ቴሌና ኢንሳ ከቢሮው ፈቃድ ያላገኙትን እንዳያስተናግዱ ሊደረግ ነው
የአዲስ አበባ ከተማ አስተደዳር ትራንስፖርት ቢሮ በ2011 ዓ.ም. ወጥቶ ውዝግብ ያስነሳውን የኤሌክትሮኒክ ታክሲ ሥምሪት (ኢታስ) አገልግሎት አሰጣጥ መመርያ እያሻሻለ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የትራንስፖርት ቢሮው በመስከረም 2014 ዓ.ም. በፀደቀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚ አካላት ተግባርና ኃላፊነት መወሰኛ አዋጅ ላይ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ በከተማዋ የሚገኙ የኢታስ ማኅበራትን እንደ አዲስ እየመዘገበ ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክ ታክሲ በሚል መጠሪያ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በትራንስፖርት ቢሮው የተመዘገቡ እንዳልሆኑ ያስታወሱት የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳዊት የሺጥላ፣ ድርጅቶቹ የሚያንቀሳቅሷቸው መኪናዎች በታወቀ የትራንስፖርት ሥምሪት ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ እንደሚደረጉ አስረድተዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ቢሮው በሚሻሻለው መመርያ ለድርጅቶቹና በሥራቸው ለሚንቀሳቀሱት መኪናዎች የተለያዩ ስታንዳርዶች ያወጣል፡፡ በድርጅቶቹ ሥር ያሉ መኪኖች ከተማው በሚያስፈልገው መጠን በሚያስፈልጉበት መስመር እንዲቀሳቀሱ እንደሚደረግም አቶ ዳዊት ገልጸዋል፡፡
‹‹ከግል ዘርፉ ትርፋማነት በተጨማሪ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ክፍተት የመሙላት ኃላፊነት አለበት፤›› ያሉ ሲሆን፣ ድርጅቶቹ የከተማዋን የትራንስፖርት ፍላጎትና ከመሠረተ ልማት አቅርቦት በማየት የትራንስፖርት ፖሊሲና ስትራቴጂ በሚያወጣው ትራንስፖርት ቢሮ ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ይህ መመርያ ለመጀመርያ በ2011 ዓ.ም. ሲወጣ፣ የዚህ አገልገሎት ሰጪ ድርጅቶችና አሽከርካሪዎች ሊከተሏቸው የሚገቡ አዳዲስ ቅድመ ሁኔታዎችና አሠራሮችን አስተዋቅቆ የነበረ ቢሆንም ከድርጅቶቹ ተቃውሞ ደርሶበት ነበር፡፡
መመርያው አገልግሎት መስጠት የሚችሉ መኪኖችን መሥፈርት ሲዘረዝር፣ በቀላሉ እንዲለዩ ነጭና ሰማያዊ ወይም ቢጫና በአረንጓዴ ቀለም መቀባት እንዳለባቸውና ሰሌዳቸውም ኮድ-1 ሊሆን እንደሚገባ ደንግጓል፡፡
የኢታስ አገልግሎት ሰጪ የሆኑ ድርጅቶች ደግሞ ፈቃዳቸውን በከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ መውሰድ እንዳለባቸው፣ ፈቃድ ለመውሰድም የድርጅቶቹ የመረጃ ቋት (Data Base) ያለው በኢትዮጵያ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው ተደንግጓል፡፡
በተጨማሪም ድርጅቹ የመተግበሪያ ሥርዓታቸውን የከተማዋ ትራንስፖርት ባለሥልጣን እንዲያየው በሚያስችል መንገድ (Read Only Access) በማድረግ ሊከፍቱ እንደሚገባ መመርያው ደንግጎ ነበር፡፡ ይህም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የመኪኖችን እንቅስቃሴ እንዲከታተል ያስችለዋል፡፡
ድርጅቶቹ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ካወጣው ታሪፍ በላይ እንዳያስከፍሉም መመርያው ይከለክላል፡፡ ይህ መመርያ ይፋ ሲደረግ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ከፍተኛ ተቃውሞ ያሰሙት ሲሆን፣ ብዙም ሳይቆም በመመርያው ውስጥ ያሉ ድንጋጌዎች ተግባራዊነቱ ተገትቷል፡፡ ድርጅቶቹም በመመርያው ላይ ያሉትን ቅድመ ሁኔታዎችና አሠራሮች ተግባራዊ ሳያደርጉ ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ይርጋዓለም ብርሃኔ፣ ‹‹አብዛኛዎቹ በእኛ ሥር የተመዘገቡ አይደሉም፣ የእኛ ዕውቅናና ፈቃድ ያላቸው አይደሉም፤›› ካሉ በኋላ፣ ድርጅቶቹ ቢሮው በሚያወጣው ስታንዳርድ መሠረት ተመዝግበው እየሠሩ መሆናቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት እየዘረጋ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አቶ ይርጋዓለም እንደሚያስረዱት፣ ድርጅቶቹ ከዚህ ቀደም ንግድ ፈቃድ ካወጡ በኋላ ለስልክ ጥሪ ማዕከል ከኢትዮ ቴሌኮም ፈቃድና ተግባራዊ ስለሚያደርጉት ያዘጋጁት ሶፍርትዌር፣ የኤሌክትሮኒክ ሥርዓትና ዳታ ቤዛቸውን ደግሞ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) በማስፈተሽ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ድርጅቶቹ በከተማዋ የትራንስፖርት ዘርፉን ወደሚመራው ቢሮ የሚመጡበት አካሄድ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
‹‹እነዚህ ተቋማት የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ ፈቃድ ሳይኖር እንዳያድሱም፣ እንዳያስተናግዱም ደብዳቤ ጽፈን ተግባብተናል፤›› ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ይህ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠው የትራንስፖርት ሥርዓቱን ከሚመራው ተቋም ይሁንታና ፈቃድ ያገኙ መሆናቸውን ግን ማረጋገጥ ያለባቸው በመሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አቶ ይርጋዓለም፣ ቢሮው በመመርያው ላይ የሚደርጋቸው ማሻሻያዎች ምን ዓይነት እንደሆኑ ከመናገር የተቆጠቡ ሲሆን፣ ማሻሻያ ለማድረግ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናት እያጠናቀቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የወዝ ራይድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ናርዶስ አዲስ፣ ቢሮው እነዚህን ድርጅቶች በሥሩ ለማድረግ እየዘረጋ ያለው ሥርዓት በሌሎች አገሮችን የተለመደ መሆኑን ገልጸው፣ ለዘርፉ ስታንዳርድ ለማውጣት መታሰቡንም እንደሚደግፉ ጠቁመው፣ ‹‹በስታንዳርዱ ምክንያት ከገበያው የሚወጡ መኪኖች ሊኖሩ ይችላሉ፤›› የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
መመርያው ሲሻሻል ወደፊት የሚመጡ ድርጅቶች ለመምራት የሚያስችል ቢሆንም፣ ቀድመው በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በመመርያው ልክ እንዲሆኑ ማድረግ ቀላል እንደማይሆን አስረድተዋል፡