በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ አስተዳደር ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ የገጠር ቀበሌዎች በተከሰተ ግጭት፣ የሰዎች ሕይወት ሲጠፋ በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡
ሐምሌ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. አመሻሹ ላይ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳና በሰሜን ሸዋ አስተዳደር ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት፣ በክልሉ የልዩ ኃይል አባላትና አርሶ አደሮች ላይ የሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መድረሱን ሪፖርተር ከቦታው ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የተፈጠረው ግጭት ተጋብተውና ተዋልደው በደስታም ሆነ በችግር ጊዜ በመረዳዳት በሚኖሩት ጎረቤታሞች ሕዝቦች መካከል መሆኑን፣ እስካሁን ድረስ ግጭቱን ይኸኛው አካል ጀመረው ብሎ በግልጽ መናገር እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡
‹‹ለእኔም ለሌላውም ማኅበረሰብ አዲስ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ገጥሞን አያውቅም፤›› ያሉት የአካባቢው ነዋሪ፣ የግጭቱ መነሻ ወደ ስድስት የሚጠጉና የወታደር ዩኒፎርም የለበሱ ግለሰቦች በእርሻ ላይ በነበረ አንድ ገበሬ ላይ በከፈቱት ተኩስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሁለቱ ዞኖች 200 የሚጠጉ ከማኅበረሰቡ የተውጣጡ ተሳታፊዎች፣ ሰላማዊ የዕርቅ ስብሰባና ውይይት ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ በነበረበተ ወቅት፣ ሐምሌ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. አመሻሹ ላይ ፕሮግራሙን ለማደናቀፍ ታስቦ የተጀመረ ተኩስ ሳይሆን እንደማይቀር፣ ለሪፖርተር የገለጹት ደግሞ የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ መሀመድ ናቸው፡፡
በተመሳሳይ የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ በማኅበራዊ ድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ ግጭቱ የተቀሰቀሰው የሁለቱን ብሔሮች በሰላም አብሮ መኖር የማይፈልጉ ፅንፈኛ አካላትና የሸኔን አመለካከት ተሸክመው በሕዝቡ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተላላኪዎች እንደሆነ አስረድቷል፡፡
እሑድ አመሻሹ ላይ የተጀመረው የተኩስ ልውውጥ ሰኞ በመጠኑ ቢቆምም፣ በሌሎች አካባቢዎች የቀጠለ ተኩስ እንደነበር የገለጹት አቶ አህመድ፣ ግጭቱን ተከትሎ በአካባቢው በተደረገ የእንቅስቃሴ ክልከላ፣ ትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 5 ቀን ወደ ሌላ አካባቢ በመስፋፋት ይከሰት የነበረን ግጭት ማስቆም እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ግጭቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ በሚል የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳደር የእንቅስቃሴ ክልከላ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት በወረዳውና በከተማ ውስጥ የሚገኙ የሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን (ባጃጆችን) ላልተወሰነ ጊዜያት በቀንም ሆነ በማታ እንዳይሽከረከሩ አግዷል፡፡
በሌላ በኩል ከመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ውጪ ማንኛውንም አካል የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻል፣ ከተፈቀደለት የፀጥታ አስከባሪ መዋቅር ውጪ ማንኛውም ግለሰብ ከቀበሌ ወደ ቀበሌ መንቀሳቀስ እንደማይቻልና በኅብረተሰቡ ውስጥና በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ተጨባጭ ያልሆኑ መረጃዎችን የሚያናፍሱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሲል ገደብና ማስጠንቀቂያ አስቀምጧል፡፡
የሰሜን ሸዋ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪና የፀጥታ ኃላፊውን ለማናገር በተደጋጋሚ የተደረገው ጥረት ስልካቸውን ሊያነሱ ባለመቻላቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡
በአሁኑ ወቅት የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ የፀጥታ አካላት በሥፍራው እንደሚገኙ፣ አካባቢውም ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ ገልጸዋል፡፡