Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የዝርፊያው መዋቅር ይመንጠር!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የ14ኛ ዙር ዕጣ ሲያወጣ የነበረው ጉሮ ወሸባዬ፣ ውሎ ሳያድር ደግሞ በዕጣ ማውጫ መተግበሪያው ላይ ተፈጸመ የተባለው የዳታ ማጭበርበር፣ ከዚያ በመቀጠል ተደረገ በተባለው ኦዲት ዕጣው እንዲሰረዝ የመደረጉ ውሳኔ የፈጠረው ግራ መጋባት ራሱን የቻለ ትራጄዲያዊ ትዕይንት ነበር ቢባል አያንሰውም፡፡ ለበርካታ ዓመታት ከፈታኙ የኑሮ ውድነት ጋር እየታገሉ ሲቆጥቡ በነበሩ የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች ላይ የደረሰው መሳቀቅና የሥነ ልቦና ጉዳት፣ ይህንን ትራጄዲያዊ ትዕይንት የክፍለ ዘመኑ አስፈሪና አስደንጋጭ ክስተት ያደርገዋል፡፡ የከተማው አስተዳደርም ሆነ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የዕጣ ስረዛውን ውሳኔና ይቅርታ መጠየቃቸውን በተመለከተ ከሰጡት መግለጫ በላይ፣ መዋቅራቸው ውስጥ የተሰገሰገውን የደለላና የዝርፊያ ቡድን በግልጽ መንጥረው በማውጣት ለሕዝብ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ዕርምጃ ከላይ ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ የሌብነት አጋፋሪዎችን በግልጽነትና በፍትሐዊነት መመንጠር ይጠበቅበታል፡፡ ሌብነትን ማጥፋት የሚቻለው ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በተግባር ሲረጋገጥ ነው፡፡

ዕጣ ከማውጣት ሥነ ሥርዓቱ ጀምሮ አጋጥሟል በተባለው ችግር ላይ እስከ ተሰጡ መግለጫዎች ድረስ የተስተዋለው ግርግር፣ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የተንሰራፋውን አደገኛ ዝንባሌ በሚገባ ያመለክታል፡፡ ለዕጣ አወጣጡ በለፀገ የተባለውን ሶፍትዌር በተመለከተ የተሰጡ ሁለት ተቃራኒ መግለጫዎች የሚሉትን ማየት ብዙ ችግሮች እንዳሉ ያሳያል፡፡ በመጀመሪያ ከሰው ንክኪ ሆኖ የተሠራው መተግበሪያ ለሕገወጥ ድርጊቶች እንደማይጋለጥ፣ አስተማማኝ፣ ግልጽና ፍትሐዊ አሠራር መዘርጋት መቻሉ ተነገረ፡፡ እንዲሁም መተግበሪያው በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ የበለፀገ መሆኑንና የፌዴራልን ጨምሮ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ይሁንታ ማግኘቱን፣ በግል ተቋማት ታዛቢዎች ጭምር የተረጋገጠ መሆኑ ተገልጾ ነበር ከንቲባዋ በተገኙበት ሥነ ሥርዓት የዕጣ አወጣጡ የተከናወነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ማጭበርበሩ መታወቁ ተገልጾ ሌላ መግለጫ ተከተለ፡፡ መተግበሪያው በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ያልተረጋገጠ፣ በግለሰቦች ግንኙነት ብቻ የተከናወነ፣ ማንም ሰው ሊያስተካክለው የሚችልና በግለሰቦች ሲነካካ እንደነበረ መረጋገጡ ተነገረ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን ሕዝብ የማይመጥንና በጥቂት ግለሰቦች የቴክኖሎጂ ውንብድና የተፈጸመበት በመሆኑ፣ ዕጣው ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ በሙሉ እንደተሰረዘ ተወሰነ፡፡

እንዲህ ዓይነቱን ውሉ የጠፋበት የብልሹ አሠራር ውጤት የሆነ አደገኛ ድርጊት ታቅፎ፣ ቀለል ባሉ መግለጫዎችና ማሳሰቢያዎች ይቅርታ ብሎ ማለፍ አይቻልም፡፡ ተመዝጋቢዎች ላባቸውን አንጠፍጥፈው በከፍተኛ ድካም የሚያገኙትን ገንዘብ ከአምሮታቸው ላይ ቀንሰው ሲቆጥቡ ኖረው፣ የተማመኑበት መንግሥት ወይም የከተማ አስተዳደር በራሱ ድክመትና ስንፍና ሳቢያ ተስፋቸው እንደ ጉም ሲበተን በቀላሉ ይቅርታ ብሎ መታጠፍ አይሞከርም፡፡ በፌዴራል መንግሥት፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መዋቅሮች ውስጥ በየጊዜው የሚስተዋሉ ነውሮች ከሚታገሱዋቸው በላይ እየሆኑ ነው፡፡ በሐሜት ደረጃ ከሚሰሙ አስነዋሪ ድርጊቶች በተጨማሪ በግላጭ በአደባባይ የሚፈጸሙ የዝርፊያ ጀብዱዎች፣ የመንግሥት አመራሮችን እንኳንስ ሥልጣን ላይ በዘፈቀደ ሊያስቆዩ በወንጀል የሚያስጠይቁ ለመሆናቸው ዋቢ መጥራት አያስፈልግም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ ክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎች ጀምሮ በየሴክተር መሥሪያ ቤቱ የሚፈጸሙ ሌብነቶች፣ ማጭበርበሮች፣ ጉቦዎች፣ የመሬት ወረራዎችና የተለያዩ ብልሹ አሠራሮች ብዙ የተባለባቸው ናቸው፡፡ ሕዝብ በትዕግሥት ዓይቶ እንዳላየ የሚያልፋቸው በርካታ እንከኖች፣ አሁን ተጠናክረው የለየላቸው ውንብድናዎች ላይ ሲደርሱ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ የግድ መሆን አለበት፡፡

አዲስ አበባን የሚያህል ትልቅ ከተማ ማስተዳደር ግዙፍ የአመራር ዕውቀት፣ ክህሎት፣ አስተዋይነት፣ ልምድ፣ ትጋት፣ ብልህነትና ሌሎች ፀጋዎችን ይጠይቃል፡፡ ከንቲባዋም ሆኑ በዙሪያቸው ያሉ አመራሮች በዚህ ደረጃ ላይ እንዲገኙ ይጠበቃል፡፡ እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብርቱ አመራር ካገኘ፣ ከሚታሰበው በላይ አስደማሚ አስተዋፅኦ ለማበርከት ወደኋላ የሚል አይደለም፡፡ ከአገሩ በፊት የሚያስቀድመው ምንም ነገር ስለሌለም ነው ባለፈው ምርጫ በዚያ ወጀብ ውስጥ ሆኖ ብልፅግና ፓርቲን የመረጠው፡፡ በቅርቡም በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተካሄዱ ሕዝባዊ ውይይቶችም አስረግጦ ያስታወቀው፣ በኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖ ልማት እንዲከናወን አመራሩ በሚፈለገው ቁመና ላይ መገኘት እንዳለበት ነው፡፡ እግረ መንገዱንም ሌብነት፣ ሥርዓተ አልበኝነት፣ ሕገወጥነት፣ ለሰላም ተፃራሪ የሆኑ ድርጊቶችና አገር አፍራሽ እንቅስቃሴዎች እንዲመክኑ ነው ያሳሰበው፡፡ ይህ ማሳሰቢያው ግን ትኩረት የተሰጠው አይመስልም፡፡ በከተማም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ነውረኞች በዝተው ዝርፊያና ማናለብኝነት ተንሰራፍተዋል፡፡ በሕግ እንደማይጠየቁ የተማመኑ የሹም ዶሮዎች በግላጭ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመዝረፍ የተነሱትም ለዚህ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሰሞነኛውን የጋራ ቤቶች ዕጣ መተግበሪያ መጭበርበር በተመለከተ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው፣ ‹‹…የሕዝብ አመኔታን መቼም ቢሆን አንዘነጋም፣ ክብራችን ሕዝብን በፍትሐዊነት ማገልገል ስለሆነ ሌቦችና እምነታቸውን ሸጠው የሚበሉ ሁሉ ለጊዜው ቢታገሉንም አያሸንፉንም፣ እውነት ምንጊዜም ታሸንፋለች…›› ባሉት መሠረት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ሹማምንትና ባለሙያዎች በተጨማሪ፣ የከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የመሸጉ የዝርፊያ ቡድኖችን ነቃቅለው ለሕግ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከራሳቸው ቢሮ ጀምሮ በተለያዩ አካላት ውስጥ የተሰገሰጉ ዘራፊዎችንና ቢጤዎቻቸውንም ማጋለጥ አለባቸው፡፡ የከተማ አስተዳደሩን በአንድ አፍ ሁለት ምላስ ያደረጉትንና አጋሮቻቸውንም የመመንጠር ግዴታ አለባቸው፡፡ ሕዝብ በችግር ጊዜ ድምፁን ሰጥቶ የመረጣቸውና ኃላፊነቱን የሰጣቸው በእምነት ስለሆነ አሠራራቸው በግልጽነት፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መርህ እንደሚመራ በአርዓያነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አዲስ አበባ ብዙ ጉዶችን የተሸከመች ታሪካዊ ከተማ ናት፡፡ በርካታ ሚሊዮን ምንዱባን መንግሥትን ተማምነው የሚኖሩባት ከተማ ደግሞ፣ የወረበሎች መጫወቻ እንዳትሆን የመከላከል ኃላፊነት የከንቲባዋና በሥራቸው የሚገኙ ተሿሚዎች ነው፡፡ መዋቅራችሁን ፈትሹና አፅዱ፡፡

በሌላ በኩል የከተማ አስተዳደሩ ከጊዜያዊ ሆይ ሆይታና ከንቱ ድጋፍ ሰጪዎች ራሱን ማፅዳት አለበት፡፡ ለከተማው ነዋሪዎች የኑሮ ዕድገት፣ እኩልነት፣ ፍትሕ፣ ሰላም፣ ነፃነትና መልካም አስተዳደር አስተዋፅኦ ሊኖራቸው የሚችሉ ባለሙያዎችንና የልምድ ባለቤቶችን ምክር ይስማ፡፡ እነዚህ ወገኖች በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች የሚያቀርቧቸውን ምክረ ሐሳቦች አስሶ በማግኘትና እነሱንም በአካል በመቅረብ ልምድ ይቅሰም፡፡ ለአገርም ሆነ ለከተማዋ የሚጠቅሙ በርካታ ምክረ ሐሳቦችን በነፃ የማግኘት ዕድል እያለ፣ በአስመሳዮችና በአድርባዮች ከንቱ ሽንገላ ብልሹ አሠራሮች ውስጥ መዘፈቅ ይብቃ፡፡ አስመሳዮችና አድርባዮች እንደ ጆፌ አሞራ የከተማ አስተዳደሩን የሚዞሩት ያልተገቡ ጥቅማ ጥቅሞችን ለማግበስበስ እንጂ፣ ለከተማዋም ሆነ ለነዋሪዎች ዕድገት አስበው እንዳልሆነ የማንም ልቦና ያውቀዋል፡፡ ከተማ የሚያድገው በዕውቀትና በአስተውሎት በሚመራ አስተዳደር እንጂ፣ ሌቦችና ዋሾዎች እንደ እንቧይ እየካቡ በሚንዱት ዝና ፈላጊ ስብስብ እንዳልሆነም ሊታወቅ ይገባል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከእንዲህ ዓይነቱ እንከን ራሱን እያፀዳ፣ የውስጡን የዝርፊያ መዋቅር ይመንጥር!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...