በሕግ ከተደነገጉ ዓመታት ቢያስቆጥሩም በአፈጻጸም ተግባራዊ አልተደረጉም የተባሉት፣ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ሕጎች ክለሳ እየተደረገ እንደሆነ ታወቀ፡፡
የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ፈትያ ድደግባ ለሪፖርተር እንደነገሩት፣ በአሁኑ ጊዜ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ 208/2003 እና 395/2009 ክለሳ እየተደረገ ነው፡፡
ሁለቱን በተለይም ከትራፊክ ቅጣት አተገባበር ጋር የሚያያዙትን ሕጎች በአንድ ላይ አዳብሎ አንድ አገራዊ ሕግ ለማውጣት ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ ያስታወቁት ወ/ሮ ፈትያ፣ በዚህ ወቅት ባለድርሻ ከሚባሉት አካላት ጋር ውይይቶች በመደረግ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
አገሪቱ ለአሥር ዓመታት የሚተገበር ብሔራዊ የመንገድ ስትራቴጂ ይፋ ከማድረጓ ጋር ተያይዞ፣ ብሔራዊ የመንገድ ደኅንነት ሕጎችን የማሻሻል ሥራ አንዱ በመንግሥት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሁለቱ የትራፊክ መቅጫ ሕጎች በሥራ ላይ ቢውሉም በሚገባ ባለመተግበራቸው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ፣ ከዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ጋር ያልተስማሙ (ደረጃ ያላሟሉ) ነጥቦች ስላላቸው ጂአርኤስፒ የሚባል ዓለም አቀፍ ተቋም ድጋፍ አድርጎ ሕጎችን የመከለስ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል፡፡
የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት (ማሻሻያ) ደንብ 395/2009 የተለያዩ ድንጋጌዎችን አጠቃሎ በሥራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ከአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ አሽከርካሪ በስተቀር ማንኛውም አሽከርካሪ ተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም ሬዲዮ በእጁ ይዞ እየተነጋገረ፣ አጭር መልዕክት እየጻፈ፣ እየላከ፣ ወይም እያነበበ ማሽከርከር የለበትም የሚለው ይገኝበታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪ በሞተር ብስክሌቱ ላይ ዕቃን ለመጫን ተብሎ ከተሠራለት የዕቃ መጫኛ ሳጥን ውጪ፣ ማናቸውንም ዓይነት ጭነት መጫን ወይም ከአንድ ሰው በላይ ማሳፈር የለበትም የሚለው ሌላው የሚሻሻል ደንብ ነው፡፡
በተያያዘም የትራስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከብሉምበርግ ኢንሼቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ከተባለ ተቋም ጋር በመተባበር፣ የመንገድ ደኅንነትን ለማሻሻል አጋዥ ነው የተባለ በአሥር ዓመት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ የመንገድ ደኅንነት ስትራቴጂ ዓርብ ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በኤሊያና ሆቴል ይፋ አድርገዋል፡፡
የስትራቴጂው ዋና ግብ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት እ.ኤ.አ በ2021 ከነበረበት 4,161 እ.ኤ.አ. 30 በግማሽ መቀነስ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ የተዘጋጀው ስትራቴጂ ስድስት የመንገድ ደኅንነት ምሰሶዎችን ለማሳካት መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ የመንገድ ደኅንነት ተቋማቀዊ ብቃትና የአስተዳደር ዘዴ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ ፍጥነት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ ደኅንነቱ የጠበቀ ተሽከርካሪ፣ ደኅንነቱ የጠበቀ የመንገድ ተጠቃሚ፣ እንዲሁም ድኅረ አደጋ የሕክምና አገልግሎት ናቸው፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት በትራፊክ አደጋ በአሥር ሺሕ ተሽከርካሪዎች የሞት መጠኑ 32.6 በመቶ እንደነበር ተጠቁሞ፣ በአሥር ዓመቱ ስትራቴጂካዊ ትግበራ ወደ አሥር በመቶ ለማውረድ መታቀዱ ተገልጿል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን ባደረጉት ንግግር፣ የዓለም አቀፍ ሁኔታዎችና የኢትዮጵያን ተሞክሮ በማቀናጀት የተቀረጸው የመንገድ ደኅንነት ስትራቴጂ በመንገድ ደኅንነት ላይ ለውጥ ያመጣል ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ፊቲያ እንዳስረዱት፣ በመንገድ ደኅንነት ስትራቴጂው ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ በሆነው ለትራፊክ አደጋ መንስዔ የሆነው የአሽከርካሪነት መንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሒደት ወጥ እንዲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት ከሁለት ዓመታት በኋላ ተግባራዊ ይሆናል፡፡
የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅሶ እንዳቀረበው፣ በመንገድ ትራፊክ ግጭት ሳቢያ በየቀኑ በአማካይ ከ11 የማያንሱ ሰዎች ሕይወት የሚቀጠፍ ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም. ደግሞ 4,161 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የደኅንነት ቆብ (ሔልሜት) አለማድረግና የደኅንነት ቀበቶ ወይም የሕፃናት ግጭት መከላከያ ማቀፊያ አለመጠቀም ዋነኞቹ የመንገድ ትራፊክ አደጋ መንስዔዎች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡