Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበአገራዊ ውይይት ውስጥ የውጭ ኃይሎች የተሳትፎ ሚናና የሌሎች አገሮች ተሞክሮ (ክፍል...

በአገራዊ ውይይት ውስጥ የውጭ ኃይሎች የተሳትፎ ሚናና የሌሎች አገሮች ተሞክሮ (ክፍል ሦስት)

ቀን:

በመኮንን ዛጋ

የቴክኒክና የባለሙያ ድጋፍ አቅራቢነት ሚና

እንደሚታወቀው አገራዊ ውይይት በጽንሰ ሐሳብ ደረጃም ሆነ እንደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በሚገባው ልክ በስፋት ያልተተነተነ፣ የጥናትና ምርምር ጽሑፎች በሚገባው ልክ ያልተሰነዱለት የሰላም ግንባታ ፈርጅ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከእዚህ አንፃር አብዛኞቹ ዘርፉ ምሁራን ጽንሰ-ሐሳቡን ለማፍታታት የተለያዩ አገሮችን ተጨባጭ ተሞክሮ እንደመነሻ እየወሰዱ ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡ ለእንደኛ ዓይነቱ አገርም ዘርፉ በሚገባው ልክ ያልተብራራና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባሉ የፖለቲካ ትርክቶች የሚነሳ በመሆኑ የክህሎት፣ የመረጃ፣ የአሠራር ሥርዓትና የአተገባበር ዕውቀት ክፍተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከዚህ አንፃር በዘርፉ ጥናትና ምርምር የሠሩ እንዲሁም፣ የሌሎች አገሮች መሰል ሁነቶች ያደራጁ፣ ያስተባበሩና ወደ ትግበራ ያስገቡ ዓለም አቀፍና ክልላዊ ተቋማት፣ አገር፣ እንዲሁም ከእነሱ ጋር አብረው የሠሩ ባለሙያዎች ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ስለሚኖራቸው አገራዊ ውይይትን ለመደገፍ ክህሎታቸውን ቢያዋጡ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህም ‘የቴክኒካዊና የሙያዊ ድጋፍ ሰጪነት’ የውጭ ተዋናዮች ሚና የሚከናወነው እነዚህ አካላት በውይይቱ ሒደት ውስጥ አንድ ልዩ ዓይነት ዕውቀት ወይም ክህሎት ወደ ውይይቱና ተሳታፊዎች ሲያመጡ ነው።

አገራዊ ውይይቶችን ማዘጋጀት በተለይም የክንውን ሒደቱን ለመንደፍ ወይም በድርድሩ ተጨባጭ ጉዳዮች ላይ ለአብነት እንደ ሥልጣን መጋራት፣ ወይም ሀብት ክፍፍል ያሉ አንገብጋቢና አከራካሪ ጉዳዮች ላይ ዕገዛ ለመስጠት ቴክኒካዊ ዕውቀት ይጠይቃል። ለምሳሌ በተለያዩ የሽምግልና ሒደቶች ውስጥ በመሳተፍ እየተሻሻለ ከመጣው ሚናው፣ ካዳበረው ተዓማኒነትና ጥልቅ ተሞክሮው አንፃር የአፍሪካ ኅብረት የቴክኒክ ክህሎትና የባለሙያዎችን ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል።

የአፍሪካ ኅብረት ከእነዚህ ሚናዎች መካከል አንዳንዶቹን ከእዚህ ቀደም በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በማከናወኑ ተጨባጭ ተሞክሮዎችን ለማዳበር ችሏል፡፡ ለዚህም ተጠቃሹ በኬንያ እ.ኤ.አ. በ2007 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የተፈጠረውን የድኅረምርጫ ውዝግብ በውስጣዊ ፖለቲካዊ ኃይሎች በአግባቡ መፍታት ባለመቻሉ፣ የተከሰተውን ደም አፋሳሽ ብጥብጥ ወደ ከፋ ደረጃ ሳይደርስ ለማርገብ የአፍሪካ ኅብረት በኬንያ ብሔራዊ የውይይት መድረክ እንዲቋቋም ረድቷል፡፡ እንዲሁም የኬንያ ብሔራዊ ውይይትና ዕርቅ (KNDR) ሒደትን ለመደገፍ የታዋቂ አፍሪካዊ ሰብዕናዎች ቡድን በመሾም የረዳ ሲሆን፣ የልዑካን ቡድኑ የተመራው በቀድሞው የተመድ ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ነበር። ይህ የኬንያ ብሔራዊ ውይይትና ዕርቅ ኮሚሽን በሥልጣን ክፍፍል መርህ ብጥብጡ ሳይራገብ ለማስቆም እንዲቻል፣ የፖለቲካ ኃይሎቹ ድርድር እንዲያደርጉ ረድቷል። እንዲሁም ልዩ ተቋማትን በማቋቋምም አንዳንድ የረዥም ጊዜ አገራዊ ችግሮችን መፍታት አስጀምሯል።

የውጭ ኃይሎች የድጋፍ ዓላማ ዋነኛው ጉዳይ የብሔራዊ ውይይት ተሳታፊዎች አግባብነት ያለው ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው በማድረግ፣ በውይይቱ ሒደት ውስጥ በብቃትና በምሉዕ ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት በዘላቂነት እንዲሳተፉ ማድረግ ነው። የቴክኒካዊ ድጋፍ የምንለው በተወሰኑ የውይይቱ ደረጃዎችና አጀንዳዎች ላይ ለሚፈጠሩ ቅርቃሮች መፍቻ እንዲሆኑ ከሚቀርቡ ቁልፎች ተጨባጭ ግብዓቶች (የውይይት ሒደት ንድፍ፣ የሥልጣን መጋራት፣ የውሳኔ አሰጣጥ፣ አደረጃጀት፣ ወዘተ…) ጀምሮ እስከ ክህሎት ሥልጠናና የንፅፅር ዕውቀት ድረስ ይደርሳል። በተጨማሪም በተለያዩ የብሔራዊ ውይይት ተሳታፊዎች መካከል እርስ በርሳቸው ወይም በውጭ ባለሙያዎችና በተሳታፊዎች መካከል የሚደረጉ የልምድ ልውውጥና የምክክር ስብሰባዎችን ማመቻቸት፣ የእርስ በርስ መተማመንን የሚገነቡ ልምምዶችን ማዳበር፣ ለሒደቱ ውጤታማ አፈጻጸም የሚረዱ ጽንሰ ሐሳቦችን ማብራራት ወይም ስለጽንሰ ሐሳቦቹ የጀርባ ትንተና መስጠትና የአጫጭር የሐሳብ መግለጫዎች ፓኬጆችን ሊያካትት ይችላል።

ስለሆነም የቴክኒካዊና የሙያዊ ድጋፍ ጊዜያዊ በሆነ መንገድ (አጀንዳና ሁነት መር ሆኖ)፣ በቋሚነት በተደራጀ አካል (የባለሙያዎችና የምሁራን መድረክ በማቋቋም) ወይም የተወሰኑ ጥያቄዎችን ለማብራራት በሚረዳ ቅርፅ ሊቀርብ ይችላል። ለዚህም እንደ ማሳያ የሚቆጠረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) በዮርዳኖስ አገራዊ ውይይት የነበረው ተሳትፎ ሲሆን፣ ይኸውም በብሔራዊ የውይይት ኮሚቴ አባላት አለመግባባት ወይም እንቢ ባይነት ድርድሩ ሲታገድ የምክክሩ አዘጋጅ አካል ይፋዊ ጥያቄ በማቅረብ በጉዳዩ ላይ በቀጥታ እንዲገባበት እየተደረገ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ሲደረግ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይህን መሰሉ ሙያዊ ድጋፍ ብሔራዊ ውይይትን ለመደገፍና ለማሳለጥ በተቋቋሙ ኢቀጥተኛ ወይም ባለልዩ መድረኮች አማካይነት ሊሰጥ ይችላል።

በአንዳንድ ወቅቶች ከመደበኛ የቴክኒካዊ ድጋፍ በተለየ እነዚህ የልዩ መድረክ ሥርዓቶች እጅግ ጠቃሚ ናቸው፡፡ በተለይም ኦፊሴላዊው የውይይትና ድርድር ሒደት የመጨረሻ ሳንካ ሲያጋጥመው ወይም ቅርቃር ውስጥ ሲገባ፣ እነዚህ መድረኮች ቴክኒካዊ ዕውቀት ከመስጠት በተጨማሪ እንደ መደበኛ ያልሆነ የድርድር ሥፍራዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ለምሳሌ በኔፓል የተካሄደው የኔፓል ሽግግር ወደ ሰላም ሥልት (Nepal Transition to Peace Mechanism-NTTP) እነዚህን ሁለት የሙያዊ ድጋፍ ሥልቶች ተግባራት በሚገባው ሁኔታና ሥፍራ አጣምሮ ሲጠቀም ነበር። በሌላ በኩል በሊባኖስ ውስጥ የተዋቀረው የሊባኖስ የጋራ ፖለቲካዊ ምኅዳር ተነሳሽነት (Common Space Initiative in Lebanon) መድረክ ሌላው ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። ይህ መድረክ እ.ኤ.አ. የ2008 የሊባኖስ የአገር አቀፍ ውይይት ክንውን መሠረቱን ለማስፋት በጎንዮሽ የተዋቀረ ሲሆን፣ በአብዛኛው በፖለቲካ ልሂቃን የሚመራ ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎችንና የሲቪክ ማኅበራትን በማካተት በቁልፍ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሙያዊና ቴክኒካዊ ሥልጠና፣ ምርምርና ጥናት፣ እንዲሁም ግንዛቤ በማስጨበጫ በመስጠት የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያስቻለ ነበር።

በአገራዊ ውይይት ሒደት ውስጥ እነዚህ የቴክኒክና የሙያዊ ድጋፍ ሚናዎች የሚተገበሩባቸው ደረጃዎች የተለያዩ ቢሆኑም በዋናነት በጥንስስ፣ በዝግጅትና በክንውን ሒደት ምዕራፍ ውስጥ በጣም ጠቃሚ ናቸው። በተለይም በብሔራዊ ውይይት የትግበራ ምዕራፍ ላይም ወሳኝ ሚና መጫወት ይችላሉ።

አስተባባሪነት/አመቻች ወይም አሳላጭ ሚና

የውጭ ተዋናዮች ከዚህ ሚናቸው አንፃር ሲታዩ ‘የጎን ህዳግ አበረታቾች፣ በመሀል የሚፈጠርን ልዩነት የሚያስታርቁ አስተባባሪዎች’ በመሆን የሚያግዙ ሲሆን፣ በተቃራኒ ወገኖች መካከል የጋራ እምነትን ለመፍጠር ወይም በሒደቱ ውስጥ የተለዩ አከራካሪ ጉዳዮችን ለመፍታት እንደ መሀል አማካይ ሆነው የሚሠሩና የሚረዱ ናቸው። በእርግጥ በብሔራዊ የውይይት ሒደቶች ውስጥ ዋነኞቹ አስተባባሪዎችና ተዋናዮች በቀዳሚነት ውስጠ-አገራዊ ባለ ድርሻዎች (ግለሰቦችና ቡድኖች) ቢሆኑም፣ የውጭ አካላት ለተወሰኑ ዓላማዎች ስኬትና የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደ ሦስተኛ አካል አመቻች ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።

ለእዚህ ምሳሌ የሚሆነው የውጭ ተዋናዮች የብሔራዊ ውይይት ተሳታፊዎችን አከራካሪ በሆኑ አጀንዳዎችና የኃይል ሚዛን ሲያጋድል፣ ገዥው መንግሥት በኃይል መጨቆን ሲያበዛ መደበኛ ባልሆነ መንገድ (ዲፕሎማሲ በመጠቀም) በማደራደርና በማወያየት እንዲሁም በማግባባት፣ ወደ አንድ ሐሳብና የጋራ አሸናፊነትን ወደ የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ ለማምጣት ረጅም ርቀት መሄድ ይችላሉ፡፡ ይህም ተወያዮች በይፋዊ መቼትና ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ሊገለጽ በማይቻል መንገድ ሁሉን ወገን አሸናፊ የመፍትሔ አማራጮችን ሰከን ብለው እንዲመረምሩ ያስችላቸዋል። ይህንን ሚና በሁሉም በተቃራኒ ወገኖች ዘንድ አመኔታን ለማግኘት በአብዛኛው በሚል አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተደጋግሞ እንዲወጡት ሲደረግ ይታያል። ከእነዚህ መካከል በሱዳንና በየመን የቤርግሆፍ ፋውንዴሽን፣ እንዲሁም የሰብዓዊ ጉዳዮች ውይይት ማዕከል ተቋማት የተጫወቷቸው ገንቢ ሚናዎች ለአብነት ይጠቀሳሉ።

እንደሚታወቀው እንደ የመንና ሊቢያ ባሉ አንዳንድ አገሮች በተካሄዱ ብሔራዊ ውይይቶች ውስጥ የውጭ ተዋናዮች አልፎ አልፎም ቢሆን ኦፊሴላዊ (ይፋዊና ሕጋዊ) አስተባባሪዎች ሆነው አገልግለዋል። ለዚህም በሊቢያ ባለው የአገራዊ ፖለቲካዊ ውይይት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአመቻችነት ሚና አንዱና ተጠቃሹ ነው። ሌላው ምሳሌ በሱዳን የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ደረጃ የትግበራ ቡድን የተጫወተው የአሳላጭነት ሚና ነው፡፡ በእርግጥ ይህ የከፍተኛ ባለሙያዎች ስብስብ የሱዳን ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድ በራሱ ወይም ለብቻው ሁኔታውን ያመቻቸ ባይሆንም፣ ነገር ግን ፓርቲዎች ሁሉን አቀፍና ተተግባሪ የፖለቲካ ስምምነት ላይ እንዲደራደሩ በመደገፍ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የአገራዊ ውይይት ጥንስስ እንዲዘጋጅና ለውይይት መድረክ ክንውን ሒደት ምቹ መደላድል እንዲፈጠር የሚያስችል መንገድ የጠረገ ስብስብ ነበር።

ከዚህ ተሳትፎ የምንገነዘበውና ለአገራችን እንደተሞክሮ የምንወስደው ቁልፍ ነገር ቢኖር በሙሉ ሒደቱ ውስጥ ሳይሆን በአንዳንድ የአገራዊ ውይይት ዓውዶች ውስጥ የውጭ ተዋናዮች እንደ ይፋዊ አስተባባሪ ሆነው ሊያገለግሉ መቻላቸው ነው፡፡ በተለይም በውይይቶች መካከል በሚፈጠሩ አለመግባባቶችና የአቋም መፈራቀቆች የተነሳ የውይይት አጀንዳዎች መሀል ላይ ተቸክለው ሲቀሩ፣ በውይይቱ አዎንታዊ ዕርምጃዎች ለማምጣት የጀርባ አቅምና አቋምን (Leverage) መጠቀም በሚያስፈልግበት ወቅት፣ እንደ ሁነኛ ማሳለጫ ሆነው ያገለግላሉ። ሆኖም ለአዘጋጁ አካልም ሆነ ለውጭ ተዋናዮች አንዱ ተጠቃሽ ተግዳሮት የሚሆንባቸው የአመቻችነት ሚናቸውን ሲወጡ፣ የውይይት ሒደቱ ገጸ ምሥል የአገር አቀፍ ባለቤትነት እንዲኖረው ከማድረግ ጋር በተያያዘ የሚኖረውን አሉታዊ ስሜት ለማጣጣም በሚጓዙበት አካሄድ ረገድ ነው።

ቀጥሎ የውጭ ኃይሎች እንደ አስተባባሪዎች ሆነው የሚመጡት ወይም መምጣት ያለባቸው በየትኞቹ የውይይት ምዕራፎች ለሚለው ጥያቄ ሁነኛ ምላሽ የሚሆነው፣ በዝግጅትና በክንውን ሒደቱ ወቅት የሚል ነው።

ለአብነት ያህል በመሰናዶ ምዕራፍ ውስጥ በሚደረጉ መደበኛ ባልሆኑ የአጀንዳ ቀረፃዎች፣ የባለድርሻ አካላት ስብሰባዎችና የሐሳብ ልውውጥ መድረኮች አማካይነት ምቹ የመግባቢያ ቦታዎችን መክፈት የሚችሉ ሲሆን፣ በዚህም በተዋናዮች መካከል ጥልቅ የመተማመን ስሜትን ያስፋፋሉ፡፡ በክንውን ሒደቱ ምዕራፍ ውስጥ ደግሞ የውጭ አስተባባሪዎች በስምምነት ያልተቋጩ ከባድ ችግሮችን ለመፍታትና ቅርቃሮችን ለመስበር፣ እንዲሁም ፈታኝ ሁኔታዎችን አስቀድሞ በመለየትና መፍትሔ በማበጀት (መፍትሔ ፈጣሪዎች ሆነው)፣ በተጨማሪም ሒደቱ በአንድ ሥፍራ እንዳይደናቀፍ አፋጣኝ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በመለየት መፍታት ይችላሉ።

አስፈጻሚ፣ ተቆጣጣሪና አረጋጋጭ

በዚህ ተግባር የሚካተቱ የውጭ ተዋናዮች ሚና በውይይቱ መባቻ መግባቢያ የተደረሰባቸውን ነጥቦች፣ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች፣ የተፈረሙ ስምምነቶችን ድምዳሜ የተደረሰባቸው ሐሳቦች ወደ ተግባር ለመተርጎም፣ ለመከታተል ወይም ከብሔራዊ ውይይት የተገኙ ውጤቶችን ትግበራ የመቆጣጠር ኃላፊነት ሲኖራቸው ነው፡፡ በዚህ ሚናቸው ‘አስፈጻሚዎች’ ወይም በአማራጭነት መገለጫ ደግሞ ‘ተቆጣጣሪዎችና አረጋጋጮች’ ተብለው ይጠራሉ። በእርግጥ ይህ ሚና ከላይ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ከተጠቀሱት የውጭ ኃይሎች ሌሎች አምስት ሚናዎች ጋር በተደጋጋሚ ጊዜና ሁኔታ የመደራረብ ባህሪ አለው፡፡ ለምሳሌ ቴክኒካዊ ዕውቀት ከማስተላለፍ፣ ከፈንዶች አቅርቦትና ከዋስትና ሰጪነት፣ ወዘተ ጋር የሚያያዝ ሲሆን ይህ ብዙ ጊዜ በአተገባበር ደረጃም ይቀጥላል። የየመንና የኬንያ ሁኔታ እንደሚያሳየው ከሆነ በዚህ ሚና ውስጥ የሚካተቱ የተተግባሪ ሥራዎች መጠን በዓይነት መበራከትና ተከታታይነት የተነሳ፣ ይህ ተግባር በአብዛኛው የሚፈጸመው በክልላዊ ወይም በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ነው።

የየመን ምሳሌ እንደሚያሳየው ከሆነ ደግሞ በትግበራው ምዕራፍ ላይ የልማት ደጋፊ ተዋናዮች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። በአንፃሩ ደግሞ በዚህ የትግበራ ምዕራፍ የውጭ ተዋናዮች ሥራዎች በአብዛኛው በአካባቢያዊ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የቁጥጥር ተቋማትና መሰል የትስስር መረባቸው አማካይነት በውጤታማነት ሊሟላ ይችላል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አካላት ከውጭ ኃይሎች በተሻለና በተለየ መንገድ የችግሩን ውስጣዊ ዓውድ በቅጡ ስለሚረዱ፣ ነገረ ጉዳዩን በፍፁም ባለቤትነት ስለሚይዙት፣ አጠቃላይ ሁኔታው ውስጥ የተካተቱ በመሆናቸውና ትግበራ የሚሹ እጅግ በጣም ሩቅ ሥፍራዎች ላይ ሊደርሱ ስለሚችሉ ነው፡፡

ይህን ተግባር ከውይይት ሒደት ደረጃዎች አንፃር ካየነው፣ ጠቀሜታው በአብዛኛው በአተገባበር ምዕራፍ ላይ እጅግ የጎላ ነው። ይሁን እንጂ በዝግጅት ወይም በክንውን ሒደቱ መጀመሪያ ላይ ወይም በክንውን ሒደቱ ወቅት፣ የጦርነት ማቆም ወይም የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ የውጭ ፈጻሚዎች/ትግበራ ተከታታዮች ወደ ቅድመ ውይይቱ የመግቢያ ነጥቦችን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...