Sunday, June 23, 2024

‹‹የክረምቱ ንጉሥ›› ሐምሌ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ክረምቱ ከባተ ዐሥራ አንደኛው ቀን ላይ ደርሷል፡፡ ክረምቱ ጫን ያለ፣ የአየር በረራዎችንም እስከማስተጓጎል እንደደረሰ የሰሞኑ ዜና ነበር፡፡

ከመደበኛ በላይና  መደበኛ ዝናብን እያሳየ መሆኑንና  በሐምሌ የመጀመርያዎቹ ሳምንታት ከፍተኛ የሆነ ነጎድጓዳማና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ እንደሚኖር ብሔራዊ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትም  ያሳሰበው ከጥንቃቄ መልዕክት ጋር  ነበር፡፡

በወሩ ከሚከሰተው የአየር ፀባይ አዝማሚያ ትንታኔና በውኃና በእርሻ ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ አስመልክቶ የገለጸውም ‹‹በተከታታይ ቀናት የሚኖረው የዝናብ መጠን ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ሊፈጥር ስለሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፤›› በማለት ነው፡፡

ወርኃ ሐምሌ ሲገለጽ

የዓመቱን ዙር ጠብቆ የክረምት ወቅት ከች አለ፡፡ ክረምት ሲመጣ ደስታን ይዘራል፣ ፍሥሐን ያነግሣል፡፡ በተለይ በአርሶ አደሩ ዘንድ፡፡ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር የወቅት አከፋፈል ባሕረ ሐሳብ መሠረት ሰኔ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. የክረምት ወቅት በይፋ ገብቷል፡፡ ሥልጣኑን የተረከበው ደግሞ ሰኔ 25 ከወጣው፣ ከተሰናበተው ፀደይ ከሚባለው በልግ ነው፡፡

በመዝገበ ቃላዊ ፍችው ክረምት ዝናም የዝናም ወራት፣ በፀደይና በመፀው መካከል ያለ የዓመት ክፍል ነው፡፡ ‹‹ለምድርም ዝናብን ይሰጣል፡፡ በተራሮችም ላይ ሣር ያበቅላል፡፡›› እንዲል፡፡

በስድስተኛው ምዕት ዓመት የኖረው ቅዱስ ያሬድ፣ በአራቱ የኢትዮጵያ ወቅቶች ላይ ተመሥርቶ ባዘጋጀው ድጓ በተሰኘው መጽሐፉ፣ ለክረምት መቀበያ ባዘጋጀው መዝሙሩ ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም›› – የዝናብ ኮቴው ተሰማ- ይላል፡፡ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ያዘኑ ይደሰታሉ፣ የተራቡም ይጠግባሉ ሲልም ያክላል፡፡

ሰኔ 26 ቀን የገባው የክረምት ወቅት የዝናብ ወራት በሐምሌና ነሐሴ ጳጉሜንም ይዞ መዝለቅ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ መስከረም ተሻግሮ እስከ 25ኛው ቀን ድረስ ይቆያል፡፡

ሐምሌ በብዙ ነገሩ የክረምትን ውበትና ጣዕም ያሳያል፡፡ ክረምትን ተከትለው የሚመጡት ለመብል የሚውሉት እነ በቆሎ፣ በለስና ስኳር ድንች ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ ክረምት ለማሰላሰያ ዕድል ይሰጣል የሚሉም አሉ፡፡ ተማሪዎችና መምህራን ሌሎችም ባመዛኙ የሚያርፉበት በመሆኑ የጽሞና ጊዜን እንዲያሳልፉ ዕድል ይሰጣል።

መዝሙረኛው እንደሚለው ሰማዩ በደመናት የሚሸፈንበት ለምድርም ዝናብ የሚዘጋጅበት ሣር በተራሮች ላይ የሚበቅልበት ለምለሙ ሁሉ ለሰው ልጆች ጥቅም የሚውልበት ነው ክረምት፡፡ በረዶውና ውሽንፍሩ ብርቱውም ዝናብ በምድር ላይ የሚወድቁበት ነው ክረምት፡፡

የደመናትን ንብርብር፣ ከድንኳኑም የሚሰማውን ነጎድጓድ ማን ሊያስተውል ይችላል? በረዶውን እንደ ፍርፋሪ ያወርዳል፣ በበረዶውስ ፊት ማን ይቆማል?  ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትም እንደተዘጋጁ ክረምትና በጋ (ሐጋይ) ፣ መፀው (መከር) እና ፀደይ  (በልግ) ለሰው ልጅ ሁሉ ተዘጋጁ፡፡

በአማን ነጸረ ‹‹የክረምት ጓዝና ቅኔያት›› በሚለው መጣጥፉ ዕፀዋትና ዝናም ያላቸውን ተዘምዶ የሚያጠቃቅስ የአንድ መምህር ቅኔን ምስጢር በአንድ ዓረፍተ ነገር ያጠቃለለው ‹‹ወዳጄ! የሰማይ ጉድለት፣ ምድርን በዕፀዋት ስትከድናት ይሞላል›› በሚል ነው አከለበትም፡፡ ‹‹ዕፀዋት ካሉ፣ ዝናማት አሉ! የዝናም መውረድ መቆም በዕፅዋት ነው!››

ሰኔ ላይ ግም ብሎ (‹ም› ይጠብቃል)፣ የሐምሌን ጨለማ፣ የነሐሴን ሙላት ተሻግሮ በመስከረም መሰስ ብሎ የሚወጣውን ክረምትን ባለቅኔዎች የዝናብ የዘመን (የወቅት) ለውጥ ጌታ ይሉታል፡፡ ገጣሚው ይህንኑ ንጥረ ሐሳብ እንዲህ አሳይቶታል፡፡

‹‹ሰኔ ደግሞ መጣ ክረምት አስከትሎ

ገበሬው ተነሳ ማረሻውን ስሎ፡፡

ሐምሌም ተከተለ ገባ ዝናብ ጭኖ

ቀንና ሌሊቱን በዝናብ ጨፍኖ፡፡

ነሐሴ ተተካ ኃይለኛው ክረምት

ያወርደው ጀመረ የዝናብ መዓት››

ክረምትና ክፍሎቹ

እስከ መስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚዘልቀው የክረምት ቆይታ በ95 ቀኖች ውስጥ፣ ዘጠኝ ንዑሳን ክፍሎችን እንደሚስተናግድ የስድስተኛው መቶ ዘመኑ ቅዱስ ያሬድ በጻፈው ‹‹ድጓ›› በተሰኘውና በአራቱ የኢትዮጵያ ወቅቶች ላይ በተመሠረተው ድርሰቱ እንደሚቀጥለው ተገልጿል፡-

(1) ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 18 ዘር፣ ደመና፣ (2) ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 9 መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ ወንዞች፣ ጠል፣ (3) ከነሐሴ 10 እስከ 27 የቁራ ጫጩት፣ ደሴቶች፣ የሁሉም ዓይን፣ (4) ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜን 5 – (6) ወጋገን፣ ንጋት፣ ጠዋት፣ ብርሃን፣ ቀን፣ ልደት፣ (5) ከመስከረም 1 እስከ 7 ዘመነ ዮሐንስ (6) መስከረም 8 ዘካርያስ፣ (7) ከመስከረም 9 እስከ 15 ዘመነ ፍሬ፣ (8) መስከረም 16 ሕንፀት፣ (9) ከመስከረም 17 እስከ 25 ዘመነ መስቀል ናቸው፡፡

የክረምቱ ዝናብ መዝነቡን ተያይዞታል፡፡ ይህ በተለይ ለአርሶ አደሩ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ክረምቱ ገበሬውን በሥራ የሚወጥር በመሆኑ ገበሬና ግብርናውን በሥነ ቃል አማካይነት ለመመልከት እንሞክራለን፡፡ ሥነ ቃል  ጎበዞችን በማወደስ፣ ሰነፎችን በመተቸት የሥራ መነሳሳት እንዲፈጠር ያግዛል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አቶ ዘሪሁን አስፋው በየሥነ ጽሑፍ መሠረታውያን መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ገበሬዎች በዓመቱ ወቅቶች ብዙ ሥራዎች እንደሚያከናውኑ እንደየአካባቢያቸው የአየር ንብረት፣ በጋ ከክረምት በማሳዎቻቸው ላይ የሚፈጽሟቸው የግብርና ሥራዎች እንደየባህላቸው በዘፈኖችና በእንጉርጉሮዎች ይታጀባሉ፡፡ መሬቱን ለእርሻ ከማዘጋጀት ጀምሮ እስከ ምርት ማስገባት ድረስ በየወቅቱ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ የተለያዩ ሥነ ቃላዊ ግጥሞች ያሰማሉ፡፡

ከእያንዳንዱ የሥራ ዓይነት ጋር የተጣጣሙ ግጥሞች ዜማ ተበጅቶላቸው ገበሬው ያንጎራጉራቸዋል፡፡ በሥነ ጽሑፍ መሠረታውያን የተጠቀሱትን አብነቶች አለፍ አለፍ እያልን እንመለከታቸዋለን፡፡  

በእርሻ ጊዜ ገበሬው ከሚያንጎራጉራቸው መካከል ጥቂቶቹን እነሆ፡-

የበሮቹ ቄስ የበሬው መምህር

አቆላላፊ ክምር በክምር

ሐምሌ ነሐሴ ያልተራበ ሰው

ሞፈር ቀንበሩን አፈር ያለብሰው፡፡

       ሆ ይላል ገበሬ

       ሆ ይላል ገበሬ

       ድብ እያፈረሰ ባሻልማ በሬ፡፡

በግብርናው ወቅቱን ጠብቆ ያልሠራ ገበሬ ይወረፋል፡፡ በስንፍናው ይወቀሳል፣ ይሰደባል፡፡

አንተ እርሻ አትረስ ይረስ አገሩ

እንዳይነካህ ጓልና አፈሩ

አንተ እርሻ አትረስ ይረስ አባትህ

ጭቃ እንዳይነካው ድንቡሌው ባትህ፡፡

በበጋው እረስ ቢሉት ፀሐዩን ፈራና

በዝናብ እረስ ቢሉት ዝናቡን ፈራና

ልጁ እንጀራ ቢለው በጅብ አስፈራራ፡፡

ሰነፉ ሲወቀስ ታታሪው ደግሞ ይወደሳል፡፡ የሥነ ጽሑፍ መሠረታውያን ታታሪውን ገበሬ እንዲህ ይገልፀዋል፡፡

በሬ ገራፊ እስከ ቅንድቡ

ነጭ ጤፍ አብቃይ እስከ ድንበሩ

በፌሮ ማረሻ ምድር አስጨናቂ

እስከ ረፋድ አርሶ መቶ መቶ ወቂ

ቆይ ባለመቶ ባለሺ ይናገር

መስከረም አዝላቂ፣ አንድ ምስለኤ አገር

በተለያዩ የዓለም ክፍል ኅብረተሰቦች ዘንድ ለዛፎች ልዩ ክብር እንደሚሰጡ በየአገሮቻቸው ስለዛፍ ከተነገሩ ቁም ነገሮች መረዳት ይቻላል፡፡ የሥነ ሕይወት ባለሙያው ለገሠ ነጋሽ (ፕሮፌሰር) ካጠናቀሩት የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

«የዛፍ ምስጢሩ ውበቱ ብቻ ሳይሆን፣ ተስፋን ማጫሩ፣ ሕይወትን ማደሱ ነው፤ «ዕውነትን መሻት ጥሩ ነው፡፡ የበለጠ ጥሩው ግን ስለዛፍ እውነቱን መናገር ነው (የዓረቦች አባባል)፣

«ሠርግ ደግስ፣ ደስታ! ያንድ ቀን ነው፡፡ ተሾም ተሸለም፣ ደስታ! ያንድ ወር ነው፡፡ ዛፍ ትከል፣ ደስታ! የዕድሜ ልክ ነው፡፡

ኤመርሰን «በዛፎች ስታጀብ በጥበብና እምነት እታጀባለሁ» እንዳለው ሁሉ እኛም በጥበብና በእምነት ለመታጀብ ዛፍን በተለይም አገር በቀሉን እንትከል ይላሉ የሥነ ሕይወት ባለሙያው፡፡

አገርኛው ብሂል፣ ፀደዩን ሰኔ 25 ቀን እንዳስፈጸመን ክረምቱንም መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰላም አስፈጽሞ ለመፀው (መስከረም 26) ያብቃን፣ ደኅና ያክርመን ይላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -