Tuesday, November 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሌብነት የሚንሰራፋው ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጠፋ ነው!

ሌብነት ሲስፋፋ ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚያጋልጠው ሁሉ፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ደግሞ ለፖለቲካዊ ቀውስ ይዳርጋል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከአገሩ ሀብት ፍትሐዊ የሆነ ድርሻ፣ ተመጣጣኝ የሆነ የሥራ ዕድልና ተጠቃሚነት ሊኖሩት ይገባል፡፡ ዜጎች በሀብት ክፍፍል፣ በሥራ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመኖሪያ ቤትና በመሳሰሉት በጥረታቸው ልክ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ የሚረጋገጠው ዜጎች መብትና ግዴታቸው በግልጽ ታውቆ ዕውቅና ሲሰጠው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሌብነት በመብዛቱ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን እየጠፋ ነው፡፡ መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ የተሰገሰገው የሌባ ሠራዊት፣ ከመሬት ወረራ እስከ በጀት ዝርፊያ የተሰማራ ለመሆኑ ብዙ ተብሎበታል፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ የዳታ ማጭበርበር መከሰቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በዜጎች መካከል ልዩነት የሚፈጠረውና ተመጣጣኝ ያልሆነ የኑሮ ዘይቤ የሚስተዋለው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለበት ሥርዓት ሲሰፍን ነው፡፡ በአድልኦ የተሞላ ብልሹ አሠራርን ማስወገድ የሚቻለው ማኅበራዊ ፍትሕ በማስፈን ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕግ የበላይነት ትልቅ ሚና አለው፡፡ ብዙኃኑ ሠርቶ አደር ሕዝብ የሚፈለግበትን የዜግነት ግዴታውን ሲወጣ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለሌብነት የሚጠቀሙበትና በኔትወርክ ተቧድነው ዘረፋን ሙያ ያደረጉ ሞልተዋል፡፡

ግብር በመሰወር፣ ቀረጥ ባለመክፈል፣ በኮንትሮባንድ በመነገድና በመሳሰሉት ሕገወጥ ድርጊቶች በቢሊዮኖች የሚቆጠር የአገር ሀብት የሚዘርፉ እየተፈጠሩ ሲሆን፣ የተለያዩ ጫናዎችንና የዋጋ ግሽበትን መቋቋም ተስኗቸው የሚደቆሱ ሚሊዮኖች ቁጥራቸው እያሻቀበ ነው፡፡ ዕድሜ ልክ ተለፍቶ እንኳን ለማግኘት ለማሰብ የሚያዳግቱ ንብረቶችን በጥቂት ወራት ውስጥ ማከማቸት የሚችሉ ዘመነኞች በየቀኑ በሚፈለፈሉበት አገር ውስጥ እንዴት ስለእኩልነት መነጋገር ይቻላል? ምንጩ በማይታወቅ ገንዘብ እጅግ በጣም ዘመናዊና ውድ ተሽከርካሪዎች፣ ቪላዎች፣ ሕንፃዎችና የመሳሰሉትን የሚያካብቱትን የሚጠይቅ የለም ወይ? በየቦታው እንደ አሸን እየፈሉ ያሉ የአየር በአየር ሚሊየነሮች የት ነው የሚፈለፈሉት? አገራቸውን በቅንነት የሚያገለግሉ ዜጎች አንገታቸውን ደፍተው፣ ኃፍረተ ቢሶች አገርን እንዲዘርፉ መፍቀድ ያሳፍራል፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በሕጉ መሠረት ለጨረታ መቅረብ የሚገባቸው ፕሮጀክቶች በአቋራጭ በሙስና ሲጠለፉ፣ ግንባታቸው ከሚያወጣው ዋጋ በላይ በእጥፍ ሲጠየቅባቸው፣ በተፈለገው ጊዜ ሳይጠናቀቁ ሲቀሩና የትም ሲባክኑ በስፋት ይታያል፡፡ በጥቅም ሸሪክነትና በመሳሰሉት የተደራጁ ኃይሎች ያላግባብ የ20/80 እና የ40/60 ቤቶች እየታደላቸው እንዴት ስለማኅበራዊ ፍትሕ መነጋገር ይቻላል?

በመንግሥት በጀት የሚገነቡ ሆስፒታሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ መንገዶች፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ የመስተዳድር ሕንፃዎች፣ ወዘተ ጨረታዎች በሌቦች ተጠልፈው ከፍተኛ የአገር ሀብት ይወድማል፡፡ የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸምና የወጣባቸው ወጪ አይገናኝም፡፡ በስንት መከራ ተገንብተው ተጠናቀቁ ሲባል የጥራት ችግር ፈጦ ይወጣል፡፡ የተዘረፈው ሀብትና የሚገኘው ውጤት አይመጣጠንም፡፡ ጥቂት ምርጦች ተቧድነው ሲበለፅጉ ብዙኃኑ ዕዳ ይከፍላሉ፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለበት አሠራር እንዲህ ዓይነቱን አሳፋሪ ድርጊት ነው የሚያፈራው፡፡ በመንግሥት ዕቃ ግዥ፣ ጨረታና የኮንትራት አስተዳደር ላይ ፍትሐዊ አሠራሮች እየተገፉ ሌብነቶች ስለሚበረታቱ፣ ጤናማ ሥርዓት እንዳይኖር እያደረጉ ነው፡፡ ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ ተወዳድሮ ከማሸነፍ ይልቅ አማራጭ ማሳደድ የተለመደ ሆኗል፡፡ በዘመኑ ‹ጉዳይ ገዳይ› ተብለው በሚታወቁ ደላሎች አማካይነት ሕገወጥ ድርጊቶች በመስፋፋታቸው፣ ግዥዎችንና ጨረታዎችን በሕጋዊ መንገድ ተወዳድሮ ማግኘት ፈተና የሆነባቸው ዜጎች ብሶትና ምሬት ጣሪያ ነክቷል፡፡ ሕጋዊው መንገድ እኩል ተጠቃሚነትን የሚደግፍ አሠራር ቢሆንም፣ ሕገወጥነት የበላይነት ይዞ የጥቂቶች መፈንጠዣ ሆኗል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ዓይን አውጣ አሠራር ምክንያት ብዙኃን እየተገፉ፣ ጥቂቶች በአቋራጭ ባገኙት ሲሳይ ይከብራሉ፡፡ አሠራሮች ግልጽነትና ተጠያቂነት ስለሌላቸው በሕጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ሞኝነት፣ ሕገወጡን ጎዳና መያዝ ደግሞ የብልጥነት መለያ ሆነዋል፡፡ ብልጥነቱ ግን አገርን እየገዘገዘ ሕዝብን እያስለቀሰ ነው፡፡ በዜጎች መካከልም ደረጃ እያወጣ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነትን አኩሪ እሴቶች እየሸረሸረ ነው፡፡

በአንድ አገር ሰላም የሚኖረው ዜጎች ማኅበራዊ ፍትሕ አለ ብለው ሲያምኑ ነው፡፡ ጥቂቶች በማይታመን ፍጥነት የአገሪቱን ሀብት ሲቀራመቱና ብዙኃኑ ከድህነት ወለል በታች ሲሆኑ ስለሰላም መነጋገር አይቻልም፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ የሚፈለግበትን ግብር በአግባቡ ሲከፍል፣ ጥቂቶች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ሲሰውሩ ማኅበራዊ ፍትሕ ስለሚጠፋ ብጥብጥ ይነሳል፡፡ ጥቂቶች የአገሪቱን መሬት ወረው እየቸበቸቡ ሲከብሩና ቢጤዎቻቸውን ሲያበለፅጉ፣ ብዙኃኑ አንጀታቸውን አስረው የሚቆጥቡለት የጋራ መኖሪያ ቤት በልዩ ሁኔታ እየተባለ ለማንም ሲታደል አገር ሰላም አይሆንም፡፡ በቂ የሆነ ምግብ፣ ልብስ፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎት፣ ለኑሮ ተስማሚ የሆነ መኖሪያ፣ ወዘተ የሌለው ሠርቶ አደር ሕዝብ በብዛት በሚኖርባት አገር ውስጥ፣ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ የሚንደላቀቁ ሰዎችን ማየት ያሳፍራል፡፡ ለአገር ህልውናም አደጋ ነው፡፡ የአገር ህልውና የሚያሳስባቸው ወገኖች እንዲህ ዓይነቱን ኢፍትሐዊነት ለማስወገድ መረባረብ አለባቸው፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲ መብቶቻቸው የሚከበሩበት፣ በሁሉም መስኮች ጥቅሞቻቸው በአግባቡ የሚስተናገዱበት፣ በጥረታቸው መጠን የሚያገኙበት፣ በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበት፣ ሐሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበት፣ የመንግሥት ጥበቃ የሚያገኙበት፣ በሕጉ መሠረት ብቻ የሚዳኙበት፣ ወዘተ ማዕቀፍ ነው፡፡

ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ከፍተኛው ኃላፊነት ያለበት በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መንግሥት አሠራሩ ግልጽነትና ተጠያቂነት ስላለበት ለሕዝብ ፈቃድ ታዛዥ ነው፡፡ ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣል፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መዛባትና በሌብነት በምትናጥ አገር መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ፡፡ ችግሮቹ መኖራቸውን አምኖ ዕርምጃ ለመውሰድ እየሠራሁ ነኝ ከማለት ውጪ፣ ጠብሰቅ ያለና የሚያረካ ዕርምጃ ቢወስድ ይመረጣል፡፡ በእነዚህ ችግሮች የተማረረ ሕዝብ በየቦታው ምሬቱን እየገለጸ ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ለማድበስበስ ቢሞከርም፣ የሕዝብ ብሶት ገንፍሎ ከወጣ ለአገር ህልውና አደገኛ ነው፡፡ የሕዝብን የልብ ትርታ እያዳመጡ ምላሽ መስጠት የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ ከመጠን በላይ የሆነ የአገር ሀብት እየተዘረፈ ጥቂቶች ያላግባብ የሚበለፅጉበትን ሕገወጥ እንቅስቃሴ ማስቆም የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ኃላፊነት ብቻም ሳይሆን የህልውናውም ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡

ሕዝብ ጥያቄ ሲያነሳ በቅጡ አዳምጦ ምላሽ መስጠት ሲገባ፣ ያልሆነ አተካሮ እየፈጠሩ ግጭት እንዲባባስ ማድረግ ማብቃት አለበት፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎችን በማፈንና የተጣመመ ትርጉም በመስጠት የጥጋበኞችን አጀንዳ ማራመድ አገርን ይጎዳል፡፡ በዝርፊያ በሚገኝ ጥቅም ልባቸው የተደፈነ ወገኖች ማኅበራዊ ፍትሕ እንዳይኖርና ተጠያቂነት እንዳይነሳባቸው፣ የሕዝብን ድምፅ ከማፈን ወደኋላ አይሉም፡፡ ሕግ መከበር አለበት፡፡ መንግሥት በሕግ የሚገደድበትን አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ ያድርግ፡፡ መሸፋፈኑ ይበቃል፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ብቃት የሌላቸው፣ ከዝርፊያ በስተቀር ምንም የማይታያቸው፣ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ የማያሳስባቸው፣ ከጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት የዘለለ ዓላማ የሌላቸውና በደመነፍስ የሚኖሩ በቃችሁ ሊባሉ ይገባል፡፡ አንዳችም እሴት ሳይጨምሩ በንፋስ አመጣሽ ጥቅማ ጥቅም መክበር ሲለመድ፣ ሕጋዊው መንገድ እየተተወ ሥርዓተ አልበኝነት እንዲሰፍን ጥርጊያውን ያመቻቻል፡፡ ይህ ደግሞ ፀረ እኩልነትና ፀረ ፍትሐዊነት ስለሆነ ይዞት የሚመጣው አደጋ ከባድ ነው፡፡ ሌብነት የሚንሰራፋው ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጠፋ እንደሆነ ይታወቅ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...

ከድህነት ወለል በታች ከሆኑት አፍሪካዊያን ውስጥ 36 በመቶው በኢትዮጵያ ናይጄሪያና ኮንጎ እንደሚገኙ ተጠቆመ

‹‹ለሺሕ ዓመት በድህነት ውስጥ የነበረች አገርን በአሥር ዓመት ልንቀይር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...

አስጨናቂውን የኑሮ ውድነት የማርገብ ኃላፊነት የመንግሥት ነው!

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንደኛው የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ነበር፡፡...