የሥነ አዕምሮ ሕክምና ባለሙያ ቢሆኑም፣ በሚያነሷቸው ሞጋችና ደፋር የፖለቲካ ሐሳቦች ይታወቃሉ፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ በዘለቀው የሙያ ሕይወታቸው በአማካሪነትና በአሠልጣኝነት ከመሥራት ባለፈ፣ መጽሐፍና በርካታ ጽሑፎችን አበርክተዋል፡፡ ኤርሲዶ ለንደቦ (ዶ/ር) የአደባባይ ምሁራን ተብለው ከሚመደቡ ጥቂቶች አንዱ ሲሆኑ፣ በሚዲያ ተሳትፏቸውም በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡ ዮናስ አማረ በተቋማት ግንባታና አስፈላጊነት ላይ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡- የተቋማት ግንባታን በተመለከተ በኢትዮጵያ ምን ዓይነት ልምድ ነው ያለው ይላሉ?
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- ገቨርንመንት (Government) የሚለውን ቃል በትክክል የሚተካው አቻ ፍቺ፣ መንግሥት ወይም ሥርዓት ማለት ይሁን መተርጎም ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚያግባባው ነገር ጥሩ መንግሥት የሚባለው፣ በሕግ የሚመራ መንግሥት ነው የሚለው ገለጻ ነው፡፡ እኔ በግሌ ስለተቋማት ግንባታና አስፈላጊነት የውጭ ሰዎችን ከመጠየቅ ይልቅ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ ባለፉት አሥር ዓመታት በርዕሰ አንቀጾቹ ያነሳቸውን ሐሳቦች መከለስ ጠቃሚ ነው እላለሁ፡፡ ሕወሓት ኢሕአዴግ የማዕከላዊውን ፖለቲካ በተቆጣጠሩበት ወቅት ሁሉ ሪፖርተር ስለተቋማት በርዕሰ አንቀጾቹ በደንብ ጽፏል፡፡ የእናንተ ጋዜጣም ሆነ ብዙዎች ተቋማት፣ ተቋማት፣ ተቋማት፣ እያሉ ሲወተውቱ የነበረው ጉዳዩ አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡ ለሁሉም ዜጋ የሚመች አገር መፍጠር ካስፈለገ፣ በሕግ የሚገዛ መንግሥትን መፍጠር ነው የሚያስፈልገው ማለት ነው፡፡
ከዚህ አንፃር በአገራችን የነበረውን ሒደት ግልጽ ሆነን እንናገር ከተባለ፣ ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ እየተጓዝን ነው የመጣነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በመላው ዓለም የሚታወቁ ብዙ ጥናቶችና በርካታ መጻሕፍት አሉ፡፡ አገሮች ለምን ይፈርሳሉ? (Why Nations Fail?) በሚል ርዕስ የተጻፈውን የእነ ዳረን አሲሞግሉ መጽሐፍን ብታየው፣ ከአክሱም ሥልጣኔ እስከ ደርግ ያለውን የኢትዮጵያ ታሪክን ፈትሸው ይህንኑ የተቋማትን አስፈላጊነት አስቀምጧል፡፡ ቆንጆ አገሮችን ቆንጆ የሚያደርጋቸው፣ የሠለጠኑ አገሮችን ሥልጡን ያደረጋቸው፣ ወይም ደሃ አገሮችን ደሃ የሚያደርጋቸው ሦስት መሠረታዊ ነገር ተቋም፣ ተቋም፣ ተቋም ነው ሲል ነው
የሚያስረዳው፡፡
ተቋማት በአብዛኛው ከፖለቲካ ሥልጣን (ኃይል) ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ተቋማትን ለመገንባት ተቋማት እንዲገነቡ ሙሉ ፍላጎቱና ፈቃደኝነቱ ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ይህን መሰል ሥርዓት ሲኖር ነው ተቋማት የሚገነቡት፡፡ ስለዚህ ባለፉት 31 ዓመታት ማለትም ሕወሓት/ኢሕአዴግ ይህን አገር ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሥልጣን ላይ ያሉ ሥርዓቶች በሙሉ፣ ተቋማትን ለመገንባት ሙሉ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ኖሯቸው አያውቅም፡፡ ስለተቋም ግንባታም ሆነ አስፈላጊነት በወሬ ደረጃ ሁሉም ሊያወሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ጠንካራ ተቋማት እንዲገነቡ ግድ ኖሯቸው አያውቅም፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥታቱ ጠንካራ ተቋማት ለመገንባት ፍላጎት ያጡት ለምን ይመስልዎታል?
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- ተቋማት ጠንካራ እየሆኑ ከመጡ ፍላጎቶች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች በተቋማት ሥር ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ ፖለቲከኞች የፈለጉትን እንዳያደርጉ ዕድል ያሳጣቸዋል፡፡ የሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነትና ሁሉም ሰው በሕግ የሚዳኝበት ሥርዓት ያለው አገር የሚፈጠር ከሆነና ሁሉም በሕግ ፊት እኩል የሚዳኝበት ሁኔታ ከተፈጠረ፣ ምክንያታዊ የሆኑና በነፃነት የሚያምኑ ወገኖች ብቻ ይሆናሉ ቦታ የሚያገኙት፡፡ በዚህ መሰሉ ሥርዓት ውስጥ መጨቆን፣ መስረቅም ሆነ መዝረፍ የሚፈልጉ ወገኖች ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ስለሆነም ይህ ጥቅማቸው እንዳይነካ ጠንካራ ተቋማት እንዳይገነቡ ወጥረው ይሠራሉ፡፡ ይህ ነው የተቋማት ግንባታ መሰናክል፡፡
ሪፖርተር፡- ተቋማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን የተገነቡትን ማጠናከርም አስፈላጊ ነው ይባላል፡፡ ለምሳሌ የፀረ ሙስና ተቋም ቢገነባም ነገር ግን ሥልጣንና አቅሙን እንዳይጠቀም ተደርጓል፡፡
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- እሱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ሲጀመር ለመሞሰን የሚያመች ሥርዓት እንዲፈጠር ካደረክ በኋላ ሙስናን እዋጋለሁ ማለት አግባብ አይደለም፡፡ የአገር ሀብት የማንም እንዳይሆን ካመቻቸህ በኋላ ለሙስና እንዳይጋለጥ አለማድረግ አትችልም፡፡ የሁሉም የሆነ የማንም አይሆንም እንላለን በአብዛኛው፡፡ ኑሮ “Map” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት መጽሐፍ ላይ “ዘ ትራጀዲ ኦፍ ዘ ኮመንስ” በሚል ስለሚቀመጥ ሕግ አንስቻለሁ፡፡ አንድን ነገር ዝም ብለህ በጋራ ወይም በወል የሁሉም ነው ካልከው የማንም አይሆንም፡፡ የኢትዮጵያ ሙስና የምትለው ነገር ፀረ ሙስና ኮሚሽን በማቋቋም የሚፈታ ችግር አይደለም፡፡ ሲጀመር ፀረ ሙስና የሚባል ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሚሞሰን ነገር እንዲፈጠር ካደረግክ በኋላ፣ እሱን እከላከላለሁ ብሎ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለማቋቋም መነሳት ወለፈንድ ነው፣ ይጋጫል፡፡
ጥያቄው መሆን ያለበት ማንም የሚዘርፈውና የሚሞስነው ሀብት እንዲኖር መፍቀድ ላይ ማተኮር አለበት፡፡ የማንም ያልሆነ በወል ስም የጋራ ነው ተብሎ ከተፈጠረ ሀብት ነው ችግሩ የሚመነጨው፡፡ ይህን ነገር በተጨባጭ ምሳሌ ለማስቀመጥ ያኔ ፀረ ሙስና በሚባል ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከተናገሩት መነሳት እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሙስና ምንጭ ተብለው ከተለዩ (በአብዛኛው ወይም 90 በመቶ ሙስና ከሚመነጭባቸው) ዘርፎች መካከል አንዱ መሬት ሲሆን፣ ሁለተኛው የመንግሥት ጨረታና ግዥ፣ ሦስተኛው የጉምሩክና ቀረጥ ዘርፍ ናቸው ብለው አስቀምጠው ነበር፡፡ እነዚህ ሦስቱም ዘርፎች መንግሥት ዋና የሀብት ተቆጣጣሪና ምንጭ ሆኖ ከመዋቀሩ ጋር የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡
ይህ ደግሞ ኢሕአዴጎች ራሳቸው ሀብትን በአንድ ቦታ በማከማቸት ለሀብታሞችም ሆነ ለድሆች ፍትሐዊ በማድረግ እናከፋፍላለን ብለው ካመጡት የፖለቲካ ፍልስፍና የተቀዳ ነው፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ የፈጠረው ኪራይ የማከፋፈል የፖለቲካ ሥርዓት ነው፡፡ ኪራይ የምናከፋፍለው እኛ ነን፣ ነገር ግን ኪራይ በማከፋፈል ሒደት የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ሊፈጠር ይችላል፣ ይህም የሥርዓቱ አደጋ በመሆኑ ታግለን ኪራዩን እኩል እናከፋፍላለን፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሥርዓቱን ለኒዮ ሊበራሊዝም ትተን እንወጣለን በሚል ተነሱ፡፡ ይህ በጣም የተሳሳተ፣ የተምታታና ልክ ያልሆነ አስተሳሰብ የፈጠረው ሥርዓት ነበር፡፡ ስለዚህ መሬት የመንግሥት ነው ብለህ ለሙስና ኮሚሽን ማጋለጥ፣ ጉምሩክ የእኔ ነው ብለህ ማስሞሰን፣ እንዲሁም ሀብት በሙሉ በመንግሥት ሥር ሆነ ብለህ አምጥተህ በግዥና ጨረታ ማዘረፍን ፈጠረ፡፡ የሀብቱን አከፋፋዮችና ጠባቂዎቹ እንዳይሞስኑ ብለህ ፀረ ሙስና በላያቸው ላይ መሾም ፈፅሞ የተሳሳተ ነበር፡፡
መሬት የመንግሥት፣ የሕዝብና የብሔር ብሔረሰቦች ነው ይላል ሕገ መንግሥቱ፡፡ እኔ ግን መሬት የካድሬ ነው እላለሁ፡፡ ካድሬ ከፈለገ ይሰጥሃል፣ ካልፈለገ ይነሳሀል፡፡ ፀረ ሙስና የሚለውን ምሳሌ እዚህ ጋ እናውጣው፡፡ መጀመርያም ፀረ ሙስና የሚል መሥሪያ ቤት አያስፈልግም፡፡ እንዳይሞሰን መጀመሪያ ሀብት በሰው ልጅ ጭንቅላት እንዲፈጠር ማድረግ፣ የተፈጠረውን ሀብትም የመንግሥት ሳይሆን የግል ማድረግ ነው መፍትሔው፡፡ ሁሉንም ሀብት የግለሰብ ካደረግክ ሙስና ስለማይኖር ፀረ ሙስና አያስፈልግም፡፡ ለአገር መሠረታዊና በቀዳሚነት አስፈላጊ የሆነው ተቋም የሰው ልጆችን በሕይወት የመኖር መብት የሚጠብቀው ነው፡፡ ፀጥታ፣ ፖሊስና ፍርድ ቤት ናቸው፡፡ ከግዛት ውጪ ለሆነና በአገር ላይ ለሚፈጸም ጥቃት የሚከላከል የመከላከያ ተቋም ነው፡፡ መንግሥት በቀዳሚነት ሊገነባቸው የሚገባ ተቋማት የወንጀልና ፍትሐ ብሔር ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ ደኅንነትና መከላከያ መሆን አለበት፡፡ ከእነዚህ ውጪ መንግሥት ከገባ ሁሌም ችግር ይፈጠራል፡፡ መንግሥት መገንባት ያለበት 21 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ሳይሆን አንደኛ ፖሊስ፣ ሁለተኛ ፍርድ ቤት፣ ሦስተኛ መከላከያ ነው፡፡
በፍትሕ ሥርዓቱ ሥር ለምሳሌ የውልና ማስረጃ መሥሪያ ቤቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በየትኛውም አገር ብትሄድ ውልና ማስረጃ የጠበቃ ቢሮዎች የሚሠሩት እንጂ የመንግሥት ሥራ አይደለም፡፡ ደቡብ ሱዳን ቢኬድ ውልና ማስረጃ በጠበቃ ቢሮዎች የሚፈጸም ነው፡፡ የመንግሥት ውልና ማስረጃ የሚባል የለም፡፡ የተቋማት ግንባታ ሲባል ዋና ትኩረታችን ከመከላከያ፣ ከፖሊስና ከፍትሕ ተቋማት ውጪ ሊወጣ አይችልም፡፡ ጤናም ቢባል ግብርናና ሌላ በግል ዘርፍ መሠራት የሚችል ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት በግል ሊሸፈኑ የሚችሉትን ትቶ መሠረታዊ ተቋማትን መገንባት ኃላፊነቱ መሆን አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ተቋማት ከተገነቡ በኋላ የማስፈጸም ሙሉ ኃላፊነትና ሥልጣኑ ካልተሰጣቸው ጥርስ የሌለው አንበሳ ናቸውና ተቋማት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ምን መደረግ አለበት?
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- በመጀመሪያ መቋቋም ያለበትንና የሌለበትን ተቋም መለየት አለብን፡፡ መቋቋም የሌለበትን ተቋም አቋቁመህ ጥርስ ብትሰጠውም ባትሰጠውም ዋጋ የለውም፡፡ እንዲያውም በሰጠኸው ጥርስ ሕዝቡን ነው መልሶ የሚነክስበት፡፡ ለምሳሌ ደንብ ማስከበር የሚባል ተቋም አቋቋምክ፡፡ ነገር ግን መንገድ ላይ የሚነግዱ ሕፃናትን ሲያስጨንቅ ነው የምታየው፡፡ ሰዎች ሲበደሉና ሲታረዱ የማይደርሱ ፖሊስና መከላከያ አቋቁመህ፣ ሰዎች ግቢያቸው ውስጥ ቤት ለመሥራት ቆርቆሮ ሲመቱ ሮጦ የሚመጣ ደንብ ማስከበር ማቋቋም ምን የሚሉት ጨዋታ ነው? ስለዚህ ከጅምሩም እነዚህ ደንብና የኢኮኖሚ ተቋማት የሚባሉ የማያስፈልጉ ናቸው፡፡ የማያስፈልገውን ግብርና አቋቁመህ የመንግሥት ሥራ ብቻ የሆኑትን የሰዎችን ሕይወት የሚጠብቁ ፖሊስና ደኅንነትን ማቋቋም ሥራ አለማድረግ አግባብ አይሆንም፡፡
የመንግሥት ሥራ ያልሆኑ ተቋማትን ለማቋቋም መንደፋደፍ ወለፈንድ ነው፡፡ በመጀመርያ ተቋም ሲባል በመንግሥት መገንባት ያለባቸውን ተቋማት መለየት አለባቸው፡፡ መንግሥት የእርሱ ሳይሆን የእኔ ሥራ ናቸው እያለ እነርሱን ለማቋቋም የሚንደፋደፉባቸው ተቋማት አሉ፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽን ለምሳሌ የግል ዘርፍ ተቋም መሆን ያለበት እንጂ የመንግሥት ሊሆን አይገባም፡፡ የብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ነው፣ ሜቴክ ምናምን እያልክ፣ ደግሞ በብልፅግና ዘመን ኢንጂነሪንግ የሚል ቀለም የምትቀባባው ድርጅት የመንግሥት ተቋም መሆን የለበትም፡፡ እንዲህ ያለው ተቋም የመንግሥት ሳይሆን የግል ወይም የሕዝብ ድርጅት ነው፡፡ ብረት መቀጥቀጥን የግሉ ዘርፍ በደንብ ይሠራዋል፡፡ ማሩ ወይም መስፍን ኢንጂነሪንግ ወይም በግለሰቦች ይሠራል፡፡ የመንግሥት ተቋም ማለት ፍርድ ቤት ነው፡፡ የመንግሥት ተቋም ማለት ፖሊስ ነው፡፡ የመንግሥት ተቋም ማለት መከላከያ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ መንግሥት ካላቋቋምኳቸው የሚላቸው ተቋማት በሙሉ የመንግሥት የዘረፋ ተቋማት ናቸው፡፡
ተቋማት ስንል መሠረታዊ የተቋማት ፍልስፍና ላይ ነው በደንብ መስማማት ያለብን፡፡ ማቋቋም የሌለብህን ተቋም አቋቁመህ ጥርስ ብትሰጠው ዜጎችን ነው የሚያርድበት፡፡ መጀመርያ መንግሥትና መንግሥት ብቻ የሚሠራቸው በግል ዘርፍ የማይሠሩ ተቋማት መለየት አለባቸው፡፡ መንግሥት ብቻ የሚሠራው ተቋም ደግሞ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ፍርድ ቤትን ለኢንቨስተር ሥራው ብለህ መስጠት አትችልም፡፡ መንግሥት ብቻ የሚሠራውና ለኢንቨስተር መስጠት የማይቻለው ተቋም ፖሊስ ነው፡፡ መከላከያም ለግል ዘርፍ የማትሰጠው መንግሥትና መንግሥት ብቻ የሚሠራው ተቋም ነው፡፡ መነጋገር ካለብን መነጋገር የሚኖርብን፣ መንግሥት ብቻ የሚገነባቸው ተቋማት በአንድ አገር እነማን ናቸው? እንዲሁም እነዚህን ተቋማት መንግሥት ለመገንባት ምን አድርጓል? የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በተለምዶ ተቋማት ሲባል የሚጠቀሱት ግን ብዙ ናቸው እኮ?
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- ዓለም ስለተሳሳተ ወይም የዚህ አገር ምሁር ነኝ ባይ ሁሉ ስለዘላበደ፣ እኛም እሱን እየደገምን መቸገር አይኖርብንም ነው የምለው፡፡
ሪፖርተር፡– በተቋማት ምንነት ላይ ያለውን አረዳድ ለማቃናት በዚህ ላይ ውይይት አስፈላጊ ነው?
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- እሱ ልክ ነው፣ ማንሳቱ አስፈላጊ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ተቋማትን ከመገንባት ባለፈ ለተገነቡት ተቋማት ውጤታማ የአሠራር ሥርዓት መገንባት ላይም ኢትዮጵያ ትፈተናለች፡፡ ቀልጣፋ አሠራር፣ ቢፒአር፣ ውጤት ተኮር፣ ወዘተ. እየተባለ በርካታ የአሠራር ሥርዓቶች ታይተዋል፡፡
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- በየትኛው ተቋም የሚለውን ነው መነጋገር ያለብን፡፡ ቢፒአር የት ጋ? ቢፒአር ግብርናና ትምህርት ቢሮ ነው ወይስ የት? ቢፒአር ፍርድ ቤት፣ ቢፒአር ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤትና መከላከያ ጋር ከሆነ እሺ፡፡ የመንግሥት አይደሉም በምንላቸው ተቋማት ላይ ስለሚዘረጋ የአሠራር ሥርዓት ማውራት የለብንም፡፡ ማውራት ያለብን በመንግሥት ብቻ በሚገነቡ ተቋማት ስላለው አሠራር ይሆናል፡፡ የመንግሥት መሆን አለባቸው በምንላቸው ተቋማት ደግሞ ቢፒአርም ሆነ ሌላ ነገር አያስፈልግም፡፡ ዋርካ ሥርም ተቀምጠህ ፍርድ ስጥ ወይም ያረጀ ቆመ ጠብቀኝ ፖሊሱን አስታጥቀህ ጥበቃ አርግ በለው የተቋማቱን ማንነት አይቀይረውም፡፡ ፖሊስ ፖሊስ ነው፣ ፍርድ ቤትም ፍርድ ቤት፡፡ እነዚህ ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ ከማያስፈልጉ ተቋማት ጋር መንደፋደፉን አቁሞ የሚያገባውን ተቋም ይሥራ፡፡
ለምሳሌ የመንግሥት ዋና ሥራ ከሆኑት አንዱ የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት መጠበቅ ነው፡፡ የመንግሥት ዋና ሥራ ሰብዓዊ መብትን ማስከበር እንጂ ስኳር ማቅረብ አይደለም፡፡ የመንግሥት ሥራ ብረት አይደለም፡፡ የመንግሥት ዋና ኃላፊነቱን የሰብዓዊ መብት መጠበቅን ትቶ ስኳር፣ ስንዴና ብረት ላይ ከተንደፋደፈ ስኳር፣ ስንዴ፣ ዘይት ወይም ብረት ይወደዳሉ፡፡ በተቃራኒው ግን ውድ የሰው ሕይወትና ሰብዓዊ መብት ይረክሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ይኼ ነው፡፡ ስኳር፣ ስንዴ፣ ዘይትና ብረት ተወደዋል፣ የሰው ሕይወት ግን ረክሷል፡፡ ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት መንግሥት የሚመለከተውን ሥራ ትቶ በማይመለከተው በመጠመዱ ነው፡፡
ስለዚህ ወደዚህ መሠረታዊ ነጥብ መመለስ አለብን፡፡ ተቋም፣ ተቋም፣ ወይም የተቋማት አሠራር ይባላል፡፡ ነገር ግን የሚቀድም መሠረታዊ ጉዳይ አለ፡፡ ንጉሡም እኮ ተቋማት ነበሯቸው፡፡ ለ50 ዓመታት የንጉሡን ተቋማት ስታፈርስ ቆይተህ ያለ ተቋም ስለግንባታ ማውራት ሰውን ማደናገርና ምንም ዋጋ የሌለው ነው፡፡
ጉዳዩ ግንባታ ወይም የተቋም የአሠራር ሥርዓት ዝርጋታ ብሎ ነገር ማወሳሰብን አይጠይቅም፡፡ የፖሊስ ሥራ ምንድነው? ወንጀለኛን ሄዶ መያዝ ነው፡፡ ተቋምና የአሠራር ሥርዓት እየተባለ እየተደጋገመ ስለተወራ እንጂ፣ የተቋም ግንባታም ሆነ አሠራር የተወሳሰበ ነገር ሆኖ አይደለም፡፡ እኛ አገር ምክንያት እየተደረደረና ውሸት እየተደጋገመ ሕዝብን ለማሳመን ይሞክራል እንጂ፣ ወሳኙ ነገር መንግሥት የትኞቹን ተቋማት መገንባት አለበት የሚለው ነው፡፡ መንግሥት 100 ተቋማትን ካልገነባ ካልክ ለዘለዓለምም ሊገነባ አይችልም፡፡ የእኛም ዕጣ ፈንታ እየተገዳደሉ መኖር ነው፡፡
የመንግሥት ዋና ሥራ የ120 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንን በሕይወት የመኖር መብት መጠበቅ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ መጀመርያ መሠራት ያለበት ፖሊስ፣ ፍርድ ቤትና መከላከያ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ስኳር ቢባል ዜጎች ያመርቱታል፡፡ ስኳር የዛሬ 70 ዓመት ያውም በውጭ ኩባንያ የተጀመረ ዘርፍ ነው በኢትዮጵያ፡፡ ብረት ማንም ግለሰብ ሊሠራው የሚችል ሥራ ነው፡፡ ከ3,000 ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን ብረት ማንጠርና መቀጥቀጥን ያውቁበታል፡፡ ብረት አንጥረኞች ቀጥቃጭ እየተባሉ የኖሩበት አገር ነው፡፡ ስለዚህ ሜቴክ ምናምን አያስፈልግም፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ የአገር ምሰሶ ናቸው የሚባሉ መሠረታዊ ተቋማትስ ቢሆኑ እንዴት ይገንቡ? እንዴት የሚጨበጥ ቀልጣፋ አገልግሎት ይስጡ? በማንም ሌባ ተብለው ላይፈረጁ በተሰጣቸው ሥልጣንና የኃላፊነት ወሰን ውስጥ ሆነው በነፃነት እንዲሠሩ ሜዳው ሊመቻችላቸው አይገባም ወይ?
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- እንግዲህ ሌባ የተባሉት ተቋማት እንጂ፣ እኔ አይደለሁም ለዚህ መልስ መስጠት የሚኖርብኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌባ ብለዋችኋልና ምን ትላላችሁ ብለህ እነሱኑ ጠይቅ፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት አካላት ሦስት ናቸው፡፡ ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ ብሎ ሕገ መንግሥቱ አስቀምጧል፡፡ የአስፈጻሚው የመጨረሻና ቁንጮ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕግ ተርጓሚውን ሌባ ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለእኔ ሳይሆን ለክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ መቅረብ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በተቋማት ላይ መንግሥት ጫና ያሳድራል ወይም ጣልቃ ይገባል መባሉ አዲስ አይደለም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጀምሮ የሚቀርብ ወቀሳ ነው፡፡ የአሁኑን አጋጣሚ ከዚህ የተለየ የሚያደርገው ወይም ፖለቲካዊ መነሻ የለውም ወይ የሚለው ላይ የእርስዎን ምልከታ እንዲያጋሩ ነበር ጥያቄውን ያነሳሁት፡፡
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- መነሻውን አላውቅም፡፡ ትርጉምም መስጠት ያለብኝ አልመሰለኝም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውንጀላ መነሻ ምክንያት ለማወቅ በግሌ ምንም ፍላጎት የለኝም፡፡ ግን በጣም ግልጽ የሆነው ነገር ሦስት የራሳቸው ሥልጣን አላቸው ተብለው ከሚታመኑ ተቋማት፣ ሕግ አውጪው አካል መድረክ ላይ ተገኝቶ ሕግ ተርጓሚውን ሲሳደብ ዓይተናል፡፡ ስለዚህ ሕግ ተርጓሚውን ስለዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ ብሎ መጠየቅ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አስፈጻሚው ሌባ ነው ብሎ የበየነው ተቋም የሚያገለግለው ሁላችንም በመሆኑ፣ ከዚህ አንፃር ጉዳዩ ሊፈጥር የሚችለውን ተፅዕኖ መነጋገር አንችልም?
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- በመጀመርያ ራሳቸው ሌባ የተባሉ አካላት መልስ ይስጡበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያን ነገር ሊናገሩ ያስቻላቸው መረጃ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፡፡ እኔ እዚህ ላይ ተነስቼ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዳኞችን፣ ፖሊሶችንና ዓቃቢያን ሕጎችን ሌባ ናቸው ማለታቸው ስህተት ነው ብል ከምን መረጃ ተነስተህ ነው ሊሉኝ ይችላሉ፡፡ ሌባ የተባሉት ከተጠየቁና ሌባ የተባሉበትን ጉዳይ ካስተባበሉ፣ ወይም ከተቀበሉ በኋላ ነው እኔ እንደ አንድ ዜጋ አስተያየት መስጠት የምችለው፡፡
እነዚህን ተቋማት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለ ተጨባጭ መረጃ ከወነጀሉ ተሳስተው ነበር እንላለን፡፡ ጥፋቱ ከተገኘ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትክክል ነበሩ እንላለን፡፡ ሆኖም እሳቸው ለተናገሩት ነገር እኛ ሌባ አይደለንም ብለው ቀድመው መከራከር ያለባቸው ራሳቸው ተቋማቱ ናቸው፡፡
ሌባ አይደለሁም ብለው ወጥተው መከራከር ያለባቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ክብርት መዓዛ አሸናፊ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊሶችና ዓቃቢያን ሕጎችን ሌባ ብለው የተናገሩት ሲሰርቁ አግኝቷቸው ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ተቋማት ካልሰረቁ ሌባ አይደለንም ብለው ወጥተው መከላከል ይችላሉ፡፡ የጉዳዩ አመክኖአዊ ተዛምዶ ይህ ነው፡፡ ችግሩ የሚመነጨው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋማቱን ሌባ በማለታቸው ሳይሆን፣ ሌባ ተብለው በጉዳዩ ላይ መልስ ሳይሰጡ ሌባ የተባሉት ለምን ፀጥ አሉ የሚለው ነጥብ ላይ ነው፡፡ ሌባ የተባሉት ራሳቸውን ይከላከላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ውጤታማ የሆኑ ተቋማትን ለመገንባት ከምንና ከማን ተሞክሮ መማር ይቻላል? ውጤታማ ተቋማትን መገንባት የሚቻለው እንዴት ነው?
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- የተቋማት ኃላፊ ነን ብለው የተቀመጡ ሰዎች አሉን፡፡ ይህን በተመለከተ አንደኛ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ ሁለተኛም ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስን ትጠይቃለህ፡፡ ሦስተኛ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ብርሃኑ ጁላ አሉ፡፡ እነዚህ አገር የሚቆምባቸው ተቋማት አመራሮች በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ ይስጡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ሐሳብ ሰውን፣ ሰው ደግሞ ተቋምን፣ ተቋማትም አገርን ይገነባሉ ብለው ተናግረዋል፡፡ የአገር ምሰሶ ከሆኑት ተቋማት አንዱ የሆነውን የፍትሕ ተቋማም የሚመሩት የተከበሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እንደመሆናቸው ጠንካራ የፍትሕ ተቋም እንዴት ነው እየገነቡ ያሉት ብሎ እሳቸውን መጠየቅ ይቻላል፡፡ ሁለተኛ ፍርድ ቤቶች፣ ከዚያም መከላከያ ይጠየቁበታል፡፡
ተሞክሮ ይባላል፣ ነገር ግን በዓለም ላይ ተቋም እንዴት እንደሚገነባ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ጽሑፎች ተጽፈው ሊሆን ይችላል፡፡ የአገር ተሞክሮዎችም ቢሆኑ መቶና ከዚያ በላይ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በየዘርፉ ተቋም ገንቡ ተብለው የተቀጠሩና የደለበ ደመወዝ የሚበሉ ሰዎች ሞልተዋል፡፡ እኔና አንተ በጣም ስለሚታወቅና ሆን ተብሎ ስለማይሠራ ሥራ ነው እየለፋን ያለነው፡፡ ተቋም እንዴት እንደሚገነባም ሆነ ስለተቋም አስፈላጊነት የሪፖርተርን የአሥር ዓመታት ርዕሰ አንቀጽ መከለስ ያሻላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በየዘርፉ በጀት እየበሉ ተቋም ለመገንባት የተሾሙ የሥራ ኃላፊዎች አገሪቱ የረባና ውጤታማ ተቋማት ለምን እንዳላፈራች መልስ ይስጡበት፡፡ ተቋም እንዴት እንደሚገነባ እነዚህ ሰዎች የማያውቁ ከሆነ ግን መረጃ ካለበት ፈላልጎ ለእነሱ ዕውቀትም ተሞክሮም ማቅረብ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- የመረጃም ሆነ የዕውቀት ክፍተት መኖሩን በተጨባጭ ምሳሌ አስደግፎ ማቅረብ ይቻላል?
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- በምርምርና ጥናት የዕውቀት ችግር መኖሩን የደረሰበት ሰው ካለ ለፍትሕ ተቋማቱ ማቅረብ ይችላል፡፡ ችግሩ የዕውቀት ወይስ የፍላጎት ማጣት መሆኑ ሳይረጋገጥ ግን ይህን ማድረግ አይቻልም፡፡
ሪፖርተር፡- የቅርብ ጊዜ ሁነትን ለአብነት እናንሳ፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አዋጅ በቅርቡ ፀድቋል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ላይ የሰፈረ ድንጋጌ በግልጽ ቢከለክልም፣ ነገር ግን የመንግሥት ባለሥልጣናትን በአባልነት ያካተተ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ በፓርላማው ተሰይሟል፡፡ እንዲህ ያለው የተቋማት ግንባታ የዕውቀት ችግር ካልተባለ የምን ችግር ሊባል ይችላል?
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- እኔ ይህን ዓይነቱን ግድፈት የዕውቀት ችግር ነው አልለውም፡፡ ይህን መሰሉ ነገር ሆን ብሎ እንደ ማጥፋት ሥራ የሚመደብ ነው፡፡ በግልጽ ማናለብኝነት የሚታይበት እንጂ የመረጃ ክፍተት ነው ልንለው አንችልም፡፡ በአዋጁ በግልጽ የመገናኛ ብዙኃን መከታተያ ቦርዱ ገለልተኛ መሆን አለበት፣ ገለልተኝነቱ ስለሚጣስ የመንግሥት ባለሥልጣናት በአባልነት መግባት የለባቸውም ብለህ አስቀምጠሃል፡፡ ሆኖም ራስህ የጻፍከውን አዋጅ መልሰህ ካጠፋህ ይህ አውቀህ ያደረግከው አጥፊነትና ግብዝነት እንጂ፣ በዕውቀት ችግር የፈጠርከው አይደለም፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ችግር ቀላል ፍቺ እንስጠው ከተባለም የሕግ የበላይነት የለም ማለት ነው፡፡
ማንም የፈለገው የሚያደርግበት ሥርዓት ከሌለ በስተቀር፣ በኢትዮጵያ የዕውቀትም የመረጃም ችግር አለ ብዬ አላምንም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚያ ይልቅ ያለው የተጠያቂነት ችግር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሕግ የበላይነት ችግር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፈለኩትን ባደርግም የሚጠይቀኝ የለም የሚል ችግር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው በሕግና በመርህ የሚገዛ ሳይሆን፣ በግለሰብ ፍላጎት መገዛት ነው፡፡ የዕውቀት ችግር የለም፡፡
በነገራችን ላይ አሁን ባለንበት ዘመን በየትም አገር ቢሆን የዕውቀት ችግር የለም፡፡ ዓለማችን በዕውቀት ብዛት እንጂ እጥረት የምትቸገርበት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የመረጃ እጥረት (Information Shortage) ሳይሆን የመረጃ ብክለት (Information Pollution) ችግር ነው ያለው፡፡ የመረጃ ብዛት፣ ብክነትና ብክለት ከመብዛቱ የተነሳ የሚጠቅምን መረጃ ከማይጠቅም የመለየት ለፋት ካልጠየቀ በስተቀር፣ ዕውቀትም ሆነ መረጃ አጠረኝ የሚለው ችግር አያሳምንም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዕውቀት ችግር ካጋጠመ በአንድ ሰከንድ ውስጥ ከተፈለገው ቦታ መግዛት ይቻላል፡፡ የኢንተርኔት ወጪ ከበደኝ ካላለ በስተቀር ማንም ሰው በዕውቀት ሊያሳብብ አይችልም፡፡ በስንፍና ማሳበብ ይቻል ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- በማጠቃለያ ማንሳት የሚፈልጉት ሐሳብ አለ?
ኤርሲዶ (ዶ/ር)፡- ለሪፖርተር ጋዜጣ ክሬዲት መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ በተቋማት ግንባታና አስፈላጊነት የረጅም ዓመታት ዕትሞቹ ላይ ደጋግሞ በመጻፉ ማንበብ ችያለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሌሎች የመረጃ ምንጮችንና የእኛ አገር ሁኔታን ለመመልከት ሞክሬያለሁ፡፡ ጠንካራ ተቋም ከተገነባ መግዛት የሚፈልጉ፣ መጨቆን፣ መዝረፍና መመዝበር የሚፈልጉ ሰዎች መፈናፈኛ ያጣሉ፡፡ ተቋማቱ እነዚህን ሰዎች ስለማያላውሱ ጠንካራ ተቋማት እንዲፈጥሩ አይፈለግም፡፡ ተቋም እንዲፈጥሩ ሥልጣን የተሰጣቸውም ሰዎች ቢሆን ሕጉ ሥልጣኑን ሰጠን ከማለት ይልቅ፣ የሾማቸውን ሰው ስለሚያስቡ እሱን ለማስደሰት ወይም የራሳቸውን ጥቅም ለማካበት ይሠራሉ እንጂ ተቋማትን አይገነቡም፡፡