Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየሮፍናን ቀመሮች

የሮፍናን ቀመሮች

ቀን:

‹‹ነጠላሽ የዋህ

በውኃ ይነጣል

ልብሽ ግን ይቅርታ እንዴት ያጣል?

- Advertisement -

ላጠፋ ሰው ምሕረት

አሻፈረኝ ብለሽ

የለበስሽው ሸማ በለጠሽ

አምላክ የሰጠውን መቼ ከሰው ወሰደው?

ሰላምን በዳይ ጋ አስቀመጠው

ጥበቡ ጠብ ሲል

ከባህር ይጠልቃል

አንድ ይቅርታ ለዓለም ይበቃል…››

ይህ የሙዚቃ ግጥም አንጓ፣ ሰሞኑን በኤሌክትሮኒክ የሙዚቃ ሥልት ተጫዋችነቱ በሚታወቀው ሮፍናን ኑር አማካይነት ለአድማጮች በቀረበው አዲሱ አልበም ‹‹VI ስድስት›› ውስጥ የተገኘ ሲሆን፣ የዘፈኑ ርዕስ ‹‹ቢሆን›› ነው፡፡

የብዙ ወጣቶችንና ሕፃናትን ቀልብ መሳብ የቻለው ወጣቱ አቀንቃኝ የሮፍናን ኑር ለየት ያለ አመለካከት (ዕሳቤ) ባለቤት መሆኑ ይነገርለታል፡፡

ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረገው ድምፃዊው በቤተሰቡ ሙዚቃ ውስጥ የሚገኙ (የሚሠሩ) እንደሌሉና ሙዚቀኛ መሆኑ በሒደትና በጊዜ ብዛት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ሮፍናን ከዘፋኝነቱ ባሻገር የግጥም ጸሐፊ፣ ቀራፂ (ሪከርድ አድራጊ)፣ በዲጄነትና ሙዚቃን ፕሮዲውስ በማድረግም ከሌሎቹ ሙዚቀኞች እንደሚለይ ይገልጻል፡፡

የእነዚህ ሁሉ ጥምር ሙያ ባለቤት የሆነበት ምክንያት ደግሞ ነገሮችን ቀስ በቀስ እየሠራ በመምጣቱ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ከእነዚህ ሁሉ ሙያዎች የመጀመርያው ሥራው ሪከርድ ማድረግ እንደነበረ ያስረዳል፡፡ የሙዚቃን ሀሁ የጀመረው በአሥር ዓመቱ እናቱን ሪከርድ በማድረግ መሆኑን፣ ይህም የመጀመርያ የሙዚቃ ሕይወት ጅማሬው እንደሆነ ያምናል፡፡ ከዚያን በኋላ በትምህርት ቤት ለክፍል ጓደኞቹ ሙዚቃን በመጫወት እያሳደገው መምጣቱን ይገልጻል፡፡

ወጣቱ አቀንቃኝ በልጅነቱ የተበላሹ የሙዚቃ መሣሪያዎችና ሌሎችንም ነገሮች መቀጠልና መጠገን ይወድ ነበር፡፡

በአሥር ዓመቱ የእናቱን ድምፅ ከቀዳ በኋላ የቴፑ ባትሪ እስኪያልቅ ድምፃቸውን ደጋግሞ ያዳምጥ እንደነበር ይገልጻል፡፡

የታናሽ ወንድሙንና የጎረቤት ልጆችን እያዘፈነ ድምፃቸውን ይቀዳ እንደነበር ተናግሯል፡፡ ሮፍናን እንደተናገረው፣ በተለይም የእናቴን ድምፅ ደጋግሜ በማዳመጤ ‹‹ለድምፅ ፍቅር›› እንዲያድርብኝ አድርጓል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ፎቶግራፍ ደጋግመው ማየት እንደሚወዱ ሁሉ፣ የእናቱን ድምፅ በሞት እስከተለዩት ድረስ ለ21 ዓመታት ደጋግሞ ይቀርፀው እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ወጣቱ የኤሌክትሮኒክ አቀንቃኝ ድምፅ በአዕምሮ ቀለም እንደሚከሰትለትና እያንዳንዱ የቀለም አጣጣል እንደ ሙዚቃ የራሱ ፍሰት አለው ብሎ ያምናል፡፡

በምሳሌነት ያነሳው የመጀመርያ አልበሙ በዶርዜ ባህል የሠራውን ሙዚቃ ሲሆን፣ ሙዚቃው የራሱ ፍሰት እንዳለው ይናገራል፡፡

በዶርዜ ባህላዊ ልብስ ዳንጉዛ ላይ ያሉ ጥለቶችን፣ አቀማመጣቸውን በሙዚቃው በተመሳሳይ ፍሰትን መከተሉን፣ ይህም ጥበብ ተመሳሳይነት ያለው ፍሰት እንዳለውና የቀለምና የድምፅ ትስስርን እንደሚያስቃኝ ያስረዳል፡፡

የዶርዜ ማኅበረሰብ ትስስር ጠንካራነት እንዳለበትና በሙዚቃውም ይህንኑ እንዳንፀባረቀ ወጣቱ አቀንቃኝ በድምፃዊው ግጥሙ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡

‹‹ዶርዜ ዶርዜ ዩርዜ

ያብዛው ሰላሙን ለአገሬው ሰው

ፈትሉን ከቀለም ለሚያረቀው

የእናቴን ቀሰም በአሞቂያው ከቶ

እናና አማረባት ዶርዜው ሸምኖት››

ድምፁን ሲያዳምጥ ልክ እንደ ፎቶግራፍ ምሥል እንደሚከሰትለት የሚገልጸው ሮፍናን፣ ብዙ ሠዓሊያን ይህንን ሥዕል የሠራነው የእሱን ሙዚቃ እያዳመጡ መሆኑን እንደነገሩት አውግቶናል፡፡

የሙዚቃ ሥራውን ደጋግሞ በመለማመድ ያዳበረው ወጣቱ ሙዚቀኛ፣ 14 ዓመት ሲሞላው ለጓደኞቹ መጫወት እንደጀመረ፣ ከዚህም ባለፈ ሬዲዮ በጥልቀት እንደሚያዳምጥ፣ ይህም ለሥራው አመቺና አጋዥ ሆኖ እንዳገኘው አስረድቷል፡፡

‹‹በተለያዩ ባህሎችና ቋንቋዎች ላይ ሙዚቃን ለመሥራት ሳጠና አንድ ነገር እገነዘባለሁ፡፡ ሁሉም ሰው በአንድ እውነታ የተሳሰረ መሆኑን፣ ይህም ፍቅርና እውነት ነው፤›› በማለት እምነቱን አበክሮ ገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት በመጀመርያና በሁለተኛ አልበሞቹ ላይ የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ቋንቋዎችና ባህሎች ላይ ሙዚቃን መሥራት የቻለው፡፡

ሙዚቀኛው ለሙዚቃ ያለውን ክህሎት ያዳበረው ለጉዳዩ ትኩረትና ጊዜ በይበልጥ በመስጠቱ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ሮፍናን ‹‹ለዓለም የሰጠነውን አመለካከት መቀየር ይገባናል›› ሲል በምሳሌነት ያነሳውም፣ ‹‹ፓስታ እየበላን፣ ሌሎች ያመረቱትን ስልክ እየተጠቀምን፣ እኔ ከዚህ ጎሳ (ዘውግ) ነኝ ማለት ተገቢ ነው?›› በማለት ይጠይቃል፡፡     

የሮፍናን መጠሪያ

የሮፍናን የሙዚቃ አልበም መጠሪያ ሦስት III፣ ስድስት VI እና ዘጠኝ IX የተሰኙ ናቸው፡፡ የእነዚህ አልበሞች መጠሪያ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ብዙ ያነጋገሩ መሆኑን ይታወቃል፡፡

ሙዚቃኛውም ስለመጠሪያው ሲጠየቅ ምላሹ ‹‹ሰዎች ምንድነው?›› ብለው እንዲጠይቁ ለማድረግ መሆኑንና የአልበሞቹ መጠሪያ ሰዎች በዓለም ውስጥ ራሳቸውን ማየት እንደሚገባቸው መልዕክት የሚሰጡ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡

ራስን በዓለም ውስጥ ሆኖ መመልከት እንደሚገባ፣ በእነዚህም ያሉትን ሁነቶች መገንዘብ እንደሚቻል፣ ራስንና ማኅበረሰቡን ከፍ አድርጎ ማየትና እንዴት ከማኅበረሰቡ ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ የሚገልጽ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ነገር ግን ራስንና ማኅበረሰብን አስተሳስሮና አጣምሮ መሄድ ካልተቻለ ልክ እንደ አረፋ (በብል) ይሆናሉ የሚል ሥጋት እንዳለው ሳይገልጽ አላለፈም፡፡

ሮፍናን ‹‹ስድስት›› የተሰኘው አዲሱን አልበሙን በታዋቂው የዓለም አቀፍ የሙዚቃ አሳታሚ ተቋም ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ግሩፕ (ዩሚግ) አማካይነት ለአድማጭ ጆሮ  አድርሷል፡፡ 

የሦስት፣ የስድስትና ወደፊት የሚያወጣው የዘጠኝ   አልበሞች መጠሪያ የሐሳቡ መነሻ የኒኮላ ተስላ ቀመር  መሆኑን፣ የቁጥሮችን ምስጢር ያወቀ  ደግሞ የሁላዊነትን  ቁልፍ እንዳገኘ ይቆጠራል ይላል።  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትም ቁጥሮች የሚተረጎሙበት መንገድ መኖሩንም ያስታውሳል፡፡

አዲሱ አልበም በራሱ በሙዚቀኛው ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ሐምሌ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. መለቀቁንና 15 ዘፈኖችን ማካተቱንም ተመልክተናል። 

ከተለቀቁት መካከል ‹‹ቃል›› የተሰኘው ሙዚቃ አንዱ ነው፡፡

‹‹ቃል ነበረ 

ከራስ መከረ

በራሱ ምሥል ሰውን ፈጠረ

በፈጠረው ሰው ቃል አደረ

ሰው ግን በአፉ ቃል ሰውን ገደለ…›› እያለ ስለቃል ይገልጻል፡፡

ሮፍናን በዓለም አቀፍ ደረጃ የአንጋፋዎቹን ጀምስ ብራውን፣ ስቲቪ ዋንደር፣ ሪሃና የመሳሰሉ ታዋቂ ጠቢባን ሥራዎችን በማሳተምና በማስተዋወቅ የሚታወቀው ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ግሩፕ ያደረገው ስምምነት በዓይነቱ ልዩ መሆኑ ተነግሯል፡፡ 

ከኢትዮጵያ የመጀመርያው እንደሆነ የተነገረለት ይህ ስምምነት፣ ወጣቱን ድምፃዊ ለዓለም አቀፍ ዕውቅና ከማብቃቱም በላይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕርምጃ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ 

‹‹ነፀብራቅ›› በሚለው የመጀመርያ አልበሙ በወጣቶችና በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳገኘ የሚነገርለት ሮፍናን፣ ከሕፃናት ጋር በመዋል አግኝቼዋለሁ ያለውን አዲስ ዕሳቤ በ‹‹ስድስት›› ላይ እንዳንፀባረቀው ተናግሯል።

‹‹`ስድስት` ለትውልዴም፣ ለታናናሾም የሚሆን ስጦታ ነው፤›› ያለው ሮፍናን ዘፈኑ ኢትዮጵያም ለትውልዱም የተጻፈ ጦማር (ደብዳቤ) ነው ሲልም አክሎበታል፡፡

በሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ላይ ትኩረት ያደረገውና ከዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ግሩፕ ጋር የተጣመረው ሮፍናን፣ ኢትዮጵያንና ባህሎቿን ለዓለም አቀፉ የሙዚቃ አድማጭ ‹‹IX ዘጠኝ›› በተሰኘው ሌላ አልበሙ ለማድረስ እየሠራ መሆኑንም ገልጿል፡፡ 

በዚህ አልበም ዜማና ግጥም እንዲሁም ቅንብሩ ጭምር በራሱ በሮፍናን ተሠርቶ መዘጋጀቱና ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በተጨማሪ  ዕውቁ የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ የቦብ ማርሌ ልጅ  ጁሊያን ማርሌ በአጃቢነት እንደሚሳተፉበት ተሰምቷል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...