፍላጎት እያንፀባረቀም ይገኛል፡፡ ከዋናው ምርጫ ቀድሞ ምርጫ ተደርጎ የተመረጠው አካል የተቃዋሚዎቹን ፍላጎቶች እንዲያሟላ የሚል ሐሳብም ተንፀባርቋል፡፡

ብዙዎቹ ቡድኖች ዋና ጥያቄ በሆኑት የፓርላማ 225 አባላትን ጨምሮ ባለሥልጣናት እንዲለቁ በሚለው ላይ ቢስማሙም፣ ሁሉም ቡድኖች የተለያየ አጀንዳ እንዳላቸው የአልጀዚራ ዘገባ ያሳያል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1978 ጀምሮ ሲሪላንካ በኤክስኪዩቲቭ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ስትመራ ቆይታለች፡፡ በ2015 የተመሠረተው የሪፎርም መንግሥት ለፕሬዚዳንቱ ተሰጥቶ የነበረውን በርካታ ሥልጣን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስተላለፈ ሲሆን፣ በጥቅምት 2020 ጎታባያ ራጃፓክሳ ፕሬዚዳንት ሆነው ዓመት ሳይሆናቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉትና በካቢኔ ባፀደቁት መሠረት ለራሳቸው የነበረው ሥልጣንም ተቀንሷል፡፡

ሲሪላንካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ የመድኃኒት፣ የነዳጅና ምግብ እጥረት እንደገጠማት ይታወሳል፡፡ የአሁኑን ተቃውሞ ተከትሎ ደግሞ አሜሪካ በሰጠችው አስተያየት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጦርነት ያስከተለው ቀውስ ነው ብላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...