Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርእንደ ሥልጣን ሥልጣኔም ትኩረት ይሰጠው (የጉሙዝ ብሔረሰብን እንደ መነሻ)

እንደ ሥልጣን ሥልጣኔም ትኩረት ይሰጠው (የጉሙዝ ብሔረሰብን እንደ መነሻ)

ቀን:

በአብረሃም ይሄይስ

ከ1990 እስከ 1995 ዓ.ም. መጨረሻ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ሦስት ወረዳዎች በመንግሥት ሠራተኛነት የሠራሁ ሲሆን፣ ከ17 ዓመታት በኋላ በ2012 ዓ.ም. ማብቂያ አካባቢ ወደ ሠራሁባቸው አካባቢዎች ማለትም ቡለን፣ ድባጢና ማምቡክ ከተሞች ለሥራ በተንቀሳቀስኩበት ወቅት ከ20 ዓመታት በፊት በእንጨትና በጭቃ የተሠሩ የሴክተር መሥሪያ ቤት ቢሮዎች ወላልቀው እስካሁን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንና መንገዶቹ እስካሁን ፒስታ መሆናቸውን ስመለከት፣ (በመሠራት ላይ ያለው ከቻግኒ ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከሚወስደው እጅግ ዘመናዊ አስፋልት ውጪ) ብዙ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ልጆች በከፍተኛ ተቋማት የተማሩ ቢሆኑም፣ እስካሁን መጨረሻቸው የመንግሥት ሹመትና ሠራተኝነት መሆኑን ስገነዘብ፣ አንዳንዶቹም ሥራ አጥ ሆነው በቀንና በምሽት በቡድን በቡድን ሆነው ቆመው ስመለከት፣ ከተሞቹ ከ20 ዓመት በፊት ከክልሉ ሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር በሚመጡ ባለሙያዎች የቅየሳ ሥራ እንደተከናወነባቸው ባውቅም የጠበቅኩትን አዎንታዊ ለውጥ በትንሹም ቢሆን ባለማየቴ፣ እንዲሁም በእኩይ አስተሳሰብ በተገነባው ሕወሓት ሴራ (እንዲህ ለማለት መረጃዎች ስላሉኝ) በዋናነት ከጎረቤቱ ከአማራ ብሔርና ከኦሮሞ ብሔር ወንድሞቹ ጋር የገጠመው የእርስ በርስ ግጭት መነሻ፣ በጉሙዝ ብሔረሰብ ላይ ከሥልጣን እኩል በሥልጣኔ ላይ አለመሠራቱ ነው የሚል ሐሳብ ኖሮኝ ነው ይህን የግል አመለካከት ለመሰንዘር የዳዳሁት፡፡

ከ1983 ዓ.ም. በኋላ አገራችን በተለየ ርዕዮተ ዓለም መተዳደር መጀመሯ፣ ከቀደሙት የመንግሥት ሥርዓቶች በተሻለ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተሻለ ዕውቅና መስጠቷ ይታወቃል፡፡ በዚህም ለዘመናት ተረስተው የነበሩ ብዙ ብሔረሰቦች ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውንና እምነታቸውን አስተዋውቀዋል፣ አዳብረዋል፡፡ ከሁሉ በበለጠም ልጆቻቸውን በሦስቱም የመንግሥት አካላት ላይ አሳትፈዋል፡፡

በ1987 ዓ.ም. በፀደቀው ሕገ መንግሥት ስለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት በሚገልጸው አንቀጽ 39 (1-5) ሆነ በአንቀጽ 41 ስለኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና የባህል መብቶች በሚገልጹ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይበልጥም በማደግ ላይ ያሉ ሕዝቦች የሥልጣን ባለቤትነት ላይ እንጂ፣ የሥልጣኔ ባለቤት እንዴት እንደሚሆኑ አጽንኦት ሰጥቶ ባለመዘገቡ ብዙው ትኩረት ሥልጣን ማከፋፈል ላይ ብቻ ነው፡፡

በመሆኑም ከነበረኝ ተሞክሮ በመነሳት የሚከተለውን ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡

የጉሙዝ ብሔረሰብ ነባራዊ እውነታ (እስካሁን ያለ)

እጅግ ለም በሆነ ቦታ የሰፈረና የራሱ የሆነ እጅግ የሚያኮራ ባህል ያለው በመሆኑ፣ ለብዙ ነገሮች ጥቅም መስጠት የሚችለው የቀርከሃ ደን (ምርት) በብዛት ያለበት፣ ከዕለት ጉርሱ በዘለለ ተጨማሪ ምርት ማምረት ልምዱ ያልሆነ፣ ሴቶች ከወገብ በላይ ልብስ የማይለብሱ (ወደ ከተማ ከገቡት ውጪ)፣ በአደንና በባህላዊ ማዕድናት ማምረት ላይ የተሰማራ፣ በእጅ ከመቆፈር በዘለለ በቀላል ግብርና ላይ እንኳ ያልተሰማራ (በበሬ ማረስ፣ ከብት ማርባት፣ ዶሮ ማርባት)፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በበቂ ሁኔታ ያልተቀላቀለ፣ በቀስት እንስሳትን ከማደን በዘለለ ለቂም በቀል እስካሁን ቀስትን እየተጠቀመበት ያለ መሆኑ ነው፡፡

በመሻሻል ላይ የነበሩ እውነቶች

በወረዳ ከተሞች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች በቀበሌዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ጤና ኬላዎች መገንባትና በባለሙያዎች ለመሙላት ጥረቶች መኖር፣ ብዙ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት መግባት፣ በመንግሥት መዋቅር ይበልጥ በሹመት፣ በፖሊስና በመምህርነት መሳተፍ፣ ቀበሌን ከቀበሌ የሚያስተሳስሩ መንገዶች መሠራት (ጥርጊያ መንገዶች) መጀመር፡፡

የመንግሥት ርዕዮተ ዓለም (ፖለቲካው) ያለ አግባብ በመተርጎሙ ያስከተላቸው መጥፎ ጎኖች

እኔ በነበርኩበት ወቅት በወረዳዎቹ ባሉ የሹመት ቦታዎች የክልሉ ተወላጅ የሚባሉ ዜጎችን በኮታ ወንበር ማደል እንደ ትልቅ ድል ተወስዷል፡፡

ለምሳሌ በወንበራ ወረዳ የጉሙዝ፣ የሺናሻና የኦሮሞ ተወላጆች በብዛት ስላሉ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ጉሙዝ፣ ምክትሉ ሺናሻና የፖለቲካ ዘርፍ መሪ ኦሮሞ ነበር፡፡ የሴክተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎችም ከእነዚህ ብሔሮች አይወጡም፡፡

በቡለን ወረዳ የሺናሻ ብሔረሰብ በብዛት ስላለ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ሺናሻ፣ ምክትሉ ጉሙዝ፣ ሌሎች ሥራ አስፈጻሚዎችና የሴክተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ከእነዚህ ብሔር የተውጣጡ ናቸው፡፡ በዳንጉር ወረዳ የጉሙዝ፣ የሺናሻ፣ የአገውና የአማራ ብሔር ተወላጆች በብዛት ስላሉበት የወረዳው ሊቀመንበር ጉሙዝ፣ ምክትል ሺናሻ፣ ጸሐፊ አገው ወይም አማራ ይሆኑና ሌሎች ሥራ አስፈጻሚዎችና የሴክተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ከእነዚህ ብሔሮች እንዳይወጡ ይደረግ ነበር፡፡

ከእነዚህ እውነቶች መገንዘብ የሚቻለው የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላትን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ብቻ መሰግሰግ እንደ መጨረሻ ግብ ማየት (የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጥያቄን የመለሰ መምሰል) ነው፡፡

ጉሙዝን ጨምሮ በርታ፣ ሺናሻ፣ ማኦና ኮሞ የክልሉ (የሚኖሩበትን አካባቢ) ባለቤትነት የራሳቸው ብቻ እንደሆነ ማየትና ሌሎችን እንደ መጤ መቁጠር፣ በመንግሥት ሹመቶች ከአምስቱ ብሔረሰቦች ውጪ ላሉ ኢትዮጵያውያን ዕውቅና አለመስጠት ወይም ለይስሙላ እየቆነጠሩ ሹመት መስጠት፣ በመንግሥት ውሳኔዎች የሌሎች ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ሐሳብና ፍላጎት የሚደመጥበት አሠራር አለመዘርጋት ነበር፡፡

መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች (ሥልጣኔ)

የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውና እምነታቸውን የማሳደግ መብት እንደተሰጣቸው የመሠልጠን መብትም አላቸው፡፡

ለምሳሌ አካባቢው እጅግ ለም በመሆኑ በእጅ ከመቆፈር ቢያንስ በበሬ እንዲያርሱ ቢደረግ (መሬቶችን ለኢንቨስተር ከመስጠት በዘለለ ለነዋሪዎችም እንዲያርሱ ማድረግ፣ ማስተማር ማሠልጠን)፣ በየወረዳው ባሉ ማክስማ (ማኅበረሰብ ክህሎት ሥልጠና ማዕከል) ለጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ልዩ ትኩረት በመስጠት ወቅታዊና አስፈላጊ ሥልጠናዎችን መስጠት (ይህ ማዕከል አሁን ይኑር አይኑር አላውቅም)፡፡

ለከብት ርቢና ለዶሮ ዕርባታ የሚመች አካባቢ በመሆኑ ከብትና ዶሮ እንዲያረቡ ቢደረግ፣ ከገበያ ጋር ማስተሳሰርም ልክ እንደ ዕርባታው ትኩረት ቢሰጠው፣ የቀርከሃ ምርት ላይ በተደጋጋሚ ፕሮጀክቶች እየተቀረፁ ለአካባቢውም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቢገለጽም፣ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ ባለመሆኑ (ባለማየቴ) ምርቱ በየዓመቱ እየተቃጠለ እንዳይባክን ልዩ ትኩረት ቢደረግበት፣ በባህላዊ ደረጃ እጅግ በጣም ጥቂት የማኅበረሰቡ አባላት በንብ ማነብ ቢሰማሩም ከአካባቢው ዕምቅ አቅም አንጻር መጠቀስ አይችልም፡፡ እዚህ ላይም ትኩረት ቢደረግ ተገቢውን ሥልጠና በመስጠት ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በብዛት በመስጠት በማር ምርት ራሳቸውንም ሆነ አካባቢያቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ ይቻላል፡፡

በባህላዊ የወርቅ ማዕድን ፍለጋና ማምረት ቢሰማሩም ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ዕውቀታቸውን በሚያሻሽል መንገድ የቴክኖሎጂ ዕገዛ ስላልተደረገላቸው ቢሻሻል፣ (ዕምነበረድና ድንጋይ ከሰል ምርት ላይም የክልሉ ነዋሪዎች በቴክኖሎጂ ታግዘው የሚያመርቱበት መንገድ ቢመቻች፣ ለዘመናት ወርቅ ፍለጋና ማምረት ላይ ያዳበሩትን ባህላዊ ዕውቀት ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር የሚያስተሳስሩ ሥልጠናዎችን ማዘጋጀትና መስጠት፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጋር ተባብሮና ተጎራብቶ እንዲኖር የተለየ ድጋፍ ቢደረግ (አሁን ባለው የፖለቲካ ዕሳቤ ለጠላት ሐሳብ በቀላሉ የሚጋለጡ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ጎረቤቶቻቸውን እንደ ጠላት፣ ለዘመናት ሲጨቁኑዋቸውና ሲበዘብዟቸው እንደኖሩ የሚያስቆጥር አመለካከት በመሆኑ)፣ የብሔረሰቡ ነዋሪዎች በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲበለፅጉ መሠረተ ልማቶች ቢስፋፉ፣ የብሔሩ አባላት ከመንግሥት መዋቅር ውጪ በግል ሥራ (በንግድና የመሳሰሉ ዘርፎች) ላይ የሚሰማሩበት ሁኔታ ቢመቻች፣ ልጆቻቸው ከአካባቢያቸው ውጪ ልክ እንደ ሌሎች ብሔሮች በተለያዩ የአገሪቱ ዜጎች እንዲኖሩ የማድረግ ሥራዎች ቢሠሩ፣ በአካባቢው ያሉ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የአካባቢውን ማኅበረሰብ የወቅቱን ችግሮች ፈቺ በሆኑ ፕሮግራሞችና ያለውን ዕምቅ ሀብት ወደ ሀብት በሚቀይሩ ትምህርቶች እንዲያተኩሩ ቢደረግ፣ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ይበልጥም በጋምቤላ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በሐረሪ፣ በደቡብ ክልሎች የተለያዩ ዞኖች ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ችግሮች ስለሚኖሩ፣ አገርን የማሳደግ (የማበልፀግ) ድርብና የትውልድ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ‹‹ከአንጀት ካለቀሱ ዕንባ አይገድም›› እንዲል የአገሬ ሰው፣ ሰፋ ያለ ጥናት በማድረግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔዎችን እንዲያመጣ በማሳሰብ አስተያየቴን በዚህ አጠናቅቃለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...