Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ የሰጠው አጠቃላይ የብድር ክምችት 129 ቢሊዮን ብር ደረሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዋሽ ባንክ አጠቃላይ የብድር ክምች መጠን በተጠናቀቀው የ2014 የሒሳብ ዓመት 129 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም ዕድገት በማሳየት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ከ151.6 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገለጸ።

አዋሽ ባንክ ማኅበረሰቡ በነፃ እንዲገለገልበት ብሎ ያበለፀገውን የኢስኩል ማኔጅመንት የቴክኖሎጂ ሥርዓትን ሰሞኑን ይፋ ባደረገበት ፕሮግራም ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው እንዳስታወቁት፣ ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠን ክምችት በየዓመቱ እያደገ መሆኑንና በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የብድር ክምችቱ ከ129 ቢሊዮን ብር በላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡ ይህም የባንኩ የብድር ክምችት ከቀዳሚው ዓመት በ48 በመቶ ወይም በ42 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት የነበረው የብድር ክምችት 87.53 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በ2012 ሒሳብ ዓመት ላይ ደግሞ 57.27 ቢሊዮን ብር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት በተጠናቀቀው የ2014 የሒሳብ ዓመት የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠንም በ41 ቢሊዮን ብር ወይም በ43.8 በመቶ ጨማሪ በማሳየት 151.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የተከታታይ ዓመታት የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገትን የሚያመለክተው መረጃ፣ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ2013 የሒሳብ ዓመት 108.07 እንደነበር ይጠቁማል፡፡ በ2012 በጀት ዓመት ደግሞ 74.2 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ቀደም ብሎ በነበረው የ2011 ሒሳብ ዓመት የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 62.4 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያመለክታል፡፡  

ከተቀመጭ ገንዘብ መጠኑ ዕድገት ባሻገር በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ብቻ ከ2.8 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ደንበኞችን በማፈራት አጠቃላይ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ደንበኞቹን ከ7.7 ሚሊዮን በላይ ማድረስ ችሏል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለየት ባለ መንገድ መቅረቡን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያን የትምህርት ሥርዓት በዘመናዊ መንገድ ማከናወን ያስችል ዘንድ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የገዛውን ቴክኖሎጂ በነፃ ማቅረቡን ሐምሌ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. አሠራሩን ይፋ ባደረገበት ፕሮግራም ላይ ገልጿል፡፡ የትምህርት ቤቶችን፣ ኮሌጆችንና ዩኒቨርሲቲዎችን አጠቃላይ የመረጃ አሰባሰብ፣ አያያዝና አጠቃቀም፣ እንዲሁም የክፍያንና የማስታረቂያ ሥርዓቶችን ከማንዋል (ከወረቀት) ሲስተም ወደ ዲጂታል ሲስተም የሚቀይር የትምህርት ቤት አስተዳደር ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችለው ቴክኖሎጂ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቋል፡፡ 

አቶ ፀሐይ፣ ባንኩ የኢስኩል ማኔጅመንት ሥራ ላይ ማዋል መጀመሩን በይፋ ባበሰሩበት ወቅት እንደገለጹት፣ አገልግሎቱ የትምህርት መረጃዎችን በቀላሉ መሰብሰብ፣ ማጠናቀርና መተንተን የሚያስችል እንደመሆኑ መጠን፣ የተለያዩ የትምህርት ቤቶች የአስተዳደር አካላትና የተማሪ ቤተሰቦች ተዓማኒ የሆኑ መረጃዎችን በቀላሉና በፍጥነት በማግኘት፣ በመረጃ ላይ የተደገፈ ውሳኔ መስጠት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ 

 

አዋሽ ባንክ የደንበኞቹን አስተያየት፣ ጥያቄና ቅሬታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በየጊዜው የአሠራር ሒደቶቹን እያሻሻለ የደንበኞቹን ፍላጎት በማርካት ታላቅ አመኔታን ያተረፈ ባንክ ነው ያሉት አቶ ፀሐይ፣ ከዚህ አኳያ ትምህርት ቤቶችና ትምህርት ቤቶቹ የሚያስተዳድሯቸው ተማሪዎቻቸውና ሠራተኞቻቸው፣ እንዲሁም የተማሪ ወላጆች የባንኩ ደንበኞች በመሆናቸው መጠን ባንኩ ለትምህርት ቤቶች መጠናከር ልዩ ትኩረትና ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ 

አዋሽ ባንክ ለትምህርት ተቋማት ማስፋፊያና ሥራ ማስኬጃ የረዥም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ ብድር ከማመቻቸቱም በተጨማሪ፣ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በመምህራን ሥልጠናና በምርምር ሥራዎች ላይ ለመሳተፍም በዝግጅት ላይ መሆኑን አክለዋል፡፡ 

አዋሽ ባንክ የኢስኩል ማኔጅመንትን ይፋ ለማድረግ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ትምህርት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራቸው ሥራዎች የትምህርት ዘርፉን የማኑዋል የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ወደ ዲጂታል የመረጃ አያያዝ ሥርዓት መቀየር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማር ሒደትና ሌሎች የትምህርት አስተዳደር ሥራዎች በማንዋል ሲስተም የሚሠሩ በመሆናቸው የትምህርት ክፍያ ሥርዓት፣ የፋይናንስ ሥርዓት፣ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት፣ የትምህርት ተቋማት ከተማሪዎችና ከወላጆች ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ የትምህርት ዕቅድ ዝግጅት፣ የተማሪዎች፣ የመምህራንና ሠራተኞች መረጃ አያያዝን ሁሉ በዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም መተግበር እንደሚቻላቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የተማሪዎች ምዝገባ እንዲሁም ሌሎች የአስተዳደር ሥራዎች በወረቀት የሚሠሩና ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርጓቸው በመሆኑ ይህንን ለማስቀረት ይህ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ አዋሽ ባንክ ይፋ ያደረገው የኢስኩል ማኔጅመንት ሲስተም የትምህርት ተቋማትና አጠቃላይ የትምህርት ማኅበረሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ መፍትሔ ሆኖ የቀረበና ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ደኤታው በበኩላቸው፣ ይህ ቴክኖሎጂ የትምህርት ቤቶችን የክፍያ ሥርዓት ብቻ ያሻሻለ ሳይሆን፣ የትምህርት ቤቶችን የመረጃ አሰባሰብ፣ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል።

አዋሽ ባንክ በኢኮኖሚው ዘርፍ ከሚጫወተው ሚና ባሻገር የአገሪቱን የትምህርት ዘርፍ ለማሻሻልም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ ገልጸው፣ ሌሎች ተቋማትም የዚህን ዓይነት መልካም ተሞክሮ በመቅሰም ዘርፉን ለማሳደግ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡና የትምህርት ተቋማት ቴክኖሎጂውን በአግባቡ በመጠቀም የትምህርት አሰጣጣቸውንና አጠቃላይ የመረጃ አያያዛቸውን እንዲያዘምኑ ሳሙኤል (ዶ/ር) መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች