Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለክለቦች ክፍያ የሚፈጽመው ትክክለኛ የፋይናንስ ሪፖርት ሲቀርብለት ብቻ እንደሆነ የሊግ ካምፓኒው አስታወቀ

ለክለቦች ክፍያ የሚፈጽመው ትክክለኛ የፋይናንስ ሪፖርት ሲቀርብለት ብቻ እንደሆነ የሊግ ካምፓኒው አስታወቀ

ቀን:

ፌዴሬሽኑ ስለተጫዋቾች ዝውውር ከክለቦች ጋር ሊወያይ ነው

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን የሚያስተዳድረው የሊግ ካምፓኒው ክለቦች ተገቢ ካልሆነ የፋይናንስ አጠቃቀም ተላቀው፣ ሥርዓቱን የጠበቀ ትክክለኛ የፋይናንስ ሪፖርት ካላቀረቡ የዘንድሮውን የድርሻ ክፍያ እንደማይፈጸምላቸው አስታውቋል፡፡

ካምፓኒው ባለፈው ሳምንት የ2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መጠናቀቁን አስመልክቶ በሸራተን አዲስ ባዘጋጀው ፕሮግራም ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ለክለቦች እንደሚፈጸም መግለጹ ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የክፍያውን ሒደትና አፈጻጸም አስመልክቶ ሪፖርተር የጠየቃቸው የሊግ ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በፕሮግራሙ ላይ ለክለቦች ክፍያው የሚፈጸመው ክለቦቹ ባለፈው የውድድር ዘመን የተከፈላቸው ክፍያ ምን ላይ እንዳዋሉትና በምን ዓይነት የፋይናንስ ሥርዓት እንደተጠቀሙበት የሚያሳይ በውጭ ኦዲተር የተረጋገጠ የፋይናንስ ሪፖርት ለሊግ ካምፓኒው ማቅረብ ሲችሉ ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተላለፈው መመርያ መሠረት አሁን ላይ ብዙዎቹ ክለቦች የኦዲት ሪፖርታቸውን እያቀረቡ በመሆኑ እየተከፈላቸው መሆኑም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ባለፈው የውድድር ዓመት በተለይም ከተጫዋቾች ወርኃዊ ክፍያ ጋር ተያይዞ የክለቦችና የተጫዋቾች ጉዳይ ፍርድ ቤት መድረሱ ይታወሳል፡፡

ከእነዚህም መካከል ሐዲያ ሆሳዕና ውል ለገባላቸው የክለቡ ተጫዋቾች ወርኃዊ ክፍያ እንዲከፍል ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢደርሰውም ተፈጻሚ ባለማድረጉ፣ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ መፍትሔ እንዲያገኝ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ፍርድ ቤቱ ካሳለፈው ውሳኔ መካከል፣ የሐዲያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ የተጫዋቾቹን ሕጋዊ ውል እስካላከበረ ድረስ ቡድኑ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኝ ዕግድ መጣሉ ነው፡፡

የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ መሠረት በማድረግም ክለቡ በ2014 ዓ.ም. የውድድር ዓመት ከሊግ ካምፓኒው የተፈቀደለት የገንዘብ መጠን እንዳይከፈለው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ሊግ ካምፓኒው እንዳይከፈል ማገዱን አቶ ክፍሌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በተለይም ከገንዘብ አጠቃቀም፣ ከተጫዋቾች ዝውውርና በአጠቃላይ የክለቦች መዋቅራዊ ቅርፅ ምን መምሰል እንዳለበት፣ እንዲሁም ከሊግ ካምፓኒው ጋር ሊኖራቸው ስለሚችለው ግንኙነት የሚመለከት ጥናት አስጠንቶ ማጠናቀቁን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ክፍሌ አገላለጽ፣ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ በመነሳት ክለቦች ከስፖርቱ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ከፋይናንስ ሥርዓታቸው ጀምሮ መዋቅራዊ ይዘታቸውን የሚዳስስ በባለሙያዎች የታገዘ ጥናት ነው የተጠናው፡፡ በቅርቡ ክለቦች በጥናቱ ላይ ተወያይተው እንዲወስኑ እንደሚደረግ፣ በጥናቱም በአሁኑ ወቅት ለክለቦች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ተግዳሮት የሆነው እየናረ የመጣው የተጫዋቾች የዝውውር ገበያ በመካተቱ መፍትሔ እንደሚሆን እናምናለን ብለዋል፡፡

ከተጫዋቾች ዝውውር ጋር በተገናኘ ጉዳዩ ሊግ ካምፓኒው ባይመለከተውም፣ ባለፈው የውድድር ዓመት በርካታ ክለቦች የተጫዋቾቻቸውን ወርኃዊ ክፍያ መክፈል አቅቷቸው ውድድሮች በተያዘላቸው መርሐ ግብር መሠረት እንዳይከናወኑ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ እንደነበር ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፣ በቀጣዩ የውድድር ዓመት ያለፈው ዓይነት ችግር እንዳይከሰት ክለቦች ከዝውውር ገበያው ጋር ያለውን ሁኔታ ካላቸው ውስን ገቢ በመነሳት ወጪያቸውን ሊያጠኑት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽን በበኩሉ፣ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ የሚገኘው የተጫዋቾች ዝውውር ጉዳይ እንዳሳሰበው ሳይገልጽ አላለፈም፡፡ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን እንዳስታወቁት፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተጫዋቾች ከክለብ ወደ ክለብ መዘዋወር ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ለተጫዋቾች ዝውውር እየወጣ ያለው የገንዘብ መጠን ግን በክለቦች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ችግር እንዳለ ከወዲሁ መገመት አያዳግትም በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ኃላፊው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ መፍትሔ ለማፈላለግም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ዙሪያ ከክለቦች ጋር ለመምከር ለማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን ቀጠሮ ይዟል ብለዋል፡፡

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ የአንድ ተጫዋች የዝውውር ዋጋ እስከ 10 ሚሊዮን ብር መድረሱ ለዝግጅት ክፍላችን የሚደርሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...