Sunday, May 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የትራንስፖርትን ችግር ያቃልላሉ የተባሉ 60 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዛሬ ሥራ ይጀምራሉ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር 60 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባቱ ተገለጸ፡፡

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹን በማስመጣትና በመገጣጠም የሚታወቀው ግሪን ቴክ አፍሪካ የተባለው የግል ድርጅት ሲሆን፣ ለኅብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ያቀረበው ግሪን ትራንስፖርት ሰርቪስ ነው፡፡

ወደ አገልግሎት ከሚገቡት አራት የተለያየ ሞዴል ያላቸው 30 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለኅብረተሰቡ የአንድ ወር የነፃ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን፣ በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታጠቅ ነጋሽ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ለአንድ ወር የሚቆየው የነፃ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ተጠቃሚዎች የኤሌክትሪክ ትራንስፖርትን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ ለመፍጠር የታሰበ መሆኑን አቶ ታጠቅ ገልጸዋል፡፡ ተሽከርካሪዎቹ ሕዝብ በብዛት በሚገኝበትና በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣሉ ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹን ከውጭ ለሚያስመጡና በአገር ውስጥ ለሚገጣጥሙ ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑን፣ የታቀደውን የአሥር ዓመት አገራዊ ዕቅድ ለማሳካት አስተዋጽኦ እንዳለው አቶ ታጠቅ ተናግረዋል፡፡

የግሪን ቴክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፍፁም ደሬሳ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ድርጅቱ ከቻይና ካስገባቸው 400 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 60 የሚሆኑትን በይፋ ሥራ አስጀምሯል፡፡ ቀሪዎቹ 340 ተሽከርካሪዎች ክሊራንስ ያላለቀላቸው በመሆኑ፣ የሚፈለገውን ሒደት ካለፉ በኋላ ወደ ሥራ ይገባሉ ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ግሪን ቴክ እያስገባቸው የሚገኙ 500 ተሽከርካሪዎች ጂቡቲ ወደብ እንደሚገኙ፣ ከ1,000 በላይ የሚሆኑት ተመርተው መርከብ ላይ ለመጫን እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ፍፁም (ኢንጂነር) ገለጻ፣ በድሬዳዋ ከተማ በቅርቡ ሥራ የሚጀምረው የተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ እስኪገነባ ድረስ፣ ኩባንያው በዓለም ላይ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራችነታቸው ከሚታወቁ  የቻይና አምራቾች ጋር በመሆን ከአንድ ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎችን ወደ ገበያ ያስገባል፡፡ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን ደግሞ በግሪን ቴክ የኤሌክትሪካል መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በመገጣጠም ለገበያ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው የራሱ በሆነ አሠራር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ለመግዛት ለሚፈልጉ 60 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ የሚኖራቸው ሲሆን፣ 40 በመቶ ደግሞ ኩባንያው ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ነገር ግን ይህንን አሠራር ደፍሮ የሚጠቀም ገዥ ባለመገኘቱ፣ 100 ተሽከርካሪዎችን ግሪን ትራንስፖርት የተባለው የተሽከርካሪዎች አገልግሎት ሰጪ ተቋም መውሰዱን ፍፁም (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ የቀጠራቸው አሽከርካሪዎች ያሉት መሆኑን፣ በራሱ ከጀመረ በኋላ የተጠቀሰውን የ40/60 አሠራር ለተጠቃሚዎች ግንዛቤ ለመፍጠር ያግዛል ሲሉ ፍፁም (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡

‹‹ጎ ግሪን›› በሚባል ሞቶ የሚታወቀው ግሪን ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ከግሪን ቴክ፣ እንዲሁም ከሌሎች የኤሌክትሪክ አስመጪና የሚገጣጥሙ ድርጅቶች የተረከባቸውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሥራ የሚያስገባ ተቋም መሆኑ ታውቋል፡፡

‹‹ጎ ግሪን አፍሪካ›› የሚል መተግበሪያ የተዘጋጀለት ይህ የአገልግሎት ሰጪ ተቋም፣ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ሲሉ ፍፁም (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች በሊትር ከ47 ብር እስከ 52 ብር እየተጠቀሙ ሲሆን፣ የ2021 ሞዴል የሆነው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በ18 ብር ቻርጅ ተደርጎ 200 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላል ተብሏል፡፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር በአሥር ዓመታት የልማት ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱት ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ውስጥ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የማስፋፋት ሥራ አንዱ ነው፡፡ በአሥር ዓመት ውስጥ ለማሳካት በዕቅድ ከያዛቸው ተግባራት መካከል በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ 4,800 አውቶብሶችንና 148 ሺሕ አነስተኛ ተሽከርካሪዎችን (የቤት አውቶሞቢሎች) ለኅብረተሰቡ ማቅረብ መሆኑን አቶ ታጠቅ ተናግረዋል፡፡

በአሥር ዓመት ዕቅድ ውስጥ የተያዙትን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማምረት በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ የግል ድርጅቶችን ሲያሳትፍ ማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ፣ ኮረንቲ ሞተርስና ግሪን ቴክ አፍሪካ ይጠቀሳሉ፡፡

ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማዳን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቴክኖሎጂን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ጠቅሶ፣ ለዚህም የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በቴክኖሎጂ የተደገፈ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመር በቅርቡ ከተጀመረው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ጋር በመገጣጠሙ፣ የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ሚና ከፍተኛ እንዲሆን ያደርገዋል ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት ተጠቃሚዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መጠቀም ባህል እንዲያደርጉና አሁን ትክክለኛው ወቅት መሆኑን የማስተዋወቅ ሥራ ለመሥራት መታሰቡን አቶ ታጠቅ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ድርጅቶች የተገጣጠሙ 200 ያህል ኅብረተሰቡ እየተጠቀመባቸው ያሉ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች እንደሚገኙ አክለዋል፡፡

ከዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ የሚጀምሩት 60 ተሽከርካሪዎች ያቀረበው ግሪን ቴክ አፍሪካ ጥር 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ከአምስት ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ለማቅረብና ለትራንስፖርት አገልግሎት ለማዋል ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ግሪን ቴክ አፍሪካ ከስድስት ዓመታት በፊት በታዳሽ ኃይል ዙሪያ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ለመሰማራት በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ኩባንያ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች