Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቀንጢቻ ማይኒንግ ታንታለምን ጨምሮ ለሌሎች ማዕድናት ምርመራ የተሰጠው ፍቃድ ተቋረጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማዕድን ሚኒስቴር ቀንጢቻ ማይኒንግ ለተባለው ድርጅት ታንታለምን ጨምሮ የኒዮቢየም፣ ሊትየምና ሌሎች ተዛማጅ የብረት ማዕድናት ምርመራ የሰጠው ፍቃድ ከሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ማብቃቱን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሳምንት አስቀድሞ ለድርጅቱ በጻፈው ደብዳቤ እንዳስታወቀው፣ የኦሮሚያ ማዕድን አክስዮን ማኅበር የታንታለም፣ የኒዮቢየም፣ ሊትየምና ሌሎች ተዛማጅ የብረት ማዕድናት ምርመራ ፈቃድ ከሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለቀንጢቻ ማይኒንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ተላልፎ ነበር፡፡

ለድርጅቱ የተሰጠው ፍቃድ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በጉጂ ዞን ሰባቦሩ ወረዳ ቀንጢቻ አካባቢ ከላይ የተጠቀሱትን ማዕድናት ተገቢውን የማዕድን ምርመራ ሕግጋት ተከትሎ በአንድ ዓመት ውስጥ የምርመራ ሥራውን እንዲያከናውን የሚፈቅድ ነበር፡፡

የማዕድን ሥራዎች አዋጅ ቁጥር 678/2010 እንደሰፈረው ስድስት ዓይነት ፈቃዶች ሲኖሩ፣ የቅኝት፣ የምርመራ፣ ይዞ የመቆየት፣ ባህላዊ የማዕድን የማምረት ሥራ፣ የአነስተኛ ደረጃ ማዕድን የማምረት ፍቃድ አንዲሁም የከፍተኛ ደረጃ ማዕድን የማምረት ሥራ ፍቃድ ናቸው፡፡

ማዕድን ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ድርጅቱ ከሰኔ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የፍለጋ ፍቃድ ቢያገኝም፣ ነገር ግን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባፀደቀለት የሥራ መርሐ ግብር ምርመራውን ካለማከናወኑ በሻገር በተቀመጠው የጊዜ ቀነ ገደብ በተሰጠው ፍቃድ ለመሥራት የገባው ተግባራት አለመጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

በሚያዚያ ወር ለድርጅቱ በላከው ደብዳቤ የማዕድን ምርመራ ሥራውን በቀነ ገደቡ መሠረት እንዲያጠናቅቅ መግለጹን አስታውቆ፣ ማዕድን ሚኒስቴር ፕሮጀክቱን ለመደገፍ ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን ፕሮጀክቱ ለመደገፍና የሥራ ዕቅዱን አፈጻጸም መዘግየትን በተመለከተ ግልፅ ማሳሰቢያ መስጠቱን አስታውቆ፣ ሆኖም ኩባንያው የማዕድን ምርመራውን በተመለከተ የተሰጠውን ኃላፊነት ባለመወጣቱ ከዓመት አስቀድሞ የተሰጠው ፍቃድ ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. መጠናቀቁን አመላክቷል፡፡

በመሆኑም ቀንጢቻ ማይኒንግ ድርጅት ታንታለም፣ የኒዮቢየም፣ ሊትየምና ሌሎች መሰል የብረት ማዕድናትን አስመልክቶ የወሰደውን የማዕድን ምርመራ ፍቃድ በተሻሻለው የማዕድን አዋጅ ቁጥር 678/2002 አንቀፅ 46 አና 79 መሠረት መሻሩን የማዕድን ሚኒስቴር ድርጅቱን ጠቅሶ በጻፈው ደብዳቤ ተገልጿል፡፡

የቀንጢቻ ታንታለም ማዕድን ክምችት እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ውስጥ በሩሲያ የጂኦሎጂ ባለሙያዎች የተገኘ ሲሆን፣ በማዕድን ክምችቱ ከታንታለም ውጪ የዩራኒየምና ሊቲየም ማዕድናት እንደሚገኙም ተረጋግጧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች