Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎች የሚከፍሉት የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ ኢንዲሻሻል ጥያቄ አቀረቡ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአልኮል ፋብሪካዎች በምርትና በሽያጭ ሒደት ውስጥ እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸውን የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ እንዲሻሻል ጥያቄ ማቅረባቸው ተገለጸ፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ አማካሪ የሆኑት አቶ ዋሲሁን አባተ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የአልኮል መጠጥ አምራች ድርጅቶች ጥሬ ዕቃ ሲገዙ እንዲሁም በሽያጭ ወቅት እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸው የ80 እና 60 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ በዝቷል የሚል ጥያቄ አቅርበዋል ብለዋል፡፡

መንግሥት የአልኮል መጠጥ ምርቶች በሕዝብ ጤና ላይ የሚያመጡትን የጤና ጉዳት ከግምት በመክተት የሚከፈለውን የኤክሳይዝ ታክስ መጠን ከፍ ማለቱን ያስታወሱት አቶ ዋሲሁን፣ ያም ሆኖ የአልኮል ፋብሪካዎች በአልኮል ላይ የሚጣለው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን ከፍ ማለቱ ኅብረተሰቡ የኤክሳይዝ ታክስ ወደ ማይከፈልባቸው የባህላዊ መጠጦች እንዲያዘነብል በማድረግ ጤናውን ይጎዳል በሚል መንግሥት በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ መንግሥት ጥናት እያደረገበት ይገኛል ያሉት የታክስ አማካሪው፣ ጥናቱ እንዴት ተደርጎ የታክስ መጠኑ ይሻሻል ወይም ተመጣጣኝ ይሁን የሚለውን የሚመለከት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የኤክሳይዝ ታክስ ሕጉ ፋብሪካዎች መክፍል በሚገባቸው የታክስ ምጣኔ ላይ ግን ግልጽ ማብራሪያ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም የስኳር ፋብሪካ ኤታኖል የተባለውን ምርት ለሕክምና እንዲሁም ለአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃነት እንደሚያቀርብ የተናገሩት አቶ ዋሲሁን፣ በመሆኑም ለሕክምና ግብዓት የሚውለው ሲቀር ለአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎች በሚሸጠው ኤታኖል ላይ የኤክሳይዝ ታክስ የመከፈል ግዴታ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ በኤታኖል ግዥ ሒደት የተከፈለው ኤክሳይዝ ታክስ የማምረቻ ወጪ አንዱ ክፍል መሆኑን ያስታወቁት የታክስ አማካሪው፣ ጥሬ ዕቃውን ተጠቅመው የአልኮል መጠጦች ሲያመርቱ እንዲሁም የኤክሳይዝ ታክስ እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡

በኤክሳይዝ ታክስ አዋጁ እንደተመላከተው ማናቸውም ዓይነት ንፁህ አልኮል 60 በመቶ የታክስ ምጣኔ ሲኖራቸው ከ80 በመቶ የበለጠ ወይም ያነሰ ጥንካሬ ያለው ባህሪው የተለወጠ ኢቴል አልኮል፣ ሲቢርቶዎች፣ ሊከርስ፣ ውስኪ፣ ጂን፣ ጄኔቫ፣ ቮድካ፣ ከተብላላ የሸንኮራ አገዳ ውጤት የተገኘ ረምና ስፕሪቶች 80 በመቶ የታክስ ምጣኔ ተጥሎባቸዋል፡፡

በተያያዘም በኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ 1186/2012 የተደነገገውን የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸው ዕቃዎች ላይ የታክስ ዓይነቱ የተከፈለባቸው መሆኑን ለማረጋገጥ የሚለጠፈውን ምልክት (ቴምብር) ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ የተለያዩ አገሮችን ተሞክሮ እያጠና ይገኛል ያሉት አቶ ዋሲሁን፣ ለአብነትም በሌሎች አገሮች ዲጂታል ቴምብር (ኤሌክትሮኒክ) የሚጠቀሙ ሲሆን፣ አንዳንድ አገሮች ደግሞ የወረቀቱንና ዲጂታሉን ቀላቅለው በሥራ ላይ እንደሚጠቀሙት ተመላክቷል፡፡

ገንዘብ ሚኒስቴር ይህንን የኤክሳይዝ ታክስ ቴምብር አገልግሎትን ለማስጀመር የጨረታ ሰነድ እያዘጋጀ እንደሚገኝ በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ አማካሪው አቶ ዋሲሁን አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በኤክሳይዝ ታክስ ዙሪያ ከታክስ ከፋይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሐምሌ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ባደረገው የውይይት መድረክ ላይ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ዋሲሁን፣ ከሁለት ዓመት በፊት ሥራ ላይ የዋለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ከዚህ ቀደም የታክስ ምጣኔ የተጣለባቸውን ዕቃና አገልግሎቶች እንደገና በመፈተሽ፣ በትክክል የቅንጦት ዕቃዎች ናቸው በሚባሉ፣ የኅብረተሰቡን ጤና በሚጎዱና የማኅበራዊ ችግር በሚያስከትሉ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ እንዲጣል ተፈልጎ አዋጁ መሻሻሉን ገልጸዋል፡፡

የታክስ አማካሪ አያይዘውም መሠረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው በማይቀንስ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ እንዲጣል በማስፈለጉ ምክንያት አዋጁ መሻሻሉን ገልጸው፣ አዲሱ ኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 ያጋጠሙ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል፣ ወቅታዊና ተገቢ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች