Monday, April 15, 2024

በሙስና የተጠረጠሩት የምክር ቤት አባል በጉባዔ ውስጥ ራሳቸውን ተከላከሉ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ሒደት ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል በመጠርጠራቸው ያለ መከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የተጠየቀው የአዲስ አባባ ምክር ቤት አባል ሙሉቀን ሀብቱ (ዶ/ር) በጉባዔው ላይ ራሳቸውን ተከላከሉ፡፡

ዓርብ ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሦስተኛና የበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ጉባዔ ላይ ሁለተኛ አጀንዳ የነበረው በፍትሕ ሚኒስቴር ጥያቄ፣ የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ሙሉቀን ሀብቱ (ዶ/ር) ያለ መከሰስ መብት የማንሳት ጉዳይ ነው፡፡ የምክር ቤት አባሉ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በወጣው ከ14ኛ ዙር የ20/80፣ እንዲሁም ከ40/60 ሦስተኛ ዙር ዕጣ አወጣጥ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ የ‹‹ሙስና ወንጀል ተግባር›› ተጠርጥተው ነው፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር ምክር ቤቱ የአባሉን ያለመከሰስ መብት እንዲያነሳ የላከው ደብዳቤ ከተነበበ በኋላ፣ የምክር ቤት አባሉና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊው ሙሉቀን (ዶ/ር)፣ ወደ ድምፅ መስጠት ከመሄዱ በፊት በተሰጣቸው ዕድል የተጠቀሱባቸውን ጉዳዮች ለመከላከል ሞክረዋል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ፈቃዱ ፀጋ የተጻፈውና በአፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር ለምክር ቤቱ የተነበበው ደብዳቤ የሙሉቀን (ዶ/ር) ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ሲጠይቅ ስድስት ጉዳዮችን ጠቅሷል፡፡

‹‹ከፍተኛ የዳታ ማጭበርበር ተፈጽሟል›› ያለው ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ወደ ሲስተሙ እንዲገባ የተደረገው ዳታ በማንም ያልታየ ለመሆኑ ለከተማው አመራር ጭምር በኃላፊው መግለጫ የተሰጠ ቢሆንም፣ ዕጣው ከመውጣቱ በፊት ወደ ኮምፒዩተሩ የገባው ዳታ ለአምስት ጊዜ መታየቱን በቀዳሚነት አስቀምጧል፡፡

ዕጣ እንዲወጣላቸው ብቁ የሆኑ የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች ዝርዝር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቢሮው መላኩን የጠቀሰው ደብዳቤው፣ ‹‹ነገር ግን ኃላፊው 73 ሺሕ ሰዎች በድብቅ ወደ ኮምፒዩተር በመጫን የተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ 172 … እንዲደርስ ያደረጉ በመሆኑ›› ሲል ሙሉቀንን (ዶ/ር) ወንጅሏል፡፡

ይኼንንም ከቤቶች ልማት የተላከውን የተወዳዳሪዎች መረጃ ሚስጥራዊነቱ ተጠብቆ እንዲሠራ ማድረግ ሲገባቸው፣ በቀጥታ ለአልሚው በመስጠት የዳታ ማጭበርበሩ እንዲፈጸም በማድረግ እንደከወኑ ተገልጿል፡፡ 

ሙሉቀን (ዶ/ር) የሚመሩት ቢሮ ለከተማ አስተዳደሩ የሚውሉ ሃርድዌርና ሶፍትዌሮችን በወጣው ደረጃ መሠረት እንዲዘጋጁ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሶ፣ ቢሮው ግን ይኼንን እንዳልተወጣ ሚኒስቴሩ አስረድቷል፡፡ ሲስተሙን የማልማት ተግባሩ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱን ያልጠበቀና አልሚ፣ ተጠቃሚና አረጋጋጭ አካላት የሚና ክፍፍል ሳይኖር፣ ሁሉም በአልሚው በመሠራቱ ለማጭበርበር በር የከፈተ መሆኑ በደብዳቤው ላይ ተካቷል፡፡

ብቁ የሆኑ ተመዝጋቢዎች ዳታ የተጫነበት ኮምፒዩተርም አዲስና ከእጅ ንክኪ ነፃ መሆን የነበረበት ቢሆንም፣ ኮምፒዩተሩ ለሥራው የማያስፈልግ ባዕድ ሶፍትዌር ጭምር የተጫነበት የዕጣ አወጣጡን ሥርዓት በኦንላይን እንዲከታተሉ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ሶፍትዌሩ ስለደኅንነቱ ምንም ዓይነት ፍተሻ ያልተደረገበት ሆኖ እያለ፣ የምክር ቤት አባሉ ሙሉቀን (ዶ/ር)፣ ‹‹በኢንሳ ተፈትሾ ችግር እንደሌለበት ማረጋገጫ የተሰጠበት ነው፤›› በሚል የተሳሳተ መረጃ በማቅረብ አስተዳደሩን ዕጣውን እንዲያወጣ እንዳደረጉ ማረጋገጡን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ ሲያጠቃልልም የምክር ቤት አባሉ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነትን ያላግባብ በመገልገል፣ ቴክኖሎጂውን የማልማት ሒደቱን በተዛባ ሁኔታ እንዲመራ በማድረግ የፈጸሙትን የሙስና ወንጀል በምርመራ ቡድኑ ለመመርመር እንዲቻል የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብታቸው እንዲያነሱ ጠይቋል፡፡

ከዚህ ደብዳቤ መነበብ በኋላ አስተያየት መስጠት ሲጀመር የመጀመርያውን ዕድል የወሰዱት እኒሁ የምክር ቤት አባል በቅድሚያ የግል ስብዕናቸውን በመጥቀስ ተከላክለዋል፡፡ ‹‹ምስኪን ሕዝብ ቆጥቦ ቤት እንዲያገኝ ነው ፍላጎቴ፡፡ ከነበረኝ ስብዕና አንፃር የሚገልጸኝ አይደለም፣ ተፈጽሞም ከሆነ እኔም አዝኛለሁ፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ሙሉቀን (ዶ/ር)፣ ‹‹ለታሪክም መቀመጥ ስላለበት፤›› በሚል ባቀረቡት አስተያየታቸው የቢሮ ኃላፊነታቸው ስትራቴጂክ የሆነ አቅጣጫ የመስጠት እንጂ ትናንሽ ሥራዎችን የማዘዝ እንዳልሆነ ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡

‹‹ሶፍትዌሩ በኢንሳ የተረጋገጠ ነው፤›› በሚል በሐሰት ተናግረዋል በሚል የቀረበባቸውን ውንጀላ ሲከላከሉም፣ ‹‹እኔ በፕረዘንቴሽኔ በኢንሳ ተረጋገጠ ብዬ አላልኩም፡፡ ምናልባት የቪዲዮ ቅጂ ስላለ እሱን ማየት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡ ይልቁንም ኢንሳ ፈቃደኛ ዕገዛ ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልነበር አንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ የከተማዋ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አመራር በተለያዩ ጊዜያት የሶፍትዌሩንና የዕጣ ማውጣት ሒደቱ ዝግጅት ላይ የጻፏቸውን ደብዳቤዎችና ያደረጓቸውን ክትትሎች የጠቀሱት ሙሉቀን (ዶ/ር)፣ በእነዚህ ጊዜያት በፈቃድ ምክንያት ሥራ ላይ እንዳልነበሩ ተናግረዋል፡፡

የዕጣው ማውጫ ቀናት ሲቃረቡም ሶፍትዌሩ ከንቲባዋ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ባሉበት ጭምር ሙከራ እንደተደረገለት አስረድተዋል፡፡ ‹‹ባዕድ ሶፍትዌር ጭምር ተጭኖበታል›› የተባለው ኮምፒዩተር ጉዳይንም፣ ‹‹ዕጣው ከመውጣቱ በፊት ማታ ምንም ዳታ እንደሌለው ታይቶ ታሸገ፡፡ እኔ ኮምፒዩተሩ ጋር ቀርቤም አላውቅም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አንድ ክስ ሆኖ የተነሳባቸው በዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ላይ ስለሶፍትዌሩ አስተማማኝነት ያደረጉትን ንግግር በተመለከተም፣ ‹‹ለቢሮው ይመጥናል አንተ ብታቀርበው ተብዬ እናዳቀርብ ተደረገ፡፡ ፕረዘንቴሽን ላይ ያቀረብኩት የተሰጠኝን ሐሳብ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የትምህርት ዝግጅታቸው ሰላምና ደኅንነት ላይ ያተኮረ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ከሶፍትዌር ጋር በተያያዘ ያሉ ዝርዝር ነገሮችን እንደማያውቁ ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻ ላይ አስተያየት ለመስጠት ዕድል የተሰጣቸው ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ‹‹ይኼ ምክር ቤት ኃላፊነት ሲሰጣቸው እሳቸውም እኔ በዘርፉ ሙያው የለኝም ብቁ አይደለሁም ብለው አላቀረቡም፤›› ሲሉ የምክር ቤት አባሉን ሐሳብ አጣጥለዋል፡፡ አባሉ ኃላፊነት ሲሰጣቸው ከዚህ በፊት የሠሩባቸው ቦታዎችና ቀደምት የትምህርት ዝግጅቶች ከግምት ውስጥ እንደገቡ ገልጸዋል፡፡

 ሙሉቀን (ዶ/ር) ያነሷቸው የመከላከያ ሐሳቦች በማስረጃ የሚደገፉ ከሆነ በሒደቱ ላይ መታየት እንደሚችሉ የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ ምርመራ እንዲቀጥል ግን ያለመከሰስ መብታቸው መነሳት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ ‹‹ምርመራ ለማድረግ እንኳን ይኼ ከለላ መነሳት ስላለበት ነው እንጂ፣ ወንጀለኛ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው አይደለም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹ከንቲባዋ ጭምር በተገኙበት ሙከራ ተደርጓል፤›› ለሚለውም ሐሳብ ምላሽ የሰጡት ወ/ሮ አዳነች፣ ይኼም ቢሆን ፍትሕ ሚኒስቴር ቢሮው ውስጥ ዳታዎች ይታዩ እንደነበር የጠቀሰው ጉዳይ አለመፈጸሙን እንደማያሳይ ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤት አባሉ በኋላ ላይ የሚያቀርቧቸው መረጃዎች ሌሎች የአስተዳደሩ ኃላፊዎችን ተጠያቂነት የሚያሳይ ከሆነ በቁጥጥር ሥር የማዋል ተግባሩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም በተሰጠው ድምፅ በ93 ድጋፍና በስድስት ድምፀ ተዓቅቦ የምክር ቤት አባሉ ሙሉቀን ሀብቱ (ዶ/ር) ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ተወስኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -