Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊክረምትና የጎዳና ላይ ነዋሪዎች

ክረምትና የጎዳና ላይ ነዋሪዎች

ቀን:

ችግር የጣላቸው ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ የአዕምሮ ታማሚዎችና አካል ጉዳተኞች  ጎዳና ላይ ኑሮቸውን ካደረጉ ሰነባብተዋል፡፡

በቆሻሻ ገንዳ ትቦ ውስጥ፣ በመንገድ አካፋይ ሥር፣ በየአጥር ጥግ የሚኖሩ፣ ምግባቸውን የማያገኙ፣ የነተበ ጨርቅ ለብሰው ራሳቸውን ንቀው የሚኖሩ፣ ቢታመሙ አስታማሚም ሆነ ሕክምና የማያገኙ፣ ቤተሰብ፣ ምግብ፣ ትምህርትና ማደሪያ ቅንጦት የሆነባቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡

ችግራቸውን ለመርሳት ለተለያዩ ሱሶች የተጋለጡ ከመሆናቸው በበለጠ፣ ክረምቱ ሐዘን፣ ረሃብና ብርድ ሆኖባቸዋል፡፡

ወደ አዲስ አበባ ከብዙ ከተሞች እየተመሙ የመጡ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ከበጎ ፈቃደኞች፣ ከድጋፍ ሰጪ አካላትና ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚገባ፣ እየተሠራ እንደሆነም የሚገልጹ ጥቂቶች ባይሆኑም ችግሩ ዛሬም አፍጥጦ ይታያል፡፡

ጎዳና ተዳዳሪዎች ተለውጠው፣ ለራሳቸውም ሆነ ለአገርም የሚጠቅሙ ዜጎች ከማድረግ አንፃር ለዓመታት እየተሠራ ነው ቢባልም፣ ችግሩን ማስወገድ አልተቻለም፡፡ ዛሬም በተለያዩ ችግሮች፣ ግጭቶችና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ አዲስ አበባ ደርሰው የጎዳና ሲሳይ የሆኑ አሉ፡፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ ሥፍራዎች ተዘዋውረን ያየነውም፣ በተለይ በዚህ በቅዝቃዜ ወቅት በርካታ ጎዳና ተዳዳሪዎች በችግር ውስጥ መዘፈቃቸውን ነው፡፡

ማለዳ ላይ ከአሥር ያላነሱ ታዳጊዎች ተደራርበው ተገኝተዋል፡፡ በጠዋቱ ዝናብና ቅዝቃዜው ያየለ ቢሆንም፣ እነዚህን ታዳጊዎች ጎዳና ላይ እንቅልፍ ከመተኛት አልከለከላቸውም፡፡ ከእነዚህ ታዳጊዎች ውስጥ ልጅነታቸውን ያልጨረሱ ሴቶች ልጅ ታቅፈው ጥጋቸውን ይዘው ኩርምት ብለዋል፡፡

ከላይ ዝናብ ከሥር ጎርፍ የሚያልፍባቸው ጎዳና ተዳዳሪዎች ብርዱን ለማምለጥ የተለያዩ ሱስ አምጪ ነገሮችን እንደሚስቡም ከአንደበታቸው ሰምተናል፡፡

አንዳንዶች ደግሞ ሆነ ብለው ጥፋት በማጥፋት እስር ቤት እንደሚገቡ የሚናገሩ ሲሆን፣ ሕፃናት (ታዳጊዎች) ከሆኑ ስለማይታሰሩ ይህኛው ዕድል እንደሚያመልጣቸው ተናግረዋል፡፡

ዝናብና ብርድን ለመከላከል ማስቲሽ እንደሚስቡ፣ ሊነጋጋ ሲል የማስቲሹ ድንዛዜ እየለቀቀ ሲሄድ ብርድ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡

ዋለልኝ ደሳለኝ ከአላማጣ እንደመጣ ይናገራል፡፡ ዕድሜውን በቅጡ የማያውቀው ታዳጊ፣ ወደ ከተማው (ቀዬው) መመለስ እንደሚፈልግ ነግሮን ነበር፡፡ ይህንን የነገረን ታዳጊ ዋለለልኝ ጠዋት ሲሆን፣ ከሰዓት ወደሚገኝበት ሥፍራ ሄደን መመለስ ትፈልጋለህ እናመቻችልህ? ተብሎ ሲጠየቅ እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡

ጠዋት ላይ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት ማስቲሽ ያልሳበ ሲሆን፣ ከሰዓት ማስቲሽ በመውሰዱ ሲዘበራረቅበት ለመታዘብ ችለናል፡፡

እንደ አብዛኛው ጎዳና ተዳዳሪ ለምኖ በሚያገኘው ሳንቲም ለዕለት ጉርሱና ለማስቲሽ መግዣነት እንደሚጠቀም ይናገራል፡፡

በኢትዮጵያ በአሥራ አንድ ከተሞች 88,960 ጎዳና ተዳዳሪዎች ያሉ መሆናቸው፣ 50,000 ያህሉ በዋና ከተማዋ ጎዳናዎች እንደሚኖሩ ከዚህ ቀደም የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

 ቦሌ መድኃኔዓለም፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ፣ ኮሜርስ፣ መስቀል አደባባይና ፒያሳ አካባቢዎች  የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚበዙበት ነው፡፡ መኪኖች የትራፊክ መብራት በያዛቸው  ቁጥር ልመና አሊያም መስታወት ጠርገው ብር የሚጠይቁ የጎዳና ልጆች ማየት የተለመደ ነው። ከመኪና ውስጥ ንብረት መንትፈው የሚሮጡም አሉ፡፡

ምክንያቱ ብዙ መሆኑ የሚነገርለትን የጎዳና ሕይወት፣ የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት፣ ድህነት፣ አለማወቅና ሌሎች ምክንያቶች እንዳባባሱት ይታወቃል ።

ታዳጊዎቹን ከጎዳና ሕይወት ለማውጣት ሥራዎች ቢሠሩም፣ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ነው፡፡ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል  የተጀመረው ፕሮጀክትም ለዚህ ማሳያ ነው፡፡  

ለጎዳና ሕይወት ተጋላጭ ከሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች ወጣቱ ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዝ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ለጎዳና ሕይወት ተጋላጭ የሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች አምራች የሚባሉት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ክልል ያሉት ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።

በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ መፍትሔ ያልተገኘለት ችግር መሆኑን፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ ሥራዎች ቢሠሩም ዛሬም ሥር ነቀል ዕልባት ላይ አለመደረሱን መታዘብ ይቻላል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2014 በጀት ዓመት 20,993 ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ማንሳቱን መግለጹ ይታወሳል፡፡

በዚህም 6,267 ሕፃናት፣ 6,083 እናቶች ከልጆቻቸው ጋር፣ 4,107 አረጋውያንና 4,107 ጎልማሶች (ወጣቶች) ከጎዳና ላይ ማንሳቱን ጠቁሟል፡፡

ሚኒስቴሩ ለጎዳና ተወዳዳሪነት የሚያጋልጡ ችግሮችን ከምንጩ ለማድረቅ ከሚመለከታቸው አካላትና ማኅበረሰቡ ጋር እየሠራ እንደሚገኝ፣ ዜጎቹን ከጎዳና ላይ ለማንሳት የዓለም ባንክ፣ አገር በቀል ተራድዖ ተቋማት መተባበራቸውን ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...