Monday, May 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በየጊዜው ለሚፈጠረው አሰቃቂ ግድያ ተጠያቂው ማን ነው? መፍትሔውስ?

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ጥንትም ሆነ ዛሬ እዚህም እዚያም ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ ይገደላል። የጦር መሪ ነው የሚባለው ሰው ከተማረከ በሕይወቱ እያለ በፈረስ ጫካ ለጫካ  ይጎተት ነበር። በአዳራሽ ቤት የታጨቁ እስረኞች እሳት እየተለቀቀባቸው ይገደሉ ነበር። የአንድ መንደር ነዋሪ እስከ ከብቱና ንብረቱ እንዲያልቅም በጦር ተከቦ የእሳት ሰደድ ይለቀቅበት ነበር።

ወደ እሩቁ 300 ዓመታት ወደ ወሰደው የእርስ በርስ መጨፋጨፍ ታሪካችን መሄድ በእጅጉ አዳጋች ቢሆንብን ከ1983 ወዲህ ያለውን በተለይም እስከ 1985  የነበሩትን ዓመታት ብንመለከት የመገናኛ ብዙኃን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች፣ የዳያስፖራዎች ዕይታ ባለማግኘታቸው በእጅጉ ጭንቀትን የሚያስከትሉ ግጭቶችና ግድያዎች ተፈጽመው እናገኛለን።

ከነዚህም መካከል በሥልጣን ግጭት ምክንያት በበደኖና በወተር (ምሥራቅ ሐረርጌ) ያለቀው ሕዝብ እስካሁን ቁጥሩ በትክክል አይታወቅም፡፡ በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን የቀረበውም የመንግሥትን አቋም የሚያንፀባርቅ ነበር። አንዳንዱም መጥፎውን ጥሩ፣ ጥሩውን መጥፎ አድርጎ ዘግቧል። የሚነገረው እውነት ስለመሆኑም በወቅቱ የታተሙትን ጋዜጦችና መጽሔቶች አገላብጦ ማየት ይቻላል። ለማንኛውም ከላይ የተጠቀሰው በመረጃ የተደገፈ መሆኑን ለማሳየት የተወሰኑትን እንደሚከተለው እንመልከታቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ጥር 14 ቀን 1984 ዓ.ም. ባካሄደው 32ተኛ መደበኛ ስብሰባው በኦነግ (የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር) እና በቤህነን (በቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃ አውጭ ንቅናቄ) ግጭት ምክንያት በርካታ ሰዎች ሞተው እንደዚህ ያለው ችግር ሌላ ጊዜ እንዳይፈጠር ምን መደረግ እንዳለበት ተነጋግሯል፡፡

ምክር ቤቱ ከዚህም በተጨማሪ በተጠቀሰው ዓመት ሚያዝያ 13 ቀን ባካሄደው 40ኛ መደበኛ ስብሰባው ኦነግ በበደኖ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ በወተር፣ ኦነግ በየም ላይ ስለፈጸሙት ግድያ በሰፊው ተወያይቷል፡፡ ክርክሩም ከፍተኛ ነበር፡፡ ጉዳዩ እንዲጣራም ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡

እንዲሁም ምክር ቤቱ ግንቦት 6 ቀን ባካሄደው 42ኛ መደበኛ ስብሰባም ቤህነን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በሰፋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ማካሄዱን በሚመለከት ተወያይቷል፡፡ ያኔ ያልተጣሩ መረጃዎች እንዳቀረቡት  በአንድ ሌሊት የ500 ሰፋሪዎች ቤቶች የዶግ አመድ ሆነዋል። ቁጥሩ ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል፡፡ ይህም በቅርቡ የቅማንንቶች መኖሪያዎች የዶግ አመድ እንደሆኑት ሁሉ ማለት ነው። በዚያው ዓመት ሰኔ 30 ቀንና ሐምሌ 2 ቀን በርካታ ከኤርትራ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን  በስድስት ኪሎ አካባቢ ተሰባስበው ከተማ»ቱን አስጨንቀዋት ነበር፡፡

ምክር ቤቱ ሐምሌ 23፣ 28 እና 30 ቀን 1984 ዓ.ም. ባካሄደው 50ኛ መደበኛ ስብሰባው በወላይታ ሶዶ በአረካ ከተማ ብዙ ሰዎች (ከወላጆቻቸው ጋር ወደ ገበያ ታዝለው ወይም ተጎትተው የመጡ ሕፃናት)፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አቅመ ደካሞችና ከብቶች ተገድለዋል።

በጋምቤላ በርካታ ሰፋሪዎች አልቀዋል። በዚህ ጊዜ ለጭፍጨፋው የተሰጠው ምክንያት ‹‹ትግሬዎችና አማራ ሰፋሪዎች ዛፎቻቸውን በገፍ ስለቆረጡባቸው ሲሆን ጋምቤላዎች ደግሞ ዛፍ ማለት ሕይወት ነው፤›› የሚል ነበር። ያኔ ታዲያ ዛፍ ቢቆረጥ ዛፍ ይተካል፣ ሺሕ ዛፍ ከተቆረጠ 10 ሺሕ ዛፍ ይተከላል እንጂ መንግሥትን አምኖ ከሩቅ ሥፍራ የመጣው ወገን መገደል አለበትን?›› ብሎ የጠየቀ በበኩሌ አላስታውስም፡፡ በርካታ ሕዝብ እንዳለቀ የሽግግር መንግሥቱ ቃለ ጉባዔ ያረጋግጣል። ለምሳሌ ሌሎችንም ጊዜው ሲደርስ በመረጃ አስደግፌ አቀርባለሁ። 

ሁሉም ግድያዎች አሰቃቂዎች ቢሆኑም ባለፉት ሦስት ዓመታት የሰማናቸው ግን (ምናልባት በሥዕልና በድምፅ ተደግፈው ስለሚተላለፉ ይመስላል)፣ የጭካኔ ድንበሩ ሰውን በአሰቃቂ ሁኔታ ከመግደል በላይ ሆኗል። በመሆኑም ዓለም አቀፍ ውግዘትን አስከትሏል።

‹‹ለመሆኑ የዚህ ሁሉ ምንጩ ምንድነው? ከቶ ይህ ለምን ይሆናል? ወደፊትስ ዕልቂቱ ያባራ ይሆን?›› ብለን የምንጠይቅ ከሆነ በመጀመርያ ‹‹እኔ እራሴ ለሕዝብ እርስ በእርስ መጨፋጨፍ ያበረከትኩት አለን?›› ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። በግል፣ በቡድን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ፣  በመገናኛ ብዙኃን፣ በቤተ እምነት፣ በትምህርት ቤት፣ በፖለቲካዊ መድረክ፣ በግልጽ በአደባባይ፣ በረቀቀ ምስጢር በዘረኝነት የጠቆሙት የጥላቻ መርዝ ረጭተን ከሆነ በደረሰው ጥፋት ሁሉ እጃችን አለበት። ወገን እርስ በርሱ በማንኛውም ምክንያት ሲጨፋጨፍ ይኸ ነገር ትክክል አይደለም፡፡ ልብ ግዙ፡፡ እናንተ የጫራችሁት የእሳት ቋያ ለሌላው ይተርፋል፡፡ ከመከፋፈል አንድነት፣ ከመናቆር መከባበር፣ ከመጣላት መፋቀር ብለን ካልመከርን የኛም እጅ አለበት፡፡ እሳቱ ሲቀጣጠል ወደ እኛ አይደርስም ብለን እሩቅ ሆነን ጠብን አፋፍመን ወይም ለዘብተኛ ከሆንን የኛም እጅ አለበት። የአንድ አካባቢን ሕዝብ ስንጠላ በሌላ ከአባቢ የሚኖር ሕዝብ ‹‹ሰኔ ነገም ለኔ›› የማይል መስሎን በሠራውም ባልሠራውም የምንኮነን፣ የምናወግዝ፣ የምንጨክን ከሆነ ዛሬ በየቦታው በሚፈጸመው ግፍ እጃችን አለበት፡፡ ይህን በአንድ ተጨባጭ ምሳሌ ላቅርብ፡፡

በቅርቡ አንድ የታወቀ አርቲስት ‹‹ሰው በቁሙ ተቃጠለ›› ቢሉት ‹‹ደግ ተደረገ። ለእነሱ፣ ይህ ሲያንሳቸው ነው፣ ምን ተጎዱ እሳት እየሞቁኮ ነው የሞቱት፤›› የሚል ዓይነት አስተያየት ሰጠ። ያ ከጭካኔ ድንበር ያለፈ አስተያየት በሚዲያ ተላለፈ።  ‹‹ገና ቀቅለን እንበላቸዋለን›› የሚል አስተያየት የሰጠውም እንደዚሁ። ‹‹እነሱን ገና አልጠላናቸውም፡፡ ከዚህ በበለጠ መጥላት አለብን፤›› ያለ ትልቅ የሚባል ሰው አለን። ሌላውም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ጥላቻውን ገልጧል። ሌላም ለመግለጥ የሚቀፍ ጥላቻ አለ፡፡  ሌላም ምሳሌ ላቅርብ፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ሰው ከነነፍሱ ዘቅዝቀው ሲያቃጥሉ እየጨፈሩና እየዘፈኑ ነበር። በቅርቡ ጎንደር ውስጥ ለቀብር የወጡ ሰዎች አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ሲደርስባቸው፣ ሀብት ንብረታቸው ሲወድም አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ ሲገባ ይባስ ብሎ ድርጊቱን ለማድበስበ፣ ‹‹ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› እንዲሉ (በሁሉም መስክ አጋሮቻቸው የሆኑ) የጎንደር ሙስሊሞችን አሸባሪ ለማድረግ፣ የሌለ የጦር መሣሪያ በወሬ ለማስታጠቅ የተኬደበት መንገድ ታሪክ መዝግቦታልና እዚህ ላይ ብዙ የምንሄድበት አይደለም፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች በረሃብና በችግር እንዲሞቱ መንገዶች ለዓመታት ሲዘጉ ‹‹እሰየው፣  ደግ አደረጉ  ይገባቸዋል›› የሚሉና ሌሎች ከጭካኔ ድንበር ያለፉ ጽሑፎችና ድምፆች በማኅበራዊ ሚዲያም፣ በጋዜጣም በመጻሕፍትም  ወጥተዋል፡፡  

ተዘፍኗል፣ እስክስታም ተወርዷል፡፡  የታወቁ ጋዜጠኞች፣ ደራሲያን፣ ቀራፂያን ወዘተ. ወገንተኛ ሆነው መርዘኛ የዘረኝነት አመለካከታቸውን አንፀባርቀዋል። ‹‹አሳደህ በለው…›› እያሉ ሲቀሰቅሱ፣ ሲወጉ፣ ሲያዋጉና ሲያወጋጉ፣ ሲያወድሙ፣ ሲያዋድሙ፣ ሲዘፍኑ፣ ዳንኪራ ሲረግጡ ከቆዩ በኋላ በኋላ ነገሮች እንደተመኟቸው ሳይሆኑ ሲቀሩ ደግሞ የሞተባቸውን ሰውና የወደመባቸውን ንብረት ቆጣሪ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሙሾ አውራጅ ሆነዋል።

 ‹‹እንዴት ትናንት የናቁት፣ ያዋረዱት፣ ያሳደዱት ወዘተ ሙሾ አውራጆች አደረጋቸው?›› ተብሎ ቢጠየቅ ምክንያቱን ወደ ሌሎች ያላክካሉ እንጂ የራሳቸው መርዘኛና ወገን አይምሬ ጥላቻቸው አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል አይገነዘቡም። ለመገንዘብም ጥረት አያደርጉም። በዓለም ላይ የመጨረሻ ፈሪ የሆነችው አይጥ ከማታመልጥበት ቦታ ከሆነች በአሳዳጇ ላይ አደገኛ ዕርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ከግምት ውስጥ አያስገቡም።

በእጅጉ የሚያሳዝነው ደግሞ ከሙሾ አውራጆቹ መካከል ለጥፋት ይውል ዘንድ ያወጡትን ገንዘብ ‹‹ለምን አዋጣሁ! በቀረብኝ!›› ብለው የሚቆጠቁጣቸው፣ ባደረጉት እኩይ ድርጊት የሚያፍሩ ሳይሆኑ ከአጋራቸው ጋር የሚኳረፉ፣ የራሳቸውን ጥፋት ለሌላው የሚያላክኩ፣ ወዘተ ሆነው መገኘታቸው ነው።

በልዩ ልዩ የዕውቀት መስክ የተማሩ ምሁራን፣ ከአገራቸው ርቀው የሚኖሩ ወገኖች፣ የዘረኝነት ዛር ተጠናውቷቸው የጥላቻ መርዝ ረጭተዋል። አንዱ ሌላውን እንዲጨፈጭፍም የገንዘብና የሞራል አስተዋጽኦ አድርገዋል። ወደ አገር ተመልሰውም የእርስ በርሱ ጦርነት በሚወግኑት አካል ድል አድራጊነት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አፍራሽ ተልዕኮ ፈጽመዋል።

በዚህ ዓይነት የዘረኝነት አመለካከታችን ከዳር ድንበሩ አልፎ በአሥር ቤት ሳይሆን በመቶ ቤት፣ በመቶ ቤት ሳይወሰን በሺሕ ቤት፣ ከሺሕ ቤት አልፎ በመቶ ሺሕ ቤት የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ አልቋል። ሚሊዮንም ሊደርስ ይችላል። በጦርነት ምክንያት የወደመው ንብረት፣ የደረሰው መፈናቀል፣ የተከሰተው የኑሮ መመሰቃቀል የዘረኝነት፣ የክፋት ውጤታችን ነው። የእያንዳንዱ ፀብ ጫሪ፣ የእያንዳንዱ የዕብሪተኛ ደጋፊ፣ የእያንዳንዱ አቅራሪ፣ የእያንዳንዱ ፎካሪ፣ ለእያንዳንዱ ለእርስ በርስ ጦርነት ገንዘብ ያዋጣ፣ የእያንዳንዱ ደም ተበቃይ መርዛማ ጥላቻ ወዘተ መሆኑ ግን ቅንጣት ያህል እንኳን አያጠራጥርም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከ1970 ዓ.ም. ጀምሮ የአንዱ ክልል ሕዝብ በሌላው ክልል ውስጥ በውድም ሆነ በግድ እንዲሠፍር መደረጉ እየታወቀ የክልል ድንበር ጥያቄ ይነሳል። የድንበር ጥያቄ ሲነሳ፣ በድንበር ምክንያት ማቅራራትና መፎከር፣ በዘረኝነት የተሞላ የጥላቻ መርዝ መረጨት ሲጀመር፣ በሌላ ክልል የሠፈረው ሰላማዊ ሰው ጠላት ተደርጎ ይታያል። የግፍ ሰለባ ይሆናል። አገሬ ነው ብሎ፣ መንግሥት ይጠብቀኛል ብሎ፣ ወገኔ ነው ብሎ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያፈራው ሀብት ይዘረፋል። ቀደም ሲል በተጠናከረ መረጃ እንደቀረበው ሁሉ በ1980ዎቹ በበደኖ፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉልና ጉሙዝ የተካሄደው በዘረኝነት የተመሠረተ ጭፍጨፋ በዚህ መልኩ የተፈጸመ ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ‹‹ለምን ይህ ይሆናል? ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የትም መኖር መብቱ ነው፤›› ብንል ኖሮ ችግራችን በረገበ ነበር። ነገር ግን ሌላው መጥፎ ነገር ሲያደርግብን እንጂ እኛ ስናደርግ ስለማይቆረቁረን ግፍ በግፍ ተመለሰ። ከዚህም በላይ የሰፋሪው መንፈስ በጥላቻ ሲመረዝና የሌላውን ጥላቻ ስሜት ሲያነሳሳ የጥላቻው ድንበር ይሻገርና እብሪት ለተሞላበት አደጋ ተጋለጠ። ነገሩ ‹‹በደረቅ አበሳ እርጥብ ይነዳል›› እንዲሉ ሆነ።

‹‹ብሔር ብሔረሰብ›› ብለን ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ድንበር አበጀን። የኢትዮጵያ ድንበር የተፈጥሮ ባህሪ ይኸው ነውና እያንዳንዱ ድንበር በሌላው ክልል ሕዝብ ድንበር መኖሩ ግድ ሆነ። በድንበር ጉዳይ ፀብ ከተነሳ ወደ ማያባራ ጦርነት እንደምንገባ እንደ ፀሐይ ግልጽ ሆኖ እያለ፣ ችግሩን በሕግና በሰላም ለመፍታት ጥረት ማድረግ ሲገባው ‹‹ኧረ የታባቱ፣ አካኪ ዘራፍ›› ተባለ። በዘረኝነት ስሜት፣ በመረረ ጥላቻ ምክንያት የተነሳው የእርስ በርስ የጦርነት ውጤቱ ምን እንደሆነ አይተናል። አውቀናል።

በኔ ግምት፣ ዛሬም በትናንቱ መንገድ ሄደን ሀቁን የምናድበሰብስ ከሆነ፣ ተራራ ያህል ችግራችንን በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ቀብረን ኩይሳ የሚያካክሉትን ችግሮች ተራራ ልናስመስላቸው ብንሞክር ሕዝብ የሚፈልገውን ሰላም ማስገኘት አንችልም።

ዛሬ የአማራና የትግራይ ክልል ጎልቶ በሌላው የሌለ ቢመስለንም፣ ዛሬ መላ ካላበጀንለት በስተቀር ካለፈው ይልቅ የወደፊቱ የላቀ ሊሆን እንደሚችል አያጠያይቅም፡፡ የበኩሌን የመፍትሔ ሐሳብ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

መፍትሔ አንድ፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ብዙ ብሔራዊ ሰላምን የሚያደፈርሱ ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው ሁሉ የደረሰው ጥፋት በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ ለዕርቀ ሰላም መፈጠር ይቅርታና ምሕረት ወሳኝ ነው፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ጽሑፍ የምናወሳው ይቅርታና ምሕረት ሰፋ ያለ፣ ጠለቅ ያለ ፍልስፍናን የተከተለ፣ እንዲሁም ከባቢያዊ፣ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ባህሪ ቢኖረውም እንደ መንደርደሪያ፣ ከራሳችን የይቅርታና የምሕረት ታሪክ በመነሳት ነገሩን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

የሩቁን ዘመን ትተን ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ያለውን ብንመለከት ከሚቀድሟቸው መንግሥታት ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ተኳርፈው፣ ተጣልተው፣ አምፀው ጫካ የገቡ፣ አገር ጥለው የተሰደዱና ራሳቸውን የሰወሩ ይቅርታና ምሕረት እየተደረገላቸው ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመልሰዋል፡፡ የበደሉትን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው፣ መካስ ካለባቸውም ክሰው ከወገኖቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል፡፡ ከእሳቸው ጎን ተሠልፈውም ለኢትዮጵያ አንድነት ግንባር ቀደም ተሠላፊዎች ሆነዋል፡፡

ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር የተኳረፉትም በአፄ ዮሐንስ ምሕረትና ይቅርታ አግኝተው ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው ተመልሰዋል፡፡ ከአፄ ዮሐንስ ጋር የተኳረፉ በአፄ ምኒልክ ምሕረትና ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው ተመልሰዋል፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ያኮረፉ፣ የተቆጡ፣ በመጀመርያ ዘውድ ሲጭኑ፣ ለሁለተኛ ጊዜ በጣሊያን ወረራ ከእሳቸው አንፃር የቆሙትን ይቅርታም ምሕረትም አድርገው ሰላማዊ ሕይወታቸውን እንዲመሩ አስችለዋል፡፡ ደርግም በልዩ ልዩ ምክንያቶች (በፖለቲካ፣ በግል ፀብ፣ በአመፅ) የወጡት ዜጎች ምሕረት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ይቅርታና ምሕረት አንዱ መንግሥት ወድቆ በሌላው እስኪተካ መቆየት የለበትም፡፡ ትሁት መንግሥት፣ በሕዝብ የበላይነት የሚያምን መንግሥት፣ እራሱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ ለመሄድ የሚፈልግ መንግሥት መቶ ጊዜ ቢያጠፋ መቶ ጊዜ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ሌላው መቶ ጊዜ ቢያጠፋም መቶ ጊዜ ይቅርታ ያደርጋል፡፡ መቶ ጊዜ ይምራል፡፡ ይማማራል፡፡ በማቴዎስ ወንጌልም ይቅርታ ሰባት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሰባ ጊዜ ሰባ መሆን እንደሚገባው ተጠቅሷል (ማቴ18፡21)፡፡ በዚሁ ምዕራፍ እስከ ቁጥር 35 ያለውም ቢሆን ስለይቅርታና ምሕረት የሚያወሳ ጥሩ መልዕክት ስላለው አንባቢው እንዲመለከተው ይጋብዛል፡፡ መላው የቁርዓን ምዕራፎች የሚያወሱት ስለይቅርታና ምሕረት ስለሆነ ጸሐፊው አንቀጽ እየጠቀሰ የአንባቢውን ጊዜ ለማባከን አይፈልግም፡፡  ፍላጎት ላለው ግን 40ኛው ምዕራፍ በሙሉ ስለይቅርታ የወረደ መሆኑን ለመጠቆም ይወዳል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይቅርታ ማድረግና ይቅርታ መጠየቅ ስድስት ጎኖች ያሉት ደስታን ያስገኛል፡፡ እነሱም ይቅርታ አድራጊው፣ ይቅርታ ጠያቂው፣ የይቅርታ ጠያቂው ወገን፣ የይቅርታ አድራጊው ወገን፣ ይቅርታ ባለመደረጉ ምክንያት (ሁለቱ ዝሆኖች ሲታገሉ የሚጎዳው ሳሩ ነው እንዲሉ) ይቅርታ ባለመደራረጉ ምክንያት ያለጥፋቱ የሚጎዳው ሦስተኛ ወገንና ፈጣሪ ናቸው፡፡ ሸሊ የተባለው እንግሊዛዊ ባለቅኔ (1792 እስከ 1822) ‹‹ፕሮሚተስ አን ባውንድ›› በተሰኘው ቅኔው ‹‹የተፈጸመው ስህተት ከሞትና ከጽልመት የጠቆረ እንኳን ቢሆን ይቅርታ ማድረግ የሚሰጠውን ደስታ ያህል የሚያስደስት ነገር የለም፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ ጥንታውያን ባቢሎናውያንም ወደ መኝታቸው ገብተው ሲተኙ ‹‹ፈጣሪ ሆይ ያበሳጩኝን ሁሉ ይቅርታ አድርግላቸው፤›› እንደሚሉ በታልሙዳቸው ሰፍሯል፡፡ ከልደተ ክርስቶስ 600 ዓመት በፊት  የነበረው ዲዮጋን ላርቲየስ ፒታከስ የተባለው የግሪክ መሪ፣ አልሺየስ የተባለ ጠላቱን ድል ካደረገና ሁኔታዎችን ካገናዘበ በኋላ ‹‹ይቅርታ ከመበቀል የተሻለ ነው›› በማለት በነፃነት እንዳሰናበተው ይኸው ታሪኩ ለ2618 ዓመተት ሲነገርለት ኖሯል፡፡ ከ2150 ዓመት በፊት የነበረው ፐብሊሊየስ ሲይረስ የተባለው ሌላው ግሪካዊም ‹‹አበርክቶ ይቅርታ ማድረግ ኃያልን የበለጠ ኃያል ያደርገዋል፤›› በማለት ይመክራል፡፡ ከ2180 ዓመታት በፊት የኖረው ኢፒክተተስ የተባለ ግሪካዊ ፈላስፋም ‹‹ከመበቀል ይቅርታ ማድረግ ይሻላል፡፡ ይቅርታ ማድረግ የደግ፣ የጨዋ፣ የክቡር ሰው መገለጫ ሲሆን መበቀል ግን የአራዊነት ምልክት ነው፤›› በማለት ግልጹን ያስቀምጣል፡፡ ሴነከ የተባለው ሌላው ፈላስፋም ‹‹ይቅርታ አድርግ፣ ይቅርታ ይደረግልህ ዘንድ›› በማለት ከ2078 ዓመት መክሯል፡፡ ለመሆኑ ይቅርታ ምንድነው? ምሕረትስ?

ይቅርታ ምንድነው?

ይቅርታ ጥፋት ተፈጽሞብኛል ብሎ እንደሚያምነውና ጥፋት አላጠፋሁም ብሎ በሚያምነው ወገን በሚያቀርበው ማስረጃ የሚወሰን ሊሆን ሲችል የይቅርታውም ዓይነት በዚያው መጠን ልዩነት ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ብዙም ግምት ሳይሰጠው የሚታለፍ ጥፋት፣ መጠነኛ ቁጣን የሚጭር ጥፋት፣ በእጅጉ የከረረ ቁጣንና የበቀል ዕርምጃ የሚያስወስድ ጥፋት ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙበት ‹‹ይቅርታ›› የሚባለው ‹‹ይህ ሰው ያጠፋው፣ የበደለኝ፣ ያስከፋኝ፣ ያበሳጨኝ፣ እንደኔ ሰው በመሆኑ ነው፤›› በማለት የመበቀል ስሜትን ድል በማድረግ ነው፡፡ ዴቪድ ዋይት (David Whyte) የተባለውና ዛሬም በሕይወት የሚገኘው እንግሊዛዊ ፈላስፋና ባለቅኔ፣ ‹‹ይቅርታ በደልን መርሳት ሳይሆን ያ የቆሰለንበት፣ ደግሞም የማንረሳውን፣ ከርህራሄና ከእዝነት በመነጨ ስሜት ይቅር ማለት ነው፤›› በማለት ይገልጸዋል፡፡

ይቅርታ እራስን በራስ፣ ሕዝብን በሕዝብ፣ መንግሥትን በመንግሥት ወይም መንግሥትን በሕዝብ ወይም ሕዝብን በመንግሥት፣ ወይም አንድ ለአንድ፣ አንድ ለብዙ፣ ብዙ ለአንድ እያልን ከፋፍለን ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ዋናው ቁምነገር፣ የተለያዩ ሊቃውንት እንደሚነግሩን ከተጎዱ በኋላ፣ ከቆሰሉ በኋላ የተነሳ፣ መስዋዕትነትን ከከፈሉ በኋላ ይቅርታን በማድረግ እራስንና ይቅርታ የተደረገለትን ነፃ ማውጣት ይሆናል፡፡ በመሠረቱ ይቅርታ ማድረግ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሁሉ ከርህሩህነት፣ ከአዛኝነት፣ ከደግነት፣ ከመልካም ግንዛቤ የተነሳ ወይም ፖለቲካዊው መፍትሔ እርሱ ሆኖ በመገኘቱ ከሚደረግ ምሕረት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፡፡

ይሁንና ይቅርታና ምሕረት የሚያመሳስለው ቀጭን መስመር እንዳለው ሁሉ የሚያለያየው ቀጭን መስመር አለ፡፡ ስለዚህም ሁለቱም የሕጋዊ ትርጓሜ ልዩነት ስላላቸው ሰዎች ለማስታረቅም ሆነ ምሕረት እንዲደረግ ለመጠየቅ ሲሄዱ ይህን ቀጭን መስመር መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ይቅርታና ምሕረት ሁለቱም ርህሩህነት፣ ከአዛኝነት፣ ከደግነት፣ ከመልካም ግንዛቤ የሚመነጩ ቢሆኑም ይቅርታ፣ በይቅርታ አድራጊውና ይቅርታ በሚደረግለት መካከል የሚከናወን ነው፡፡ ይህም ማለት ጥፋቱ ጨርሶ ተረስቷል፣ ወይም ዳግም ጥፋት ሲፈጸም አይታይም ማለት ሳይሆን ‹‹እሺ ይሁን ማጥፋቱን አጥፍተሃል ዳሩ ግን ለአሁኑ ይቅርታ አድርጌልሃለሁ፤›› ተብሎ የሚገለጽ ሲሆን፣ ይቅርታው በይቅርታ አድራጊው ፈቃድ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ይቅርታ የተደረገለት ሰው ከይቅርታ አድራጊው ጋር ወደፊት አብሮ ሊሠራም ላይሠራም ይችላል፡፡

ምሕረትስ ምንድነው?

ምሕረት በመዝገበ ቃላዊ ትርጉሙ፣ ማረ ወይም መሐረ የሚለው የግሥ ውልድ ቃል  ሲሆን፣ በአማርኛና በትግርኛ ነፃ አደረገ፣ ሰላም ሰጠ፣  በደሉን፣ ዕዳውን ፋቀ፣ ወይም ይቅር አለ የሚል ትርጉም አለው፡፡ በግእዝ ደግሞ (ከሌስላው መዝገበ ቃላት እንደምናገኘው) መሐረ ከሚለው ይምሐር፣ አምሐረ፣ ተምሐራ፣ አስተምሐረ፣ የሚሉ ውልድ ቃላት ሲኖሩት  መሐረ የሚለው ቃልም ርህራሔ ይኑረው፣ ይራራ፣ እዝነትን ያሳይ የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ አምሐረ የሚለው ቃል ደግሞ እንዲራራ፣ እንዲያዝን፣ አደረገ የሚል ትርጓሜ ይኖረዋል፡፡ አስተምሐረ የሚለው ቃልም ምሕረትን፣ እዝነትን፣ ርህራሄን እንዲያገኝ አማለደ፣ ተለማመጠ፣ አሻ፣ እንዲሁም አዛኝ ሁን፣ ሩህሩህ ሁን፣ የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ምሑር የሚለው ቃልም ምሕረት የተደረገለት፣ ነፃ የወጣ፣ የታዘነለት፣ የተራራለት ማለት ሲሆን፣ ምሕረት ማለት ደግሞ ርህራሄ፣ ሐዘኔታ፣ ይቅርታ ማለት ይሆናል፡፡ 

ምሕረትን ዊኪፔዲያ የተባለው የድረ ገጽ ዓውደ ጥበብ፣ አምነስቲን ማለትም ምሕረትን እንደተረጐመው ቃሉ ከግሪክ የተገኘ ሲሆን፣ አምነስቲያ የተባለ ሥርወ ቃሉም መርሳት፣ ማለፍ ከሚለው ፍች ይነሳና መንግሥት ለቡድኖች ወይም በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ ለፈረጃቸው (አብዛኛውን ጊዜም ፖለቲካዊ ጥቃት ፈጽመዋል ብሎ ለመደባቸው) ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት ችሎት ሳይሆን በምሕረት እስረኛን በነፃ መልቀቅ በማለት ይፈታዋል፡፡ ይህም ሆኖ የሰውን ሀብት የዘረፉ፣ ግለሰቦችን በጊዜያዊ ጠብ ምክንያት የገደሉ፣ የተጣለባቸውን አደራ ክደው የሰውን ሀብትና ንብረት የወሰዱ፣ የሚጠበቅባቸውን ግብር ያልከፈሉ ወዘተም የተቃዋሚው ኃይል አጋር ሆነው ጥላ ከለላ የሚያገኙበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ተቃዋሚና እስረኛ ነፃ የማድረጉ ሒደት እንደየአገሩ ሕግ የተለያየ ሲሆን፣ በአገሪቱ መሪ (ንጉሥ፣ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጸሐፊ) የሚፀድቅ ይሆናል፡፡ ምሕረት አብዛኛውን ጊዜ የሚደረገው መንግሥት ደም የሚያፋስስ ሁኔታ እንዳይመጣ ለመከላከል የሚያስችል ፍቱን መሣሪያ ሲሆን፣ ሕዝብን በበለጠ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመግዛት እንደመልካም አማራጭ ሲወስድ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ምሕረት ማድረግ ከዚህም በተጨማሪ፣ የመንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎች በአብዛኛው ትግላቸውን የሚያካሂዱት ሕገወጥ በሆነ መንገድ በሚገኝ ገቢ ሊሆን ስለሚችል እንደ አደገኛ ዕፅ፣ የጦር መሣሪያዎች፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕጋዊ ባልሆኑ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጦች ያሉ አስከፊ ሥራዎች እንዲገቱ ብሎም እንዲወገዱ የማገዝ ባህሪም አለው፡፡

አብዛኛው ትንታኔ በይቅርታው ንዑስ ርዕስ የተተነተነ ስለሆነ በድጋሚ ማቅረብ ሳያስፈልግ ሁለቱን ስለሚመለከቱ ተነሽ ጥያቄዎች ላይ እናተኩር፡፡

ቁም ነገሩ ይህ ሆኖ ሳለ የብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ፣ አንድና አንድ ብቻ ሆኖ ከመታያቱ በተጨማሪ  ከ1844 እስከ 1900 የኖረውና ላይፕዚሽ በተባለችው የጀርመን ከተማ የተወለደው ከፍሬድሪክ ዊልያም ኔሹ የተባለው ፈላስፋ ‹‹ዘስ ስፖክ ዛራቱስትራ›› በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፉ (ገጽ 75 እስከ 78) በተለይም ‹‹አዲሱ ጣኦት›› ብሎ ባሰፈረው ንዑስ ርዕስ እንደገለጠው፣ የብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ ከሐሳብነት አልፎ ወደ ጣኦትነት እየተለወጠ መሄዱ ነው፡፡

ነገር ግን በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው በአንድ በኩል አንዱ ኢትዮጵያዊነት እንደ ቆሻሻ ነገር በተረገጠበት፣ በሌላው በኩል ደግሞ ከፍ ያለ ሰንደቅ ይዘው ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት በሚያቀነቅኑበት፣ ከነዚህም ጋር ኢትዮጵያ ኖረች አልኖረች አንዳችም ደንታ የማይሰጣቸው ሰዎች ባሉበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ዋነኛ በሽታ፣ የታሪክ መቃወስ፣ የታሪክ ሸፍጥ፣ የታሪክ ቅሚያ፣ የታሪክ ሽሚያ፣ የታሪክ ሕመም ወይስ በብሔራዊ ዕርቅና ድርድር የሚወገድ ቀላል ችግር ነው? ብሔራዊ ዕርቅ በአገሪቱና በሕዝቧ ውስጥ ሥር ተከል ለውጥ የሚያመጣ ወይስ እራስ ምታትን ለማስታገስ ከሚወሰድ ባህላዊም ዘመናዊም መድኃኒት ያልተለየ ፈውስ? ስለሆነም ቀደም ሲል ከተገለጠው ሌላ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔ መሻት ይኖርብናል፡፡ ለመሆኑ መፍትሔ አለን? በርካታ የመፍትሔ ሐሳቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የኔን ግን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

መፍትሔ ሁለት፡-

ምንም የሌለ ቢመስለንምና ትልልቆቹ ችግራችን ምንድን ናቸው? ዋና ዋናዎቹ ችግሮቻችንን እናንሳ፡፡

ታሪካችን የጦርነት ታሪክ ነውና ከሁሉ አስቀድሞ ታሪካችን መታረቅ ይኖርበታል፡፡ ታሪካችን ሲታረቅ የደመኝነት ቁስሉ ሊድን ይችላል። በሒደትም አንዱ ክልል የሌላው ክልል ጠላት ሆኖ መቀጠሉ ይቀራል።

የድንበር ጭቅጭቅ ካልቆመ አሁን ካለው የባሰ ጠብና መጨፋጨፍን ሊያስከትል ስለሚችል፣ በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት ሁሉም ክልሎች በጋራና በተናጠል መላ መፍጠር ይኖርባቸዋል። ቢያንስ ቢያንስ ማርገብ ይኖርባቸዋል።

ፖለቲከኞች በእውነት አገራቸው ወደከፋ ቀውስ እንድትገባ የማይሹ ከሆነ በገሃድ የሚታየው የፅንፈኝነትና የአክራሪነት ስሜት ወደ አሸባሪነት እንዳያመራ ለሰላም፣ ለዕርቅና ለመግባባት መሥራት ይኖርባቸዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የሁሉም ሚዲያ ሰዎች ከአድርባይነት ተላቀው ጥፋተኛውን ‹‹ጥፋተኛ ነህ›› ብለው መገሰጽ አለባቸው። ስለሰላምና አብሮነት መነገር አለበት።

መደምደሚያ

በጭፍን ወገንተኛነት ስሜት አንዱን አጥፊ ኮንነን ሌላውን አጥፊ ለማመስገን ካልፈለግን በስተቀር በተቃራኒ ወገኖች በተካሄደው የረዥም ጊዜ ጦርነት በትውልድ፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህል በሥነ ባህሪና በኢኮኖሚ አንዱ ከሌላው ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ወንድም መሆኑን በመምከርና ወደ ብሔራዊ አንድነት የሚወስደውን መንገድ በማስተማርና በመምራት ፈንታ በአፍቃሬ ሥልጣንና በራስ ወዳድ የመንግሥታትና ሃይማኖት መሪዎ­ቻችን አማካይነት ጥላቻና ደመኛነት ተሰብኳል፡፡ ሆኖም የመንግሥታቱ  አቋም ወደ አንድ አቅጣጫ ያዘነበለ በነበረበት ዘመንም ቢሆን ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሁሉ፣ ለሕዝቡና ለአገር ዕድገትና ልማት ፋይዳ ባልነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እንድንጨፋጨፍ ቢደረግም የጦርነቱ ደመና ሲገፍ፣ የደሙ አበላና ጎርፍ ሲያልፍ፣ እንደነበረውና እንደለመደው በአንድ ላይ ተስማምተን ኖረናል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ አገራችን በነዚህ ኃይሎች በአስመራሪ ሁኔታ ተጎድታለች፡፡ ለአሁኑ ድህነታችን በተለይም ለተፈጥሮ ሀብታችን መጥፋት፣ ለሥልጣኔያችን እጅግ በተፋጠነ መንገድ ወደ ኋላ መጎተት አንዱ መሠረታዊ ምክንያትም የእርስ በርስ መናቆር እንደሆነው ሁሉ በጦርነት ምክንያትም የምንቀላቀልበት፣ የሥጋ ዘመዶች የምንሆንበት፣ ልምድ የምንጋራበት፣ በዚህም ሒደት ሰብእናችንን የምንገነባበት ሁኔታንም ይዞልን ስለመጣ መጥፎውን ትዝታ ትተን ያገኘነውን ማኅበራዊ ውህደትን እንደ ጠቀሜታ እንድንወስድ ያስችለናል፡፡ 

ምንም እንኳን የክርስቲያኖችና የሙስሊሞች ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶች ብቻም ሳይሆኑ የኦሪታውያንና የአይሁዳውያን እንዲሁም ከነሱ በፊትና በኋላም ህልውናቸው ያልከሰመው የአረማውያን ሕይወት፣ ንብረት፣ ታሪካዊ ቅርስ ከምድረ ገጽ ቢጠፉም የሕዝቡ ግንኙነት አሁንም ቢሆን መጥፎ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ወግና ልምድ እንደሚያመለክተውና እኛ እስከምናውቀው ድረስ ከሙስሊም ወገን የሚወለዱ ቄሰ ገበዞች እስከ ጳጳሳት ሲኖሩ ከክርስቲያን የሚወለዱ ሸኾና ወሊዮ­ች አሉ፡፡

ስለሆነም፣ አሁን የምንገኘው ደግሞ በተለየ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አድማስ ውስጥ ሲሆን በዚህ አዲስ አድማስ ውስጥ ለመኖር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ኢትዮጵያችንን በአንድ ወቅት ወደ ነበረችበት የሥልጣኔ አቅጣጫ እንድታመራ ለማድረግ ለዳግማዊ መንሰራራትና ለዳግማዊ ህዳሴ በአዲስ መንፈስ መነሳሳት ይኖርብናል፡፡ የጠፋንና የተረሳን ዝና እንደገና የመመለስ የሚደረገው ጥረትም፣ በሌላ አገላለጥ የተናጋውን ማኅበረሰብ፣ የጎበጠውን አመለካከት ለማቅናት/ያፈነገጠውን ለመጠገን፣ አዲስና ጤናማ ሕይወት ለመመሥረት፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሳተፍ አለበት፡፡ ይህም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካዊ አመለካከት በየትኛውም ጊዜና ቦታ ያለ ሁሉንም ሕይወት የምታቅፍ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡

የጠፋንና የተረሳን ዝና እንደገና ለመመለስ ጊዜያዊ ታይታን፣ ስንፍናን፣ አጉል ዝናን፣ ራስ ወዳድነትን፣ የወሬ ዝባዝንኬን፣ ጠባብ አመለካከትን፣ በጭካኔ የተሞላበት ኃይል መጠቀምን የመሳሰሉ በሽታ­ችን ማስወገድ አለብን፡፡ በምትኩ ቁም ነገረኛነት፣ ወኔ፣ ትህትና፣ ለሌሎች መኖርን፣ ዕውቀት፣ ሠናይ ምግባር፣ ለሁሉም (ለዓለም) ማሰብና የመሳሰሉ ሰብዓዊ እሴቶችን በተግባር ማዋል ያስፈልገናል፡፡

የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እንደገና መንሰራራት፣ የጠፋንና የተረሳን ዝና እንደገና ለመመለስና ዕውን ሊያደርግ የሚችለው ይህን አመለካከት በሚጋሩ የአገሪቱ ዜጎች እንጂ በሌሎች ሊሆን አይችልም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ስሜት ለመጓዝ ስትችል ለዘመናት ጠፍቶ የቆየውን አመኔታ መልሳ በመጨበጥ ዓለማትን ገነት የመሰለች ምድር ትሆናለች፡፡

ኅብረተሰቡ ታድሶ በተሻለ የሕይወት አቅጣጫ ለመጓዝ ደግሞ ሕዝቡ መለወጥንና መታደስን ከልቡ/ከራሱ በመጀመር ይሻል፡፡ ኅብረተሰቡ ለልማትና ዕድገት የሕግንና የሥርዓት ጠቃሚነትን መገንዘብ በጎ ነገር የሚያስብ ማኅበረሰብ በጭቆናና በአፈና ሊገነባ እንደማይችል ማመን ይኖርበታል፡፡ ልዩ ልዩ ልዩ ጎሳ­ች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች አንዳቸው ከሌላቸው በመማር ተጨባጭ የዕድገት ለውጥ እንደሚያመጡ መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ‹‹በእኔ ይበልጣል›› አጉል ትምክህት ተጀቡኖ አዲሱን የሥልጣኔ  ዘመን የማይቀበልና ዕድገት የሌለው አስተሳሰብ ሊቀጥል አይገባውም፡፡ ስለሆነም ለመለወጥ ከለውጥ ሒደቱ ጋር አብሮ የሚጓዝ አመለካከትን አጥብቆ መፈተሽ፣ መገንባት ይኖርበታል፡፡  ይህ ከሆነ ልጆቻችን ተፈቃቅረውና ተፈቃቅደው ለመኖር የሚሹ አዲስ ዓይነት ሕዝቦች ይሆናሉ፡፡ በኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ይንገሥ! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles