Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገሪቱ ባንኮች በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 2.3 ትሪሊዮን ብር አጠቃላይ ሀብት አስመዘገቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱት ዘርፎች መካከል ግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የአገልግሎት ዘርፍ ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ ያለማቋረጥ በማደግ ላይ የሚገኘው ደግሞ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ የባንክ (የፋይናንስ) አገልግሎት ዘርፍ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲያስመዘግብ የነበረውን ከፍተኛ ዕድገት፣ አገሪቱ በተለያዩ ቀውሶች በተናጠችበት የ2014 የሒሳብ ዓመትም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ማስቀጠል ችሏል። የአገሪቱ ባንኮች በ2014 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ፣ የሰጡት ብድርና ሌሎች የሥራ አፈጻጸሞቻቸው ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ብልጫ የታየበት ሲሆን፣ ከትርፍ አንፃርም የ2014 ሒሳብ ዓመት አፈጻጸማቸው ከቀደመው ዓመት የተሻለ መሆኑን ሪፖርተር የተመለከታቸው የየባንኮቹ ዓመታዊ ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ 

ሁሉም የመንግሥትና የግል ባንኮች የትርፍ ምጣኔያቸው ይለያይ እንጂ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመትም በአትራፊነታቸው የቀጠሉ ሲሆን፣ የሀብት መጠናቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግም በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 2.3 ትሪሊዮን ብር አጠቃላይ ሀብት ማስመዝገብ ችለዋል። ባንኮቹ ያስመዘገቡት አጠቃላይ 

የሀብት መጠን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀርም በ21 በመቶ ብልጫ እንዳለው መረጃዎቹ ያመለክታሉ።

ሁሉም ባንኮች የሰበሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 1.6 ትሪሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ ባንኮቹ በ2013 የሒሳብ ዓመት አሰባስበውት የነበረው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 1.4 ትሪሊዮን ብር እንደነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2013 የሒሳብ ዓመት ሪፖርት ያመለክታል፡፡ የባንኮቹ የቅርንጫፎች ቁጥርና የባንክ ተገልጋዮችን የሚመለከተው መረጃም ዕድገት የታየበት ሲሆን፣ ከአንድ በላይ የቁጠባ ሒሳብ ደብተር ያላቸው የባንክ ደንበኞች መኖራቸውን ታሳቢ በማድረግም በባንኮቹ የቁጠባ ደብተር ያወጡ ደንበኞች ቁጥር ከ82 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ከመረጃዎቹ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ የሁሉም ባንኮች ቅርንጫፎች ቁጥር በ2014 መጨረሻ ላይ 8,242 የደረሰ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ከ17 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው መረጃው ያመለክታል፡፡ ሁሉም የመንግሥትና የግል ባንኮች በ2013 የሒሳብ ዓመት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ያሏቸው ቅርንጫፎች 7,344 እንደነበር ይታወሳል፡፡ 

የባንኮቹን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም የሚያሳዩት ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ሁሉም ባንኮች በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የሰጡት የብድር መጠን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዕድገት አሳይቷል። የግልም ሆኑ የመንግሥት ባንኮች በ2014 የሒሳብ ዓመት የሰጡት የብድር መጠን ከ353 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ይህ የብድር መጠን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ዕቅድነት የታየበት እንደሆነ ከመረጃዎቹ ለመረዳት ተችሏል።

የ16ቱን የግል ባንኮች አፈጻጸም ከሚያመለክተው የ2014 ሒሳብ ዓመት ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ በሒሳብ ዓመቱ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከተሰጠው ብድር ውስጥ የግል ባንኮች ድርሻ ከመንግሥት ባንኮች የብድር አቅርቦት ብልጫ ይዟል። ከ16ቱ የግል ባንኮች ውስጥ ሰባቱ ባንኮች በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የሰጡት የብድር መጠን 150.47 ቢሊዮን ብር መሆኑን መረጃው ያመለክታል። ከሰባቱ የግል ባንኮች መካከል አዋሽ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክና የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንኮች ከፍተኛ ብድር በመስጠት በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህም መሠረት አዋሽ ባንክ 42.1 ቢሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ ባንክ 41.2 ቢሊዮን ብር፣ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ 28.9 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ሰጥተዋል፡፡

ከተጠቀሱት ሦስት ባንኮች በተጨማሪ፣ ዳሸን ባንክ 14.7 ቢሊዮን ብር፣ ኅብረት ባንክ 9.17 ቢሊዮን ብር፣ ቡና ባንክ 7.25 ቢሊዮን ብር፣ ዘመን ባንክ 7.15 ቢሊዮን ብር አዳዲስ ብድሮችን እንደሰጡ ሪፖርተር ከተመለከታቸው መረጃዎች ለማወቅ ችሏል።

ሁሉም ባንኮች በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ1.6 ትሪሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ በ16ቱ የግል ባንኮች የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ደግሞ ከ807 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን መረጃው ያመለክታል፡፡ ይህም በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከተደረሰበት አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ብልጫ ያለውን ማሰባሰብ የቻሉት የግል ባንኮች ናቸው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከ1.4 እስከ 45.6 ቢሊዮን ብር የሚደርስ አዳዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ከቻሉት 16 የግል ባንኮች ውስጥ አዋሽ ባንክ 45.6 ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ቀዳሚው ደረጃ ይዟል። አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ 33.07 ቢሊዮን ብር፣ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ 25.6 ቢሊዮን ብር፣ ዳሸን ባንክ 16.53 ቢሊዮን ብር፣ ኅብረት ባንክ 10.06 ቢሊዮን ብር፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ደግሞ 9.1 ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችለዋል፡፡ 

የባንኮቹ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብን የሚያመለክተው የመረጃው ክፍል እንደሚያስረዳው፣ ከ16ቱ የግል ባንኮች ውስጥ የተቀማጭ ገንዘብ ክምችታቸውን ከአንድ መቶ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻሉት ሁለት ባንኮች ናቸው። የሌሎች ስድስት ባንኮች አጠቀላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከ45 እስከ 87 ቢሊዮን ብር መድረሱን መረጃው ይገልጻል።

የተቀማጭ ገንዘባቸውን መጠን ከአንድ መቶ ቢሊዮን ብር በላይ ያደረሱት ሁለቱ ባንኮች አዋሽና አቢሲኒያ ሲሆኑ፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ አዋሽ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 147.6 ቢሊዮን ብር ሲያደርስ፣ አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ 121.8 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ አዋሽ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለው በ2013 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ሲሆን፣ አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለው በዘንድሮ የ2014 የሒሳብ ዓመት ነው፡፡ አቢሲኒያ ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት የነበረው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 88.7 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ አዋሽ ባንክ ደግሞ 101.9 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችሎ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች