Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየዘር ማጥፋት ምንድነው? ዓለም አቀፋዊ ተጠያቂነትስ? (ክፍል ሦስት)

የዘር ማጥፋት ምንድነው? ዓለም አቀፋዊ ተጠያቂነትስ? (ክፍል ሦስት)

ቀን:

በያሬድ ኃይለ መስቀል

ብዙ የፖለቲካ ቀስቃሾች በየንግግራቸው ውስጥ ሁሉ “ጄኖሳይድ”ን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲሉ ይሰማሉ። ለመሆኑ “ጄኖሳይድ” ምንድነው? አንድ ሰው መግደል፣ አንድ ሺሕ ሰው መግደል ወይስ አሥር ሺሕ? ጄኖሳይድ ወይም የዘር ማጥፋት የሚባለው በሁለተኛም የዓለም ጦርነት ገደማ እ.ኤ.አ. በ1944 ቃሉ ተፈጠረ። “ጄኖ” የሚለው የግሪክ ቃል “ዘረመል” ወይም “ሕዝብ” ማለት ሲሆን፣ “ሳይድ” የሚለው የግሪክ ቃል ደግሞ ግድያ ወይም ማጥፋት ነው። ይህ ወደ አማርኛ ሲተረጎም ዘር ማጥፋት ተብሎ ተተርጉሞ እናያለን። ይሁንና ዘር ማጥፋት ሲባል ሰውን “በጎሳ፣ በብሔሩ ወይም በሃይማኖቱ” ምክንያት ከተገደለ ነው። “ጄኖሳይድ” በቁጥሩ የሚመደብ ሳይሆን በግድያው ዓላማ ላይ የተንጠለጠለ ነው። አንድ ቡድን አንድን ሰው እንኳን በማንነቱ ምክንያት ከገደለ ጀኖሳይድ ፈጸመ ነው የሚባለው።

እ.ኤ.አ. በ1948 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጄኖሳይድ ዓለም አቀፋዊ ሕጋዊ ስምምነት መሠረት፣ የመግደያው ምክንያት ነው ግድያው የዘር ማጥፋት የሚያስብለው እንጂ ቁጥሩ አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕግ፣ “Genocide means any of the following acts committed with intent to destroy, in whole or in part, a national, ethnical, racial or religious group, as such/killing members of the group; causing serious bodily or mental harm to members of the group; deliberately inflicting on the group conditions of life calculated to bring about its physical destruction in whole or in part; imposing measures intended to prevent births within the group; forcibly transferring children of the group to another group.

ዘር ማጥፋት የሚሆነው አንድ ሰው በማይመለከተውና ባላጠፋው ወንጀል የተወሰነ ቡድን አባል በመሆኑ፣ ወይም ነው ተብሎ በመፈረጁ ብቻ ሲገደል ነው። ለምሳሌ ወለጋ የሚገደሉ ሰዎች በግላቸው የሚጠየቁበት ወንጀል የለም። በብዛት ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ፣ በኢትዮጵያ ነገሥታትና ፖለቲከኞች በረሃብ ሲጠቁና ዘመዶቻቸው ሲረግፉ አልደረሱልንም ብለው ያዘኑ፣ ግማሾቹም ራሳቸውን እስላም እንጂ “አማራ” ብለው ጠርተው የማያውቁ፣ ምናልባትም ከወሎ ስለመጡ በሰገሌ ጦርነትና ወይም በኢያሱ ምክንያት ከወለጋ በላይ የሸዋን ገዥ መደብ የሚቃወሙና ቅሬታም የሚኖራቸው፣ ከኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር ተጋብተው፣ ተዋልደው፣ ሸምተው፣ ሸጠው፣ ልጆቻቸውን በቁቤ አስተምረው ያሳደጉ፣ እንደ እነሱ ካሉ ደሃ ገበሬዎች ጋር በደቦ የሚያጭዱ፣ አብረው ደግሰው የሚድሩ፣ አብረው አልቅሰው የሚቀብሩ፣ እንደ ማንኛውም ደሃ ገበሬ የኦፒዲኦ/ብልፅግና ገዥዎቻቸውን ከጠዋት እስከ ማታ ተሠልፈው ድምፃቸውን የሰጡና የመረቁ ሰዎች ናቸው።

አንዳንዶቹም አፋቸውን ያልፈቱ፣ ብሔራቸውን ቀርቶ እሳትና ውኃን የማይለዩ፣ ከእናቶቻቸው እቅፍ ያልወረዱ ናቸው። እነዚህ ሕፃናት ወንጀል በተሳሳተ የመልክዓ ምድር፣ በጥላቻ ህሊናው የታወረ ማኅበረሰብ መሀልና በተሳሳተ ዘመን በመወለዳቸው ብቻ ነው`። ጄኖሳይድ ማለት እንግዲህ አንድ መንግሥት ወይም የመንግሥት ድጋፍ ያለው ቡድን፣ ሰዎችን ሳይጠይቅ እንዲህ ናቸው ብሎ ፈርጆ መግደል ነው።

የዘር ማጥፋትም አቀፋዊ ወንጀልነት

ኢትዮጵያ የተባበሩትን መንግሥታት ድርጅት ከመሠረቱ 51 ነፃ አገሮች ውስጥ አንዷ ስትሆን፣ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተጠናቀቀ እ.ኤ.አ. በ1945 ከኃያላኖቹ አገሮች እኩል ስብሰባ ተሰብስባ፣ እጅ አውጥታ መርጣ፣ በፊርማዋ የተባበሩትን መንግሥታት ድርጅትን የመሠረተች ናት። መሥራች ብቻ ሳትሆን ጦርነቱ ሲጠናቀቅ በናዚ ጀርመን በይሁዳውያን ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ካወገዙትና ዓለም አቀፋዊ ከለላ እንዲሰጥ ከጣሩት አገሮች መሀል ነበረች።

በይሁዳውያን ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳይደገም እ.ኤ.አ. በ1948 በፓሪስ በተጠራው ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ተገኝታ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ዓለም አቀፋዊ ወንጀል እንደሆነ ተቀብላ በፊርማዋ ያፀደቀች አገር ነበረች። ኢትዮጵያ በዲሴምበር 11 የፈረመች ሲሆን ይህንን ዓለም አቀፋዊ ወንጀል በማፅደቅ ካናዳና ስዊዲንን ትቀድማለች።

ይህ ማለት በዘር ማጥፋት የተወነጀለ ሰው በየትኛውም ዓለም በየትኛውም አገር ሕግ የሚከሰስ፣ በየትኛውም አየር ማረፊያ ሲተላለፍ ከተገኘ ታስሮ ለሕግ የማቅረብ የሁሉም አገር ግዴታ መሆኑን ተቀብላለች። አንድ ዘመዱን በጄኖሳይድ ያጣ ሰው የማንኛውንም አገር መሪ ከሶ የማሳሰር መብት ይሰጣል። ለምሳሌ የቺሊው ጄኔራል ፒኖሼ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርግሬት ታቸር ወዳጅ ቢሆንም፣ በእንግሊዝ የሚኖሩ የቺሊ ተወላጆች ፋይል ከፍተው ሊያሳስሩት መሆኑን መረጃ ስለደረሰው፣ የእንግሊዝ ወዳጆቹ ከሕግ ሊያድኑት እንደማይችሉ ስለገባው የፍርድ ቤት እስር ትዕዛዝ ሳይወጣ አውሮፕላኑን አስነስቶ ነው ከእንግሊዝ የአየር ክልል የወጣው። 

የሱዳኑም ጄኔራል አል በሽር ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ደቡብ አፍሪካ ሄዶ ፋይል እየተከፈተበት መሆኑን ሲሰማ፣ እሱም አውሮፕላኑን አስነስቶ ወደ ሱዳን ነው የበረረው። ምክንያቱም የደቡብ አፍሪካ ዳኞች በፖለቲከኞች የሚታዘዙ ሳይሆኑ ሕጉን የሚተረጉሙ ስለሆኑ።

በእርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃ ባልሆነባቸው አገሮች ማንም ደፍሮ አል በሽርን አሰሩልኝ ብሎ ክስ አይመሠርትም፣ ፋይሉንም የሚያየው ዳኛ ኢትዮጵያ የ1948 የፀረ ጄኖሳይድ ሕግ ፈራሚ እንደሆነች ቢረዳም አል በሽርን እሰሩ ብሎ ትዕዛዝ አይሰጥም። ይሁንና ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በዘር ማጥፋት ከተከሰሰ በየትኞቹም የአውሮፓ አገሮች፣ በአሜሪካ ወይም በካናዳ የእስር ትዕዛዝ ወጥቶበት ይጣራል እንጂ የሌላ አገር ባለሥልጣን ስለሆነ ከእስር አይድንም።

ለዚህ ነው በሃይማኖት፣ በጎሳና በብሔር ላይ ያነጣጠረ ግድያ በየትም አገር ከተጠያቂነት አይድንም የሚባለው። አንድ ቡድንም በዘር ማጥፋት ወንጀል በተፈረጀ የዚህ ቡድን አባል የሆነ በማንኛውም የምዕራብ አገሮች የቪዛም ሆነ የዝውውርም ፈቃድ አያገኝም። የካናዳ ሕግ እንኳን በጄኖሳይድ የተከሰሰ ቀርቶ፣ ጄኖሳይድን ወይም ወታደራዊ ወንጀል ሲፈጸም ያላስቆመ ባለሥልጣንንም ወንጀለኛ ነው ብሎ ይፈርጃል። በአገሩ ውስጥም ጥገኝነት እንዲጠይቅ አይፈቅድም። ለምሳሌ የካናዳ ሕግ ይህንን ይላል፡፡ “Persons believed to save committed or been complicit in war crimes, crimes against humanity or genocide 35 (1) (b) being a prescribed senior official in the service of a government that, in the opinion of the minister, engages or has engaged in terrorism, systematic or gross human rights violations, or genocide, a war crime or a crime against humanity within the meaning of subsections 6(3) to (5) of the crimes against humanity and war crimes act;”

እንኳን በጄኖሳይድ የተጠረጠረና ማስቆም ያልቻለ ባለሥልጣንም በወንጀል ተጠያቂ ነው። በምዕራብያዊያን አገሮችም ስደተኝነት መጠየቅ አይችልም። ዋሽቶ ቢገባ እንኳ አንደ ቀልቤሳ ነገዎ አንድ የሚያውቀው ሰው የጠቆመበት ቀን ወደ እስር ይወረወራል። ታዲያ ይህች አገር የዘር ማጥፋትን ወንጀል በዓለም አቀፋዊ ሕግነት እንዲፀድቅ ያደረገች ቢሆንም፣ ከ76 ዓመታት በኋላ ራሷዋ ስለዘር ማጥፋት ምንም ግንዛቤ በሌላቸው ፖለቲከኞችዋ፣ ታጣቂዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናትም አገር ሆናለች። እኔ በግድያው እስካልተካፈልኩ ድረስ ከደሙ ንፁህ ነኝ እየተባለ ነው።

ዛሬ በወለጋ በሚፈጸሙ ወንጀሎች በማንኛውም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት፣ ነገ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ባለማስቆማቸው ምክንያት ብቻ ታስረው በምዕራባዊያን እስር ቤት ሊወረወሩ እንደሚችሉ የነገራቸው ሰው ያለ አይመስለኝም። ለዛሬው በዚህ እናብቃና በክፍል አራት የዘር ማጥፋት ዓይነቶችን እንወያያለን።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የዋይኤችኤም የማማከርና የኮሙዩኒኬሽን ኤጀንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

ፅንፈኝነት እንዴት ይፈጠራል? ማርከሻውስ ምንድነው? (ክፍል ሁለት)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...