Saturday, May 25, 2024

ፍትሕ ሚኒስቴር የስልጤ ዞን አመራሮችን የፀጥታ አካላትንና ፍርድ ቤትን ወቀሰ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን በተለይም በወራቤ ከተማ በተፈጸመው ‹‹ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት›› ላይ ምርመራ ያደረገው የፍትሕ ሚኒስቴር፣ በግጭቱ አፈጻጸም፣ ምርመራና የፍትሕ ሒደቶች ላይ የዞኑን አመራሮች፣ የፀጥታ አካላትንና ፍርድ ቤትን በወንጀል ተባባሪነት ወቀሰ፡፡

ሚኒስቴሩ በተለይ በዞኑ የሚገኘውን ፍርድ ቤት፣ ‹‹ፍፁም ገለልተኛ መሆን ያቃተው›› በሚል የገለጸ ሲሆን፣ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችን ሆን ብሎ በዋስትና እንዲለቀቁ ማድረጉን በመጥቀስ ወቀሳውን አሰምቷል፡፡

በዞኑ የተከሰተው ግጭት ሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰው ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት ቅጥያ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ በጎንደር ከተማ ግጭቱን ለመመርመር ባደረገው ጥረት፣ ከእስልምናም ሆነ ከክርስትና ሃይማኖት አባቶች በአግባቡ ድጋፍ እንዳላገኘና በአንዳንድ ቦታዎች ለምርመራ ቡድኑ ቃል እንዳይሰጥ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበር አስታውቋል፡፡ በዚህም የተነሳ ምርመራው በዕለቱ የደረሰውን ጉዳት በሙሉና እያንዳንዱን ተደርሶበታል በማያስብል ሁኔታ የተጠናቀቀ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር እነዚህን ወቀሳዎች ያቀረበው በጎንደርና በስልጤ ዞን የተነሱ ‹‹ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች››፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ የተነሳውን ‹‹ማንነትን መሠረት ያደረገ ግጭት›› አስመልክቶ ስለተደረጉ ምርመራዎች፣ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን ሐሙስ ሐምሌ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ነው፡፡

በሚኒስቴሩ በኩል መግለጫውን የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ፈቃዱ ፀጋ፣ መጀመሪያ ጎንደር ቀጥሎም ወደ ስልጤ ዞን ለተዛመተው ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት መነሻው፣ በሐጂ ኤልያስ መካነ መቃብር ይፈጸም የነበረው የሼኽ ከማል ለጋስ ቀብር መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

መካነ መቃብሩ አበራ ጊዮርጊስ ከሚባል ቤተ ክርስቲያን ጋር እንደሚጎራበት ገልጸው፣ በቤተ ክርስቲያኑ የነበሩ የአብነት ተማሪዎች ‹‹ድንበር ሊያካልሉ ነው›› በሚል ለቀብሩ ድንጋይ ሲወስዱ በነበሩ ሰዎች ላይ ድንጋይ መወርወራቸውን፣ የቤተ ክርስቲያኑ ጥበቃ የሆኑ ግለሰብ ደግሞ ጥይት ወደ ሕዝቡ በመተኮስ ቦምብ እንዲወረወር ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በሥፍራው የሦስት ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ማለፉን አስረድተዋል፡፡

በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ በተጀመረው ግጭት የሞቱ ሰዎች ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲቀበሩና በተከታታይ ቀናት መቀጠሉ ተገልጿል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው፣ ‹‹ግጭቱ ወደ ከተማ ከሄደ በኋላ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የእስልምና እምነት ተከታዮችን የማምለኪያ ቦታ፣ የንግድ ቦታና የመኖሪያ ቤት በመምረጥ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች ደግሞ አፀፋ መልስ በሚሆን መንገድ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የንግድ ድርጅቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የምርመራ መዝገቦቻችን ያስረዳሉ፤›› ብለዋል፡፡

በጎንደሩ ክስተት 20 ሰዎች መሞታቸውንና ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ 250 የሰው ምስክሮች ከተሰበሰቡ በኋላ፣ በ69 የተያዙና በ34 ያልተያዙ ሰዎች ላይ ክስ መመሥረቱን አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡

የጎንደሩን ክስተት የተከተለው የስልጤ ዞን ግጭት ሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት ላይ በአንድ አሰጋጅና በአንድ ዑስታዝ አማካይነት ቅስቀሳ እንደተፈጸመ የገለጹት አቶ ፈቃዱ፣ ‹‹ጎንደር የፈሰሰው ደም እናንተ ልትበቀሉት የሚገባ ነው፤›› የሚልና ተመሳሳይ ቅስቀሳዎች ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በማግሥቱም በትምህርት ቤቶች ‹‹መስጊድ ተቃጥሏል›› የሚል ወሬ በመሠራጨቱ ወደ ብጥብጥ መገባቱን አስረድተዋል፡፡

በእነዚህ ቅስቀሳዎች የተነሳሱ ሰዎች በወራቤ ከተማ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ላይ ውድመት ማድረስ ሲጀምሩ፣ በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ደግሞ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን እየተቃጠለ ነው፤›› ብለው በመምጣታቸው ብጥብጡ መባባሱን አቶ ፈቃዱ አውስተዋል፡፡ ቀጥሎም በአካባቢው ያለ መስጊድም ሊቃጠል ነው ከሚል የአደጋ ጊዜ ‹‹የአዛን ድምፅ›› በማሰማቱ፣ የበለጠ የሰው ቁጥር እንዲመጣ መደረጉንና ቤተ ክርስቲያኑ ላይ ቤንዚን ተርከፍክፎ ሙሉ ለሙሉ መቃጠሉን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በስልጤ ዞን አራት የኦርቶዶክስና ሦስት የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያኖች መቃጠላቸው ተገልጿል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው፣ ‹‹በዚህ መዝገብ 97 ሰዎች ላይ ክስ መሥርተናል፡፡ ከዚህ ውስጥ በእኛ እጅ ያሉት አሥር ብቻ ናቸው፡፡ 21 ሰዎች አስቀድመን ይዘን በተለያዩ ምክንያቶች ተፈተዋል፤›› ካሉ በኋላ፣ ሚኒስቴሩ ከእነዚህ ክስተቶች ጋር በተያያዙ የወንጀል ምርመራዎች ላይ ያገጠሙትን ችግሮች ገልጸዋል፡፡

የስልጤ ዞን ከዋና አስተዳዳሪው ጀምሮ ያሉ አመራሮች የፌዴራል መንግሥት የምርመራ መዋቅር ወንጀሉን ለመርመር መግባቱን መቃወማቸውን፣ በሒደቱም ለምርመራው ተባባሪ እንዳልሆኑ አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡

‹‹ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታ በተለይም ወራቤ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል በቦታው የነበረው የፀጥታ መዋቅር ሰዎች ድርጊቱን ለማስቆም ፍፁም ፈቃደኛ ያልነበሩ፣ ጥረት ያላደረጉ፣ በቦታው ቆመው እንደ ታዛቢ ሲያዩ እንደነበሩ የምርመራ መዝገባችን ያሳያል፤›› በማለትም የፀጥታ መዋቅሩን ተችተዋል፡፡ በመጠርጠራቸው ክስ የተመሠረተባቸው፣ ነገር ግን በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ሰዎችን በተመለከተም፣ ‹‹አሁንም ከተማው ውስጥ እንደ ልባቸው እየተንቀሳቀሱ የዞኑ የፀጥታ መዋቅር ለመያዝ ፈቃደኛ አለመሆኑን ተረድተናል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ፈቃዱ በምርመራው ሒደት የጊዜ ቀጠሮ የሚሰጠውን ፍርድ ቤት፣ ‹‹ፍፁም ገለልተኛ መሆን ያቃተው›› በማለት ወቅሰው፣ ‹‹በንብረት ማውደም፣ ቤተ ክርስቲያንን በሚያህል ቃጠሎና የሰው ሕይወት ባለፈበት የተጠረጠሩ ሰዎች፣ በዋስትና ሆነ ተብሎ የተለቀቀበትና የወንጀሉ ተባባሪ የሆነበት፣ የመንግሥት የፍትሕ ሥርዓት መዋቅሩ ወንጀሉን የደገፈበት ሆኖ ያገኘንበት ቦታ ነው፤›› በማለት ቅሬታ አሰምተዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው መሥሪያ ቤታቸው በዞኑ ባካሄደው የምርመራ ሒደት ላይ በመንግሥት መዋቅር ካጋጠሙት ችግሮች ‹‹የከፋው›› ሲሉ የገለጹት የፍርድ ቤቱን ሁኔታ ሲሆን፣ ሰው የሞተበት ወንጀል ዋስትና የሚያስከለክል ስለመሆኑ ጭምር እየታወቀ ተጠርጣሪዎች የመለቀቃቸውን ጉዳይ ደጋግመው አንስተውታል፡፡ 97 ሰዎችን መጀመርያ ከተያዙት 31 ሰዎች ውስጥ 21 በዋስ እንዲወጡ መደረጉን ተቃውመዋል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ወለጋና ጋምቤላ ክልልን ጨምሮ ወንጀል በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ምርመራ እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ፈቃዱ፣ ‹‹ለምርመራው በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር የማያግዝ፣ የማይተባብር፣ ኅብረተሰቡም ደግሞ ኩርፊያ ውስጥ ሳይገባ የማያግዝ፣ የማይተባበር ከሆነ ወንጀልን በአግባቡ መርምሮ ዳር ማድረስ ፈተና እንደሚሆን መታወቅ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -