Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉለኢትዮጵያም ውኃ ሕይወት መሆኑን የዘነጉት ሱዳንና ግብፅ

ለኢትዮጵያም ውኃ ሕይወት መሆኑን የዘነጉት ሱዳንና ግብፅ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

በአንድ ወቅት በካይሮ ከግብፁ ማርሻል አልሲሲ ጋር ለፕሬዚዳንትነት እወዳደራለሁ ያሉ አንድ አዛውንት እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹ውኃ ለእኛ ሕይወት ነው፡፡ ስለዚህ ውኃችንን ላለማስነካት ማንኛውንም ዕርምጃ እንወስዳለን… ፕሬዚዳንት ሆኜ ብመረጥ በዓባይ የተነሳ ጦርነት አውጃለሁ…›› ዓይነት አባባል ተሰምቶባቸው ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ማሳዘናቸውን እናስታውሳለን፡፡ ይህ በርከት ያሉ የካይሮ ፖለቲከኞች አስተሳሰብ ነው፡፡

በእርግጥ ውኃ ሕይወት መሆኑን ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለግብፃውያን መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ እኛ ሰጪ ሆነን እነሱ ተቀባይ ሆነው በውኃ ጉዳይ ላይ ብዙ ሺሕ ዓመታት ኖረናል፡፡ ተርታው ሕዝብ ሳይቀር ውኃ ሕይወት መሆኑን ከዕለት ተዕለት ሕይወቱ ካገኘው ልምድና የተፈጥሮ ዕውቀት ተነስቶ ያውቀዋል፡፡ ሁሉም ነገር ከውኃ የተሠራ መሆኑ በታላላቆቹ የእምነት መጻሕፍት ውስጥ ሁሉ መኖሩም ሊካድ አይችልም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተለይ በአሁኑ ወቅት ውኃ እጅግ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በውኃ ዙሪያ ግን ተስማምቶ ከመጠቀም የተሻለ አማራጭ የለም፡፡ የወደፊቱን የውኃ ሁኔታ ስናይ ደግሞ ተስማምቶ የመጠቀምን አማራጭ ወደር የለሽነት እንገነዘባለን፡፡ አሁን እንደሚታየው ግን በግብፃዊያን የሴራ ፖለቲከኞች ግፊት ዋዣቂና ከንቱ አካሄድ የመረጡ የሱዳን ጀሌዎች፣ ይህንን እውነት ክደው ድንፋታ ማብዛታቸው ማንንም የማይበጅ ድርጊት ነው፡፡

ለምሳሌ በሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት የዓለም የንፁህ መጠጥ ውኃ ፍላጎት በብዙ የዓለም አገሮች ካለሰው የውኃ አቅርቦት መጠን በእጅጉ የበለጠ ይሆናል፡፡ የንፁህ ውኃ ፍላጎታችን አገራችን ከምታቀርብልን የውኃ አቅርቦት የበለጠ ይሆናል እንደ ማለት ነው፡፡ በየጊዜው በሚያድገው የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና እየተስፋፋና እየተጠናከረ በመጣው የእርሻ ሥራ የተነሳ፣ የሰው ልጅ ያሉትን የውኃ (የወንዝ) ተፋሰሶች በጋራ የመጠቀምንና የጉድጓድ ውኃ ፍለጋን አጠናክሮ ተያይዞታል፡፡ ታዲያ እኛስ ብንሆን ማን ነንና ነው የራሳችንን በትነን በተስፋ ልንኖር የምንችለው?

የዓለም ሙቀት በየጊዜው መጨመሩ የውኃ እጥረት ባለባቸው አገሮች ላይ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይሆንባቸው የሚሠጋውም ለዚህ ነው፡፡ ውኃ ያላቸው አገሮችም ቢሆኑ ከረጅም ጊዜ አንፃር ሲያሰሉት የሥጋታቸው ምንጭ ይህ የዓለም ድርቅ ሁኔታ ሆኗል፡፡ የሙቀት መጨመር የሰው ልጅ ዋነኛ የውኃ ምንጭ የሆኑትን የበረዶ ግግሮች በፍጥነት እያቀለጠ ለትነት ማጋለጡ ለወደፊቱ የውኃ ችግር የማይወጡት ፈተና (ተግዳሮት) እንደሚሆን ማሳያ ነው፡፡ እናም በዘልማድ ሳይሆን የውኃ ሀብትን በቁጠባና በመተሳሰብ መጠቀሙ ነው የሚበጀው፡፡

በቅርቡ ግሎባል ዋተር ሴኩሪቲ የተባለው የአሜሪካ የመረጃ ምርምር ተቋም ጥናት እንዳመለከተው፣ እ.ኤ.አ. በ2030 የዓለም ሕዝብ ዓመታዊ የውኃ ፍላጎት አሁን ካለው ዘላቂ የውኃ አቅርቦት 40 እጥፍ ይበልጣል፡፡ ከውኃ አቅርቦት አቅማችን 40 ጊዜ እጥፍ የሆነ የውኃ ፍላጎት አለብን፡፡ ይህን እውነት የምሥራቅ አፍሪካ በተለይም የግብፅና የሱዳን የውኃ ፖለቲከኞች ይስቱታል ባይባልም፣ በነባሩ ጠቅላይነት አስተሳሰብ ለመጓዝ መሻታቸው ፍፁም ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም፡፡ ለማናችንም ቢሆን ውኃ ሕይወታችን ነውና፡፡

እንደ ዓለም አቀፍ መረጃዎች ከሆነ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ውኃ በአንዴ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚገኝ ሆኖ ሳለ፣ በዚያው መጠን የውኃ እጥረት መኖሩ ከምድራችን አስገራሚ ክስተቶች አንዱ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ የውኃ ግብዓት የሆኑት የኃይድሮጂን (ሁለት እጅ) እና የኦክስጂን (አንድ እጅ) የተፈጥሮ ግብዓቶች 97.5 በመቶ ያህሉ የሚገኙት በውቅያኖሶቻችን ውስጥ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡

ከተቀረው ንፁህ ውኃ 2.5 በመቶ ከሚያህለው ውስጥ ደግሞ ሁለት ሦስተኛው በአንታርክቲካና በግሪንላንድ የበረዶ ግግሮችና በከርሰ ምድር ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ የውኃ ክምር በሁሉም ቦታዎች ላይ እያለ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በሁሉም ቦታዎች ላይ ችግር የሚሆንበት ሚስጥር አለ፡፡ በእርግጥ አስተማማኝ የውኃ ምንጭ ፍላጎት የሰውን ልጅ ዕድሜ ያህል ያስቆጠረ ፍላጎት ነው፡፡ ዛሬ አዲስ የሆነብን በጣም አናሳ ለሆነ የንፁህ ውኃ የማያባራ የተጣመረ ዓለም አቀፍ ጥያቄ (ፍላጎት)፣ መልካም አስተዳደር በሌለባቸው አካባቢዎች እየተባባሰ መምጣቱ ነው፡፡

መጠኑ እያነሰ ለመጣው የንፁህ ውኃ ችግር መባባስ በምክንያትነት የሚጠቀሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዱና ዋናው የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እ.ኤ.አ. በ2025 የዓለም ሕዝብ ቁጥር አሁን ካለበት ሰባት ቢሊዮን ወደ ስምንት ቢሊዮን ያድጋል፡፡ አብዛኛው የሕዝብ ቁጥር ጭማሪ የሚኖረው ደግሞ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች በተለይም በአፍሪካ ነው፡፡ በፈጣን ሁኔታ በሚስፋፉት የከተማ ማዕከላት የንፁህ ውኃ ጥያቄ (ፍላጎት) በከፍተኛ መጠን ይጨምራል፡፡ ለግል ፍጆታ፣ ለፅዳት፣ ለኢንዱስትሪና ለኃይል ማመንጫ ሥራዎች ውኃ በጣም ይፈለጋል፡፡ ክልል በክልል ላይ፣ አገር በአገር ላይ የሚነሳበት የፖለቲካ ግጭት ጭምር ሊከሰት እንዳይችል መንግሥታት በመተሳሰብና በፍትሐዊነት የውኃ ሀብትን ለሕዝብ ጥቅም ቢያውሉ ነው የሚጠቅማቸው፡፡

በሌላ በኩል የውኃ ግብዓት የሆኑ የተፈጥሮ ንጥረ ነገሮች (ኃይድሮጂንና ኦክሲጂን አቅርቦት ማነስ እጥረቱን እንዳያባብስ ያለውን ሳይንሳዊ ሥጋት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እ.ኤ.አ. በ2030 ከዓለማችን ሕዝብ አንድ ሦስተኛው (ሲሶው) የሚኖረው የውኃ እጥረት ከ50 በመቶ በላይ ባሉባቸው ውኃ አጠር ተፋሰሶችና ገበቴዎች አካባቢ ይሆናል፡፡

አሁን ውኃ አጠር የሆኑ በርካታ አካባቢዎች ከ30 ዓመታት በኋላ የባሰ ውኃ አጠር ይሆናሉ፡፡ የከርሰ ምድር ውኃ ይደርቃል፣ የበረዶ ግግሮች ይቀልጣሉ፣ ይንሸራተታሉ፡፡ በበረዶ መልክ የነበሩ ውኃዎች ይጠፋሉ፡፡ የበጋ (የደረቅ) ወቅት የውኃ ማግኛ የነበሩ ምንጮች ይመክናሉ፡፡ ይህም የዓለምን የውኃ ችግር ለጦርነትና ለፖለቲካ ሽኩቻ ዋነኛ መንስዔ ያደርገዋል፡፡

ሌላው የውኃ ችግር ምክንያት የሰዎች የአመጋገብ ምርጫ ፍላጎት መለወጥ ነው ይላሉ ጥናታዊ መረጃዎች፡፡ ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት በዓለማችን ያለው ባለ መካከለኛ ገቢ ሕዝብ ቁጥር አሁን ካለበት 1.8 ቢሊዮን እ.ኤ.አ. በ2030 ቁጥሩ ወደ 4.9 ቢሊዮን ይደርሳል፡፡ ገቢው ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ ደግሞ ተቀዳሚ የምግብ ምርጫው ሥጋ ነው፡፡ አመጋገቡ ብዙ ኃይልና ውኃ አዘል ወደ ሆኑ የምግብ ዓይነቶች ይቀየራል፡፡ ይህም ከፍተኛ የከብት ርቢና የመኖ አቅራቢነትን ይጠይቃል (ኢትዮጵያዊያን በአብዛኛው በዚህ ጎራ ውስጥ እንደምንገኝ ማስታወስ ይገባል)፡፡

በአሁኑ ጊዜ 93 በመቶ የሚሆነው የንፁህ ውኃ ፍጆታ የሚውለው ለግብርና ሥራዎች ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ ይህ መጠን ብዙ እጅ እጥፍ እየሆነ ያድጋል፡፡ በዚህ ምክንያት መጠነ ሰፊ የባህሪ ለውጥ የመሬት አጠቃቀምንና የምግብ ፍጆታን አካሄድ ለመለወጥ መነሳት፣ በንፁህ ውኃ ሀብቶች ላይ የባሰ ጫና ከመፍጠር የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ለውኃ ችግር መባባስ ሌላኛው ዓብይ ምክንያት ደካማና ብቃት የሌለው የውኃ አስተዳደርና አያያዝ ሥርዓት ነው፡፡ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች አዲሱን የውኃ እጥረት ዘመን ለመገዳደር፣ በተቀናጀ የውኃ አስተዳደር ሥርዓት የሚመራ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ (ኢንቨስትመንት) ይጠይቃል፡፡

ይህም በአዳዲስ የመስኖ ልማት ሥርዓቶችና ድርቅን ለመቋቋም የሚችሉ እህሎችን በማምረት፣ በከተማ ያለውንና በአማካይ ከ30 እስከ 50 ከመቶ የሚሆነውን የውኃ ብክነት ለማሻሻል የውኃ መሠረተ ልማቶችን በአዲስ መልክ መሥራትና የውኃን እውነተኛ ኢኮኖሚ ፋይዳ የሚገልጹ የዋጋ ሥርዓትን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ እኛ እንደ አገር መበርታት ያለብን እዚህ ላይ ነው፡፡

እርግጥ ነው ነባሩን አሠራር መቀየርና የውኃ አጠቃቀም ሪፎርም መጀመር  የፖለቲካ መንገራገጭ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ውኃን በነፃ ወይም በርካሽ እንደ ልቡ ሲጠቀም የነበረን ኅብረተሰብ ‹‹እውነተኛው የውኃ ዋጋ ይህ ነው›› ቢሉትና በዚያ መሠረት እንዲከፍል ቢጠይቁት ላይስማማ ይችላል፡፡ ቢሆንም ጠንክሮ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ብዙዎቹ ታዳጊ አገሮች በእኛም አገር  ውኃ ተገቢውን ዋጋ  እንዳላገኘ ተገንዝቦ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ከውኃ ሽያጭ የሚገኘው ገቢም የውኃን መስመርና ሥርጭት ለማስፋትና ለማሳለጥ የራሱን ሚና እንዲጫወት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ፣ በዓባይ/ናይል ወንዝ ተፋሰስ ዙሪያ ያለው ውጥረትም ስክነት የሚያስፈልገው ለዚህ ነው፡፡ በዚያው መጠን አገሮች ከዚህ በፊት የያዙት ወይም ሲያገኙ የነበሩት የውኃ መጠን እንዳይቀንስባቸው፣ በዲፕሎማሲና በሌሎች ልዩ ልዩ መንገዶች መንቀሳቀሳቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ በተለይ ውኃው የሚመነጭባቸውና በዋናነት የሚያልፍባቸው የላይኞች ተፋሰስ አገሮች ውኃቸውን እንደ ዲፕሎማሲ መሣሪያ በመጠቀም፣ በውኃ ተቀባይ የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ላይ ፍላጎታቸውን ሊጭኑ የሚሞክሩበት ሁኔታ አለ፡፡

ወንዙን ገድበው የውኃውን ፍሰት በመግታት በውኃ ችግር እንዲጨናነቁና ወደ ማይፈልጉት ውል ውስጥ እንዲገቡ የሚደረግበት ሁኔታም አለ፡፡ በዓለም ላይ በሚገኙ 263 የጋራ ዓለም አቀፍ የውኃ ተፋሰሶች መካከል ብዙ ችግር አጋጥሞ ነበር፡፡ የተፈታም፣ ያልተፈታና በእንጥልጥል ላይ ያለውም አጀንዳ በርከት ያለ ነው፡፡ የግብፅ፣ የኢትዮጵያና የሱዳን ከነባሩ አሠራር ያልተላቀቀውና ኢፍትሐዊው እሰጥ አገባም ከእነዚሁ ተርታ የሚመደብ ነው፡፡

በእኛ ሁኔታ ግን ሁኔታው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ማስፈራራት ያለብን ኢትዮጵያዊያን መሆን ሲገባን በዓባይ ተፋሰስ ተጠቃሚነታችን ተቆጪያችንና ‹‹ዋ›› ባያችን ግብፅ መሆኗ አንዱ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ያለ እፍረት በእጅ አዙር ተፅዕኖ ማድረጓ አንሶ ‹‹ውኃውን ትነኩና ወዮላችሁ›› እያለችን ነው፡፡ ‹‹የግድቡን ሥራ አቁሙ›› የሚል ዘባተሎ ሐሳብም ሲነገር ሰምተናል፡፡ ‹‹የግድቡን ቁመት አሳጥሩ፣ ውኃ የመያዝ አቅሙን ቀንሱ፣ በግብፅ ኢንጂነሮች ተቆጣጣሪነት ሥሩ…›› ወዘተ. እያለች ክብረ ነክ ሐሳቦችን ስታቀርብ መቆየቷም ቢያንስ ከኢትዮጵያዊያን አዕምሮ የሚጠፋ አይደለም፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የዓባይ ግድብን ሥራ ለማስቆም በዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ዓለምን ጫፍ እስከ ጫፍ አድርሳለች ግብፅ፡፡ ‹‹ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትም እሄዳለሁ›› ከማለት አልፋ ያልተረጋጋችውን ሱዳን ገዥዎችን ከዚያና ከእዚህ እያላጋች በርካታ ተፅዕኖዎችን በአገራችን ላይ ለማድረስ ሞክራለች፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የካርቱም ወታደራዊ መንግሥት (የጁንታውን ጥቃት ተከትሎ) በአገራችን ላይ በድንበር ይገባኛል ስም ወረራ እስከ መፈጸም የደረሰውም፣ በካይሮ አይዞህ ባይነት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

አሁንም ቢሆን መዘናጋት የለብንም የሚያስብለው ታዲያ አገራችን በውስጥ እንዳትረጋጋ ከማድረግ አልፋ፣ ግብፅ የተዛባውን የውኃ አጠቃቀም ለማስቀጠል በእጅ አዙርም ቢሆን ጦርነት ከማወጅ ወደኋላ አትልም የሚሉ ተንታኞች ሐሳብ በመኖሩ ነው፡፡ የመጨረሻ ምርጫዋ ይሆን እንዲሆን እንጂ የጦርነት አጀንዳዋ አይታጠፍም፡፡ የዓባይን ግድብ ለማስቆም ከዘረጋቻቸው ተንኮሎች በሰባተኛ ደረጃ ያስቀመጠችው የመጨረሻ ዕርምጃዋ ጦርነት እንደነበር፣ ሕይወቱ እስር ቤት ውስጥ ካለፈው የሙስሊም ወንድማማቾቹ መሪ መሐመድ ሙርሲ ማዳመጣችንን አንዘነጋውም፡፡

ከዚያ በፊት ግን ቀደም ብላ የጀመረቻቸው፣ አሁንም እያደረገች ያለችውና ወደፊትም የምታደርጋቸው ስድስት መሰናክሎች አሏት፡፡ ሁሉንም እየተጠቀመችባቸው ነው፡፡ የተንኮል መረቦቿ ሰባትም ሆኑ ሰባ ዋንኛው የሴራ ምሶሶ ‹‹መንግሥትን ማናጋት›› (State Destabilization) ተብሎ በአንድ ቃል ሊጠቃለል እንደሚችል፣ የአገራችን ምሁራንና የፖለቲካ ተንታኞች ደጋግመው አረጋግጠውታል፡፡

መንግሥትን ማናጋት ማለት በሁሉም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ፣ ወዘተ መስተጋብሮች ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖረው ማድረግ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት አኃዞችን አዛብቶና አሳንሶ ማቅረብ፣ የፀረ ድህነት ትግሉ አንዲት ዕርምጃ እንዳልተራመደ፣ ልማት እንዳልተካሄደ ማወጅ ዋነኛ ሥራቸው ነው፡፡ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ፣ ኢንቨስትመንት እንዲስተጓጎል፣ ወደ አገራችን ድጋፍም ሆነ ብድር እንዳይገባ፣ ወዘተ ሲኳትኑ ኖረዋል፣ ይኖራሉ፡፡

በክልሎች፣ በብሔር ብሔረሰቦችና በእምነቶች መካከል መግባባት እንዳይኖር ብቻ ሳይሆን ወደ ግጭትና ዕልቂት የሚያመራ እኩይ ተግባር መፈጸም ዓላማቸው ነው፡፡ እነሆ የአሁኑ መከራችን አንዱ ምንጭ ይህ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ መንግሥትም ፈራ ተባ እያለ በዘውግ ፌዴራሊዝም ለመንገታገት የሚያደርገው ሙከራ፣ ያውም ያለ ምንም ለውጥ በከሰረው መንገድ ለመመለስ መሻቱ የመከራውን ጊዜ እያራዘመው መሆኑ እየታየ ነው፡፡

ብሔራዊ አንድነትን በተመለከቱ ጉዳዮች በተለይ በውኃ ሀብቶቻችን ዙሪያ፣ በዓባይ ግድብ ሥራ፣ ዙሪያ… አንድ ዓይነት አመለካከት ወይም ብሔራዊ መግባባት እንዳይኖረን ለማድረግ ያለ መታከት ይሠራሉ፡፡ የውስጥ ተቃዋሚዎችን በገንዘብ በማጠናከር ከአገር ውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያንቀሳቅሳሉ፡፡ የሰላማዊ ዜጎችን ጥያቄና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አጀንዳ ጠልፈው እንቅስቃሴው መንግሥትን ወደ ማናጋት እንዲሸጋገር ያደርጋሉ፡፡ በሚያሳዝን ደረጃ አሁንማ የዘር ፍጅት ፈጻሚ ኤጀንቶችን እስከ ማፍራት ደርሰዋል፡፡

በተጨባጭ እየታየ እንዳለውም የጎረቤት ጠላቶችን ተጠቅመው የአገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ ይሠራሉ (የሱዳን ወታደራዊ መንግሥትን እንቅስቃሴ ይመለከቷል)፡፡  ዓለማቸው የእነሱን የውኃ ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ አንዲት ጣሳ ውኃ የማይቀንስባቸውና እነሱ እንደፈለጉ የሚያሽከረክሩት፣ የእነሱ መጫወቻና የእጅ ሥራ የሆነ፣ በእነሱ ሳምባ የሚተነፍስ መንግሥት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ምንም ያህል ልዩነት ቢኖረን ይህ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም፡፡

የካይሮ ፖለቲከኞች ሌሎች እክሎችንም በመፍጠር የመንግሥትን ራስ ከማዞር አይተኙም፡፡ ግድቡን ለመጎብኘት በሚሄዱ የእኛ ሰዎችና የውጭ ቱሪስቶች ላይ አደጋ በመጣል አካባቢው ሰላም እንዳልሆነ በማስመሰል ገጽታ ሲያጠለሹ መክረማቸው አይዘነጋም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጉባና አካባቢው ብቻ ሳይሆን፣ የምዕራቡ ቀጣና የጦርነት ዓውድማ ሆኖ መቆየቱ አንዱ ምክንያት ይኼ ነበር፡፡

መፍትሔው ግን መንግሥት ለማንም ሆነ ለምንም ሳይበገር፣ በእውነትና በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ የውኃ ፖለቲካውን መምራት ነው ያለበት፡፡ እኛም እንደ ሕዝብ “ውኃ ሕይወት” መሆኑን በሚገባ ተገንዝበን ለዛሬው ብቻ ሳይሆን ለመጭው ትውልድም የምትተርፍ አገር ለመገንባት መደማመጥ፣ አንድነትን መጠበቅና ለጠላት በር አለመክፈት ነው የሚጠበቅብን፡፡ የሱዳን የግብፅ ከንቱ ጥምረት ግን በእኛ ብቻ ሳይሆን በዓለም ፊትም መዋረዱ አይቀርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...