Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንደ ቃል ከባድ የለም!

ከጀሞ ወደ ፒያሳ ጉዞ ሊጀመር ነው። “እዚህ ጋ ጠጋ! ጠጋ! ‘ማዘር’ እዚህ ተጠጉላቸው…” ተለምዷዊ የወያላ ቀጭን ትዕዛዝ ናት። ዛሬ ግን መብት አስከባሪ ገጥሞታል። “አልጠጋም! ለምንድነው የምጠጋው? የከፈልኩህ እኮ ለአንድ መቀመጫዬ ብቻ ነው…” ተጠጊ የተባለችው ወይዘሮው ብልጭ ብሎባታል። “ምናለበት በሁለቱም መቀመጫችን ተዘፍዝፈን ወያላና መንግሥትን ከማማት እርስ በርስ ብንተባበር? የእኛ ነገር ተቀምጦ ሰማይ ቀዶ መስፋት ብቻ…” ወያላው አጋዥ ለማግኘት አሳባሪ መንገዶችን በሙሉ በመጠቀም ላይ ነው። “እዚያ ያስለመዱህ ይጠጋጉልህ፣ ጊዜው የመጠጋጋት ነው ብለህ ከሆነ አናምንበትም…” ወይዘሮዋ እንደ እንዝርት ሾራለች። ሹረቷን ትክ ብሎ እያየ ያዞረው ደግሞ፣ “ምናለበት ብትጠጋና ብንቀሳቀስ? የእኛ ነገር እኮ ይገርማል…” ይላል አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት። ከኋላችን ሦስተኛው ረድፍ ላይ ደግሞ፣ “ልክ ነሽ እንዳትሰሚው…” እያለ አንድ ጎልማሳ ያጉተመትማል። ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር!

አጠገቡ ‘ማች በማች’ የለበሰች ዝንጥ ያለች ወጣት ቦርሳዋን እንቅ አድርጋ ታቅፋ አልሰማሁም አላየሁም ያለች ትመስላለች፡፡ ከመጨረሻ ወንበር አንድ አዛውንት፣ አንድ ጎልማሳና ዕድሜያቸው በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገመቱ ወጣቶች ጎን ለጎን ተሰይመዋል። ወያላው እልህ ይዞት አጠጋግቶ ሊያስቀምጣቸው የነበሩትን ተሳፋሪዎች አንዱን ጎማ ላይ፣ አንዱን ከጋቢና ወንበር ጀርባ፣ ሌላውን ሞተር ላይ አደላድሎ አስቀምጦ “ሳበው!” ብሎ በሩን ከረቸመ። ወይዘሮዋ በድል አድራጊነት ስሜት ፈገግ ብላ፣ “እኛን የሰለቸን ከእናንተ ጀምሮ ጉድለታችንና ክፍተታችንን ምክንያት አድርጎ ሙሴያችሁ ነኝ ተቀበሉኝ፣ ተከተሉኝ፣ እመኑኝ የሚለን ሐሰተኛ ነብይ ብዛት ነው። ራሳችን ለራሳችን መብት ብንቆም ከመጀመሪያው መቼ በየአቅጣጫው ነጂ ይልክብን ነበር…” ብላ በራሷ ዓለም ጠፋች። ነገሩ ከምኔው የነጂና ተነጂ አተካራ ውስጥ እንደገባ ፈጣሪ ይወቀው!

ጉዟችን ተጀምሯል። ለምግብነት አልደርስ ስላለቅ የበጋ ስንዴ ጨዋታ የጀመሩ አሉ። “እኔ መጀመሪያ ‘መቼስ በኑሯችን መቀለድ እንጂ መደሰት ስለማናውቅ እናጋንናለን’ ብዬ ትቼው ነበር ለካ እውነት ነው…” እያለ፣ ከአዛውንቱ አጠገብ የተቀመጠው ሞላ ያለ ተክለ ሰውነት ያለው ጎልማሳ ያወራል። “ምኑ ነው እውነት?” አዛውንቱ አፋቸውን ማንቀሳቀስ የደከማቸው ናቸው። “የበጋ ስንዴው ቶሎ ደርሶ ለምን በቶሎ ዳቦ አይሆንም ሲባል የሰማሁት ተረብ እውነት መሆን እያደረ ገርሞኛል…” አለ ጎልማሳው። “ኤድያ! አትተወውም?” አዛውንቱ ነገሩን በአጭሩ ለመቅጨት ትግል የያዙ ይመስላሉ። “ምኑን ነው የምተወው?” ጎልማሳው መነዝነዙን ተያያዘው። “ስንዴውንም ሥራ ፈቶ የሚያወራውንም፣ መንገዱንም፣ ታክሲውንም፣ ተረቡንም፣ መንግሥትንም ሆነ ሁሉንም መተው ተለማመድ እንደ እኔ…” ብለው ምራቃቸውን እግራቸው ሥር ተፉ። ወያላው አበደ። “ምን ነካዎት ትልቅ ሰው አይደሉም እንዴ? እንዴት ሕዝብ መሀል ይተፋሉ?” ተንጫጫ ወያላው። ሥርዓት አስከባሪ መሆኑ ነው! 

ሁላችንንም ተራ በተራ ሲያየን ቆይቶ፣ “አሁን እናንተ አይደለም ተሠልፋችሁ መዋል፣ ምንስ ብትሆኑ ይታዘንላችኋል?” እያለ ወያላው ፊቱን ሲያዞር፣ “ምን ያበሳጨዋል ይኼ፣ ይኼው ዙሪያችንን የሌለ መመርያና ነቀፌታ፣ ሕግና ትዕዛዝ ያለጠፍክበት ቦታ የለም። አትትፉ የሚል ግን አለ? ንገረኛ፣ ከየትኛው ሕግ ነው ጠቅሰህ የምትከሰኝ? ማታ በዜና ተመርቆ ተከፈተ ተብሎ የታየን አስፋልት መንገድ፣ ጠዋት ለማኝ ሳይቀድመው ተነስቶ ፊኛውን የሚያስተነፍስበት የዕድገት ምቀኛ ሳይታሰር እኔ ልታሰር ነው? ወይስ ስንቱ በዕድሜያችንና በህልማችን ተጫውቶ አላምጦ እየተፋን መኖራችን አናዳጅ ሆኖ ተገኝቶ ነው እንደ ቻይና አትትፉ የሚል ትዕዛዝ የወጣው?” ብለው አዛውንቱ ባሱ። ይኼን ጊዜ ጎን ለጎን ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ፣ “ወይ ኢቲዮ ቻይና፣ በስማችሁ ስንቱን እንስማ?” ሲል ሰማን፡፡ ምን የማይሰማ አለ!

ወያላው ሞተር ላይ ያስቀመጠው ተሳፋሪ ሚጢጢ ስልኩ ትጮሃለች። በስንት ስቃይ በስንት አሳር ካለችበት ታስሳ ወጣች። “ይኼ ሰውዬ ነዳጅና የከበሩ የተፈጥሮ ማዕድናት ላይ ቢሠራ ያው መጀመሪያ ራሱን፣ ከዚያ ምናልባት ራርቶ አገሩን ሊጠቅም የሚችል ሰው ይመስላል…” ይላል ከጎኔ የተቀመጠው። ባለ ስልኩ “ሃሎ!” የጆሯችን ታንቡር እስኪበሳ መጮህ ጀመረ። “ይሰማኛል፣ ቅድም እኮ ተቋረጠ። ምን ይታወቃል ሚሊዮን እያልኩ ሳወራ ቴሌ ትን ብሎት ይሆናላ››› ሃ…ሃ…ሃ…” ገልመጥ ገልመጥ እያለ ያየናል፣ ቀጥሏል። “ስድስት ሚሊዮን እጄ ላይ አለ። ቀሪው እህል እጃችን ሲገባ በባንክ ትራንስፈር ይደረግልሃል ብለውኛል። አዎ ተፈራርመናል እንጂ…” እያለ ስለሥራው ቀጠለ። ተሳፋሪዎች እያልጎመጎሙ ወሬ ጀመሩ። “እህም ወይ ሚሊዮን እንዲህ ሳናስበው አፋችን ይግባ?” አለች ከወያላው የተናቆረችው ወይዘሮ። “እኛ የአችን ነገር መቼ ቸገረን፣ የሆዳችን እንጂ የሚያንገዋልለን። እንይዘዋለን ባዶ። መቶ ብር ብን ስትል አትራራ። አብሮ በልቶ ጠጥቶ የሚንሸራተተው ወዳጅ በዛ ብለን ሳንጨርስ፣ በላባችን የምናመጣው ገንዘብ ረድኤተ አልባ መሆኑ ደግሞ…” ትላለች አጠገቧ የተቀመጠች ደርባባ። ሦስተኛ ረድፍ ላይ ደግሞ ያ ጎልማሳ፣ “እኔ ግን  እንደ ምንም ብዬ ፌስታል ነው ማምረት ያለብኝ። አይመስልሽም?” ከመነጽር እስከ አልቦ በ‘ማች’ ያበደችውን ተሳፋሪ አስጨነቃት። ዞር ብላ “አልገባኝም?” ከማለቷ፣ “በዚህ አያያዝ እንደ ዚምባቡዌ በዘንቢልና በፌስታል ገንዘብ ተሸክመን ጉልት መውጣታችን አይቀርማ፡፡ ዋናው ማደጋችን ነው…” ሲላት እንሰማለን። ሰው ግን እንዴት አዙሮ ተኳሽ ሆኗል!

ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። ወያላችን አንድ ሚሊዮነር ሞተር ላይ አስቀምጦ እየተጓዘ መሆኑን ሲሰማ የባሰውን ተናደደ። “ወይ አይጠቀሙ፣ ወይ አያስጠቅሙ፣ ወይ አይጠጉ፣ ወይ አያስጠጉ…” ይላል። ነጋዴው ስልኩን እንደ ቀጠለ ነው። ጋቢና ከተሰየሙት ተሳፋሪዎች አንዱ ወያላውን ሰምቶት ኖሮ፣ “እባክህ በተጠጋጋ ብቻ አይደለም፣ ዕድል ያስፈልጋል። ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ሲሄድ የሚታለፍ አለ፣ ወይም የማይታይ። እንደ እኔ ያለው ደግሞ አለላችሁ በትንኝ የሚጋለጥ። ሌብነትም እኮ ‘ታለንት’ ይጠይቃል…” አለ። “በቃ እኛ ግን መጠቃቀም ወይም መጠጋጋት ስንባል የሚታየን ሌብነት ብቻ ነው? የሥራ ዕድል ማግኘት፣ በጎ በሆነ መንገድ መረዳዳት አይታየንም?” ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠችው አቋርጣ ገባች። “ሆ…ሆ… መጀመሪያ ያለ ‘አይዲ’ የሚያስጠጋህ አለ እንዴ? የለም እኮ፡፡ እንደ እኛ ዓይነቱ ከምኑም የሌለበት ወይ ግንባር የለው ወይ የሚያጋጨው ብር የለውም፡፡ ዝርዝር ሳንቲሙን እያንቃጨለ ዕድሜው በታክሲ ሠልፍ ያልቃል። ምናልባት ከቀናህ ደግሞ አገርህ በሀብት ከ184 አገሮች 171ኛ ሆነች የሚል ዜና ቢመረቅልህ ነው። በማትሞቀው እሳት አገርህ ደረጃ ስትመደብ፣ አንተም ቶሎ ብለህ ምድብህን ማስተካከል ነው…” ከጎኔ የተሰየመው ይለፈልፍብኛል። ይኼን ሲል የሰማው ሌላ ጎልማሳ “ማስተካከል ካልቻልክስ? ምድቡ የሞት ምድብ ከሆነስ?” ብሎ መጣብን። “አሁን ይኼ ጥያቄ ነው? ልማታዊ ኑሮ ካቃተህ ልማታዊ ሞት አለልህ…” ብሎ ወሽመጡን በጠሰው። “ልማታዊ ኑሮን እያየነው ነው፣ ልማታዊ ሞት ደግሞ እንዴት ያለ ነው?” ሲሉ አዛውንቱ፣ “ለመንግሥት ሳያሳሙ፣ ቀባሪ ሳያስቸግሩ ‘ሳይለንት’ ሆኖ ማለፍ ማለት ነዋ። ሌላ ምን ይሆናል? ወይ ስም ሳያስነሱ መመንተፍ ወይ ተረስቶ ማለፍ ነው…” ብትል ቆንጂት፣ ሁሉም ተሳፋሪዎች ተገርመው እየተገላመጡ አዩዋት። ብሶት በታረዘና በተጠማ መሀል ብቻ ነው ያለው ግን ማን ይሆን!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። “ያዝ እንግዲህ! ወሬኛ ቢሸፍት ከፌስቡክ አያልፍም…” እያለ ወያላው አዲስ ርዕስ ጀመረ። “እኮ በስተርጅና ከዚህ ሁሉ የደም ታሪክና የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ እንደገና መተነኳኮስ ተጀመረ?” ሲሉ አዛውንቱ ከጎናቸው የተሰየመው ጎልማሳ ቀበል አድርጎ፣ “ተናግሮ ሊያናግረን ነው። ኃላፊነት የጎደለውን የሰብዕና አምልኮ ናፋቂ ፉከራና ቀረርቶ በሰማን ቁጥር ደንፍተንማ አይሆንም…” ይላል። “ኧረ ተወኝ እባክህ፣ ላወቀበት እኮ ቃል ከባድ ነበር፡፡ ነገር ግን ቃል አክባሪነት መከነብን…” እያሉ አዛውንቱ ሲናገሩ ወያላው ደግሞ “መጨረሻ!” ብሎ በሩን ከፈተው። በዚህ መሀል ነበር አንዱ ወፈፍ ያደረገው የሚመስል፣ “…ወገኖቼ የድሮ ሰዎች ቃል አይረሳ፣ በፊት እኮ መማር ያስከብራል አገርን ያኮራል እያሉ ነበር ለአገር ፍሬ ለማፍራት የተጉት፡፡ አሁን ግን ሌብነት ጌጥ ሆኖልን መስረቅ ያስከብራል ቤተሰብ ያኮራል እየተባለልን ነው…” እያለ ሲናገር ደነገጥን፡፡ ወይ ጊዜ? ቃል ለካ ከባድ ነው የሚባለው በከንቱ አይደለም፡፡ መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት