Sunday, September 24, 2023

ለዜጎች መታፈን ኃላፊነት የሚወስደው ማን ነው?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አዲስ አበባ በተለምዶ ገርጂ መብራት ኃይል ጃክሮስ አካባቢ ‹‹በፊልም ያየሁት ነገር የተፈጠረ መሰለኝ፤›› ትላለች ስለታሰረችበት አጋጣሚ ስትናገር፡፡ ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጓደኞቿ ጋር ሻይ ቡና ስትል አምሽታ ከምሽቱ 4 ሰዓት ግድም በራይድ የታክሲ አገልግሎት ወደ ቤት ስትሄድ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ራሷን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ ሰው ከመሆን ባለፈ፣ የፖለቲካም ሆነ ሌላ የሚዲያ ተሳትፎ የሌላት አድርጋ የምትገልጸው ሜሮን ታደለ የዚያን ቀን ያጋጠማት ሁኔታ አስደንጋጭ መሆኑን ታስረዳለች፡፡

‹‹ቪ8 የሚባለው መኪና ከየት መጣ ሳልል ራይዱ ላይ መንገድ በመዝጋት አስቆመው፡፡ ሁለት ሰዎች ከግራና ከቀኝ ወርደው መጥተው ለሾፌሩ የሕግ ሰዎች/ደኅንነት ነን የሚል ወረቀት አሳይተው፣ ቆልፎት የነበረውን በር አስከፍተው ከመኪናው አወረዱኝ፡፡ ወደ ቪ8 መኪናቸው ካስገቡኝና መካከላቸው ካስቀመጡኝ በኋላ የፊት መሸፈኛ ጭምብል አለበሱኝ፤›› ስትል አያያዟን የምትናገረው ሜሮን፣ ወዴት ይዘዋት እንደሄዱ እንደማታውቅ ትናገራለች፡፡ ፊቷ እንደተሸፈነ አንድ ጨለማ ክፍል አስገብተው እንዳስቀመጧት የተናገረችው ሜሮን፣ ለሁለት ቀን በዚያው እንደቆየች ትተርካለች፡፡

በአዕምሮዋ ‹‹ለእኔ ይህ ሁሉ ያስፈልጋልን?›› የሚል ጥያቄ ሲጉላላ በጠባቧ ክፍል እንደቆየች የተናገረችው ሜሮን በእሷ መታሰር ቤተሰቧ የሚፈጠርበት ከባድ ጭንቀትና የእናቷ ሁኔታ ሲያሳሰባት እንደቆየችም ትናገራለች፡፡ ስልኳ ተከፍቶ መፈተሹን የተናገረችው ሜሮን የመረመሯት ሰዎች በፌስቡክ ስለምትለጥፋቸው መረጃዎችና ስለምትገናኛቸው ሰዎች፣ እንዲሁም በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ስላላት አቋም እንደጠየቋት ትናገራለች፡፡

ከዚህ ውጪ የእስር አያያዟ የከፋ ሁኔታ እንዳልነበረው የተናገረችው ሜሮን፣ ያቀረቡላትን ምግብ በጨጓራ ሕመም ምክንያት አልበላሁም ስትላቸው ምግብ ቀይረው እንዳመጡላት ትገልጻለች፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ይስጣቸው ምንም አልተተናኮሉኝም፤›› ስትል ስለአሳሪዎቿ የተናገረችው ሜሮን፣ የትና በማን መታሰሯን የማታውቅ በመሆኗ ምን ሊያደርጉኝ ይችላሉ? የሚል ከባድ ሥጋትና ፍራቻ ውስጥ ወድቃ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

‹‹ልጄና ታማሚዋ እናቴን እያሰብኩ ከሁለት ቀናት በኋላ በመኪና ጭነው በጭምብል ሸፍነው ወሰዱኝ፤›› ስትል ዕምባ በተቀላቀለበት ስሜት ትናገራለች፡፡ ‹‹ምን ሊያደርጉኝ ነው እያልኩ ስጨነቅ፣ ‹ሜሮን ይህ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያችን ነው፡፡ ከአሁን በኋላ እስራት አይደለም የሚጠብቅሽ፡፡ ለራስሽ የሚጠቅምሽን ታውቂያለሽ› የሚል ማስፈራሪያ ከያዙኝ ሰዎች አንዱ ሰጠኝ፤›› ብላለች፡፡

መኪናው ድንገት መቆሙንና ከመኪናው እንደወረደች የተናገረችው ሜሮን፣ ‹‹ፊትሽን ሳታዞሪ ቀጥ ብለሽ ሂጂ›› ከሚል ትዕዛዝ ጋር እንደለቀቋት ገልጻለች፡፡

ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ በተለምዶ አልታድ መስጊድ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ጥለዋት እንደሄዱ የተናገረችው ሜሮን፣ ወንድሟን በስልክ ጠርታ ወደ ቤት መግባት እንደቻለች ገልጻለች፡፡ በአጭር ጊዜ ከእስር መፈታቷንና ምንም ዓይነት አካላዊ ጉዳት ሳይገጥማት መለቀቋን እንደ ዕድል ብትቆጥረውም፣ በእሷም ሆነ በቤተሰቧ ላይ በዚህ አጭር ጊዜ የደረሰው ጭንቀትና ሥጋት ግን እጅግ ከፍተኛ እንደነበር አስረድታለች፡፡

ሜሮን ብቻ አይደለችም የዚህ ዕጣ ሰለባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማን እንደያዛቸውና ለምን እንደተያዙ ሳያውቁ፣ ከማያውቁት ቦታ ታስረው/ተሰውረው መክረማቸውን የሚናገሩ ዜጎች እየበረከቱ መጥተዋል፡፡ በተለምዶ ፈረንሣይ ለጋሲዮን ጊዮርጊስ ከሚባል ምግብ ቤት ምሣ በልቶ እንደጨረሰ ተያዝኩ ሲል ለሪፖርተር የተናገረው ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ፣ ለሳምንት ጨለማ ክፍል ውስጥ ካቆዩት በኋላ ገላን አካባቢ በመኪና ወስደው እንደለቀቁት መግለጹ አይዘነጋም፡፡ ስለምርመራው ሒደት ከመግለጽ ቢቆጠብም፣ ነገር ግን በእስር ቆይታው ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልገጠመው ነው ገጣሚ በላይ የተናገረው፡፡

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ፣ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ፣ ጋዜጠኛ አበበ ባዩ፣ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረውና ሌሎችም የሚዲያ ሰዎች ታፍነው ተወሰዱ የሚል ዜና ሲዘገብ ከርሟል፡፡ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች በፀጥታ ኃይሎች ተወሰዱ እየተባለ ተደጋግሞ ቢዘገብም ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በማን፣ የትና ለምን እንደተያዙ መንግሥት አጥጋቢ ምላሽ ሲሰጥ እስካሁን አልታየም፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተርና የሕግ ባለሙያ አቶ መሱድ ገበየሁ፣ ‹‹የተለያዩ ሰዎች መታሰራቸውን/መታገታቸውን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ አንድም ኃላፊነት የወሰደና ተጠያቂ የሆነ አካል የለም፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥትም ቢሆን ሰዎች በዚህ መሰል መንገድ አይያዙም ብሎ አላስተባበለም፤›› በማለት ነው ጉዳዩ ግራ አጋቢ ገጽታ እንዳለው የተናገሩት፡፡

በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና በተለያዩ ሕጎች በወንጀል የሚጠረጠር ሰው እንዴት መያዝ እንዳለበት በግልጽ መደንገጉን የሚናገሩት አቶ መሱድ፣ ‹‹የፍርድ ቤት መጥሪያ ተይዞ አልያም እጅ ከፍንጅ ካልተያዝክ በስተቀር፣ እንዲሁም በሥራ ሰዓት ካልሆነ በስተቀር ራስ ተሸፍኖ፣ በአጥር ተዘሎም ሆነ ከሕግ ውጪ የሚደረግ የዜጎች አያያዝ ፍፁም ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው ነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

‹‹ይህን መሰሉ ዕርምጃ አደገኛ ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ብቻ ሳይሆን ግለሰቦችና ሌሎች አካላትም በተመሳሳይ በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን ሊያፍኑ ይችላሉ፡፡ እንኳን ዛሬ ቀርቶ ድሮ አፋኝ ሥርዓት በነበረ ጊዜም፣ ለመንግሥት እንዲህ ዓይነት ሥልጣን የሚሰጥ አንዳችም አሠራር/ሕግ የለም፤›› በማለት አቶ መሱድ ያክላሉ፡፡

ሜሮን ታፈንኩ ብላ በተናገረች ጊዜ አንዳንዶች መንግሥት እንዲህ አያደርግም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ መታፈኑን በተናገረ ጊዜም የተናገራቸው ነገሮች አሳማኝነት የሌላቸው መሆናቸውን በመጥቀስ አንዳንዶች በማኅበራዊ ሚዲያ ሲተቹት ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ‹‹መንግሥት አላፈንኩትም ካለ ለምን እኔን በሐሰት ውንጀላ ከፈለገ አይከሰኝም?›› ሲል ነበር ጋዜጠኛ ጎበዜ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መቆየቱን አስረግጦ የተናገረው፡፡

‹‹እኛ ስለምንታወቅና ሚዲያ ላይ ስለምንታይ ሰዎች ጮሁልን እንጂ፣ የማይታወቁና ጠያቂ የሌላቸው መደበኛ ዜጎች ምን ዓይነት የከፋ ሁኔታ እንደሚገጥማቸው በእኛ ከደረሰው መገመት ይቻላል፤›› ሲል ነበር ለሌላኛዋ የአንድ ሰሞን ‹ታፋኝ› ጋዜጠኛ ለመዓዛ መሐመድ የገጠመውን ሁኔታ በሮሐ ቲዩብ ላይ ጎበዜ  የተናገረው፡፡

ይህ የሰዎች ባልታወቀ ሁኔታና መንገድ ተያዙ መባል፣ እንዲሁም ባልተጠበቀ ሁኔታና ቦታ ተለቀቁ መባል መደጋገሙ እንዳሳሰባቸው የሚገልጹ ወገኖች እየበረከቱ መጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹በተለያዩ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ እስራቶች›› በማለት በቂ ትኩረት እየተሰጠው አይደለም ስለሚለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢነት ይፋ አድርጓል፡፡ ኢሰመጉ ይህን መግለጫ ካወጣ ከሁለት ቀናት በኋላ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ሌላ መግለጫ፣ ‹‹ሕገወጥ እስር›› ሲል በጋዜጠኞች፣ በማኅበራዊ አንቂዎችና በፖለቲከኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን እስራት አሥጊነት ገልጿል፡፡

የኢሰመጉም ሆነ የሌሎች የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ሥጋት በዋናነት ‹ተገቢውን የሕግ ሥነ ሥርዓት ባልተከተለና አስገድዶ መሰወር (ማገት) በሚመስል ሁኔታ ሰዎች እየተያዙ ነው› የሚል መሆኑ በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ወገኖችም ሆኑ ሌሎች ዜጎች የሚያነሱትን ይህን ሥጋት ከግምት በማስገባት፣ መንግሥት ለዕርምጃው ኃላፊነት ሲወስድም ሆነ ሁኔታውን አስቆማለሁ ብሎ ሲናገር የተሰማበት አጋጣሚ የለም የሚል ጥያቄ እየተደጋገመ ይቀርባል፡፡

ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጥያቄ ያቀረቡት የምክር ቤት አባል አቶ አሳማኸኝ አስረስ፣ ‹‹ዕገታ የሚመስል እስራት›› ሲሉ ስለዚሁ ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡

መንግሥት ከመከላከያ ተቋማት ጀምሮ፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ በኢንፎርሜሸን መረብ ደኅንነት አገልግሎት፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና በመሳሰሉ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ያካሄዳቸውን የሪፎርም ሥራዎች አቶ አሳማኸኝ በጥያቄያቸው ‹‹የምክር ቤቱ አባላት ተዘዋውረን ጎብኝተናል›› በማለት በእጅጉ ሲያደንቁ ተደምጠዋል፡፡

ይሁን እንጂ አቶ አሳማኸኝ አስከትለው ባቀረቡት ጥያቄ፣ ‹‹ተገቢውን የሕግ ሥነ ሥርዓት ያልተከተሉና ዕገታም የታከለባቸው እስራቶች በአማራ ክልል ተፈጽመዋል የሚል ቅሬታ ይቀርባል፤›› ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ጠይቀው ነበር፡፡

ለዚህ ጉዳይ ሰፊ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣መንግሥት የሕግ ማስከበር ዘመቻ  የከፈተው በሕዝብ ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሚታፈንም ሆነ የሚታገት ሰው አለመኖሩን ያመለከቱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በአማራ ክልል ለተካሄደው የሕግ ማስከበር ዕርምጃ የፌዴራል መንግሥቱ ሳይሆን ራሱ የአማራ ክልል ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አስታውቀው ነበር፡፡

አክቲቪስትነት፣ ጋዜጠኝነትና ፖለቲከኝነት በኢትዮጵያ መደበላለቁን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ታዋቂ ሰዎች የመናገርና የመንቀሳቀስ መብት አላቸው እንደሚባለው ሁሉ፣ መደበኛ ዜጎችም ሰላም አግኝተው የመኖር መብት እንዳላቸው ሊታወቅ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሥርዓተ አልበኞችና የተከበረውን የጋዜጠኝነት ሙያ መደበቂያ ያደረጉ ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎችን ማስታገስ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በሚዲያ እሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚሰድቡ ሰዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሚዲያ በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያ ጥላቻ፣ ስድብና ውሸት በማሠራጨት ገንዘብ መሰብሰቢያ ሆኗል፤›› ብለው፣ ይህን ዓይነቱን የተበላሸ አካሄድ መንግሥት ለማስተካከል ዕርምጃ እንደሚወስድ ነው አጠንክረው የገለጹት፡፡

የሕግ ባለሙያና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መሱድ ግን፣ መንግሥት ለእነዚህ ዕገታ ለሚመስሉ እስራቶች ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ነው የሚናገሩት፡፡

‹‹ሰዎች አንድ ሳምንት፣ 20 ቀንና አንድ ወር የማይታወቅ ቦታ በማይታወቁ ሰዎች ተይዘን ቆየን ይላሉ፡፡ ሕጋችን ግን ማንኛውም ዜጋ በሚታወቅና የሕግ ሥነ ሥርዓትን በተከተለ መንገድ መያዝ እንዳለበት ደንግጓል፡፡ የተያዘ ሰው በሚታወቅ ቦታ መቆየት እንዳለበትም ሕጉ ያዛል፡፡ ታስሮ የቆየ ሰው የማይታወቁ ሰዎች በማይታወቅ ቦታ አቆዩኝ ብሎ የሚናገረውን ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥትም ስለዚህ ጉዳይ ኃላፊነት ወስዶ መናገር አለበት፤›› በማለት ነው የግል ባለሙያው ምልከታቸውን ያስረዱት፡፡

በአንድ አገር ውስጥ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ዋና ኃላፊነት ያለበት መንግሥት መሆኑን ያመለከቱት የሕግ ባለሙያው፣ ‹‹መንግሥት አፈና ያካሄድኩት እኔ አይደለሁም ቢል እንኳ በዚህ ጉዳይ ከተጠያቂነት አያመልጥም፤›› በማለት ነው የተናገሩት፡፡ ይህን መሰሉን ለዕገታ የቀረበ እስራት የፈጸመው አካል ማንም ቢሆን ማንም፣ ተጠያቂነቱ ዞሮ ዞሮ በመንግሥት ላይ እንደሚያርፍ ነው ባለሙያው የጠቆሙት፡፡ ‹‹የመንግሥት ተቋም፣ ባለሥልጣን፣ ደጋፊ ወይም ሌላ አካል ያድርገው ግለሰቦችን የሕግ ሥነ ሥርዓት ባልተከተለ መንገድ መያዝም ሆነ መሰወርና ማቆየት አንዳችም የሕግ ድጋፍ የለውም፤›› ሲሉ ነው አቶ መሱድ ሙያዊ አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚታወቁ ሁለት ሰዎች በአንድ ወቅት በአምቡላንስ ተወስደን ተደበደብን የሚል መረጃ ቢሰጡም፣ ይህን ያደረኩት እኔ ነኝ ብሎ ኃላፊነት የወሰደ አካል ግን እስካሁን የለም፡፡ ጋዜጠኛ አበበ ባዩ የማያውቀው ቦታ ታፍኖ መወሰዱን፣ ተደብድቦም ከማይታወቅ ቦታ መንገድ ዳር ተጥሎ ስለመገኘቱ አንድ ሰሞን ተነግሯል፡፡ ከሰሞኑ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ምሽት በተለምዶ ካራ በሚባል ሠፈር ጫካ ውስጥ ከእስር ተፈቶ ራሱን እንዳገኘ ሲናገር ተደምጧል፡፡

በገበያ ኑ በኩል ‹‹ሠርገኛ ወጎች›› በሚል የዩቲዩብ ፕሮግራም የሚታወቀው ሰለሞን ሹምዬ፣ ‹‹ፖሊስ የፍርድ ቤት መያዣ ሳይዝ ልክ እንደ ማጅራት መቺ ለምን ይይዘኛል?›› ሲል ከእስር ከተለለቀ በኋላ ተናግሮ ነበር፡፡ በአምቡላንስ ተይዞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱን የተናረው ሰለሞን፣ ከዚህ ቀደም በአምቡላንስ ተይዘን ተወሰድን ብለው የተናገሩ ሰዎችን የሚደግፍ መረጃ ነበረ የሰጠው፡፡

እነዚህ ነገሮች እጅግ ከበድ ያለ ሥጋት የሚያጭሩ ድርጊቶች መሆናቸውን የሚያመለክቱት የሕግ ባለሙያው አቶ መሱድ፣ ‹‹በዚህ ላይ መንግሥት ግልጽ የሆነ መረጃና ምላሽ ለምንድነው የማይሰጠው?›› ሲሉ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ‹‹ጉዳዩ የደኅንነት ሥራም ቢሆን ሕግ አለ፡፡ ይህን መሰሉ ዕርምጃ ግን ፖለቲካዊነቱ ያጋድላል፡፡ ይህ ከወንጀል ጥፋተኝነት አንፃር የሚታይ አይደለም፡፡ ሰው ካጠፋ/ከተጠረጠረ መጠየቅ፣ መያዝ ወይም ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ ስለሚፈጸም እስራትም ሆነ ዕገታ በሕግ አግባብ ፍቺ ለመስጠት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ወይም አሠራር እየተለመደ ከመጣ ለአገሪቱ ታላቅ ቀውስ እንደሚሆንም ነው አቶ መሱድ ሥጋታቸውን የተናገሩት፡፡

ግንቦት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዓመታዊ የአፈጻጸምና ዕቅድ ሪፖርቱን ለፓርላማው ሲያቀርብ፣ ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎችን አያያዝ የተመለከተ ጉዳይ ማንሳቱ አይዘነጋም፡፡

በዓመቱ በ270 ፖሊስ ጣቢያዎችና በ82 ማረሚያ ቤቶች ላይ ክትትል ማድረጉን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፣ ሰባት ሕፃናትን ጨምሮ 771 ያላግባብ የታሰሩ ዜጎችን ከእስር ማስፈታቱን ለፓርላማው ሪፖርት አድርጓል፡፡ ከዚሁ ጋር በማያያዝ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን አያያዝ በሚመለከት ጥልቅ ጥናት ለማካሄድ እንዳቀደ ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡

ኢሰመኮ መንግሥት የሕግ ማስከበር ዘመቻ መክፈቱን ይፋ ባደረገ ማግሥት ባወጣው መግለጫ የጋዜጠኞች፣ ማኅበራዊ አንቂዎችና ፖለቲከኞች እስራት እንዳሳሰበው መግለጹም ይታወሳል፡፡ ተቋሙ በመግለጫው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መንግሥት ዜጎችን ከማሰር እንዲቆጠብም ጠይቋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ተቋማትና የሕግ ባለሙያዎች ከሕግ ሥነ ሥርዓት ውጪ የሚካሄዱ እስራቶች አገርን ለአደጋ የሚዳርጉ መጥፎ ልምምዶች መሆናቸውን፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች እያወሱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በማናውቀው አካል፣ በማይታወቅ ቦታና ሁኔታ ታሰርን፣ ታፈንን ወይም ተፈታን የሚሉ ዜጎች ስሞታዎች አሁንም መቀጠላቸው ነው የሚነገረው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ፣ ‹‹ሳናጣራ ዜጎችን አናስርም›› የሚል ቃል መግባቱ አይዘነጋም፡፡ አስተዳደሩ በፖለቲካ የታሰሩ ጋዜጠኞችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንና ፖለቲከኞችን ከእስር በመፍታትም በዓለም አቀፍ ደረጃ መደነቁ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በሒደት አስተዳደሩ ለገባቸው ቃሎችና ለወሰዳቸው ምስጉን ዕርምጃዎች ተገዥ ሆኖ መቆየቱ እየተፈተነ እንደሚገኝ የሚናገሩ አሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ ያሉት የሕግ ሥነ ሥርዓትን ያልተከተሉ የሚባሉ እስራቶች ደግሞ፣ መንግሥትን የበለጠ እያስተቹ መሆኑን ነው ብዙዎች የሚያወሱት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -