በቀደም ዕለት የድሮ ጓደኞቼን ትዊተር ላይ ስፈልግና ሳፈላልግ በድንገት አንድ የመልዕክት ማሳወቂያ ጥልቅ ብሎ ገባ፡፡ መልዕክቱን ስከፍተው ከዓመታት በፊት የማውቀው ታንዛኒያዊ ጓደኛዬ ነው፡፡ ይህ ዳሬሰላም ዩኒቨርሲቲ የማውቀው ሰው በአሁኑ ጊዜ በትልቅ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ይገኛል፡፡ ድሮ ሳውቀው ለትምህርቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጥ፣ ለእስልምና እምነቱ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ሥፍራ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ በጣም ጨዋና ሰብዓዊነት የተሞላበት ነበር፡፡ የቀኑ ወበቅ በረድ ሲል በምሽት በዳሬሰላም ጎዳናዎች ላይ እየተራመድን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስንወያይ፣ ኢትዮጵያ ሁሌም የርዕሱ መነሻ ነበረች፡፡ በተለይ ዋናው ጎዳና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስም የተሰየመ በመሆኑ፣ ለእሳቸው ከነበረው ክብር የተነሳ ስማቸውን ሳያነሳ የቀረበት ጊዜም ትዝ አይለኝም፡፡ ይህ ሰው አገር ሰላም የምትሆነው የሰው ልጆች በእኩልነትና በነፃነት ሲኖሩ ነው የሚል እምነት ነበረው፡፡
አንድ ቀን የታንዛኒያ ‹‹ኡጃማ ሶሻሊዝም›› መሪ ስለነበሩት ጁሊየስ ኔሬሬ ሲነግረኝ፣ ‹‹ሙአሊሙ (መምህር) ኔሬሬ ዕድሜ ልኩን ሲለፋ የኖረው የታንዛኒያ ሕዝብ እንዲያልፍለት ነበረ፡፡ አንድም ቀን ለራሱ የሚሆን ቤት መሥራትና ለጡረታው ጥሪት መያዝ እንዳለበት አስቦ ስለማያውቅ፣ ሕዝቡን አገልግሎ በጡረታ ሲሸኝ ለመቋቋሚያ የሚሆን ጥቂት ሽልንጎች ያዋጣለት ሕዝቡ ነበር፡፡ እሱም የተሰጠውን በምሥጋና ተቀብሎ ገጠር ገባ…›› እያለ ሲነግረኝ በዕውን ሳይሆን በሕልም ዓለም ውስጥ ያለሁ ነበር የመሰለኝ፡፡ ‹‹ሙአሊሙ ገጠር ገብቶ ከአገሩ ገበሬዎች ጋር እርሻ ውስጥ እየዋለ ይህችን ዓለም ተሰናብቶ ሥርዓተ ቀብሩ በታላቅ ክብር ተፈጸመ፤›› ሲለኝ፣ ይህ ነገር የተፈጸመው አፍሪካ ውስጥ ይሆን እንዴ ብዬ መጠየቄን አረሳውም፡፡
እኔ እዚያ በነበርኩበት ጊዜ ኢሕአዴግን እንደ ኳስ እያንቀረቀቡ በኢትዮጵያ ምድር እንዳሻቸው ይሆኑ የነበሩ ሕወሓታውያን፣ ከአገር የዘረፉትን ሀብት ወደ ዶላርና ዩሮ እየቀየሩ ያሸሹ እንደነበር አገር አውርቶ የጨረሰው ዜና ነበር፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለ ድርጅት ውስጥ በኤክስፐርትነት ይሠራ የነበረ አንድ ሽማግሌ ፈረንጅ ጀርመን ውስጥ በአጋጣሚ ተገናኝተን እንደነገረኝ፣ የሕወሓት ሰዎች የአገር ሀብት በማሸሽ ከአፍሪካ አንደኛ ነበሩ፡፡ የአፍሪካ ሪፖርት ሲወጣም ይህ ገመናቸው ይፋ እንዳይደረግ ጉቦ እንደሚሰጡም ነግሮኛል፡፡ ኢትዮጵያ በጥቅሉ ለረዥም ጊዜ አነስተኛ ሙስና የሚፈጸምባት ተብላ እንድትጠራም ከፍተኛ ትግል ማድረጋቸውንም እንዲሁ፡፡ ይህንን ሁሉ ጉድ ተሸክማ ትኖር በነበረች አገር ውስጥ የፈጸሙዋቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ደግሞ ለኢትዮጵያዊያን ምን ያህል ከባድ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስና ታንዛኒያዊው የድሮ ጓደኛዬ ሰላምታውን በታላቅ ፍቅርና አክብሮት ከገለጸልኝ በኋላ፣ ‹‹ለመሆኑ እነዚህን ጉዶች እንዴት አድርጋችሁ ነው ተሸክማችሁ የኖራችሁት? ሕዝበ ሙስሊሙንና ክርስቲያኑን ሲያሰቃዩ ኖረው በቃችሁ ሲባሉ ምን እንሁን ብለው ነው ጦርነት ያስነሱት? ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያንን ሁሉ ግፍና መከራ እየተቀበለ አገሩ ተዘርፋ በከፋ ድህነት ውስጥ እየኖረ የአዕምሮ ጤንነቱ እንዴት ነው? በአጠቃላይ ማኅበራዊ መስተጋብሩ በጎሰኝነት ላይ በተመሠረተው ከፋፋይ ፌዴራሊዝም ምክንያት አልተጎዳም? የሥነ አዕምሮና የሥነ ልቦና ባለሙያዎችስ ምን ይላሉ?›› የሚሉ ጥያቄዎቹን ሳነብ ደነገጥኩ፡፡ ከዚህ ቀደም የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን ሲከበር የወጣው አኃዛዊ መረጃ ትዝ ሲለኝ ጉዳዩ በጣም አሳሰበኝ፡፡ ከአጠቃላዩ ሕዝብ 27 በመቶ የአዕምሮ ችግር እንዳለበት የሚገልጸው መረጃ ማለት ነው፡፡
ጎበዝ በሕወሓታውያን ምክንያት የደረሰብን ጉዳት እኮ እንዲህ በቀላሉ የምናየው አይደለም፡፡ ለ27 ዓመታት እንዳሻቸው ሲጫወቱባት የነበረችን አገር እኮ በሕዝባዊ ዕንቢታ ተገፍተው ዘወር ሲደረጉም፣ ከሁለት ዓመት ከምናምን በላይ በእጅ አዙር ግጭቶችን እየቀሰቀሱ የጅምላ ፍጅቶችን አካሂደዋል፡፡ የዘረፉትን የአገር ሀብት፣ እጃቸው ውስጥ የነበረውን የፀጥታና የደኅንነት መዋቅር፣ ለክፉ ጊዜ ያስቀመጡዋቸውን ተቃዋሚ ተብዬዎች፣ ‹የጠላትህ ጠላት ወዳጄ ነው› በሚል ጉድኝነት ለውጡ ዕድል የሰጣቸውን አፈንጋጮችና ጥቅም ቃራሚዎች በማሰባሰብ አገሪቱን ሲኦል አድርገዋታል፡፡ ከቡራዩ እስከ ወለጋ በተፈጸሙ በጣም በርካታ ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች እጃቸው አለበት፡፡ ከዚህም አልፈው ተርፈው የአገሪቱን የመከላከያ ኃይል ጨፍጭፈዋል፡፡ ንፁኃንን ያለ ርህራሔ ገድለዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ጉድ የቻለ ምስኪን ሕዝባችን አዕምሮው አለመቃወሱ የፈጣሪ ተዓምር ነው፡፡
የታንዛኒያዊው የድሮ ጓደኛዬ መጨነቅና መጠበብ ከሰብዓዊነት የመነጨ በመሆኑ፣ እኔም ይህንን ጥያቄ የመመለስ ኃላፊነት ቢኖርብኝም ሰላምታውን በአፀፋው መልሼ ለጊዜው ጉዳዩን አድበስብሼ አለፍኩት፡፡ ባድበሰብሰውም ግን ዕረፍት እንደነሳኝ ነበር፡፡ በዚህ መሀል ካናዳ ካልጋሪ የምትኖረው ታላቅ እህቴ ስልክ ደውላልኝ ስለአገር ጉዳይ ስናወራ የገጠመኝን ነገርኳት፡፡ እህቴ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ከመጀመርያ ሴት ልጇ ጋር ይህንን ያስጨነቀኝን ነገር አንስተው እንደነበረ ነገረችኝ፡፡ ይህ ጉዳይ ለካ የብዙዎች መነጋገሪያ እየሆነ ነው፡፡ እህቴ ልጇ ያለቻትን ልንገራችሁ፡፡
‹‹እማዬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ወገኖቻችን ይህንን ሁሉ መከራና ሥቃይ እየተቀበሉ እንዴት ጤነኛ ሆነው ይኖራሉ? ለመሆኑ የአዕምሮ መታከሚያ ሆስፒታሎች በበቂ መጠን አሉ ወይ? ተመራማሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የሠሩትና ያቀረቡት ሪፖርት ሊገኝ ይችላል ወይ?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ነው ያቀረበችው፡፡ ወገኖቼ ከዚህ በተጨማሪ ጥቃቶች በሚፈጸሙባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖቻችን በጅምላ ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉ፣ ሲደፈሩ፣ ሲዘረፉና የተለያዩ ሥቃዮች ሲደርሱባቸው ሰምተናል፡፡ በሕይወት የተረፉ ምስኪን ወገኖቻችን የአዕምሮ ጤና ጉዳይ እንዴት ይሆን? ጊዜያዊ አስቸኳይ ዕርዳታ ከማቅረብና ለዘለቄታው ለማቋቋም ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን ይኼ መሠረታዊ ጉዳይ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ በበኩሌ ሳስበው አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ያለን ይመስለኛል፡፡ ከአካላዊ ጉዳት በበለጠ ይኼኛው ከፍተኛ አገራዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላልና፡፡ እስቲ እናስብበት፡፡
(ያሬድ ደምሴ፣ ከሰሜን ማዘጋጃ)