Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ላይ ተፈጽሟል ስለተባለው ስህተት ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የከተማ አስተዳደሩ ይቅርታ ጠይቋ

የጋራ መኖሪያ ቤት የ14ኛው ዙር ዕጣ አወጣጥ ከተከናወነ በኋላ፣ ከተመዝጋቢዎች የመረጃ መዛባት ችግር ጋር ተያይዞ ተፈጽሟል የተባለውን ስህተት፣ አድበስብሶ ከማለፍ ባለፈ ግልጽ ማብራሪያ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሰጡ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ተመዝጋቢዎች ጥያቄ አቀረቡ፡፡

የጋራ መኖሪያ ዕጣ ከወጣበት ዕለት አንስቶ የቤት ዕድለኛ ለመሆን ሲጠባበቁ የቆዩ የ1997 ዓ.ም.፣ እንዲሁም የ2005 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች፣ በተፈጠረው የቤት ማስተላለፍ መረጃ ስህተት በተመለከተ ቅሬታቸውን እያቀረቡ ነው፡፡

ሪፖርተር በቀረቡት ቅሬታዎች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንም ሆነ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎችን በተደጋጋሚ በስልክ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

ምንም እንኳን በዚህ ዙር ለ20/80 የቤት ፕሮግራም ሙሉ ለሙሉ ዕጣ የወጣባቸውና የተስተናገዱት የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች እንደሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ቢያስታውቅም፣ እስካሁን ድረስ የዕድለኞች ስም ዝርዝር ይፋ አለመድረጉ፣ እንዲሁም ከውጤት መዛባት ጋር በተያያዘ የማጣራት ሒደቱ መቼ እንደሚጠናቅቅ አለመታወቁ ግርታ እንደፈጠረባቸው፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የ1997 ዓ.ም. የኮንዶሚንየም ቤት ቆጣቢዎች ገልጸዋል፡፡

አቶ ፍቅር የተባሉ የ1997 ዓ.ም. የቤት ልማት ተመዝጋቢ እንደተናገሩት፣ ለ17 ዓመታት ያህል ብቁ ቆጣቢ የሚያደርጋቸውን ክፍያ ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በ14ኛው ዙር የቤት ዕድለኛ መሆን አለመሆናቸውን እስካሁን ድረስ ለማረጋገጥ አልቻልኩም ብለዋል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ከሰሞኑ በከተማ አስተዳደሩ በኩል ከዕጣ ማውጣቱ ጋር በተገናኘ፣ ተገኙ በተባሉ ግድፈቶች ሳቢያ፣ ቁርጥ ያለ ማብራሪያ አለመሰጠቱ ውዥንብር ውስጥ እንደ ከተታቸው አስረድተዋል፡፡

ሌላው የ1997 ዓ.ም. የባለ አንድ መኝታ ቤት ተመዝጋቢ እንደሆኑና እስካሁን ድረስ 130 ሺሕ ብር ያህል ለ17 ዓመታት ያህል መቆጠባቸውን ያስረዱት ሌላ ነዋሪ፣ ከአንድ ዓመት በፊት ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ቀርበው ስማቸው በትክክል በመረጃ ቋት ውስጥ እንደሚገኝ አረጋግጠው ነበር፡፡ ቁጠባቸውን እንደቀጥሉና በቀጣይ የዕጣ ማውጣት ሒደት ውስጥ የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች ቅድሚያ ያገኛሉ የሚለውን ተስፋ አድርገው፣ የ14ኛው ዙር የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት በጉጉት ሲጠብቁ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለረዥም ዓመታት የቤት ባለዕድል ለመሆን የጠበቁት እልህ አስጨራሽ ጥበቃ ሳያንስ፣ የ14ኛ ዙር የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ከወጣበት ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የዕድለኞች ስም ዝርዝር ይፋ አለመሆኑ፣ እንዲሁም ከዚያ በኋላ የተስተዋለው ግልጽ ያልሆነ የመረጃ ፍሰት፣ የቤት ባለዕድል ለመሆን ያላቸውን ዕምነት መሸርሸሩን ነዋሪዎቹ አክለዋል፡፡

ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በሕጋዊው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ጉዳዩን አስመልክቶ አጭር ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ከ14ኛው ዙር ዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት በኋላ የተለያዩ ጥቆማዎች በመቅረባቸው የኦዲት ሥራ ተጀምሮ በባንክ በተላከውና ለዕጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር በተጫነው (መረጃ) ዳታ ላይ ልዩነቶች መገኘታቸውን፣ የከተማ አስተዳደሩ ባሰፈረው ማብራሪያ አስታውቋል፡፡

በዚህም ከታዩ ልዩነቶች ውስጥ ላልቆጠቡ ሰዎች ዕጣ መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ የተዓማኒነት ጉድለቶች እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገልጿል፡፡

የቤት ማስተላለፍ ሥራው በቆጣቢዎች መካከል አድልዎና ብልሹ አሠራር እንዳይኖርበት ለማድረግ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር እንዲሆን፣ እንዲሁም ባለሙያዎች በነፃነት ተዓማኒነቱን እንዲያረጋግጡ መደረጉን ያስታወቀው የከተማ አስተዳደሩ፣ ከዕጣ አወጣጥ በኋላ የተፈጠረውን ችግር ከጉዳዩ ገለልተኛ በሆኑ በሚመለከታቸው ተቋማት፣ የማጣራት ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁሞ፣ በጉዳዩ የተጠረጠሩ ባለሙያዎችና አመራሮች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገ ይገኛል ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በ2005 ዓ.ም. በተደረገው የባለ ሦስት መኝታ ቤት የጋራ መኖሪያ ቤት ምዝገባ ተመዝግበው ሲጠባበቁ የነበሩ ነዋሪዎች፣ የከተማ አስተዳደሩ በ14ኛው ዙር ከሚደረገው የዕጣ ዝርዝር ውጭ ያደረገበት አካሄድ ‹‹ትክክልና ሕጋዊ አይደለም፤›› በማለት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በ12ኛው ዙር ዕጣ አወጣጥ ወቅት የ1997 ዓ.ም. የባለ ሦስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች የቤት ዕድለኞት ሙሉ ለሙሉ እንደተጠናቀቀ ተገልጾ፣ በ13ኛው ዙር ለ2005 ዓ.ም. የባለ ሦስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች ዕጣ ወጥቶ፣ ነገር ግን ከ14ኛው ዙር የዕጣ ዝርዝር ውጭ የተደረገበት አሠራር፣ ከፍተኛ ግርታ እንደፈጠረባቸው አቶ መስፍን የተባሉ የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በተለይም ከባለ ሦስት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ በጠቅላላው ምን ያህል ቤቶች ተገንብተዋል? ከተገነቡትስ ምን ያህሉ በዕጣ ለባለዕድለኞች ተላለፉ? ምን ያህሉስ ያለ ዕጣ ተላለፉ የሚሉትን ጉዳዮች ግልጽ መረጃ መስጠት እንዳለበት የቤት ዕድል ተመዝጋቢዎቹ ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች