Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለኮንዶሚኒየም ቤቶች የተመዘገቡ ነዋሪዎች በባለሙያ የሚወከሉበት  የዕጣ አወጣጥ ሥርዓት ይስፈን!

በመንግሥት ደረጃ ተፈጸሙ የሚባሉ ግድፈቶች ወይም ስህተቶች በርካታ መገለጫዎች አሉዋቸው፡፡ አንዳንዱ ግድፈት ሆን ተብሎ የሚፈጸም ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሌላው ከብቃት ማነስ ጋር በተያያዘ የተፈጸመ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴም መንግሥትን ለማሳጣትና የሆነ ቡድን ለመጥቀም ሲባል አሠራርን በማዛባት እሳት በመጨመር የሚፈጸም አደገኛ ሁኔታም አለ፡፡

ጥቂት የማይባሉ ሹማምንት ደግሞ ኪሳቸውን ለመሙላት ሲሉ ብዙዎችን የሚጎዳ ግልጽ ሌብነት በመፈጸም መንግሥት ላይ ጣት እንዲቀሰር ያደርጋሉ፡፡ ለዜጎች የተሰጠን አገልግሎት የማግኘት መብት ገንዘብ ካላገኙበት አገልግሎቱን ለመስጠት ፈጽሞ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሹማምንት ሕዝብን በእጅጉ ሲያማርሩ መሰማት የተለመደ ሆኗል። ይህም መንግሥት የተጣለበትን ኃላፊነት ዕየተወጣ አለመሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ በውጤቱም ትልቅ ችግር እያስከተለና በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመንን እያሳጠ ነው፡፡

ሕግና ሥርዓት የተቀመጠለትን አሠራር በሕገወጥ መንገድ በማስኬድ ሕዝብን ለክፍተኛ ምሬትና እሮሮ እየዳረጉ ያሉ ሹማምንት ጥቂት አይባሉም፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ የሚካሄዱ ጨረታዎች ምን ያህል ውንድብና እንደሚፈጸምባቸው መገመት አያቅትም፡፡ በጥቅም ትስስር የጨረታ ሰነዱ ለአንዳንዶች እንዲመች ተደርጎ በማዘጋጀት የሚፈጸመው ሌብነት የሚጀምረው እዚያው በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ባሉ ሆድ አደሮች መሆኑንም መዘንጋት የለብንም፡፡ ስዚህ መንግሥት ላይ ጣት የሚያስቀስሩ ስህተቶችና ግድፈቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚፈጸሙት መንግሥት በሚያስቀምጣቸው ሹማምንትና ባለሙያዎች ነው፡፡ 

በመሆኑም በአስፈጻሚ አካላት የሚፈጸሙ ግድፈተኞች ምንም ይሁኑ ምን ይቅር የማይባሉ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ችግሩ ሕገወጥ ተግባር የፈጸሙና እንዲፈጸም በር የከፈቱትን ብቻ ተጠያቂ በማድረግ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ዓይን ያወጣ ሌብነት አጠገባቸው ሲፈጸም እንዳላየ የሆኑ ዕርምጃ ያልወሰዱ ሁሉ የሚጠየቁበት መሆን አለበት፡፡ በጥቂት ሹማምንት ግድፈትና ዓይን ያወጣ ሌብነት አገርን ቁልቁል የሚያስኬዱ ተግባራት መበራከታቸው አይቀርም፡፡ በተለይ ሌቦችንና አጭበርባሪዎችን ለይቶ ሕጋዊ ዕርምጃ ያለመውሰድ ለድርጊቱ መባባስ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡

ሕዝብ በትልቁም በትንሹም እየተማረረ መቀጠል የለበትም፡፡ ኑሮው የሚያደክመው አንሶ የገዛ መብቱን በጠራራ ፀሐይ ብር ካልከፈለበት አገልግሎት ማግኘት እንደማይቻል በሕግ የተደነገገ እስኪመስል ድረስ መዝለቁና መንግሥትም ይህንን ለማረም ከልብ ከመሥራት ይልቅ አይቶ እንዳላየ የማለፍ ልማዱ የሌብነቱን መጠን ከፍ እያደረገው ነው፡፡ 

ሰሞኑን ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ጋር ተያይዞ ተፈጸመ የተባለው እጅግ አሳፋሪ ድርጊትም ከዚሁ ጋር የተያያዘነው ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ከሰሞኑ የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ ሒደቱ የመረጃ ማጭበርበር ችግር ታይቶበታል ተብሎ ውጤቱ እንዲሰረዝ ተወስኗል፡፡ ተፈጸመ የተባለው ማጭበርበር እንደተለመደው በዋዛና በይቅርታ የሚታለፍ መሆን የለበትም።

ጉዳዩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ጉዳይ በመሆኑ ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን መንግሥት የተሰጠውን አደራ በአግባቡ አለመወጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ የዕጣ አወጣጡና መሥፈርቱም ቢሆን በፖለቲካ ሹመኞች ብቻ ተመዝኖ ውሳኔ የሚሰጥበት ሆኖ መቃኘቱ በራሱ እንደ ትልቅ ግድፈት የሚታይ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ መሠረት አድርጎ ሲካሄድ ነበር የተባለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ችግር የዛሬ ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንመረምር ይብዛም ይነስም ችግሮች የነበሩበት ነው፡፡ አሁን ላይ ግን ያፈጠጠ ሌብነት የሚፈጽመበት ሆኖ መታየቱ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት በእጅጉ የሚጎዳ ነው፡፡ ስለዚህ ከሰሞኑ የተፈጠረውን አሳፋሪ ሊባል የሚችል ግድፈት ለማረም የሚወሰዱ ተግባራት በንፅህና መሠራታቸውን በተጨባጭ መረጃ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም አንዱ መፍትሔ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አጠቃላይ የዕጣ አወጣጥ በገለልተኛ አካል ማካሄድ ነው፡፡ በጋራ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ባለቤቱ መንግሥት ብቻ አለመሆኑን በመገንዘብ አጠቃላይ ሒደቱ ግልጽ በሆነ አሠራር መደገፍ የሚገባው ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ የዕጣ አወጣጥ ሥርዓቱም ሆነ አጠቃላይ አሠራሩ የባለ ጉዳዮቹ ተወካዮች ያሉበት ጭምር ሆኖ ካልተደራጀ ለመተማመን የሚከብድ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የከተማ አስተዳደሩ ምን ያህል ኮንዶሚኒየም ቤቶች እንደገነባ? ምን ያህሉን እንዳስተላለፈ?  እንዲሁም አሁን እየተገነቡ ያሉትን  ሁሉ በትክክል ቆጥሮ በመለየት ይፋዊ መረጃ በአስቸኳይ ለሕዝቡ ማቅረብ አለበት፡፡ እየቆጠቡ ያሉት ምን ያህል እንደሆኑ በዝርዝር የሚያሳይ የባንክ መረጃ መቅረብ አለበት፡፡ ዕጣ ከመውጣቱ በፊት ለዕጣ ውድድሩ ብቁ የሆኑ የቤት ተመዝጋቢዎች ዝርዝርን ይፋ ማድረግ ግልጽኝነትን ለማስፈን የሚጠቅም አሠራር በመሆኑ በቀጣይ የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ ተግባራዊ መደረግ አለበት። ከጥርጣሬ ለመዳን ሲባል በሁሉ ረገድ ያሉ መረጃዎችን በቅድሚያ ለሕዝብ በማሳወቅ መተማመንን መፍጠርና ዳግመኛ ስህተት እንዳይፈጠር አሁንም አደራውን ለመንግሥት እንሰጣለን፡፡ 

የሰሞኑ ድርጊት ግን ሌቦች የፈለጋቸውን እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸው በሚመስል መልኩ እራሳቸው ሶፍትዌር አልሚ፣ እራሳቸው መረጃ ለሶፍትዌሩ መጋቢ፣ እራሳቸው የሶፍትዌሩ ደኅንነት አረጋጋጭና እራሳቸው ዕጣ አውጪ ሆነው እንዲሠሩ የተደረገበት ምክንያት መንግሥት ኃላፊነቱን የሚወጣበት ሥርዓት የእርስ በርስ ቁጥጥር የሌለው ማንም ያሻውን የሚያደርግበት እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ጉዳዩ የእርስ በርስ ቁጥጥር የሚደረግበት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ባሰፈነ ሥርዓት የሚመራ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ይህ ሁለት ችግር ባልተፈጠረ ነበር፡፡

ሥርዓት ማስፈን ከሁሉም ቀዳሚ ቢሆንም ተጭበረበረ በተባለው የቤት ዕጣ አወጣጥ ዕድሉ ደርሷቸው የነበሩ ንፁህ ዜጎች ጉዳዩም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በመንግሥት ስህተት ዜጎች እንዲህ ባለ ደረጃ መጎዳታቸው እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሌላው ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ ዕጣ በወጣ ቁጥር በልዩ ሁኔታ እየተባለ የሚታደለው ቤት ማብቂያ ሊኖረው ይገባል። ዜጎች አልበላም አልጠጣም ብለው በቆጠቡት ገንዘብ ምንም ያልከፈለው በጎን የቤት ባለቤት የሚሆንበት አሠራር ምክንያታዊ ያልሆነ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያዛባ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ሊቆም ይገባል። መንግሥት በልዩ ሁኔታ ቤት ሊሰጣቸው የሚፈልጉ ወገኖች ካሉ በሌላ መንገድ ሊጠቅማቸው የሚችልበት ዕድል እያለ በሌሎች ዕድል ላይ እየፈረዱ መዝለቁ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ 

ስለዚህ ሰሞኑን የወጣው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ሒደት የተበላሸ መሆኑ ተደርሶበት መታገዱ መልካም ነገር ሆኖ የተፈጠረው ስህተት ግን ትቶ የሚያልፈው ጠባሳ ቀላል አይደለም፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ ዕርምት ተብሎ የሚወሰደው ዕርምጃ በስህተቱ የተጎዱ ዜጎችን፣ በዕጣው ሳይካተቱ የቀሩ ተመዝጋቢዎችን ጭምር ታሳቢ ያደረገ እንዲሁም በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመንን የሚፈጥር ሒደቱ ግልጽ የሆነ ሥርዓትን ማበጀት ይኖሮበታል። እየሆነ ያለው ነገር ግን በእጅጉ ያሳዝናል፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት