Wednesday, February 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ በዘንድሮው የሒሳብ ዓመት 1.7 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ. በ2014 የሒሳብ ዓመት በኩባንያው ታሪክ ከፍተኛ የሚባለውን የ1.75 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ማግኘቱን፣ ነገር ግን ወቅታዊው በሆነው የዋጋ ንረት ምክንያት የካሳ ክፍያ ወጪው ከፍ ማለቱን አስታወቀ።

አዋሽ ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ያሰባሰበው የዓረቦን ገቢ መጠን በኩባንያውም ሆነ በአጠቃላይ በግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እስከዛሬ ያልተመዘገበ ከፍተኛ የዓረቦን መጠን መሆኑን የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡ አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ በየዓመቱ እያስመዘገበ ያለው የዓረቦን ገቢ በየዓመቱ እያደገ መሄዱን የሚጠቅሰው የኩባንያው መረጃ፣ በ2014 የሒሳብ ዓመትም ያገኘው የዓረቦን ገቢም ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሚባለውን የዓረቦን መሆኑን አመልክቷል፡፡ 

አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ የ2014 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት ከ470 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡ ኩባንያው ባለፈው የሒሳብ ዓመት አሰባስቦ የነበረው የዓረቦን መጠን 1.28 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የዓረቦን ገቢ መሰብሰብ የቻለ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያ መሆን የቻለበት ዓመት ነበር።

አዋሽ ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው 1.75 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ የተሰበሰበው ሕይወት ነክ ካልሆነ የመድን ሽፋን፣ ከሕይወት ዋስትናና በሸሪዓ ሕግ ከሚተዳደር የመድን ሽፋን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛ ብልጫ ያለውን ዓረቦን ያሰባሰበው ሕይወት ነክ ካልሆነ የኢንሹራስ ሽፋን ነው፡፡ ለዘንድሮው የዓረቦን ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ማደግ የተለያዩ ምክንያቶች እንደነበሩ የሚጠቅሰው የኩባንያው መረጃ፣ በተለይ ሕይወት ነክ ካልሆነ የመድን ሽፋን ከፍተኛ ዕድገት የታየበት ገቢ ማግኘቱ አንዱ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህም ሌላ ኩባንያው በውጪ ኩባንያ አስጠንቶ በቅርቡ ሥራ ላይ ያዋለው የስትራቴጂክ ዕቅድና የውስጥ አሠራር ትግበራ ፕሮጀክት ውጤት እያስገኘ መምጣቱ ለኩባንያው የዓረቦን መጠን ዕድገት የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረው የአዋሽ ኢንሹራንስ የማርኬቲንግና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ፈንታዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡     

አዋሽ ኢንሹራንስ በሸሪዓ ሕግ ከሚተዳደር የመድን ሽፋን (ተካፉል ኢንሹራንስ) በመስኮት ደረጃ ለመስጠት ፈቃድ አግኝተው እየሠሩ ካሉ ሦስት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በዚህ አገልግሎትም አዲስ ዓረቦን ማሰባሰብ መጀመሩ ለዘንድሮ የዓረቦን ገቢ ዕድገት ተጨማሪ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ አዋሽ ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ የሚባለውን የዓረቦን መጠን ማሰባሰብ ቢችልም፣ ሁለን አቀፍ በሆነው አገራዊ የዋጋ ንረቱ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው የተሽከርካሪ የመለዋወጫ ዕቃዎች የዋጋ ንረት ሳቢያ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ ወጪ ለካሳ ክፍያ እንዲያወጣ አድርጎታል። በዚህም ምክንያት በዘንድሮው ዓመት ለካሳ ክፍያ ያወጣው የገንዘብ መጠን ካለፉት ዓመታት በተለየ ጭማሪ የታየበት እንደነበር የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከመለዋወጫ ዋጋ ጭማሪ ባሻገር እንደ ጋራዥ ላሉ አገልግሎቶች የሚጠየቀው ዋጋ ከዚህ ቀደም ከነበረው በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር የኩባንያውን የካሳ ክፍያ ወጪ ከፍ እንዳደረገው ይኼው የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡ በኩባንያው መረጃ መሠረት በ2014 የሒሳብ ዓመት ሕይወት ነክ ላልሆነ የኢንሹራንስ ዘርፍ የከፈለው ካሳ 427.7 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም ከቀዳሚው የ2013 የሒሳብ ዓመት ለካሳ ክፍያ ካዋለው ገንዘብ ጋር ሲነፃፀር የ110.6 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል (ይህ የካሳ ክፍያ የሕይወትና ለተካፉል ኢንሹንራሶች የተከፈለውን ካሳ አያካትትም)፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኩባንያው ከ26 ዓመታት በላይ ሲገለገልበት የነበረውን ዓርማ ለመቀየር ያወጣውን ጨረታ ያሸነፈው ኩባንያ ያዘጋጀው አዲስ ዓርማ ለመጨረሻ ውሳኔ ለቦርድ መቅረቡ ታውቋል፡፡

ኩባንያው በኅዳር 2014 አጋማሽ ላይ ይፋ አድርጎ እንደነበረው የኩባንያውን አሁናዊ ገጽታና የወደፊት አቅጣጫ የሚያመለክት አዲስ ዓርማ ለማሠራት ባወጣው ጨረታ ‹‹ብራንድ ኢንተግሬትድ›› የተባለ የኬንያ ኩባንያ አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

በዚሁ መሠረት ብራንድ ኢንተግሬትድ ኩባንያ ያሰናዳቸው አዳዲስ ዓርማዎች ለአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ የጨረታ ኮሚቴ ቀርበው ኮሚቴው ለኩባንያው ይመጥናል ያለውን አዲሱን ዓርማ መርጧል፡፡ ኮሚቴው የተመረጠውን አዲስ ዓርማ ለኩባንያው ቦርድ አቅርቦ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ነው ተብሏል፡፡ ቦርዱ በቅርቡ ውሳኔውን ያሳውቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከቦርዱ ውሳኔ በኋላ ኩባንያው በአዲሱ ዓመት አዲሱን ዓርማ ሥራ ላይ ያውላል፡፡

የዓርማው ለውጥ የበለጠ ተወዳዳሪ ሊያደርጉ የሚያስችሉ አዳዲስ አገልግሎቶችን ይዞ ለመቅረብ እንዲያስችለው ታሳቢ የተደረገ ሲሆን፣ ኩባንያው የዓርማ ለውጡን ተከትሎ ለኢንሹራንስ ኢንደስትሪው አዳዲስ አገልግሎቶችን ይዞ የሚቀርብ መሆኑን ከአቶ ቢኒያም ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

ኩባንያው ለማድረግ ያሰበው የዓርማ ለውጥ ዓርማ ለመለወጥ ብቻ ያለመ እንዳልሆነ የሚገልጹት አቶ ቢኒያም፣ ለውጡ ኩባንያው በኢንዱስትሪው ውስጥ ሊጫወት የሚገባውን ሚና የበለጠ ለማጉላት፣ እንዲሁም አዳዲስ የመድን ሽፋኖችን አብሮ በማስተዋወቅ ለገበያ የሚቀርብበት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው አዲሱን ዓርማ ለማሠራት ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ 13 ኩባንያዎች ተሳታፊ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ 

አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ. ታኅሳስ 23 ቀን 1987 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የባለአክሲዮኖቹን ቁጥር ከ1,670 በላይ ማድረስ ችሏል፡፡

የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል መጠን 1.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ 57 ቅርንጫፎችና ስድስት አገናኝ ቢሮዎችን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በመክፈት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች