Sunday, January 29, 2023

አደጋ ላይ የወደቀው የተቃውሞ ነፃነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዓምና በነሐሴ አጋማሽ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች ነዋሪዎች በአደባባይ በመውጣት፣ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን የኦነግ ሸኔ ኃይል በመቃወም ማውገዛቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹ኦነግ ሸኔና ሕወሓት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎች ናቸው፤›› የሚሉ መልዕክቶችን ጨምሮ፣ በርካታ መፈክሮችን በማንገብ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች የተቃውሞ ሠልፍ አደረጉ የሚለው ዜና የመገናኛ ብዙኃኑን ያጣበበ ወሬ ሆኖ ነበር የከረመው፡፡

የምዕራብ ሸዋና የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች፣ የሆለታ ከተማ ነዋሪዎች፣ የገላንና የዱከም ከተማ እየተባለ በብዙ የኦሮሚያ ክፍሎች ይኸው የተቃውሞ ሠልፍ መደረጉ በሰፊው ተነገረ፡፡ ዘንድሮ በዓመቱ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ኦነግ ሸኔንና በኦሮሚያ ክልል የቀጠለውን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ የሚያወግዙ ሰላማዊ ሠልፎች የማካሄድ ጥረት ተሞከረ፡፡ ሆኖም ሁሉም አጋጣሚዎች በዱላ፣ በእስርና በግድያ ነበር የተቋጩት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ መነሻና ምክንያት ቢኖር እንኳ በተለያዩ ቦታዎች ተመሳሳይ ሰላማዊ ሠልፎች ማካሄድ ፈተና የሆነ ይመስላል፡፡ ዓምና ኦነግ ሸኔን የሚያወግዝ ሠልፍ በኦሮሚያ በሰላም ተካሄደ ተብሎ ዘንድሮ በአማራ ክልል ኦነግ ሸኔን ለማውገዝ የወጡ ሠልፈኞች ተመሳሳይ ዕድል አልገጠማቸውም፡፡ አንዳንድ ተቺዎች መንግሥት አላባራ ያለውን ግድያ ከማስቆም ይልቅ፣ በግድያው ሳቢያ ቁጣቸውንና ቅሬታቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡ ሰላማዊ ሠልፈኞች ላይ ዕርምጃ መውሰዱ የቀለለው ይመስላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰበዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹መንግሥት ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብትን በአግባቡ ያክብር፤›› ሲል ጠይቋል፡፡ በወለጋ እየደረሰ ያለውን ዘር ተኮር ጥቃት ለመቃወም ሰኔ 18 ቀን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም ሰኔ 20 ቀን በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ሞክረው እንደነበር መግለጫው ያወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በፀጥታ አካላት ዕርምጃ ሠልፎቹ መደናቀፋቸውን ይጠቁማል፡፡ ፖሊስ ሰላማዊ ሠልፈኛ ተማሪዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስና ያልተመጣጠነ የኃይል ዕርምጃ ተጠቅሟል የሚለው መግለጫው፣ ድርጊቱ አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ ያወግዘዋል፡፡

የወለጋው ዘር ተኮር ጥቃት መደጋገም በአዲስ አበባና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ከተሞችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመሳሳይ ቅዋሜ አስከትሏል፡፡ ከሰኔ 20 ጀምሮ በነበሩ ቀናት የወለጋው ጭፍጨፋ ይቁም የሚሉ ተቃውሞዎች በጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ በማጀቴ ከተማና በሸዋ ሮቢት ከተሞች በተከታታይ ተካሂደዋል፡፡ ይህንኑ የወለጋ ጭፍጨፋ የሚቃወሙ ሰላማዊ ሠልፎች በውጭ አገሮችም የተካሄዱ ሲሆን፣ በለንደንና በዋሽንግተን ዲሲ ከተሞች የተቃውሞ ትዕይንቶች ተስተናግደዋል፡፡ ይሁን እንጂ በውጭ አገሮች ከተካሄዱት ሠልፎች ይልቅ በአገር ቤት የተሰናዱት መጨረሻቸው በእስር፣ በዱላና የሰው ሕይወት በመቅጠፍ ነበር የተደመደሙት፡፡

በኢትዮጵያ ሰላማዊ ተቃውሞና ሠልፍ ማካሄድ ምን ዓይነት የሕግ ትርጓሜ አለው? ለሚለው ጥያቄ የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው አበበ የሚከተለውን ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

‹‹የመሰብሰብና ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ደንግጎታል፡፡ ከዚህ ውጪ በ1983 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ቁጥር 3/1983 ‹የሰላማዊ ሠልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት› አዋጅ ላይም በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በእነዚህ ሕጎች እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሰብሰብ፣ መሣሪያ ሳይዝ፣ በነፃነት ተቃውሞና አቤቱታውን የማቅረብ መብት እንዳለው ተቀምጧል፡፡

‹‹ይሁን እንጂ በእነዚህ ሕጎች ቅድመ ሁኔታዎችም የተቀመጡ ሲሆን፣ ከቤት ውጪ የሚደረጉ ሰላማዊ ሠልፈኞችና ተቃውሞዎች የሌሎችን እንቅስቃሴና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጋፋት እንደማይኖርባቸው ተገልጿል፡፡ የሌሎችን እንቅስቃሴ፣ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ ነፃነትና ሞራላዊ ሁኔታን ሠልፎቹ እንዳይጥሱ አስፈላጊ የሥነ ሥርዓት ደንቦች ይደነገጋሉ ተብሏል፤›› በማለት ጉዳዩ በተለያዩ ሕጎች ያለውን ቦታ ያስረዳሉ፡፡

በዚህ መነሻነት የሰላማዊ ሠልፉን ምንነት ወደ መተንተን የሚገቡት አቶ አበባው፣ ‹‹ብዙ ሕዝብ በአደባባይ፣ በጎዳና ወይም ለሰላማዊ ሠልፍ ምቹ በሆነ ሥፍራ የጦር መሣሪያ ሳይዝና የኅብረተሰቡን ሰላም ሳያውክ ሐሳቡን በንግግር፣ በጽሑፍ፣ በመፈክርና በዘፈን ሥነ ሥርዓት ባለው መንገድ የሚገልጽበት ነው፤›› ያሉት  የሕግ ባለሙያው፣ ሰላማዊ ሠልፍ ዜጎች ከመንግሥት መብትን ወይም የሆነ የሚፈልጉትን ነገር የሚጠይቁበት መንገድ እንደሆነ በእነዚህ ሕጎች በግልጽ መደንገጉን ያሰምሩበታል፡፡

በኢትዮጵያ ብዙዎች እንደሚስማሙበት በብዙ ጉዳዮች ላይ የሕግ ማዕቀፍ በማመቻቸት በኩል ሳይሆን፣ በአተገባበር ሒደት ክፍተት መኖሩ በጉልህ ይወሳል፡፡ ሰላማዊ ሠልፍና ተቃውሞ ለማካሄድ ሕጎች ቢኖሩም፣ ነገር ግን በተጨባጭ በአደባባይ ወጥቶ ተቃውሞ ማሰማትም ሆነ ቅሬታ ማቅረብ ፈተና ላይ የወደቀ ዴሞክራሲያዊ መብት ሆኗል ሲሉም በርካቶች ይናገራሉ፡፡

ከሰሞኑ በተካሄዱ የተቃውሞ ሠልፎች ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ዕርምጃ ወስደዋል ተብሎ በብዙ ወገኖች እየተተቸ ነው፡፡ ይኸው ስሞታ ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፓርላማ በተገኙ ጊዜ ቀርቦላቸው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ስለዚሁ ጉዳይ በሰጡት ምላሽ፣ መንግሥታቸው የሕዝብ ተቃውሞ ፈርቶ ሠልፎችን አለመከልከሉን ጠቁመዋል፡፡ ሰርጎ ገቦችና አሸባሪዎች ከሰላማዊ ሠልፈኛው ውስጥ ተሸሽገው ገብተው የአገሪቱን ፀጥታና የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ በማሰብ፣ መንግሥት በሰላማዊ ሠልፎቹ ላይ ዕርምጃ መውሰዱን ነው የተናገሩት፡

ይሁን እንጂ መንግሥት የሰጠው አመክንዮ አሳማኝ አለመሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት ዜጎች የሰላማዊ ሠልፍና ተቃውሞ ነፃነትን የማስከበር ዓለም አቀፍ የሕግ ግዴታን መሸከሙን አስታውሷል፡፡

ኢሰመጉ በመግለጫው የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 21 ላይ፣ ሰዎች ሰላማዊ ስብሰባ የማድረግ መብት እንዳላቸው መደንገጉን አመልክቷል፡፡ ኢሰመጉ ከዚሁ ጋር አያይዞ በሰዎችና በሕዝቦች መብቶች ላይ የወጣው የአፍሪካ ቻርተር አንቀጽ 11 ላይ፣ ማንም ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር የመሰብሰብና ተቃውሞውን በሰላም የማቅረብ መብት እንዳለው ተቀምጧል በማለት፣ ኢትዮጵያ እነዚህን ዓለም አቀፍ ሕጎች የማክበር ግዴታ እንዳለባት አስረድቷል፡፡

በሕግ ደረጃ ይህ ቢባልም መንግሥት ግን ለዜጎች ሰላምና ለአገር ደኅንነት ስል ነው ሠልፎቹን የበተንኩት ይላል፡፡ ሆኖም ለዜጎች ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ተብሎ በተፈጸመ ሰላማዊ ሠልፎችን የመበተን ዕርምጃ፣ ዜጎች ለአካላዊ ጉዳትና ለሞት መዳረጋቸው ብዙ ጥያቄ ሲያስነሳ ነው የከረመው፡፡ በተለይ በሸዋ ሮቢት ከተማ የተካሄደውን  ተቃውሞ  ተከትሎ ከሰባት ያላነሱ ሰዎች መገደላቸው ከባድ ቁጣና ቅሬታ አስነስቷል፡፡

በሕዝባዊ ተቃውሞ ግፊት ወደ ሥልጣን የመጣው መንግሥት የተቃውሞ ሠልፎችን መታገስ አቃተው የሚል ትችት አስነስቶበታል፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማይጣስባት አገር እገነባለሁ ብሎ ቃል ገብቶ ወደ ሥልጣን የመጣው መንግሥት፣ ልክ እንደ ቀደሙ አስተዳደሮች ሁሉ ሕዝብ ማፈን ጀመረ ተብሎም እየተተቸ ነው፡፡

ይህን የማይቀበሉት የመንግሥት አመራሮች ግን በየቀኑና በየጊዜው ለአመፅና ለነውጥ የተዘጋጁ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን ማክሸፍ ባይቻል ኖሮ፣ አገሪቱ ወደ ለየለት ቀውስ ትገባለች ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ፓርላማ ላይ እንደተናገሩት፣ በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የነውጥና ሽብር እንቅስቃሴዎች በየጊዜው ቢታቀዱም በፀጥታ ኃይሎች ክትትል ብዙዎቹ ይከሽፋሉ፡፡

የፓርላማ አባላቱን፣ ‹‹እናንተ አልፎ አልፎ ብትሰሙትም እኛ ግን በየቀኑና በየሰዓቱ ነው የዜጎችን ሕይወት ለአደጋ የሚዳርጉ ጥቃቶች የምንሰማው፤›› በማለትም ዓብይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ይህ ሁሉ የአደጋ ሥጋት ባለበትና አሸባሪዎች ያሏቸው ወገኖች ጥቃት ለማድረስ አጋጣሚ በሚጠብቁበት ሁኔታ፣ ዜጎች ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ ተቃውሞ እንደ ልባቸው ያድርጉ ብሎ መልቀቅ አገሪቱን የበለጠ ተጋላጭ እንደሚያደርጋት፣ የዜጎችንም ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚጥል ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ እንደራሴዎቹ የተናገሩት፡፡

አንዳንድ ወገኖች ግን ይህን የመንግሥት አመክንዮ ፈፅሞ አይቀበሉትም፡፡ የወለጋ ጭፍጨፋን በመቃወም የሚካሄዱ የተቃውሞ ሠልፎችን ብቻ ሳይሆን፣ መለስተኛና ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችንም መንግሥት መታገስ እያቃተው መጥቷል የሚሉ ትችቶ እየተስተጋቡ ነው፡፡ ከቀናት በፊት ለደም ልገሳ የተሰባሰቡ ‹‹የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አድናቂዎች ነን፤›› ያሉ ዜጎች፣ በበላይ አካላት ትዕዛዝ ‹‹ደም አትለግሱ ተባልን›› የሚል ቅሬታ ማቅረባቸው፣ መንግሥት ተቃውሞን ብቻ ሳይሆን ድጋፍንም የመቻል ትዕግሥት እያጣ መጥቷል የሚል ትችት እንዲሰማበት የሚጋብዝ አጋጣሚ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡   

የተቃውሞ ሠልፍም ሆነ የአደባባይ ሠልፍ መደረግ የሚከለክልባቸውን ሁኔታዎች የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው አበበ ሲያስረዱ፣ ‹‹በአዋጅ ቁጥር 3/1983 አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ የፈለገ አካል ከ48 ሰዓታት በፊት ጉዳዩን በጽሑፍ ማሳወቅ አለበት፡፡ የሠልፉ ዓላማ፣ ቦታ፣ ቀንና ሰዓት መታወቅ አለበት፡፡ ሰላማዊ ሠልፉን ያደራጀው ቡድን ወይም ግለሰብ መታወቅ ይኖርበታል፤›› በማለት ከሕጉ ተነስተው ያስረዳሉ፡፡ ይህንን ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ለሚካሄድ ሰላማዊ ሠልፍ መንግሥት ምንም ዓይነት ክልከላ ማድረግ እንደማይችል ሕጉ ማስቀመጡንም ያወሳሉ፡፡ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ለሚካሄድ ለሠለጠነ ሰላማዊ ሠልፍ ሰላምና ደኅንነትን በማስከበር ትብብር እንደሚያደርግ ሕጉ መደንገጉንም ያክላሉ፡፡

በቅርቡ ከወለጋ ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘ በርከት ያለ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጥሪዎች ሲደረጉ መክረሙ ይታወሳል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎትን በማቋረጥና የትራፊክ እንቅስቃሴን ዝግ በማድረግ ተቃውሞን የማቅብ ጥሪ ሲተላለፍ መቆየቱም ይታወቃል፡፡ ጥሪው በተደረገበት ዕለት አዲስ አበባ ከተማ እንደታሰበው እንቅስቃሴ አልባ ሆና ባትውልም፣ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ መጠነኛ የእጥረት ችግር መፈጠሩን መታዘብ ተችሏል፡፡

ሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ለዜጎች ሞት ሐዘን ለመግለጽ ጥቁር ልብስ ለብሶ የመዋልና የህሊና ፀሎት የማድረግ የተቃውሞ ጥሪ ተካሂዶ ነበር፡፡ በአንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጥሪው ተግባራዊ ሲሆን ቢታይም፣ በአዲስ አበባም ሆነ በመላው ኢትዮጵያ ቀኑ በመደበኛ እንቅስቃሴ ነው ያለፈው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ጨምሮ በቅርብ ጊዜ የተፈጠሩ የተቃውሞ አጋጣሚዎችን የሚጠራው አካል ማን ነው? የሚለው ጥያቄ መልስ ያለው አይመስልም፡፡ ለተቃውሞ እንቅስቃሴዎቹ በይፋ ኃላፊነት የሚወስድ ወገን በሌለበት ሁኔታ መንግሥት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን አፈነ ብሎ መወንጀል እንዴት ይቻላል? የሚለውም ያልተመለሰ ጥያቄ ነው፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው ግን መንግሥት ተቃውሞ አልይ ወይም ሰዎች በአደባባይ ድምፃቸውን አያሰሙ ሊል የሚችልበት የሕግ አግባብ ጠባብ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መንግሥት የማውጣት ሕገ መንግሥታዊ መሠረት አለው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባወጀ ጊዜ ብቻ ነው የተቃውሞ ሠልፎች የሚከለከሉት፡፡ ከዚህ ውጪ ባሉ ሁኔታዎች ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታዎችን እስካሟላ ድረስ ማንም የመሰብሰብና የተቃውሞ ማሰማት ነፃነቱ በሕግ የተረጋገጠ ነው፤›› በማለት ሕጉ አሻሚ አለመሆኑን አቶ አበባው ያስረዱት፡፡

በእሳቸው እምነት አስፈላጊ ግዴታዎችን በማሟላትና የሠለጠነ ተቃውሞ ለማቅረብ ዝግጁ በመሆን የዴሞክራሲ መብቶችን መጠቀም ይቻላል፡፡ በዚህ መሰል ሥልጡንና ሕጋዊ መንገድ በመሄድ፣ ‹‹መንግሥት ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ያለውን ቁርጠኝነት መፈተን ይቻላል፤›› ሲሉም አቶ አበባው ይናገራሉ፡፡ በሠለጠኑ አገሮች ተቃውሞ የዴሞክራሲ ልምምድ መሆኑን ያነሱት የሕግ ምሁሩ፣ ይህ ሁኔታ ግን እንደ አገሮች የዴሞክራሲ ምኅዳር መጥበብና መስፋት ሁኔታ እንደሚበየን ነው ያስረዱት፡፡

እንደ ሲሪላንካና እንደ ሱዳን የመሳሰሉ አገሮች መንግሥትን በተቃውሞ ማስጨነቅም ሆነ ለረብሻና ለአመፅ የሚጋብዝ ሁኔታ በመፍጠር፣ ሕዝቡ የሚፈልጋቸውን ጥያቄዎች ያስመልሳል የሚል እምነት እንደሌላቸው አቶ አበባው ያስረዳሉ፡፡ ሠልፍ የሚያስወጣና ተቃውሞ ለማቅረብ የሚያስገድዱ ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ ነገር ግን ይህን በሠለጠነ መንገድ ማካሄድና መንግሥትን መፈተን እየተቻለ አደገኛ የሆኑ የዘርና የሃይማኖት ፖለቲካ አጀንዳዎችን ተገን በማድረግ ለተቃውሞ መነሳት፣ አንዳንዴ አደጋን የሚጋብዝ አላስፈላጊ ነገር እንደሆነ ነው የሕግ ባለሙያው ያሳሰቡት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -