በለምለም መስክ ላይ ብዙ ልጆች ይጫወታሉ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ተለይቶ ይሮጣል፡፡ እማሆይ በመቋሚያቸው እየተደገፉ ሲያዘግሙ ከሩቅ ታይተውታል፡፡ የሚወዳቸው አያቱ ናቸው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን መመለሳቸው ነበር፡፡ ተንደርድሮ አንገታቸው ላይ ይጠመጠምና ይስማቸዋል፡፡ እርሳቸውም አበባ መሳይ ጉንጮቹን አገላብጠው ከሳሙ በኋላ ዳቦ ያመጡበትን ቅርጫት እንዲይዝላቸው ሰጥተውት ጉዞው ወደ ቤት ይቀጥላል፡፡ ልጁ ወዲያው ጥያቄውን ያቀርባል፡፡ ‹‹እማዬ እስኪ ንገሪኝ አባ ክርስቶዶሉ ዛሬ ምን አስተማሩ?›› የደብሩ አለቃ ስም መምህር ገብረ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህኛውን ስም ያወጣላቸው ተማሪ ነው፡፡ የሚናገሩት የምሁራን ቋንቋ ከሰፊው ሕዝብ ሕይወት ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑን ለማጥላላት በማሰብ፡፡ ‹‹አልያዝኩትም እንጂ ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገር ተናግረዋል›› አሉ እማሆይ ጥያቄውን ሲመልሱ፡፡ ልጁ እንደገና ‹‹አዬ የእማ ነገር ተጨባጭ የምትይዥው የምታስቀሪው ነገር የማታገኚ ከሆነ ለምን በየጊዜው ትመላለሻለሽ?›› አለ ጠንከር ባለ ድምፅ፡፡ እማሆይ ቆም ብለው እጃቸውን በመዘርጋት ‹‹ነገሩ እሱን የያዝከውን ቅርጫት የሚመስል ነው፡፡ ለውሃ መቅጃ አይሆንም፡፡ ከላይ ሲጨምሩበት ከታች ይፈሳል፡፡ ነገር ግን ውሃው በየጊዜው ባለፈበት መጠን ቅርጫቱ ይጸዳል፤ አቧራው ስለሚወገድ፡፡ የሰውነትም ነገር እንደዚሁ ነው፡፡ ጥሩ ነገር ሰምቶ ወዲያውኑ ቢረሳም ለቅፅበት ያህል ወደ ንጹሕ ቦታ ይሻገራል፡፡ ስለዚህ እንደገና መስማቱ መድገሙ ይበጃል፡፡
- እጓለ ገብረ ዮሐንስ (ዶ/ር) ‹‹ብፁዓን ንጹሐነ ልብ›› (2005)