Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በርካታ የግል ንግድ ባንኮች ለሠራተኞቻቸው ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪና የቦነስ ክፍያ ወሰኑ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የሚገኙ በርከት ያሉ የግል ንግድ ባንኮች ለሠራተኞቻቸው ከፍተኛ የሚባል የደመወዝ ዕርከን ጭማሪና እስከ ስድስት ወራት የሚደርስ የሥራ ማትጊያ (ቦነስ) ክፍያ ለመስጠት መወሰናቸው ተሰማ። 

እስካሁን የደመወዝ ዕርከን ጭማሪና እስከ ስድስት ወራት የሚደርስ የማትጊያ ክፍያ (ቦነስ) ለመክፈል ውሳኔ ካሳለፉት ባንኮች መካከል አዋሽ፣ አቢሲኒያ፣ ንብ፣ ዓባይ፣ አንበሳ፣ ቡናና ዳሸን ባንኮች ይገኙበታል፡፡

የባንኮቹ ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔያቸውን በማሥላትና የውስጥ የምዝና ሥርዓታቸውን በመጠቀም ካደረጉት የደመወዝ ጭማሪና የቦነስ ክፍያ በተጨማሪ፣ አዲስ የደመወዝ ማሻሻያ እንዲደረግ የፈቀዱ ባንኮች መኖራቸውም ታውቋል።

ሰሞኑን የማትጊያ ክፍያና የደመወዝ ዕርከን ጭማሪ ካደረጉ ባንኮች መካከል አዋሽ ባንክ ከፍተኛ መጠን ያለው ጭማሪና ክፍያ በመወሰን የቀዳሚነቱን ደረጃ ይዟል። ባንኩ ለሁሉም ሠራተኞቹ ከሦስት እስከ ስድስት ወራት የሚደረስ ደመወዝ በሥራ ማትጊያ (በቦነስ) መልክ እንዲከፈላቸው መወሰኑን አስታውቋል፡፡

በአዋሽ ባንክ በፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው በኩል በተላለፈው የውስጥ ማስታወቂያ መሠረት፣ ባንኩ በሁሉም መለኪያዎች ከግል ባንኮች የመሪነት ሥፍራውን ይዞ በማጠናቀቁና የላቀ ውጤት በመመዝገቡ ይህንኑ የሥራ አፈጻጸም ከግምት ውስጥ በማስገባት የማትጊያ ክፍያና የደመወዝ ጭማሪ ለባንኩ ሠራተኞች መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ከማኔጅመንቱ በቀረበ የውሳኔ ሐሳብ መሠረት የዳይሬክተሮች ቦርድ ባስተላለፈው ውሳኔ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ሥርዓትን (ፐርፎርማንስ ማኔጅመንት ሲስተም) በመከተል ለሁሉም ሠራተኞች እንደ የሥራ አፈጻጸማቸው ከሦስት እስከ ስድስት ወራት የማትጊያ ክፍያ (ቦነስ) እንዲከፈላቸው ወስኗል፡፡ 

ከማትጊያ ክፍያው በተጨማሪ እያንዳንዱ ሠራተኛ እንደ የሥራ አፈጻጸሙ ተገምግሞ ከአራት እስከ አምስት ዕርከን የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግለት መወሰኑንም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ የቦነስና የደመወዝ ዕርከን ጭማሪ ባሻገር፣ የባንኩ ሠራተኞች የተሻለ ተከፋይ የሚያደርግ አዲስ የደመወዝ ዕርከንና የጥቅማ ጥቅም ጥናት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ተግባራዊ እንደሚያደርግም ፕሬዚዳንቱ ባስተላለፉት የውስጥ ማስታወቂያ ለሠራተኞቻቸው ቃል ገብተዋል፡፡  

የአዋሽ ባንክን የቦነስና የደመወዝ ዕርከን ጭማሪ ከሌሎች ባንኮች ለየት የሚያደርገው ሌላው መገለጫ ደግሞ በተለያዩ ጥፋቶች የተቀጡ ሠራተኞች ጭምር ምሕረት ተደርጎላቸው የማትጊያ ክፍያውና የደመወዝ ዕርከን ጭማሪው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መወሰኑ ነው።

ከሰሞኑ የማትጊያ ክፍያ (ቦነስ) ለሠራተኞቹ ለመስጠት የወሰነው ሌላው ባንክ ዳሸን ባንክ ሲሆን፣ የባንኩ ሠራተኞች በባንኩ የውስጥ መመዘኛ መሥፈርት ተመዝነው ባስመዘገቡት ውጤት መሠረት እስከ አምስት ወራት የሚደርስ ደመወዛቸው በቦነስ መልክ እንዲከፈላቸው ወስኗል። የዳሽን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ፣ ለሠራተኞቻቸው ባስተላለፉት የውስጥ መልዕክት የቦነስ ክፍያው (ጉርሻው) የሥራ አፈጻጸምን መሠረት በማድረግ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። የሥራ አፈጻጸሙ ከ50 በመቶ በታች ለሆነ በየትኛውም ደረጃ ላይ ያለ ሠራተኛ የቦነስ ክፍያውን እንደማያገኝ፣ ከ50 በላይ ውጤት ላገኙ ሠራተኞች ከግማሽ ወር ጀምሮ እስከ አምስት ወራት የሚደርስ ደመወዝ ጉርሻ መፈቀዱን አስታውቀዋል። ዳሸን ባንክ ይህንን ቦነስ የሰጠው ባንኩ ለመጀመርያ ጊዜ ባቀደው ልክ ትርፍ ማግኘት በመቻሉ ስለመሆኑም በዚሁ ማስታወቂያ ላይ ተጠቅሷል፡፡ 

ዳሸን ባንክ ለሠራተኞቹ ‹‹በሥራ ትጋታቸው እሰጣለሁ›› ብሎ ከወሰነው ቦነስ ሌላ፣ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ቅርንጫፎች ሠራተኞቹ በአገር ውስጥና የውጭ ጉዞ ጉብኝት ሽልማትም አብሮ እንዲካተትላቸው ማድረጉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከግል ባንኮች ቀዳሚ ከሚባሉ ሦስት ባንኮች ውስጥ አንዱ የሆነው የአቢሲኒያ ባንክ ቦርድም የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል አዲስ ደመወዝ ስኬል ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ማድረጉን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ አስታውቀዋል፡፡ 

ሆኖም የባንኩ የደመወዝ ጭማሪ ዝርዝር መረጃ ባይገለጽም፣ በዚህ ወር ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን፣ የደመወዝ ጭማሪው ከዚህ ቀደም ይሰጥ ከነበረው በላይ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ 

የባንክ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀለ አሥረኛ ዓመቱን የያዘው ቡና ባንክም ለሠራተኞቹ እስከ አምስት ወራት የሚደርስ ደመወዛቸው በቦነስ ወይም በሥራ ማትጊያነት እንዲከፈላቸው የወሰነ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም እስከ ሦስት ዕርከን የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡ ከዚህም ሌላ ሁሉንም ሠራተኞች ለማትጋት ሲባል፣ የመኖሪያ ወጪ ማካካስን ከግምት በማስገባት የደመወዝ ዕርከን ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ 

ንብ ባንክ ደግሞ ባንኩ የሚጠቀምበት መለኪያዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በአማካይ የሁለት ወራት ደመወዝ ማትጊያ (ቦነስ) ፈቅዷል፡፡ ከዚህም ሌላ ሦስት ዕርከን የደመወዝ ጭማሪ፣ ከዚህ ውስጥ አንዱ ዕርከን የኑሮ ውድነትን ታሳቢ በማድረግ እንዲፈጸም የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ወስኗል፡፡ 

ሌሎች ባንኮችም በተመሳሳይ ጭማሪ እያደረጉ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለየ ምጣኔ የደመወዝ ማስተካከያና ቦነስ መፍቀዳቸውን ካሳወቁት መካከል ዓባይ፣ አንበሳና የኦሮሚ ኅብረት ሥራ ባንክ ይገኙበታል፡፡ ከሰሞኑ ባንኮች በተከታታይ ያሳወቁት ደመወዝ ጭማሪና የቦነስ ክፍያ ውሳኔዎች የተመለከቱ መረጃዎች ከተሠራጩ በኋላ በዚህ ጉዳይ ውሳኔ ያላሳለፉ ባንኮችም ተመሳሳይ ዕርምጃ ለመውሰድ ለየቦርዶቻቸው ጥያቄ እያቀረቡ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

የደመወዝ ጭማሪና ቦነስ ባንኮቹን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ወጪ ያስወጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባንኮች በየዓመቱ ከሚያወጡት ወጪ ውስጥ የደመወዝ የማይናቅ ወጪያቸው ሲሆን፣ ከዓመታዊ ወጪያቸው በአማካይ ከ30 በመቶው በላይ የሚሆነው ለደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የሚያውሉ ባንኮች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የተከታታይ ዓመታት የባንኮች ዓመታዊ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት፣ በዓመቱ ውስጥ ከሚያወጡት ጠቅላላ ወጪዎች ውስጥ በዋናነት ከሚጠቀሱ ሦስት ዋና ዋና ወጪዎች ውስጥ አንዱ የሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ነው፡፡ በሁሉም ባንኮች ዓመታዊ ወጪ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት የተቀማጭ ገንዘብ ወለድ፣ የሠራተኞች ደመወዝ፣ ጥቅማ ጥቅምና አስተዳደራዊ ወጪዎች ናቸው፡፡   

አዋሽ ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት እንዳስታወቀው፣ ጠቅላላ ዓመታዊ ወጪው 8.9 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ለደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ያዋለው የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ለደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ያወጣው 3.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላ ወጪው 39 በመቶ ደርሻ እንዳለው ከሪፖርቱ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡   

አቢሲኒያ ባንክ የ2013 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ደግሞ፣ በሒሳብ ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ወጪ 8.15 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ከዚህ ጠቅላላ ወጪ ውስጥ 39.6 በመቶ ወይም 3.23 ቢሊዮን ብር ለደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የዋለው መሆኑን ያሳያል፡፡ ከደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ቀጥሎ ከፍተኛ ወጪ የወጣው ለተቀማጭ ገንዘብ የከፈለው ወለድ ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላ ዓመታዊ ወጪ 33.1 በመቶ ወይም 2.7 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወጪ ደግሞ ለጠቅላላ አስተዳደራዊ ሥራዎች የወጣው ወጪ ሲሆን፣ ለዚህ 1.35 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጓል፡፡ ይህ ከጠቅላላ ወጪው 16.6 በመቶ የሚይዝ መሆኑን የ2013 ዓ.ም. የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ 

በተመሳሳይም ዳሸን ባንክ በዚሁ የሒሳብ ዓመት ለሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ያወጣው ወጪ 2.14 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ የዳሸን ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት ጠቅላላ ወጪው 7.8 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያመለክታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ 37.08 በመቶ የሚሆነው ወይም 2.96 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ለተቀማጭ ገንዘብ ወለድ ክፍያ ያዋለው ሲሆን፣ ለሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ያዋለው 2.14 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም ከጠቅላላ ዓመታዊ ወጪ 27.4 በመቶ ይይዛል፡፡ ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የነበሩት ሠራተኞች ቁጥር 10,492 ነበር፡፡ 

 እንዲህ ዓይነቱ የደመወዝ ዕርከን ጭማሪና ቦነስ በተለይ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የተለመደ ቢሆንም፣ የዘንድሮ ከሌላው ጊዜ በተለየ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሰው ወቅታዊ የዋጋ ንረት እንደሆነ ይገለጻል። የቦነስ አሰጣጡ ባንኮች ያስመዘገቡትን ውጤት መሠረት ያደረገ ነው ቢባልም፣ ወቅታዊው የዋጋ ንረት ባንኮቹን ከዚህ ቀደም ሲሰጡ ከነበረው ቦነስ የበለጠ እንዲሰጡ ያስገደዳቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ ቀደም አብዛኛዎቹ ባንኮች በአማካይ የሚሰጡት የቦነስ ክፍያ ከሁለት ወራት ደመወዝ የማይበልጥ ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን እስከ አምስትና ስድስት ወራት የሚደርስ ቦነስ ለመስጠት ውሳኔ ላይ ለመድረሳቸው ዋነኛ ምክንያት የኑሮ ውድነት ነው፡፡ 

በሌላ በኩል ግን በተለይ ነባር ባንኮች በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የሆነ ውድድር ከግምት በማስገባት ሠራተኞቻቸውን ከፍልሰት ለመከላከል ሲሉ ከዚህ ቀደም ከሚያደርጉት በተለየ የደመወዝ ጭማሪና ቦነስ እንዲሰጡ እንዳስገደዳቸው ይጠቀሳል፡፡ በአንዳንድ ባንኮች ውስጥ የደመወዝ ጭማሪ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን የታለመ ጭምር ነው፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ የባለሙያ እጥረት በመኖሩ ባንኮች መካከል ሠራተኞችን መነጣጠቅ የተለመደ ሆኖ በመቆየቱ፣ ይህንን ለመከላከል ነባር ባንኮች በተለይ ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ላሉ ሠራተኞች ጠቅም ያለ የደመወዝ ጭማሪ እያደረጉ ናቸው፡፡ አዳዲስ ባንኮች የሚፈልጉትን የሰው ኃይል ለማሟላት ከነባር ባንኮች ለሚወስዷቸው ሠራተኞች ከፍተኛ የሚባል ጭማሪ በማድረግ ሠራተኞችን እየወሰዱ መሆኑንም በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡    

አሁን ካለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት አንፃር ባንኮቹ ያደረጉት ጭማሪ ተገቢ መሆኑን ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የባንክ ሠራተኞች በተደረገላቸው ጭማሪና የቦነስ ክፍያ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የባንክ ሠራተኞች ከሥራቸው ባህሪ አንፃር የተሻለ ተከፋይ መሆናቸው ተገቢ ስለመሆኑም የገለጹ አሉ፡፡ ይሁን እንጂ የጭማሪዎቻቸው መጠንና ተሰጠ የተባለው ቦነስ በትክክል ‹‹ኢኮኖሚያዊ ነው ወይ?›› የሚለውን ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል በሚል ጥያቄ የሚያነሱ ግን አልጠፉም፡፡

በሰሞነኛው የደመወዝ ጭማሪና ቦነስ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ ከፍተኛ የባንክ የሥራ ኃላፊ ይህንኑ የሚያጠናክር ሐሳብ አላቸው፡፡ እኚህ ከፍተኛ የባንክ የሥራ ኃላፊ ባንኮች ካላቸው የሥራ ባህሪ አንፃር በተለይ ከገንዘብ ጋር የተገናኘ ሥራ ስላላቸው በሥራ ሒደታቸው ያልተገባ ተግባር እንዳይፈጽሙ በቂ ደመወዝ ሊኖራቸው ይገባል ይላሉ፡፡ አሁን ካለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት አንፃርም እንደ ሌላው ኅብረተሰብ ክፍል እየተፈተኑ በመሆኑ ቢያንስ ኑሯቸውን ሊደግፍ የሚገባ የደመወዝ ማስተካከያ በመደረጉ ይስማማሉ፡፡ 

ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አካሄድ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሚመጥን ደረጃ ተሠልቶ ተፈጻሚ የተደረገ ነው? ብሎ ለማመን እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ። የተጋነነ ጭማሪና ቦነስ በመስጠት ውድድሩን ለማክረር ታሳቢ የተደረገ ከሆነም አደጋ እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ ከሰሞኑ እንኳን የትርፍ ምጣኔያቸውን አሥልተው መጠነኛ የደመወዝ ማስተካከያ ለማድረግ ውሳኔ አሳልፈው የነበሩ ባንኮች ሳይቀሩ አንዳንድ ባንኮች ያደረጉት ከፍተኛ የሚባል ደመወዝ ጭማሪና ቦነስ ቀድመው ታሳቢ ያደረጉትን ውሳኔያቸውን መልሰው እንዲያዩ ያስገደዳቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ እንዲህ ያለው ውድድር ጤነኛ ላይሆን ይችላል የሚል ሥጋታቸውንም አክለዋል፡፡ 

ከሁሉም በላይ ግን ይህ ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪና የቦነስ ክፍያ ወጪ እንዴት ነው የሚሸፍነው የሚለው ጥያቄ በትክክል መመለስ እንደሚገባው የገለጹት እኚሁ የባንክ የሥራ ኃላፊ፣ ጭማሪውና ቦነሱ በትክክል አቅምንና ኢኮኖሚውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተቃኘ ከሆነ ችግር እንደማይኖረው ያስረዳሉ። ይሁን እንጂ ይህንን ከፍተኛ ወጪ ለመሸፈን ባንኮች ኢኮኖሚያዊ ጫና በሚፈጥር መልኩ በሚሰጡት ብድር ወለድ ላይ ተጨማሪ በማድረግ ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ወጪ ለመሸፈን ታሳቢ አድርገው ከተነሱ ከፍተኛ ችግር እንደሚኖረው ገልጸዋል። የብድር ወለድ ምጣኔያቸው ላይ ጭማሪ ካደረጉ ጫናውን ኅብረተሰቡ ላይ በማሳረፍ ሌላ ለዋጋ ንረት መንስዔ ሊሆን ይችላልና ይህ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል። 

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ ግን ባንኮቹ እንዲህ ያለውን ጭማሪ ማድረጋቸው የሚጠበቅ እንደሆነ ገልጸዋል። ጭማሪውንና ቦነሱን ዓመታዊ ትርፋቸውን አሥልተው እስከሆነ ድረስ ችግር እንደሌለው የገለጹት ባለሙያው፣ ደመወዝ ለመጨመር ብለው የአገልግሎታቸው ላይ ዋጋ ሊጨምሩ ይችላሉ የሚለውን ሥጋት ግን አይጋሩትም፡፡ 

በባንኮች የቦነስ አሰጣጥና የደመወዝ ጭማሪ ዕርከን ዙሪያ ጥያቄ የሚያነሱት ያነጋገርናቸው የባንክ የሥራ ኃላፊ ግን ሌላም ሥጋት አላቸው፡፡ እነዚህ ባንኮች ሀብት እስካላቸው ድረስ እንደፈለጉ ደመወዝና ቦነስ መክፈል የሚችሉ ቢሆንም፣ እነሱ በእጃቸው ያለውን ሀብት ለተለጠጠ የደመወዝና ጭማሪና የቦነስ ክፍያ ማዋላቸው ኢኮኖሚው ላይ ጫና እንደሚያስከትል ሊታወቅ ይገባል ብለዋል። በአብዛኛው ግን እንዲህ ያለው ጭማሪ ወቅታዊ ነው በሚለው ይስማማሉ፡፡ 

ከወቅታዊ የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሽን ‹‹የተቀጣሪ ሠራተኞች ደመወዝ ማስተካከያ ሊደረግላቸው ይገባል›› በማለት በይፋ እየሞገተ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች