አንዳንድ ጥበቃዎች የተሰጣቸውን መሣሪያ ይዘው እንደሚጠፉ ተገልጿል
በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ዝርፊያዎች የግል ኤጀንሲዎች በሚቀጥሯቸው ጥበቃዎች መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው ይህን ያስታወቀው ሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በከተማው ውስጥ የግል ጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲዎች አማካይነት እየተከሰቱ ባሉት ችግሮች ላይ ባደረጉት ውይይት ላይ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የፀጥታ ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ሀብቴ እንደተናገሩት፣ የ24 ሰዓታትና ሳምንታዊ የባንኮች ዝርፊያ ሪፖርቶች እንደሚቀርቡ ጠቁመው፣ ዘረፋ ከሚፈጽሙት መካከል ጥበቃዎች ይገኙበታል፡፡
ከሚቀርበው ሪፖርት በቀን አንድ የግል ባንክ መዘረፉን የሚገልጹ መረጃዎች እንደሚደርሳቸው የተናገሩት አቶ ማስረሻ፣ ዘረፋው የሚፈጸመው በባንኩ ጥበቃዎች መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ወንጀሉ የሚፈጸመው ከውጭ በሚመጡ ሳይሆን፣ ከባንኩ ተቀጣሪ ጥበቃዎች መሀል ዝርፊያውን በሚያቀናጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹የምርመራ ውጤቶች እንደሚያሳዩት፣ በአመዛኙ ወንጀሉ የሚፈጸመው በኤጀንሲዎች በሚቀጠሩ ጥበቃዎች ዘረፋውን እንደሚያቀናጁ አልያም ራሳቸው እንዳሉበት ነው፤›› ሲሉም ከጥበቃዎች መሀል አንዳንዶቹ ገልጸዋል፡፡
ከጥበቃዎች መሀል ከፋይናንስ ተቋም የወሰዱትን የጦር መሣሪያ ይዞ የመጥፋት ችግሮች እንዳሉ ያከሉት አቶ ማስረሻ፣ የጦር መሣሪያዎቹ በአሥር ሺሕ ብር እንደሚሸጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ ብለዋል፡፡
በዘረፋ የተያዙ ተጠርጣሪዎች መረጃ ሲጣራ ሐሰተኛ ዋስ፣ ሐሰተኛ ሰነድ (መታወቂያ) እና ሌሎችም ችግሮች ያሉባቸው ናቸው ተብሏል፡፡
በፋይናንስ ተቋማት በዘረፋ ወንጀል የሚጠረጠሩ ጥበቃዎች ዋሶቻቸው ቀድመው እንደሚሰወሩም ተገልጿል፡፡
ከፖሊስና ከመከላከያ በጡረታና በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ የተሰናበቱ ዜጎች፣ ለጥበቃ የተቀጠሩ ቢኖሩም፣ በጥበቃ አገልግሎት ላይ የሚሠሩት በአመዛኙ ምንም ዓይነት ሥልጠና ያላገኙ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
የዘረፋ ድርጊቱ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች የሚታይ መሆኑንና ከፋይናንስ ተቋማት በተጨማሪ በሌሎች ተቋማት ላይም ይፈጸማል ተብሏል፡፡
ለዚህም የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች የሚንቀሳቀሱበትና የሚተዳደሩበት ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱን አቶ ማስረሻ ገልጸዋል፡፡ በተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ፣ የፀጥታ ተቋማት፣ ፖሊስ፣ ኤጀንሲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ለውይይት ይቀርባል ብለዋል፡፡
ወንጀል ሲፈጸም በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆኑት ተቀጣሪውና ዋስ የሆኑ ግለሰቦች መሆናቸውን የገለጹት አቶ ማስረሻ፣ ረቂቅ ሕጉ ሲፀድቅ ኤጀንሲውም ተጠያቂ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
የጥበቃ ሠራተኞች ክፍያ አነስተኛ መሆን፣ ለመቀጠር የሚያቀርቡት ማስረጃ ትክክለኛ አለመሆን እንደ ችግር ተነስቷል፡፡ በአነስተኛ ዋጋ ለመቅጠር ሲባል ዕድሜያቸው የገፋና የጤና ችግር ያለባቸውን ለጥበቃ የሚመለምሉ ኤጀንሲዎች እንዳሉም ተነግሯል፡፡
ሐሰተኛ ማስረጃ የያዙ ተቀጣሪዎችን ተገቢውን ማጣራት ሳያደርጉ እንደሚቀጥሩ፣ ሐሰተኛ መታወቂያ ጭምር እንደ ዋስትና የሚይዙ ኤጀንሲዎች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡