የብሔራዊ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳና ልጃቸው አቶ ኢያሱ ምትኩ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ተብለው በተጠረጠሩበት ሙስናና በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም ወንጀል ባለፈው ሐሙስ ሐምሌ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው የተጠየቀባቸው ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት ተፈቀደ፡፡
በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እየሠራ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የምርመራ ሒደቱን ለሚያየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት እንዳስረዳው፣ አቶ ምትኩ የብሔራዊ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሲሠሩ ከኤልሻዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመመሳጠር፣ በጎዳና ያሉ ዜጎችን ለማሠልጠን በሚል ለኤልሻዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከ2006 እስከ 2012 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ 472,886,304 ብር ወጪ ተደርጎ መከፈሉን፣ የተረጂዎችን ቁጥር ከፍ በማድረግና የሌሉ ተረጂዎችን እንዳሉ በማስመሰል አገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገባችውን ከ700,200 ኩንታል በላይ የስንዴና በቆሎ፣ እንዲሁም 208 ሺሕ ሊትር የዘይትና ጥሬ ገንዘብ ከኮሚሽኑ ወጪ ተደርጎ ለኤልሻዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
መርማሪ ቡድኑ እንዳብራራው፣ ኤልሻዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከአባቱ ጋር ተጠርጥሮ በእስር ላይ ለሚገኘው በአቶ እያሱ ምትኩ ስም ሁለት ተሽከርካሪዎችን እንደገዛለትና ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በወር 15 ሺሕ ብር ቤት ኪራይ ተከራይቶለት እንደሚኖር ፖሊስ አስረድቷል። መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪዎቹ ያልተገባ ጥቅም በማግኘት ቤትና የተለያዩ ንብረቶችን ማፍራታቸውንና ምንጩ ያልታወቀ የውጭ አገር ገንዘብ በምርመራ ወቅት መገኘቱንም አስረድቷል። አገሪቱ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ላይ መሆኗ እየታወቀ ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ የውጭ አገሮች ገንዘቦችን አከማችተው በመገኘቱ ፖሊስ ምንጩን እያጣራን መሆኑን አስታውቆ፣ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ የ15 ምስክሮችን ቃል መቀበሉንና በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን አስረድቷል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ቀሪ የአሥር ምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ ግብረ አበሮችን ለመያዝና ቀሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸ አማካይነት ባቀረቡት ክርክር፣ መርማሪ ቡድኑ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ምርመራ አጠናቆና ኦዲት ተደርጎ በቂ ማስረጃ መሰብሰቡንና በሚዳያ ማሳወቁን አስረድተው፣ ተጨማሪ ማስረጃ ለመሰብሰብ 14 ቀን እንዲሰጠው መጠየቁ አሳማኝ ባለመሆኑ ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ምትኩ የተረጂዎችን ቁጥር መጨመርና የሌሉትን እንዳሉ በማድረግ የመመዝገብና የማሳወቅ ኃላፊነት እንደሌላቸው፣ ዕርዳታውንም በተመለከተ ገንዘብ ሚኒስቴር ሲፈቅድ እንጂ በእሳቸው ኃላፊነት ፍቃድ የሚሰጥ እንዳልሆነ ተናግረው፣ ከመንግሥት ተቋም የሚሰበሰብ ማስረጃን ማጥፋት ስለማይችሉ በዋስ ወጥተው ምርመራው እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
መርማሪ ቡድኑ የዋስትና ጥያቄውን በመቃወም የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
ክርክሩን የሰማው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጎ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።