Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ780 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተው ፀሐይ ባንክ አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሌሎች ባንኮች በተለየ አነስተኛ ባለአክሲዮኖችን ይዞ የተቋቋመውና የአገሪቱን የባንክ ገበያ ለመቀላቀል ዝግጅቱን ያጠናቀቀው ፀሐይ ባንክ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በአንዴ 30 ቅርንጫፎችን በመክፈት በይፋ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ባንኩ ሥራ ሲጀምር ከሚከፈቱት ከ30 በላይ ከሚሆኑ ቅርንጫፎች ውስጥ 20ዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ በክልል ከተሞች የሚገኙ መሆናቸውን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩት 30ዎቹ ቅርንጫፎች ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተገኘባቸውና ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ እስከ ምርቃቱ ዕለት ድረስ ተጨማሪ ቅርንጫፎች ሊኖሩ የሚችሉ መሆኑን ይኼው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

ፀሐይ ባንክ ከሌሎች የኢትዮጵያ ባንኮች በተለየ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ባለአክሲዮኖች ይዞ የተቋቋመ ነው፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ባለአክሲዮኖች ቁጥር 370 ብቻ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ታዋቂ የሆኑ ትልልቅ ኩባንያዎችና ነጋዴዎች መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ባንኮች አማካይ የባለአክስዮኖች ብዛት አራት ሺሕ እና ከዛ በላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ ፣ ፀሐይ ባንክ ግን በ370 ባለአክሲዮኖች ብቻ በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠውን የካፒታል መጠን አሟልቶ የተመሠረተ ነው።

ከእነዚህ 370 ባለአክሲዮኖች ወደ 780 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በማሰባሰብ ባንኩን በመመሠረት ሥራ ለማስጀመር የሚያስችለውን ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ አግኝቷል፡፡ የባንኩ ባለአክሲዮኖች የሦስት ቢሊዮን ብር አክሲዮን ለመግዛት የፈረሙ ሲሆን፣ አሁን ባንኩ የተመሠረተበት የተከፈለ ካፒታልም ከዚሁ ሦስት ቢሊዮን ብር በቅድሚያ የተከፈለ ነው፡፡   

በዚሁ የአክሲዮን ሽያጭ መሠረት ባንኩ የተፈረመ ሦስት ቢሊዮን ብርና የተከፈለ 780 ሚሊዮን ብር ካፒታል ይዞ ገበያውን የሚቀላቀል መሆኑ ታውቋል፡፡ ፀሐይ ባንክ አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችለው ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ ከመውሰዱ ባሻገር የባንኩ የመጀመርያው ፕሬዚዳንት በመሆን የታጩትን አቶ ያሬድ መስፍን ሹመት በብሔራዊ ባንክ አፀድቋል፡፡ እንደ ሌሎቹ አዳዲስ ባንኮች ሁሉ ፀሐይ ባንክ የባንኩ ፕሬዚዳንት አድርጎ የሰየማቸው ባለሙያ በሌላ ባንክ ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ካገለግሉባቸው ባንኮች መካከልም ዳሽን ባንክ የሚጠቀስ ሲሆን፣ አቶ ያሬድ የፀሐይ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመሰየማቸው በፊት በዳሸን ባንክ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በ780 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተው ፀሐይ ባንክ አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ፀሐይ ባንክን ጨምሮ በቅርቡ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀሉ አዳዲስ ባንኮች፣ ባንኮቻቸውን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ከተለያዩ የግልና የመንግሥት ባንኮች ከወሰዷቸው የሥራ ኃላፊዎች መካከል የአማራ፣ የጎህ፣ የዘምዘምና የአኃዱ ባንኮች ይገኙበታል፡፡ የአማራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ሔኖክ ከበደ የዳሸን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባው አኃዱ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፈንታዬ የቡና ባንክ ፕሬዚዳንት እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ 

ከዚህም ሌላ የመጀመርያው ከወለድ ነፃ ባንክ በመሆን የሚጠቀሰው ዘምዘም ባንክም የባንኩ ፕሬዚዳንት አድርጎ የሰየማቸው ወ/ሮ መሊካ በድሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩ ሲሆን፣ የጎህ ቤቶች ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት አቶ ሙሉጌታ አስማረ ደግሞ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ሌሎችም አዳዲስ ባንኮች በአብዛኛው የሾሟቸው ፕሬዚዳንቶች በተለያዩ ባንኮች በተለይ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩ ባለሙያዎችን በማጨት እየሾሙ ይገኛሉ፡፡ 

በተመሳሳይ ፀሐይ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አድርጎ የሰየማቸው አቶ ታዬ ዲበኩሉ ደግሞ የኅብረት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንትና ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለገሉ የነበረ ሲሆን፣ ከፀሐይ ባንክ መሥራቾች አንዱ መሆናቸውም ይታወቃል።

የፀሐይ ባንክን አገልግሎት መጀመር አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ፣ ባንኩ ወደ ገበያው የሚቀላቀለው ከፍተኛ የሚባል ውድድር ባለበት ወቅት በመሆኑ ጠንካራ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችለውን ዝግጅት ሲደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ተወዳዳሪ ሊያደርገው የሚችሉ የባንክ አገልግሎቶችን የሚተገብር መሆኑን የገለጹት እኚሁ ኃላፊ፣ ለኢንዱስትሪው አዳዲስ የሚባሉ አገልግሎቶችን የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ቴክኖሎጂን መሠረት በማድረግ የባንክ ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችል አገልግሎት ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሠራና ለዚህም ከወዲሁ ዝግጅት ማድረጉን አመልክተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች