Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአማራ ክልል 55 የቴሌኮም ኔትወርክ ጣቢያዎች በፀጥታና በኃይል አቅርቦት ችግር አገልግሎት አይሰጡም ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም በአማራ ክልል በዋግህምራ፣ በሰሜን ወሎና በሰሜን ጎንደር ዞኖች ካሉት 219 የቴሌኮም አገልግሎት ጣቢያዎች መካከል 55 ያህሉ፣ በፀጥታና በኃይል አቅርቦት ችግር ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ እንደተናገሩት፣ በሰሜን ጎንደር ከሚገኙ 55 የቴሌኮም ኔትወርክ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች መካከል 15 ያህሉ በፀጥታ ምክንያት፣ በዋግህምራ ከሚገኙ 40 ጣቢያዎች 20 ያህሉ በፀጥታ ምክንያት፣ እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞን ከሚገኙት 124 ጣቢያዎች 27 ያህሉ በኃይል እጥረትና በውድመት ምክንያት አገልግሎት አይሰጡም፡፡

በተጨማሪም በዋግህምራ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት 20 ጣቢያዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ፣ በጄኔሬተር አገልገሎት እየቀረበ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ኩባንያው ቀላል የሚባል የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የኔትወርክ ጣቢያዎችን እየጠገነ ወደ ሥራ እያስገባ ቢሆንም፣ ከበድ ያለ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ውስጥ በመግባት ጠግኖ ወደ አገልግሎት ለመመለስ ግን አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ይህን የተናገሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየካቲት ወር 2014 ዓ.ም. በምርጫ ክልላቸው በመገኘት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር በተወያዩበት ወቅት ከሕዝቡ በተነሱ ጥያቄዎች ላይ፣ ከአስፈጻሚ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር ሐምሌ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ውይይት ባደረገበት ወቅት ነበር፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ለአገልግሎት ከገጠማቸው 7648 የሞባይል ኔትወርክ ጣቢያዎች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑት አዋጭ እንዳልሆኑ የገለጹት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ጣቢያዎቹ አዋጭ ባይሆኑንም ማኅበረሰቡ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኝ ተብሎ የተዘረጉ በመሆኑ እነዚህን አካባቢዎች ከቀሪዎቹና አዋጭ ከተባሉት 48 በመቶ ጣቢያዎች ውስጥ ከሚገኘው ገቢ በመደጎም እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 የቴሌኮም አገልግሎት ማስፋፊያ ቀመር የሕዝብ አሰፋፈር፣ እንቅስቃሴና አዋጭነትን ታሳቢ በማድረግ ለሕዝብ ተደረሽ ለማድረግ የሚሠራ ቢሆንም ብዙ ሕዝብ በማይኖርባቸውም አካባቢዎች ዜጎች ዜጎች አገልግሎት እንዲያገኙ ሲባል የሚዘረጉ ምሰሶዎች መኖራቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ አጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽነት 99 በመቶ፣ የቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር 65.5 ሚሊዮን፣ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ቁጥር 63.4 ሚሊዮን፣ እንዲሁም የመደበኛ ስልክ ተጠቃሚ 888 ሺሕ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ በመላ አገሪቱ 360 ሺሕ አጋር የቴሌኮም አቅራቢዎች መኖራቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አክለዋል፡፡

ከተዘረጉት የሞባይል ጣቢያዎች መካከል 23 በመቶ የሚሆኑት በጄኔሬተርና በፀኃይ ብርሃን ከሚገኝ ኃይል እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች