Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትከልምድ አለመማር ለካንስ ይጎለምሳል!?

ከልምድ አለመማር ለካንስ ይጎለምሳል!?

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ሀ. ‹አገሬ የአንቺን ክፉ አያሳየኝ› ማለትን አገር ከመናጥ ጋር ማዋደደም ተቻለ!

‹‹ከአሁን በኋላ ዴሞክራሲን ካላሳካን በቀር ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ አትሆንም›› የሚል ማስጠንቀቂያ ተደጋግሞ መነገር ከጀመረ ሰናባብቷል፡፡ ወደ ዴሞክራሲ ማለፍ፣ ሰው ሰውን ከሚገዛበት ሥርዓት ሕግ ሰውን ወደሚገዛበት ሥርዓት ማለፍ ማለት ነው፡፡ እዚህ ሥርዓት ላይ የሚደረሰውም ምላስና ብዕር በማሾል ሳይሆን፣ ከልምድ በሚማር ብልህ ጉዞ ነው፡፡ ‹‹ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲ›› እያልን ከልምድ መማር የጠላ ገመናችንን ማየት ብንችል ጥቂት ነጥቦችን ለማስታወስ ልሞክር፡፡

- Advertisement -
  1. ሕወሓት/ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን አገረ መንግሥት አተያይና መዋቅር በአምሳያው ማሟሸቱ ለአገር ዳፋ እንደሚሆን፣ ለሕወሓት/ኢሕአዴግ ቅጥፈትና ሸር የትግል መሣሪያዎቹ እንደሆኑ፣ ቡድኑ ሲቀጥፍና ሸር ሲሠራም የራሱን ኃጢያት የሌሎች ኃጢያት አድርጎ ከመላከክም በላይ፣ በልበ ሙሉነት መታበይንና ንፁህ መምሰልን የመታመን ዘዴዬ ብሎ እንደሚጠቀም፣ የኢትዮጵያ 2000 ዓመት ከመድፈኑ በፊት ተደጋግሞ የተነገረና የታወቀ ጉዳይ ነበር፡፡

ከዚህ አኳያ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ለአገር ዳፉ ለመሆን መቻሉ ተቃዋሚ ፖለቲከኖች ገብቷቸው ከነበር፡፡ ይህ እንዳይመጣ ገና የቅዋሜና የለውጥ ፍላጎት መጋጋል በታየባቸው ዓመታት (2006-9) የተባበረ ኃይል ፈጥረው ሕወሓት/ኢሕአዴግ የተመጠኑ፣ ደረጃ በደረጃ የሚራመዱ ዴሞክራሲ ነክ ለውጦችን ወደ ማድረግ ውስጥ እንዲገባ ማደፋፈር (አብሮ የመሥራት ፍላጎትን ያሳየ ጉዞ ማድረግ) በቻሉ ነበር፡፡

በሕወሓት/ኢሕአዴግ የ27 ዓመታት ገዥነት ውስጥ በኦሮሞ ወጣት አካባቢ ዘንድ የኦነግን ቅኝ ተገዛሁ ባይ አቋም ኦነግ በሌለበት ሜዳ ማጥናትና ማፍቀር፣ እየጨመረ መጥቶ የነበረው በአገዛዙ ግፍ ምክንያት ብቻ አልነበረም፡፡ የተሳሳተ የቅኝ ግንዛቤን እያንጎላጩ ‹‹ኢትዮጵያዊ አይደለሁም›› ከማለት የተሻለ የፖለቲካ ንቃት የሚሰጠው የውስጥ አታጋይ ስላጣም (እንደ ኦፌኮ ያለ ተቃዋሚ ነን ባይ ቡድኖች የሚጠበቅባቸውን ሥራ ስላልሠሩ) ነበር፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን በአገዛዙና በገዥው ቡድን ባህርይ ውስጥም ሆነ በሕዝብ ገብ የፖለቲካ ግንዛቤ ውስጥ የነበሩትን ጣጠኛ ገመናዎች ያስተዋለና ሕወሓትን ከርቀትም ሆነ ከቅርበት በብልኃት ያቀፈ፣ ግን ጠንቃቃ የለውጥ ጉዞ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ሕወሓቶች ተያይዘው አውሬያዊ አዘቅት ውስጥ ባልወረዱ፣ የተወሰኑት ቢያፈነግጡ እንኳ፣ በኢትዮጵያ ማዕቀፍና በለውጡ ሠፈር ውስጥ የሚቆዩት በበረከቱ ነበር፡፡ በዚህ አኳኋን በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ማዕቀፍ ውስጥ የሚያስቡት የፖለቲካ ኃይሎች፣ ትልም ያበጀ የኅብረት እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው ቢሆን ኖሮ፣ ኦነግን ቁርጥ ያለ አቋምህን ለይ ብሎ መወጠር በተቻለ ነበር፡፡ በይፋ አቋም አሞኝቼ በቦሌና በጠረፍ ሰርጌ በትጥቅ ትግል ላምስ ቢል እንኳ ፈፅሞ ቀላል ባልሆነለት ነበር፡፡ ከኃይለ ማሪያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነት የመጨረሻ ዓመታት እስከ ዓብይ መንግሥት አፍላ ጊዜያት (ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም.) ድረስ የነበረው በውድመት የቀለመ የፖለቲካ ትኩሳት የተባበረ ብልህ ትግልን ክፉኛ የተራበበት ወቅት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ጉድለት ሳይሞላ ማለፉ ለውጡን ምን ያህል ኪሳራ እንዳደረሰበት የዛሬ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቡድኖች ካስተዋሉና ከተቆጩ፣ የእነሱ ጥፋትና ስንፍና ከዓብይ መንግሥት መምጣት በፊትና በኋላም የነበረና ያለ ጊዜን የሚሸፍን መሆኑን ማስተዋላቸው ነው፡፡ በዓብይ መንግሥት ቸልታ ላይ ከሚያሳርፉት ወቀሳ ይልቅ በራሳቸው ስንፍና ላይ የሚያርፈው ወቀሳ መብለጡም ነው፡፡ ከዓብይ መንግሥት መምጣት በፊትም ሆነ በኋላ ዕርቅ/የጋራ መግባባት እያልን ስንት ጊዜ መግለጫ በማውጣት ጮኸናል በማለት ራሳቸውን ከሸነገሉ መቼም፣ ሌላ ኃፍረት ነው!

ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ልምድ በኋላ የኢትዮጵያ ችግር በኢሕአዴግም ሆነ በተቃዋሚዎች የብቻ ሩጫ የማይፈታ መሆኑን ምርኩዝ በማድረግ፣ በአገር ውስጥ የነበሩ ሕጋዊ ተቃዋሚዎችና በስደት/በትጥቅ ትግል ውስጥ የተሰማሩ ተቃዋሚዎች ከገዥው ቡድን ጋር ኢትዮጵያን ለማራመድ የወጠነ የሰላም ጥሪ አቅርበው በውስጥና በዓለም አቀፍ መድረክ ትኩረት የሚያገኝ ትግል እንዲያደርጉ የጠቆሙ ነበሩ፡፡ ይህ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ‹‹ማን ተጣላና ዕርቅ? የቻለ በምርጫ መወዳደር ነው›› እያሉ ማላገጥ ለሕወሓት/ኢሕአዴግ ባልቀለለው ነበር፡፡ የዓብይም መንግሥት እንደመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ (በአገር ውስጥም በውጭም የነበረ ሁሉ) ለዓብይ መንግሥት ድጋፍ የሰጠው፣ ዓብይን ብሎ ሳይሆን የለውጥ ዕድልን ከወቅቱ ሁኔታ አንብቦ ነበር፡፡ በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የአብዮት አደባባይ ትዕይንት ላይም የሕዝብ አባላት የተሰነዘረውን የቦምብ ፍንዳታ ሕይወት እስከ ማጣት በደረሰ ቁርጠኝነት የተናነቁትም፣ የግለሰብ ፍቅር አውሯቸው ሳይሆን፣ በግለሰብ ላይ የተቃጣው ጥቃት በለውጡ ላይ የተቃጣ ስለነበር ነው፡፡ ልክ ሕዝብ እንዳደረገው ለውጡን የሚደግፉ ተቃዋሚ ቡድኖች አንድ ላይ መቆም ችለው ቢሆን ኖሮ (የዓብይ መንግሥት ጠርቷቸው በክብ ጠረጴዛ መፈራረምን የሚጠብቁ ዓይነት ባይሆኑ ኖሮ)፣ ለለውጡ መጎልበት ከወረቀት ይልቅ በተግባር ፊርማውን ያሳረፈ የጋራ ትግል መቋጠር ይችሉ ነበር፡፡ ከዚህ ይልቅ የሆነው ዳር ቆሞ አቃቂር እያወጡ እርጥባን ታህል ድጋፍ መለገስ ነበር፡፡

  1. ሕወሓትን በነቀፋ ከመቀጥቀጥ ይልቅ በዕርቅ አቅፎ ዳፋን እንደ አንቀላፋ የማቆየት ተግባር ፖለቲካችን ከብዶት፣ መካረር ንሮ የውስጥ ወረራ (በሰሜን ዕዝ ላይ) ተከፈተ፡፡ በአገራዊ ህልውናችን ላይ እንዲህ ያለ ጥቃት ሲመጣ መሀል ሜዳ ላይ ተገትሮ ‹‹እንዲህ ባለመደረጉ፣ እንዲህ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ›› የሚል ምላስ ቦታ የለውም፡፡ በሚችሉት አቅምና መስክ የህልውና ፍልሚያውን መቀላቀል የማያቅማሙበት የሁሉ ተግባር ይሆናል፡፡

ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የአልሞት ባይ ተጋዳይነት አንስቶ እየተታኮሱ መሰዋት፣ ከባልደረባ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠርና ለመተጋገዝ መሞከር፣ ራስን አትርፎ የጎረቤትንና የወገን ዕገዛን መፈለግ፣ በእነዚህ ዕገዛዎች አማካይነት የተበታተነ አቅምን አሰባስቦም (አገሬን ያለ የሕዝብ ቁጣን እየሞቁ) ፈጣን መልሶ ማጥቃት ውስጥ መግባት ተከተለ፡፡ በዚህም አገር ነካሾችን እያሳደዱ የመቅጣት ፈጣን እንቅስቃሴና የተዘረፈ የጦር ትጥቅ የማስተፋት፣ የታገቱና ጋሻ የተደረጉ መኮንኖችን የማስለቀቅ ድል የተጨበጠበትና የትግራይ ሕዝብ በጊዜያዊ አስተዳዳር እንዲረጋጋና አዲስ ዕይታ ውስጥ እንዲገባ የተሞከረበት ሒደት፣ የመጀመርያው አገራዊ ህልውናን የማትረፍ ምዕራፍ ነበር፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በፖለቲካም ሆነ የሕዝብን ሰላምንና ደኅንነትን በማስተዳደር ከሽፎ፣ በዚሁ ክሽፈቱም አማካይነት የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝቦች ለትግራይ ሕዝብ የሰጡት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዕገዛ ባክኖና የመከላከያ የሕዝብ ተቀባይነት ተጎሳቁሎ (በሌላ አነጋገር የትግራይ ሕዝብ ህሊናና ልቦና የሕወሓት ሸርና ጥላቻ መጫወቻ ሆኖ) መከላከያ በይፋ ከትግራይ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ወጣ፡፡ ከዚያ ወዲህ የሕወሓት ጦረኞች ሌላ የወረራ ጦርነት ደግሰው አፋርና አማራ ክልሎች ላይ ከመዝመታቸውም በላይ፣ አዲስ አበባ ለመግባት ተንጠራርተው፣ በአፀፋ ፈጣን ጥቃት የተደቆሱበት እስከ 2014 ዓ.ም. የመጀመርያ ሦስት ወራት ያለው ጊዜ፣ ሁለተኛው የአገራዊ ህልውና የተጋድሎ ምዕራፍ ሊባል ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከዚህ ቀደም ከአፄ ኃይለ ሥላሴ እስካሁኑ የዓብይ መንግሥት ድረስ፣ በእኔ ዕድሜ ታይቶ የማይታወቅ በልባዊ ነዲድ የተሞላ አገራዊ ርብርብ ተከስቷል፡፡ ቀደም ብሎ በምዕራፍ አንድ ተጋድሎ ላይ የተጀመረው ርብርብ በተለያየ አቅጣጫ (በስንቅ መዋጮና መሰናዶ፣ ወደ ልዩ ልዩ የውትድርና ሥልጠናዎች በመሰማራት፣ በወዶ ገባ ዘማችነትና በአካባቢ ፀጥታ ጥበቃ ተሳትፎ) ተገማሽሯል፡፡ ግፈኛውን ወረራ ባለ በሌለ ኃይል እየተናነቁ አቅም ሰንቆ ወደ ሙሉ የማጥቃት ዕርምጃ በተዞረበትም ጊዜ የነበረው ሕዝብ-ገብ ተሳትፎ እኔም፣ እኔም ያለ ነበር፡፡

እውነታን መቀበልና የኢትዮጵያ መትረፍ ከጅብ መንጋጋ የመውጣት ያህል እንደነበር ማየት ኮሶ የሆነባቸው አንዳንድ ፖለቲከኞች፣ የሕወሓት ዘራፊና አውዳሚ ኃይል አፋርና አማራን እየላጨ ሸዋ ድረስ መዝለቁን የመንግሥት ሆነ ብሎ የማስጠቃት ሥራ አድርገው ያቅርቡት እንጂ፣ የኢትዮጵያን ጓዳ ጎድጓዳ በደንብ የሚያቁት የሕወሓት ከሃዲዎች ሰሜን ዕዝ ላይ ያደለቡትን የኢትዮጵያ ኃይል እስከ ሰባበሩ ድረስ ኢትዮጵያ እነሱን የሚመክት አቅም እንደማይኖራት እርግጠኛ መሆናቸውና በሁለተኛው ወረራቸውም እንደሚያሸንፉ መተማመናቸው በምድር ጦር የኃይል ሚዛን ከመንግሥት ጋር የትናየት ልዩነት እንዳላቸው ‹‹ከማወቅ›› የመጣ መሆኑን ወደ መገመት የሚወስድ ነው፡፡ የምድር ጦርን የሚያህል ግዙፍ ነገር የሰላይ ችግር ከሌለበት ሕወሓት መደበቅ ቀላል አለመሆኑም ወደ እዚህ ግምት ለማድላት ያግዛል፡፡ የሕወሓት ከሃዲዎች የማያውቁት ነገር ነበር ቢባል የኢትዮጵያን የብልህነት ዕምቅ አቅምና በሽሽግ የተሰናዳችን የአየር ኃይል አቅም ነበር፡፡ ለዚህም አሁንም የሕወሓቶችን የኋላ ግርምትና ንጭንጭን ምስክርነት መጥራት ይቻላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ምክትል ኤታ ማዦር ሹሙ የሰጡትን መረጃ በጭፍኑ ማመን ሳያስፈልግ፣ የኢትዮጵያ ቆሳስሎ ተሰውቶ ማንሰራራትና እየተናነቁ ማፈግፈግ በሞላበት አኳኋን ወደ ሙሉ ብልጫ የመሸጋገር ጉዞ (በግዙፍ የሕዝብ ማዕበላዊ ርብርብ ታጅቦ በውስን ውድ አቅም እየተግደረደሩ ገመናን በጠንካራ ኃይል የመሙላት ተጋድሎ) ተደርጎ ሊብራራ የሚችል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አፋርና አማራ መሬት ቀረኝ ለሚል ጥቃት ተጋልጦና የኢትዮጵያ እየተናነቁ ማፈግፈጊያ ሜዳ ሆኖ በቁሳቁስ ሀብትና በሕይወት ብዙ ኪሳራ ደርሶበታል፡፡ የመንፈስ ጉዳቱም ከባድ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብም ያንኑ ያህል በሕወሓት ጦረኞች ጥላቻና በቀል ተመርዞ እየተጋዘ በግፍ ሥራ እንዲጨማለቅና በመቶ ሺዎች እንዲረግፍ መደረጉ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ ሦስቱም ክልሎች ላይ በጉልህ የደረሰው ጉዳት የኢትዮጵያ ጉዳት ነው፣ የኢትዮጵያ ጥቃት ነው፡፡

ሦስቱም ሕዝቦች ላይ የደረሰው ባለ ብዙ ገጽ ጉዳት ግን በከንቱ ባክኖ የትም የቀረ አይደለም፡፡ የሁሉም መስዋዕትነት ማጭበርበርና መደበቅ በማያስችል አኳኋን የሕወሓት የጦር አበጋዞችን የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ ቀዳዷል፡፡ ቀዳዶም ለሕዝብ ሰቆቃና ነፍስ የማያስቡ፣ በደምና በዕንባ የሚዋኙ፣ በውድመት፣ በሰው ስቃይ፣ በሰው ውርደትና ርሸና የሚረኩ ወንጀለኞች መሆናቸውን ሜዳ ለሜዳ እንዲታይ አስችሏል፡፡ ምን ቅጥፈት ቢደረደር፣ የምዕራብ ሚዲያዎችና መንግሥታት እንዳላየ በማየትም ሆነ ተበዳይ በማስመሰል ሲኳኩሉት ቢቆዩም የሕወሓት ጦረኞች ክስረት ለይቶለታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከትግራይ፣ ከአማራ፣ ከአፋር አንስቶ እስከ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ወዘተ፣ ወዘተ ድረስ በመስዋዕትነታቸው ያከናወኑት ግፈኞችን የማጋለጥ አስተዋጽኦ ለአገራዊ ህልውናቸው የነፃነት ጉዞ ትልቅ የፖለቲካ ድል ነው፡፡ ከዚህ ድል አኳያ የኢትዮጵያ ሠራዊት ወራሪዎችን እያፀዳ ትግራይ ድረስ አለመዝለቁ ፖለቲካዊ ድሉን የመጠበቅና የሕወሓት ጦረኞችን ግፈኝነት እንዳገጠጠ እንዲቆይ የማድረግ አስተዋይነት ነበር፡፡ በመልሶ ማጥቃት ከተቀጡም በኋላ፣ በውጊያ ግንባር አካባቢዎች ውስን ጥቃት በማድረስ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ዘልቆ የመግባት ስህተት እንዲሠራላቸው ሲያባብሉ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት ትግራይ ውስጥ ገብቶ ቢሆን ኖሮ የሕወሓት ግፈኞች፣ ‹‹እሰይ ስለቴ ደረሰ›› እያሉ በጨፈሩ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት ትግራይ ውስጥ በመግባቱ እንደ ወራሪ፣ እነሱ እንደ ተወራሪ የሚቆጠሩበት መልክ ተፈጥሮላቸው፣ በዚያ መልክ ውስጥ የትግራይን ሕዝብና ሕፃናት እየጋፉ በማስፈጀት (ነባር ሬሳና ትኩስ ሬሳ በማስጣት) ‹‹የጅምላ ጭፍጨፋ/የጦር ወንጀል›› ኡኡታቸውን ዓለም ድረስልኝ ከሚል ዋይታ ጋር ባቀለጡት ነበር፡፡ በዚህም እንደገና የትግራይን ሕዝብ የእነሱ የህሊና እስረኛ ባደረጉ፣ ግፍ ዋይነታቸውን በተበዳይነት ለምድ በዓለም ፊት መጋረድ በቻሉ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ ሠራዊት ትግራይ ገብቶ ቢሆን ኖሮ፣ ሕወሓቶች በትግራይ ሕዝብ ደም ነግደው የሆነ የውጭ ኃይል (ፍጅት በማስቆም ስም) እንዲገባ ባደረጉ፣ አለዚያም (ወይም በተጨማሪ) የHR6600 መሰል በሆነ አሽመድማጅ ማዕቀብ ኢትዮጵያ በተመታች ነበር፡፡ ከዚያ ዓይነት ጉድጓድ ውስጥ ወጥቶ እንደ አገር የመትረፍ ነገር ደግሞ የምናልባት ምናልባት ጉዳይ በሆነ ነበር፡፡

  1. ቀጥተኛው ጦርነት በሕወሓት የግፍ ወረራ ላይ አይቀጡ ቅጣት አድርሶ ከሞላ ጎደል ቢቆምም፣ ጥቃቱ የዕረፍት ጊዜ ወሰደ ወይም አገራዊ የህልውና ትግሉ ተጠናቀቀ የሚያሰኝ ነገር አልነበረም፡፡ እንኳን በዚያ (በኅዳር – ታኅሳስ) ወቅት ዛሬም ርብርብን ግድ በሚል የአገራዊ ህልውና ትግል ውስጥ ነን፡፡ የሕወሓት ጦረኞች ሌላ ጦርነት መደገሳቸው የማይቀር መሆኑ ለማንም ግልጽ ነበር፡፡ የእነሱም ዛቻ ይህንኑ ሲናገር ቆይቷል፡፡ ከሙሉ ቀጥተኛ ጦርነት ቢያርፉም በሌሎች ጭፍሮቻቸው በኩል የኢትዮጵያን ሰላም ማወክ እንደሚቀጥሉም ዕውቅ ነበር፡፡ ዕርዳታ ለትግራይ በአግባቡ እንዳይገባ ‹‹አወካችሁ›› የሚልና ‹‹ወደ ድርድር ካልመጣችሁ›› የሚል የአሜሪካና የውስን ምዕራባዊ አገሮች ጫና የማዕቀብ አርጩሜውን እያጮኸብንም ነበር፡፡ የፀጥታና የሰላም ችግራችንም በሰሜን ብቻ ያልተወሰነ በየአቅጣጫው ሰርሳሪና ተንኳሽ የነበረበት ነበር፡፡ ከዚያ ባሻገር የግፍ ወረራው ያደረሰው ባለ ብዙ ፈርጅ ጉዳት አፍጦብን ነበር፡፡ የታቀደ ዘረፋና ውድመት የደረሰባቸውን መሠረተ ልማቶችና ተቋማትን መልሶ የማቋቋም ነገር ሞትን ከመቀነስ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ነበረው፡፡ ይህንን መወጣት በጦርነት ውስጥ ለነበረና በውድመትና በብዝበዛ ተወርሮ ለነበረ ኢኮኖሚ ከባድ ፈተና ነበር፡፡ በዚህ ላይ በተወሰኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከባድ የድርቅ አደጋ መድረሱ ፈተናውን ከከባድም ከባድ አድርጎት ነበር፡፡

ዋናው የግንባር ጦርነቱ በተገታበት አፍላ ጊዜ የአገራዊ ርብርቡን ከባሩድ ጋር ብቻ ያያያዘ ብዥታ አልነበረም፡፡ ‹‹የበቃ (ኖ ሞር)›› እንቅስቃሴም አፍሪካዊ ደም ግባት አግኝቶ በምዕራባዊ ጫና ላይ ትግል እያጧጧፈ ነበር፡፡ በሌላ ጎን በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች ከርቀት ከሚያደርጉት የገንዘብ ዕርዳታ ባሻገር ለገናና ለጥምቀት ወደ አገራቸው እንዲገቡ የተደረገው ጥሪ፣ ሁሉም አገር ወዳድ የአገሩን ጉዳትና የማንሰራራት እጥረት ባስተዋለበት አኳኋን የመልሶ ግንባታ ርብርቡን እንዲያሞቅ የሚያስችል፣ ለወቅቱ ትክክለኛ የሆነ ዘዴ ነበር፡፡ በተግባር የተሰጠው ምላሽም የሚያኮራ (መልሶ የመገንባቱን አደራ ከአገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ እንዲሳላ ያደረገ) ነበር፡፡ ሆኖም በዚያ የርብርብ ሙቀት ውስጥ የእነ ስብሃት ነጋ መፈታት ትልቅ ክውታና ቁጣ የፈጠረ መርዶ ነበር፡፡ በአገራዊው ርብርብ ላይ ያደረሰው ቡጭሪያም ቀላል አልነበረም፡፡ የብዙዎች ብስጭት ዋና ምክንያት ደግሞ መንግሥት የፈለገ ምክንያት ቢኖረው፣ በዚያ ወቅት ያንን ውሳኔ ይፋ ማድረግን ግድ ያደረገ አሳማኝ ምክንያት ሊያቀርብ አለመቻሉ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ብዙ አገር ወዳዶች አገራችንን አላኮረፍንም፡፡ የአገራችንን ህልውና ከአደጋ አትርፎ የማስቀጠል ዋና የርብርብ መገናኛችን መንግሥት እንደመሆኑም ብስጭታችንን ውጠን ከመንግሥት ጋር አብሮ መሥራት የማይመለጥ ግዳችን ነበር፡፡ ብዙዎችም በዚህ ግዴታ ውስጥ አርበኝነታቸውን ቀጥለዋል፡፡

የተወሰኑ አኩራፊዎች ግን ‹‹ኢትዮጵያ የአንቺን ክፉ አያሳየኝ›› እያሉ አገራዊ የተጋድሎ ኃላፊነታቸውን ሸሽተው፣ ያለውን መንግሥት መተናነቅን ዋና ተልዕኳቸው እስከ ማድረግ ተስፈንጥረዋል፡፡ ወዲያውኑ የእነ ስብሃት ነጋን መፈታት ኢትዮጵያን ከጀርባ የመውጋት ሸፍጥ ባይ ደንቆሮ ውንጀላ፣ አገራዊ ርብርባችን ላይ ሾተሉን እየቀበቀበ ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ መሰለ፡፡ እስከ ሰሜን ሸዋ የዘለቀውም የሕወሓት ወራሪ ሆን ተብሎ የተካሄደ መንግሥታዊ አሻጥር ተደርጎ ተተረጎመ፡፡ ሸኔ በኦሮሚያና እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ በሰፋ አካባቢ እያደባ ሲያደርስ የቆየው ግፍ ማብቂያ ማጣቱም፣ ‹‹መንግሥት ሸኔን የማጥፋት ቁርጠኝነት የሌለው›› ስለመሆኑ የማያጠራጥር ማረጋገጫ ሆኖ ተያዘ፡፡ በጥቅሉ ነገር እየበሉ፣ ነገር እየተፉ ርብርቡን መተክተክ እየደራ መጣ፡፡ በሕዝቦች መሀል መጠራጠርን የሚያራቡ፣ የፈተና ጊዜ መንግሥትን ድጋፍ የሚበዘብዙ፣ የፀጥታ ኃይሎቻችንን ለዓላማ መታመን የሚልሱ፣ የብሔረሰቦችንና የሃይማኖቶችን ሰላም የሚተናኮሉ ንግግሮችን መርጨትና የንግግር ነፃነት ተምታቱ፡፡ መሣሪያ ታጥቆ የሚካሄድ የወሮበላነትንና የሥርዓተ አልባነት ልምምድን በአርበኝነት ሚና እስከ መከለል ድረስ የሕዝብ ግንዛቤን ማወናበድ ሲካሄድ ታየ፡፡ አገር የህልውና ፈተና ውስጥ መሆኗ የተዘነጋው እስከዚህ ድረስ ነበር፡፡ በአሜሪካ ምክር ቤቶች ዘንድ HR6600 እና S3199 የሚባሉ አማቅቆ ገዳይ ሕጎች ተረቀው ኢትዮጵያ ላይ ባፈጠጡበት ጊዜ፣ እነዚህ ሕጎች እንዳይፀድቁ በባህር ማዶ ያሉ የአገር ልጆች ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ ተቆርቋሪዎቻችን ጋር ተጋግዘው ሲታገሉ፣ ከእኛው የተፈጠሩ ጀርባ ሰጪዎች ግን ምንተፍረት አልጎበኛቸውም፡፡ እንደ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት ያለ ከሃዲ ‹‹ኢትዮጵያውያንን የበለጠ መከፋፈያው ጊዜ አሁን ነው›› የሚል የቤት ሥራ በእኛ ላይ ሲሰጥ እንኳ፣ ‹‹እስከዚህ ድረስ ለመደፈር በቃን!›› የሚል እልህና መባነን ወደ አገራዊ ርብርቡ ሠፈር ሊያዞራቸው አልቻለም፡፡ እንዲያውም ተግባራቸው ሲሰጥ የቆየው መልስ፣ ‹‹እነ ሕወሓትዬ እስካሁን እንድንባላ ብዙ ለፍታችሁልናል፡፡ አሁን አረፍ ብላችሁ ራሳችንን ችለን ለመባላት ስንለፋ እያያችሁ አጨብጭቡልን፣ አናሳፍራችሁም፡፡ የመመቀኛኘትና በጥርጣሬ የመንጨርጨር፣ በአሉባልታ መንግሥትን የማኘክና ነገር እየሠሩ የመተነኳኮስ ስልቻችን ሙሉ ነው›› የሚል መሳይ ነበር፡፡

ከንፅፅር ጋር አንድ ምሳሌ ላውሳ፡፡ በለውጡ ዓመታት ውስጥ ሙስሊሞችንና ክርስቲያኖችን ለማጋጨት በተደጋጋሚ የተሞከረ ቢሆንም፣ እነዚህንና ሌሎች ያለ መረጋጋት ቀዳዳዎችን መሹለኪያ አድርገው ‹‹የሃይማኖት›› አሸባሪዎች ሊገቡ የሞከሩ ቢሆንም፣ እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ባንዳቸውም ውስጥ ፅንፈኛ እንቅስቃሴዎች መፈልፈያ ጎሬ አላገኙም፡፡ መብቀያ ያጡትም በተዓምር አልነበረም፡፡ የትኞቹም የማጋጨት ደባዎች በሃይማኖቶቹ ውስጥ የጠለቀ ቅራኔ መፍጠር ስላልቻሉ፣ በሃይማኖቶቹ ዘንድ ያለው ተራክቦና አዎንታዊ የለውጥ አመለካከት ከጊዜ ጊዜ እየሞቀና መተሳሰብን እያለመለመ ስለመጣ ነበር፡፡ በኦርቶዶክስ ክርስትናም፣ በፕሮቴስታንት ክርስትናም፣ በእስልምናም ዘንድ አስገራሚ የዕይታ ስፋት፣ የመከባበርና የትግግዝ መንፈሳዊ ሙላት ያላቸው መሪዎችና መምህራን (ከወጣት እስከ አዛውንት) ድረስ አደባባይ፣ ለአደባባይ እንዳሁኑ ጊዜ ያየንበት ጊዜ የለም ብል ውሸት አይመስለኝም፡፡ በአንዳንዶቹ መሪዎች ላይ ያየነው ከራሳቸው ውጪ ስላለ ሃይማኖት ያላቸው ዕውቀትና ተቆርቋሪነት ለማመን ያዳገተና ‹‹እንዲህ ያሉ ሊቃውንት ከምን መቃብር ውስጥ ወጡ!›› ያሰኘም ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ጥቃት አለሁ በማለትና ሰላም ማጣት ላመሳቀላቸው ወገኖች በመድረስ የሁሉም ቤተ እምነቶች ምእመናን ስላሳዩት ርብርብማ ስንቱ ይወራል! እነዚህን የመሳሰሉትን አዎንታዊ ሁኔታዎች በመንተራስ፣ በውጭ ላሉ ወገኖቻችንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ‹‹ከኢድ እስከ ኢድ በአገር ቤት›› የሚል ጥሪ የተደረገውም የቱሪዝም ነክ ጥቅምን በማየት ብቻ አልነበረም፡፡ ከዚያ ይበልጥ ወርቃማ የትቅቅፍ ቀዳሚ ታሪክ ያለው የሃይማኖቶች መስተጋብር ዛሬ ፈክቶ በኢትዮጵያ ሲያበራና (በዓለማችን ውስጥ የተበራከተውን የሃይማኖቶች መፈራራትና ፅንፈኛነት ትዝብት ላይ ሲጥል) ማየት ትልቅ የድል ዋጋ ነበረው፡፡ ያልተጠነቀቅንባቸውና በአግባቡ ያላቃናናቸው፣ እምነቶች-ነክ የእኩል መብት መነቃቃቶችን የሚተናኮሉ ዝንባሌዎች ግን ጉድ ሠሩን፡፡ እነዚህን ገመናዎች ደበስበስ አድርገን እንጥቀሳቸው፣

‹‹የእኩልነት ጫፉን እንኳ መቼ አየንና›› የሚል የተጋነነ መብከንከንና አሮጌ ተዛነፍን እያላመጡ በዛሬ ብሩህ ዕድል ላይ እንዲያጠላ ማድረግ፣

በትንሿ የመብት ብልጭታ መሻነንና ዛሬ ካላንተረከክኳት እያሉ መቅበጥበጥ፣

የዚህ ዓይነቱ መቅበጥበጥ በአፀፋ የሚፈጥረው የሥጋት ትንኮሳ፣

ለተጎዳ እምነት ብቅ ያለች የመብት ፍንጣቂን የራስ መብት ያህል ዓይቶ በመደሰት ፈንታ የራስ መብት የተጠቃ አድርጎ መትከንና መርኮምኮም፡፡

እነዚህ አድሏዊና አሉታዊ ዝንባሌዎች ቀለም ለከፍከፍ ባደረጉ ተሬዎች አካባቢ ብቻ የሚንቀዋለሉ አይደሉም፡፡ ዶክትሬት ዲግሪ አለን ያሉ ግለሰቦች ሚዲያ ላይ ወጥተው ‹‹ሲራቀቁባቸውም›› ታዝበናል፡፡ እናም ‹‹ከኢድ እስከ ኢድ›› መርሐ ግብር የመጀመርያ መቃረቢያ ላይ፣ ሸረኞች በድክመት ቀዳዳዎቻችን ገብተው የድል ጉልላታችንን ሰበሩብን፡፡ ጎንደር የተከሰተን አሳፋሪ የግጭት ቅሌት ከአዲስ አበባ ወራቤ እያልን ተቀባበልነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከዋዜማ ጊዜያት አንስቶ በኢድ በዓል ሰሞንና ዘለግ ላለ ጊዜ፣ ስለአገራችን የሃይማኖቶች መተሳሰብ፣ ፍቅርና አብሮ መሥራት ፈርጅ፣ በፈረጅ በማውሳት ፈንታ ስለሃይማኖት አጋጭ ሴረኞች፣ የሃይማኖት ግጭት በቀላሉ የማይጠፋ ስለመሆኑ፣ የተጋጩት ሃይማኖቶች ስላለመሆናቸው ማውራት ውስጥ ገባን፡፡ ርዕሰ ጉዳያችን በተወሰነ ደረጃ ስለተቀየረና ኢድ አልፈጥር በዓላችን በነውር በመቧጨሩ የእኛን ክፉ የሚመኙ ተደሰቱ፡፡ በዚህ ብዙዎች በኃፍረት የበገንነውን ያህል፣ ጥቂት ሐሳዊ ሃይማኖተኞች (የእምነት ልብስ ያጠለቁ ጋጠ-ወጦች) በኢንተርኔት መስክ ውስጥ በአንዱ ወይ በሌላው ሃይማኖት ላይ ያላቸውን ንቀትና ስድብ በኩራት ሲደረድሩ አስተዋልን፡፡ በገዛ ድክመት መጠቃትን በተመለከተ፣ ከዚህ ዓይነቱ ልምድ በላይ አስተማሪ ምን ይምጣልን!

ለ. ሕግ፣ መንግሥትን ወደ ሚገዛበት ሥርዓት የመሸጋገር ጥረታችን አገር ከማዳን ተልዕኮ ጋር መጣበቁን ተረድተናል? ሁለቱን ተግባሮች እንዴት እንደምናስኬዳቸውስ ገብቶናል?

የሕወሓት የጦር አበጋዞችን ዳግማዊ ወረራ ቀጥቶ ከመለሰ በኋላ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያየ ሥፍራ ውርውር የሚሉ የዚሁ ጦረኛ ቡድን የጥላቻ፣ የጭፍጨፍና፣ የብተና ጭፍሮችን በመመንጠርና ሰላም በማስፈን መርሐ ግብር ላይ ማተኮሩ፣ ከዚሁ የሰላም ጉዳይ ጋር የተቆላለፉ ውስብስብ ጣጣዎችን ለማቃለል በዘርፈ ብዙ ተጋድሎዎች ላይ መጠመዱ (የአሜሪካና የምዕራባዊ አባሪዎቹን ማዕቀብ ለማምከን፣ የተጎሳቆሉ የመሠረተ ልማትና የኢኮኖሚ ፈርጆችን እንዲያገግሙ ለማድረግ፣ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል፣ የሥራ ልሽቅትና ሙስናን ለማዳከም መጣጠሩ) ትክክል ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የተጋድሎ ፈርጆች አንድ ላይ አገራዊ ህልውናን የማስተማመን ፋይዳ ያላቸው መሆናቸውም፣ አገሬን ያለ ርብርብን ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ አገራዊ ህልውናን የማረጋገጡ አርበኝነት ዕረፍት የወሰደ ሳይሆን፣ በፈርጀ ብዙ ተግባራት ተጠምዶ የቀጠለ የመሆኑ ግንዛቤ ግን ወለል ብሎ የታወቀ አልነበረም፡፡ በሐሳብ ነፃነት ውስጥ ሲታዩ የቆዩት በፖለቲካ፣ በብሔረሰብ ማንነትና በሃይማኖት መናቆርን የሚያበረታቱ፣ ያለውን መንግሥት ድጋፍ የሚበዘብዙ ምግጠቶች ሁሉ አገራዊ ህልውናን የሚተናኮል ጠንቅ ነበራቸው፡፡ በገዥው ፓርቲ ዘንድ አፈንጋጭነት ደርሶ ወይም በፓርቲ ቅርንጫፎች ግንኙነት ውስጥ መደፍረስ ተከስቶ አደባባይ የወጣ የቃላት መዘራጠጥ እንኳ አገራዊ ህልውናን የማወክ አቅም ሊኖረው በሚችልበት የቋፍ ጊዜ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ ለዚህም ነው እንዲህ ያሉ አዝማሚያዎች በተከሰቱ ጊዜ አንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖች ‹‹የአገር ዳፋ እንዳትሆኑ ንትርካችሁን በድርጅት ጓዳችሁ ውስጥ አድርጉ፣ በአስቸኳይ መፍታት ይጠበቅባችኋል…›› የሚል መግለጫ ማውጣታቸው ከአስተዋይነት ሊቆጠር የበቃው፡፡ ይህን ያህል አገራዊ ተልዕኮ የሚያሳስባቸው፣ የሥርዓት አልባነትና የአመፅ ዳር ዳርታዎችን የሚቃወሙና ገዥውን ፓርቲ በምክረ ሐሳብ የሚያግዙ ቡድኖችና ግለሰቦች በጣም ውስን ቢሆኑም ነበሩ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ መንግሥትን ድጋፍ አሳጥቶ በመከንበል የፖለቲካ ድንክነት የተጠመዱም ነበሩ፡፡ ከመንግሥት ጋር ተጋግዞ ለአገር መሥራት፣ ተቃዋሚነትን እንደ መዘንጋትና በእበላ ባይነት እንደ መልከስከስ ተደርጎ ሲብጠለጠልም ታይቷል፡፡ ኢዜማና አብን ብዙ ነቀፋ የደረሰባቸውም ከሌሎች ‹‹ተቃዋሚ›› ነን ባዮች በተሻለ ደረጃ የአገራዊ ርብርብ ኃላፊነታቸውን በማክበራቸው ነበር፡፡

አገር ፈተና ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት፣ እንዲህ ያለ መፈናገጥ የደረሰው ግን በፖለቲካ ቡድኖች የየግል ድክመት ምክንያት ብቻ አልነበረም፡፡ አገራዊው የርብርብ ጊዜ፣ አገሬን ላሉ ፓርቲዎች ሁሉ እየተመካከሩ በአገር ተልዕኮ ላይ ሰፊ መግባባት ሊፈጥሩ የሚችሉበት (የአገራዊ ምክክር ይፋ ሒደት ከመጀመሩ በፊት እነሱ የራሳቸውን የመግባባት ጥንስስ የሚፈጥሩበት) ወርቃማ ዕድል ነበር፡፡ ይህንን ዕድል ተጨባጭ ለማድረግ ከገዥው ፓርቲ አንስቶ የሚመለከታቸው ሁሉ በአግባቡ አለመልፋታቸውም፣ አገራዊ ዕይታን ለሳቱ ንቅቅፎች ሜዳ ማጣበብ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ቁልጭ፣ ንጥር ያለ የአገራዊ ርብርብ መርሐ ግብር ይዞ መሥራት ሽግግር መንግሥት መፍጠርን አይጠይቅም፡፡ በምርጫ ያሸነፈ ፓርቲ በሚመራው መንግሥት ውስጥ ሹመት ግድ ማግኘትን አይፈልግም፡፡ በዚህ ላይና በአገራዊ የርብርብ አደራ ላይ ያለ የግንዛቤ ጉድለት አገራዊ ተልዕኳችንን ጎድቷል፡፡ ጉዳታችንን በቅጡ ማየት እንድንችል ከአገራዊ ርብርብ ጋር የሚፋተጉትን የፖለቲካ አዝማሚያዎች በመልክ በመልክ እናስቀምጣቸው፡፡

  • የብሔርተኛ ፖለቲካ የመጨረሻ የዝቅጠት ሞት ውስጥ የመግባቱ ተቀዳሚ መታያ (የብተናና የጭፍጨፋ ሠልፈኞች) የሆኑት የሕወሓት ጦረኞችና በየአካባቢው በሎሌነት ያሰማሯቸው ጠመንጃ የያዙ ጭፍሮቻቸው የፊተኛውን ረድፍ ይይዛሉ፡፡ በዚህ ረድፍ ውስጥ ያሉ ቡድኖች የያዙት የዚህ፣ የዚያ ብሔር ‹‹ነፃ አውጪ››፣ ‹‹…ንቅናቄ›› የሚል ስም ሕይወት አልባ ቅርፊት ብቻ ከሆነ፣ ሁለመና ይዘታቸው የጥላቻ፣ የጭፍጨፋ፣ የወሮበላነትና የውድመት ሙላት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በእነዚህ አረመኔያዊ ኃይሎች ዘንድ በማንኛውም ጨካኝ ግፍ ሰዎችን መፍጀት ታክቲካዊ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በሽብር አዙሪት ውስጥ መክተት ታክቲክ ነው፡፡ ተቃዋሚን ወይም መንግሥትን ይደግፋል ያሉትን ሰው መዝረፍ፣ መግደል፣ መረሸን ታክቲክ ነው፡፡ ‹‹መንግሥት ተገን ሊሆነኝ አልቻለም›› በሚል የፍርኃት ቆፈን ውስጥ የትኛውም ሕዝብ እንዲገባና በመንግሥት ላይ ቁጣ እንዲያነሳ ማድረግ ታክቲክ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ግፍ የማያቀምሱትና ሰላም የማይነሱት ብሔረሰብ የለም፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በገዥነት ትርክት ውስጥ በድፍኑ የበዳይነት ምሥል የተለጠፈበትን አማራ ለይቶ መጨፍጨፍ ሁሉም ዘንድ በጉልህ የሚሠራበት ታክቲክ ነው፡፡ በዚህ የጭፍጨፋ ታክቲክ፣ ‹‹ያም፣ ያም ቡድን በጠላትነት ለምን ጠመደኝ? ለምን የተለየ ጥቃት በእኔ ላይ?›› በሚል መንጨርጨር አማራ የህሊና ሚዛን እንዲያጣ፣ ከተጠራጣሪነት፣ ከንጭንጭንና ከጀብደኛ ውርጭት ያለፈ አስተዋይ ፖለቲካ ማራመድ እንዲሳነው (እናም በኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር፣ መንግሥትም ላይ ዓይንህ ለአፈር ባይ እንዲበራከትበት) የማድረግ ሸር ሥራዬ ተብሎ ተይዟል፡፡ የዚህ ሁሉ ታክቲክዊ ሥራ መድረሻ ግብ ደግሞ ኢትዮጵያን መበተን ነው፡፡ በየትኛውም መንገድ አገር ከበተንን በኋላስ …? ብሎ ነገር የለም፡፡ በቀሉ ራሱ ዓላማ ሆኗል፡፡ እየተላለቁ መንግሥት አልባ ከመሆን ወይም መንግሥትን ጥሎ ከመተላለቅ ሰላምና ነፃነት እንደማይገኝ እነዚህ ቡድኖች የሚያስተውል አዕምሮ የላቸውም፡፡
  • የእነዚህ ቡድኖች ግፍ የማይረብሸው፣ ለእነሱ ቀውሰኛ ተግባር ሰፊ ሆድና ልዝብ አቋም ያለው ረድፍም አለ፡፡ በእነዚህ ረድፈኞች ዓይን ከጨፍጫፊዎቹ ቡድኖች ይልቅ ዋና ጥፋተኛ መንግሥት ነው፡፡ በሰሜን ሕወሓት ለጀመረው ጦርነት ተጠያቂ አድርገው የሚኮንኑት የፌዴራሉን መንግሥት ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ጨፍጫፊዎቹንና አውዳሚዎቹን ቡድኖች በግብራቸው አይገልጿቸውም፡፡ ሸኔ ለእነሱ ‹‹የኦሮሞ ነፃ አውጪ ሠራዊት›› ነው፡፡ ሕወሓትንና ጭፍሮቹን አሸባሪ አይሏቸውም፡፡ ቡድኖቹ ሲጨፈጭፉ፣ ሲዘርፉና ሲያወድሙ አያወግዟቸውም፣ ምንም እንዳልተደረገ ዝም ይላሉ፡፡ ወይም ቢበዛ ‹‹መንግሥት ያድርገው ታጣቂዎቹ ያድርጉት አይታወቅም›› የሚል ነገር ከመተንፈስ አያልፉም፡፡ በእነዚህ ቡድኖች ላይ ጥቃት ሲፈጸም ግን በብሔርና በተቃዋሚ ላይ አደገኛ ጅምላ ጥቃት የተከፈተ ያስመሰለ ጩኸት ይጮኻሉ፡፡ በዚህም ጩኸታቸው ለጨፍጨፊዎች ጃንጥላ የመዘርጋት ሚና ይጫወታሉ፡፡ የዚህ ዓይነት ሚና ባለው ጩኸታቸውና በሕዝብ ላይ ቡድኖቹ ግፍ ሲፈጽሙ ዝም በማለታቸው በሕዝብ ደምና ሬሳ ላይ ሳይሳቀቁ የመራመድ ነውርን ይፈጽማሉ፡፡ ይህ በራሱ የግፍ ሸሪክ ከመሆን አይተናነስም፡፡

ለኢትዮጵያ ሰላም አሳቢ መስለው በሚያቀርቡት ሐሳብም የጭፍጨፋ ቡድኖችን ማትረፍን ዋና ጉዳያቸው ያደረጉ ይመስላሉ፡፡ ተኩስ ቆሞ፣ የተኩስ ማቆሙንም የውጭ ኃይል የሚቆጣጠረው ሆኖ፣ የአሸባሪነት አዋጅም ተነስቶላቸው፣ በተስማሙበት የውጭ ኃይል አማካይነት ድርድር ይካሄድ ሲሉ በግፍ የተጨማለቁት ቡድኖች ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት ጋር እኩያ ሆነው እንዲቀመጡ ማድረጋቸው ነው፡፡ ወይም በሌላ አባባል በቡድኖቹና በኢትዮጵያ መንግሥት መሀል ያለውን ‹‹ግጭት›› የሁለት አገሮች ግጭት፣ ድርድሩም በውስጥ አደራዳሪ የማይሞከር የአገሮች ጉዳይ እንዲሆን ማድረጋቸው ነው፡፡ በአሸባሪነት የተፈረጁበት አዋጅ ይነሳላቸው በማለት ውስጥም ወይ ‹‹አሸባሪነት›› በትግላቸው ላይ የተለጠፈ ስም ማጠልሺያ ነው የሚል ዕሳቤ ታዝሏል፣ ወይም ወንጀልና ግፍ ቢሠሩም እንደሠሩ አይቆጠር የሚል ፍላጎት አለ፡፡ ይህም በሕዝብ ደምና ሬሳ ላይ የመቆም ሌላ ነውር ነው፡፡ የውጭ ኃይል የሚቆጣጠረው ተኩስ ማቆም ተደርጎ በውጭ ኃይል አማካይነት ድርድር ይካሄድ በሚል ሐሳብም ውስጥ፣ ችግሮችን በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ከመፍታት ይልቅ፣ ኢትዮጵያ የአገሮች ቀፎ የሆነችበት የብተና አጀንዳ ራሱን ሸሽጓል (የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ካስማዬ ያለና ሕገ መንግሥቱን ምርኩዝ ያደረገ የሰላም ፍላጎት፣ የዚህ ረድፈኞች ካቀረቡት ሐሳብ በጣም የተለየ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ የሚደንቀው ደግሞ በዚህ ረድፍ ውስጥ የምናገኘው የከሰረ ብሔርተኛ ፖለቲካን ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ቆመናል ባይነታቸው የተሰለበባቸውና የአሁኑን መንግሥት መተናነቅ የበለጠባቸውንም ቡድኖች ነው፡፡

  • ከላይ በተጠቀሰው ረድፍ ትይዩ የዚያ ተቃራኒ ነኝ ባይ ሌላ ረድፍ አለ፡፡ በላይኛው ረድፍ ውስጥ አብዛኛው ክምችት የጊዜውን መንግሥት ለመጣል በቆረጡ ብሔርተኞች የተሞላ እንደመሆኑ ላለው መንግሥት የሚሰጡት ሥዕል ‹‹አሀዳዊ ነው! ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ፈርሷል! ያለው መንግሥት በብሔር ላይ የሚዘምት ቡድን ነው! አምባገነን ነው›› የሚል ነው፡፡ ይህንን መንግሥት ባለ በሌለ ውንጀላ ተናንቀው ኢትዮጵያ ብትበተንም አያስፈራቸውም፡፡ ‹‹የብሔር›› አገሮች የመፍጠር ቅዠት በውስጣቸው አለና፡፡ ከእነዚህ በተቃራኒ የቆሙ የሚመስሉ ሠልፈኞች ውጥንቅጥ የበዛባቸውና ለአማራ አሳቢ ነኝ ባይ ብሔርተኝነት የታከለባቸው ድብክብክ ሠልፈኞች ናቸው፡፡ ከላይኞቹ በዋነኛነት የሚለዩት የአማራ ብሔርኞች ነን ባዮቹን ጨምሮ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በብሔር አገርነት እንድትበታተን አንፈልግም! ብሔርተኝነት/ዘረኝነት በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክትና ጥላቻ ጭፍጨፋን የሚያመርት አገር አፍራሽ ርዕዮተ ዓለም ነው›› ባዮች ናቸው፡፡ ያለውን መንግሥት የሚከሱትም ‹‹ለኢትዮጵያ ቆሜያለሁ ብሔርተኛ አይደለሁም ይበል እንጂ፣ ብሔርተኛነትን (ዘረኝነትን) አቅፎ የያዘ መንግሥት ነው! አማራ በዘረኞች ተጠቂ መሆኑ የቀጠለው ለዚህ ነው›› በማለት ነው፡፡ ይህንን ይበሉ እንጂ፣ ያለውን መንግሥት የመጣል የትንቅንቅ ጎዳናቸው የሚያገናኛቸው አገራዊ ህልውናን ለማዳን ከሚረባረበው ረድፍ ይልቅ ‹‹ዘረኛ›› ከሚሏቸው ቡድኖች ጋር ነው፡፡ ‹‹በዚህ አጉል ጊዜ ይህንን መንግሥት እንጥላለን ስትሉ፣ መበታተኗን አያሳየን የምትሏት አገር ብትበታተንስ?›› የሚል ጥያቄ ሲመጣባቸው ያላቸው መልስ፣ ‹‹እስከ ዛሬስ ከመበታተን የጠበቃት መንግሥት ነው!? አሁን ያለንበት ሁኔታስ መንግሥት አለ የሚያሰኝ ሆኖ ነው!? ይህች አገር መንግሥት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሳትፈራራስ ስትቆይስ በተደጋጋሚ አልታየም!?›› የሚል መሳይ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት መልስ ‹‹ያበጠው ይፈንዳ፣ የመጣው ይምጣ›› ከማለት የሎቶሪ ጨዋታ የራቀ አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነቱ የሎተሪ ጨዋታ ደግሞ አገራዊ ህልውናችንን ከማስጠበቅ ይበልጥ የብተና ግብን የሚያግዝ ነው፡፡
  • ነገሮችን ማብላላት የሌለበት የውርጭት ‹‹ፖለቲካ›› ሌላም መገለጫ አለው፡፡ በአገራዊ ርብርብ ውስጥ ያለውን ‹‹አብን›› የሚንቀውና ወደ ሥርዓተ አልባነት ያጋደለው ለአማራ በማሰብ ማን አጠገቤ ደርሶ ባዩ ተወራጭ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መቀጠል በአማራ ኪሳራ መሆን የለበትም›› ይበል እንጂ፣ ይህንን ማስቆሚያ መላ የለውም፡፡ ያለውን ፌዴራል መንግሥትም የአማራ ክልልን መንግሥትም አያምንም፡፡ መሣሪያ አንስቶ መተኮስና በአማራ ክልል ያለውን መንግሥት መጣል ያምረዋል፡፡ ተኩሶ፣ ጥሎ ምን እንደሚያደርግ ግን ይቸግረዋል፡፡ የሕወሓት አበጋዞች የትግራይን ክልል አግተው የፌዴራሉን መንግሥት አናውቅም እንዳሉ አያደርግ ነገር የአማራ ሕዝብ ራሱ ይበላዋል፡፡ በፌዴራሉ መንግሥት ላይ የትጥቅ ትግል አይጀምር ነገር የት ቦታ ላይ መሽጎ? አማራ ኅብረተሰብን ምሽጌ ብሎ የክልል መንግሥት ላይ መተኮስ ቢጀምር፣ አንገበገበኝ የሚለውን ‹‹የአማራ ኪሳራ›› ራሱ ማባዛቱ ነው፡፡ አማራ በማንነቱ እንደሚጠቃ እኔም በማንነት ላጥቃ ቢል፣ አማራን የበለጠ አስጨራሽ የመሆን ዕድሜን ለአንድ ሳምንት እንኳ አያገኝም፡፡ ምክንያቱም ብዙኃኑ አማራ ሕዝብ ዘንድ ያለው ንጭንጭን፣ ጥላቻንና በቀልን ተሸክሞ የሚንቆራጠጥ ሳይሆን፣ በማንነት ከመጠቃት ኧረ ገላግሉኝ የሚል ነው፡፡ ይህም ብሶት ጠቅላላ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ የሚሻው በሰላም ወጥቶ የመግባት (የደኅንነት ጥማት) አካል ነው፡፡ እናም በክልል መንግሥትም ላይ በፌዴራል መንግሥትም ላይ ጀርባውን ያዞረው፣ ከትናንትና የኪነት ጨፋሪነት ንቃት ያልዘለሉ ሰዎች የሚያቦኩት የአማራ የቅኝ ብሔርተኝነት፣ ምኑን ከምኑ እንደሚያደርግ መላ የጠፋው ግን የጀብደኝነት ናፍቆት የሚያንቆራጥጠው (ጨለማ ውስጥ ያፈጠጠ) እንቅስቃሴ ነው፡፡
  • አገራዊ ህልውናን በማትረፍ ሠልፍም ውስጥ የንጭንጭ ሠፈሮች አሉ፡፡ አንደኛው ሠፈር ንጭንጩ ፍዝ የሆነና ብዙ ሰው ያለበት ሠፈር ነው፡፡ በዚህ ሠፈር ውስጥ ያለውን መንግሥት በብዙ ነገሩ የሚደግፉ ሌላው ቢቀር የአገራዊ ህልውናቸው መቀጠል፣ በአሁኑ ሁኔታ ከዚህ መንግሥት መቀጠል ጋር መሆኑ የገባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ በዚያው ልክ በዚህ መንግሥት ስህተቶችና በተለይም ሰላምና ደኅነትን በማስተማመን ረገድ ባሉበት ክፍተቶች ሳቢያ መልጎምጎምና መትከን አብሯቸው ይኖራል፡፡

ሁለተኛው ሠፈር ውስጥ ያለው ንጭንጭ በደፈናው ምላስ ያወጣ ነው፡፡ በግልጽ ለውጡ አሁንም እንዳለና ለውጡንም እንደሚደግፉ፣ ይህ መንግሥት በሴራና በአመፅ እንዲወድቅ (አገሪቱ ለትርምስ እንድትጋለጥ) ፈፅሞ እንደማይፈልጉ ለመናገር አያፍሩም፡፡ በድፍኑ እንከንና ድክመት ሲያዩ ገንቢ ሒስ ለመስጠት ይጥራሉ፡፡ መንግሥት ትችት የማይሰማ ወይም የከፋ ጥፋት የሠራ ሆኖ ንጭንጭቸው ሲመር ግን፣ አንዳንዶቹ ከገንቢ ትችት አልፈው ‹‹መንግሥት ማስተዳደር ተስኖታል ወይም ሌላ ዓላማ አለው›› እስከ ማለት ድረስ ጥርጣሬን ያግዛሉ፡፡ እንደ አየሩ ሁኔታ ገድሎ የማዳን ወይም አድኖ የመግደል ዥዋዥዌ ውስጥ ይኖራሉ፡፡

በመንግሥት ላይ ነጭናጫ ትችት ከሚያቀርቡት ውስጥ የአንዳንዶቹ ትችት እውነታዊ ያልሆነና ንጭንጫቸው ከራሳቸው ችኩልነት የበቀለ ነው፡፡ ለምሳሌ የሆነ መረጃ ደርሷቸው እቅጩን የሆነ ምን ያህል ይዘት እንዳለው ሳያጣሩ ጥንብ እርኩስ የሚያወጣ ትችታቸውን ይደረድራሉ፡፡ ዋል አደር ብሎ እውነቱ ሌላ (እንዲያውም በጎ) ሆኖ ሲያገኙት ደግሞ ይቅርታ እንኳ ሳይሉ ሙገሳ ይደረድራሉ፡፡ ከልምድም አይማሩም፣ ከነቀፋ ወደ ሙገሳ ከሙገሳ ወደ ከፋ ነቀፋ መፈናጠራቸውን ይቀጥሉበታል፡፡

በተስፈንጣሪ ፍላጎት የሚመጣ ችኩልነት የሚያነጫንጫቸውም አሉ፡፡ ያለውን መንግሥት የሚመራው የብልፅግና ፓርቲ የብሔርተኛ አግላይ አደራጃጀት፣ ጭቆናን አመልጣለሁ ሲል መልሶ ጨቋኝነት ውስጥ የሚዘፈቅ አደረጃጀት መሆኑን የተረዳና ወደ ኅብረ ብሔራዊ ውህድ ፓርቲነት የተሻገረ፣ የማኅበረሰበ ብዙነት ታሪካዊ መወራረስ ላለው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጠንካራ ኢንዱስትሪያዊ አገር ሆኖ መውጣት የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያወቀ፣ ይህ እንዲሳካ ብሔርተኛነትን ሙጥኝ ማለትም ሆነ ኢብሔርተኛነት ላይ መጠምጠም እንደማያዋጣ ገብቶት የቡድንንም፣ የግልንም መብቶች ማክበር የሚያስችል ኅብረ ብሔራዊ ርዕዮተ ዓለም መያዝን የመረጠ ፓርቲ ነው፡፡ ከብሔርተኛ ቡድድኖሽ ወደ ኅብረ ብሔራዊ) ስብስብ ከመምጣቱ ጋርም ሁሉን ማኅበረሰብ የእኔ/የሁሉንም ጉዳት ጉዳቴ የሚል አተያይና ሥነ ልቦና እንዲገነባ ሲጥር ቆይቷል፣ እየጣረም ነው፡፡ ቢያንስ 27 ዓመታት በብሔርተኛ የአዕምሮ ሙሽት ውስጥ መኖር፣ ለፓርቲውም ለኅብረተሰቡም ቀላል ዕዳ አይደለም፡፡ ፓርቲው ተመርጦ ሥልጣን ላይ የመጣውም አረረም መረረ ባለው ሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ አሁን ባለው አገር የማዳን ርብርብ ውስጥ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀትና ርዕዮተ ዓለም አለን የሚሉ ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ ብሔርተኛ ቡድኖችም አሉበት፡፡ በመላ ኅብረተሰባችን ውስጥ ኅብረ ብሔራዊ አገር ወዳድነት ትርታ እንዳለ ሁሉ፣ የብሔርተኛ ሙሽት ትርታም አለ፡፡ በዚህ ውስብስብ የአገራችን እውነታ ውስጥ ሕገ መንግሥት ማሻሻል ሥልጣን ላይ የወጣ ፓርቲ ብልጠት ጉዳይ አይደለም፡፡ የሕዝብ ፍላጎትና ንቃት መጎልመስ በራሱ የሚያመጣው ነው፡፡ ይህንን ልብ ያሉ ምሁራንና ልሂቃን ጎበዝ ከሆኑ የትኛውንም ማኅበረሰብ በአንድነት ስም መዳመጥም ሆነ በብሔርተኛ አግላይ አስተሳሰብና አደረጃጀት የትኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል ማንጓለል ምን ያህል ጨቋኝና የማያኗኑር እንደሆነ ተንትነው እያስረዱ የሕዝቡን ህሊና በእኩልነት፣ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ ለተመሠረተ ሕገ መንግሥት የማዘጋጀት ሥራን መሥራት ይችላሉ፣ የከለከላቸው የለም፡፡ ይህንን ተግባር ለራሳቸው በማድረግ ፈንታ ግን መንግሥት በአሁኑ ወቅት የሕገ መንግሥት ማሻሻል እንቅስቃሴ እንዲያስጀምርላቸው፣ እንዲያውም ብሔር ‹‹ዘር›› ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝምን የመቀየር፣ ብሔር ‹‹ዘር›› የፖለቲካ ፓርቲ መደራጃ እንዳይሆን የመሥራት ራዕይ አለኝ ብሎ እንዲለፍፍላቸው ይሻሉ፡፡ አገራዊ ህልውናችን ስንት ፈተና ላይ ባለበት ሰዓት መንግሥት ይህንን ቢያደርግ ከዕብደት ቁጥር አይሆንም!? ‹‹ፌዴራሊዝም እየፈረሰ ነው! አሀዳዊነት መጥቶላችኋል!›› ለሚሉ በታኞች አገራዊ ርብርቡን ንዳችሁ ሕዝቦችን በውዥንብር እንድታምሱ አውጀንላችኋል ከማለትስ ይተናነሳል!?

ከዚህ በላይ በአጭር በአጭሩ የዳሰስናቸው አገራዊ ርብርብን የሚላፉ/የሚቀናቀኑ አሠላለፎች ትንታኔ ርብርባቸው ምን ያህል የድጋፍ መዝረክርክ እንዳለበት፣ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነትን አስተማማኝ ለማድረግ መቻል፣ ንጭንጭን የመበተንና አገራዊ ርብርብን የመጥቀም አስተዋጽኦ ምን ያህል እንዳለው ለማስተዋል የሚያስችል ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...