Sunday, May 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤሌክትሪክ ታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ ጥናት እየተደረገ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሁን በሥራ ላይ ያለውን ታሪፍ በማሻሻል፣ ከወቅቱ የዋጋ ንረት ጋር ሊሄድ የሚችል አዲስ ታሪፍ ለማውጣት ጥናት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በ2010 ዓ.ም. የፀደቀውና አሁን በሥራ ላይ ያለው የኤሌክትሪክ ታሪፍ መጀመሪያ ሲወጣ በወቅቱ ከነበረው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ጋር ታሳቢ በማድረግ የተደረገ ጭማሪ ቢሆንም፣ አሁን ገበያ ውስጥ ያለው የግብዓት የዋጋ ንረት በታሪፍ ላይ ማስተካከያ ለማድረግ እንዳስገደደ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙወርቅ ደምሴ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አቶ ብዙወርቅ እንደሚሉት በ2010 ዓ.ም. የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ በኑሮ ውድነቱ እየተዋጠ በመሆኑ፣ በቀጣይ ለሚታሰቡ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች የታሪፍ ማሻሻያው በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ተቋሙ በአገልግሎት አሰጣጡ ዙርያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ያግዘኛል በማለት በአራት ዙር በአራት ዓመታት እንዲጠናቀቅ ተደርጎ በ2010 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው የታሪፍ ማስተካከያ፣ በታኅሳስ 2014 ዓ.ም. የመጨረሻ ዙር የሆነውን ጭማሪ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በተለይም በ2013 ዓ.ም. እየተገባደደ ባለው በ2014 ዓ.ም. እየታየ ያለው የዋጋ ንረት የሚገመት እንደነበር አለመሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ በመኖሩ ምክንያት የኃይል ቆጣቢና መቆጣጠሪያ መሣሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ ገዝቶ ለማስገባት ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች በማስፈለጉ፣ የታሪፍ ማስተካከያው በከፍተኛ ሁኔታ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በዓለም ላይ ካለው የፖለቲካና የገበያ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት በመፈጠሩና ከኤሌክትሪክ ከደንበኞች የሚሰበሰበው ወርኃዊ ታሪፍ አገልግሎቱን አሻሽሎ ለማቅረብ በቂ ባለመሆኑ፣ ወቅቱን የጠበቀ የታሪፍ ማሻሻያ በማድረግ የግብዓት ዕቃዎችን በመግዛት ለኅብረተሰቡ መብራት እንዳይቆራረጥ የመልሶ ግንባታና የማስፋፊያ ሥራዎች አሉብን ብለዋል፡፡

በነዳጅ ዋጋ ላይ በየወሩ የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚደረገው ሁሉ፣ በኤሌክትሪክ አገልግሎትም ወቅቱን የጠበቀ ማሻሻያ በማድረግ የመልሶ ግንባታና ማስፋፊያ ሥራን ማከናወን እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዋጋ ንረቱ ምክንያት ወቅቱን የጠበቀ የታሪፍ ማሻሻያ ለማድረግ አዲስ የታሪፍ ፕሮፖዛል እየተዘጋጀ እንደሆነ የገለጹት አቶ ብዙወርቅ፣ በቀጣይ ፕሮፖዛሉ እንደተጠናቀቀ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ከፀደቀ የታሪፍ ማስተካከያው ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹የታሰበው የታሪፍ ማስተካከያ ተቋሙን ከገጠመው የግብዓት ዕጦትና ለወደፊት መድረስ አለብኝ ብሎ ከያዘው ዕቅድ ጋር ተያይዞ ብዙ ኢንቨስትመንት ስለሚፈልግ ይህን ማድረግ ግድ ይለናል፤›› ሲሉ አቶ ብዙወርቅ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ካሉት አጠቃላይ 4.2 ሚሊዮን ደንበኞች መካከል አንድ ሚሊዮን ደንበኛ ባለፉት አራት ዓመታት የተተገበረው የታሪፍ ማሻሻያ እንደማይመለከታቸው የገለጹት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የደንበኞቹ አጠቃቀም ከ50 ኪሎዋት ሃወር በታች በመሆኑ መቶ በመቶ በመንግሥት ድጎማ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

‹‹እስከ ኅዳር 2014 ዓ.ም. ድረስ ከዚህ በፊት ፀድቆ ወደ ሥራ የገባውን ታሪፍ እየተገበርን ነው፡፡ ነገር ግን ከታኅሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ወዲህ ግን የፀደቀ ታሪፍ ባለመኖሩ አሁን በዝግጅት ላይ ያለው የታሪፍ ማሻሻያ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቀርብና ወደ ሥራ እንዲገባ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ካሉት አጠቃላይ 4.2 ሚሊዮን ደንበኞች መካከል አንድ ሚሊዮን ደንበኞች ባለፉት አራት ዓመታት ከተተገበረው የታሪፍ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ፣ አጠቃቀማቸው ከ50 ኪሎዋት ሃወር በታች በመሆኑ መቶ በመቶ ለድጎማ አገልግሎት እየተሰጠ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ በኑሮ ውድነቱ እየተዋጠ በመሆኑ በቀጣይ ለሚታሰቡ የመልሶ ግንባታና የማስፋፊያ ሥራዎች የታሪፍ ማሻሻያው በጣም አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሁንም በአፍሪካ በትንሽ ታሪፍ አገልግሎት የሚያቀርብ በመሆኑ ተቋሙ ቆሞ እንዲሄድ ከተፈለገ ወቅቱን የጠበቀ የታሪፍ ማሻሻያ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት በአፋርና በአማራ ክልሎች 200 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት እንደወደመ፣ ተቋሙ በአጠቃላይ ከ2.6 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት አክለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከመንግሥት በየዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ብር እየተመደበለት የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን የበጀት መጠኑ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር በመውረዱ አገሪቱ የምታስበውን ዕድል ለማሳካት በታቀደው ልክ መሄድ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች