Wednesday, February 28, 2024

በኦሪገን የደመቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከተጀመረ ስድስተኛ ቀኑን የያዘው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርካታ ትዕይንቶችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ በሻምፒዮናው ላይ እየተካፈለ የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የዓለምን ቀልብ የሳበበትን ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ በሴቶች 10,000 ሜትር፣ በማራቶን በወንዶችና በሴቶች የወርቅ ሜዳልያን በጠዋቱ መሰብሰብ ችሏል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ በሻምፒዮናው በወንዶች ማራቶን፣ በሴቶች 1,500 ሜትርና በወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክል ፍፃሜ ሦስት የብር ሜዳልያን አሳክተዋል፡፡ በተለይ በማራቶን በሁለቱም ፆታ የሻምፒዮናው ክብረ ወሰን ሳይቀር በማሻሻል ጭምር የወርቅ ሜዳልያውን ማሳካት ችለዋል፡፡

Ethiopian-Athletes--Ethiopian-Reporter

ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና መካፈል ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ፣ ከሁለት ወርቅ በላይ ለማምጣት ሰባት ዓመት ፈጅቶባታል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ እ.ኤ.አ. 2015 በቤጂንግ ከተከናወነው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ሦስት የወርቅ ሜዳልያ ያሳካበት ዘመን ነበር፡፡

በወቅቱም በ1,500 ሜትር ሴቶች በገንዘቤ ዲባባ፣ 5,000 ሜትር ሴቶች አልማዝ አያናና በሴቶች ማራቶን ማሬ ዲባባ ነበር ሦስት የወርቅ ሜዳልያ በታሪኩ ማሳካት ችሏል፡፡

በአኅጉርና በዓለም አቀፍ እንዲሁም በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፎ በደበዘዘ ውጤት ሲጓዝ የነበረው ብሔራዊ ቡድኑ፣ በዘንድሮው የ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ ስድስት የፍፃሜ ውድድሮች አድርጎ፣ ሦስት ወርቅና ሦስት የብር ሜዳልያ በድምሩ ስድስት ሜዳልያዎችን በማሳካት ከዓለም አሜሪካን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ከአትሌቶች ምርጫ አንስቶ በርካታ ትችቶች ሲያጋጥመው የከረመው ብሔራዊ ቡድኑ፣ ቀሪ የፍፃሜ ውድድሮች እየቀሩት በጠዋቱ ድል ተጎናፅፎ ለበርካቶች የደስታ ምንጭ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

የለተሰንበት ግደይ የ10,000 ሜትር ድል

የዓለም 5,000 ሜትር፣ 10,000 ሜትር፣ የዓለም 15 ኪሎ ሜትር ምርጥ ሰዓት ባለቤት እንዲሁም ግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤቷ ለተሰንበት ግደይ በኦሪገን 10,000 ሜትር የምታደርገው ውድድር ይጠበቅ ነበር፡፡ አትሌቷ በመም እንዲሁም በጎዳና ላይ ሩጫ ላይ የማትበገር መሆኗን ብታስመሰክርም፣ በዓለም ሻምፒዮናው የቀራት የቤት ሥራ ነበር፡፡ ለተሰንበት በቶኪዮ ኦሊምፒክ 10,000 ሜትር የማሸነፍ ግምት ቢሰጣትም፣ በትውልድ ኢትዮጵያዊት በሆነችው በኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሰን መረታቷ ይታወሳል፡፡

ሁለቱ አትሌቶች ከ2019 የኳታር ዓለም ሻምፒዮና ጀምሮ በተለያዩ ሻምፒዮናዎች ላይ መገናኘት ቢችሉም፣ ለተሰነበት ባለችበት ሲፋን እየተገኘች ፈተና ሆና መቆየቷ፣ የኦሪገኑንም 10,000 ሜትር ወርቅ ሲፋን እንደምትወስደው ሲገመት ሰንብቷል፡፡

በርቀቱ ከሲፋን ባሻገር በዓለም ሻምፒዮና 5,000 ሜትር አይበገሬ የሆነችው ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ ሌላዋ ተጠባቂ አትሌት ነበረች፡፡ ምንም እንኳ አትሌቷ በ10,000 ሜትር የመጀመርያ ተሳትፎ ያደረገች ቢሆንም፣ ለለተሰንበት ፈታኝ መሆኗ እንደማይቀር ሲገመት ነበር፡፡

በኦሪገኑ ሴቶች 10,000 ሜትር ፍፃሜ፣ ከፍተኛ ፉክክር በታየበትና ትንቅንቅ በነበረው ውድድር ለተሰንበት ግደይ 30፡09.94 በመግባት የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ ማስገኘት ችላለች፡፡ ለለተሰንበት ገድል የሌላዋ ኢትዮጵያዊት እጅጋየሁ ታዬ የቡድን ሥራ የጎላ ሲሆን፣ የቀድሞ የኢትዮጵያውያንን የቡድን ሥራ ያስታወስ ነበር፡፡

ለተሰንበት ከኬንያውያን አትሌቶች ጋር ተናንቃ የገባችበት ሁኔታ፣ እ.ኤ.አ. 2000 በሲድኒ ኦሊምፒክ ኃይሌ ገብረሥላሴ ከፖል ቴርጋት ጋር ያደረገውን ትንቅንቅና የኢትዮጵያውያንን አይበገሬነትን ያወሳ ሆኖ አልፏል፡፡ በሻምፒዮናው በሁለት ርቀቶች የምትሳተፈው ለተሰንበት በ5,000 ሜትር ማጣሪያውን ማለፍ ከቻለች እ.ኤ.አ. 2005 በሄልሲንኪ ዓለም ሻምፒዮና በ10,000 እና 5,000 ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያ ማሳካት የቻለችውን ጥሩነሽ ዲባባ ታሪክ ትደግማለች የሚል ግምት አግኝታለች፡፡

የዓለም ሻምፒዮና ሦስተኛው የማራቶን ወርቅ

ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና መሳተፍ ከጀመረችበት ከ1975 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 183) ጀምሮ ወንዶች ማራቶን ሁለት የወርቅ ሜዳልያ ብቻ ነበር ማሳካት የቻለችው፡፡ እ.ኤ.አ. 2001 በካናዳ ኤድመንተን ዓለም ሻምፒዮና በገዛኸኝ አበራና 2019 ዶሃ ዓለም ሻምፒዮና ሌሊሳ ዲሳሳ ሁለት የወርቅ ሜዳልያ ብቻ ነበራት፡፡

በ18ኛው ኦሪገን የዓለም ሻምፒዮና ታምራት ቶላ የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር ለኢትዮጵያ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ከማሳካቱም ባሻገር ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና ሦስተኛ ወርቅ እንዲኖራት አዲስ ታሪክ መጻፍ አስችሏል፡፡ ታምራት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ሞሰነት ገረመው ጋር እየታገዘ 2፡05፡36 በመግባት የወርቅ ሜዳልያውን አጥልቋል፡፡ አትሌቱ 2016 ሪዮ ኦሊምፒክ 10,000 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ፣ እ.ኤ.አ. 2017 በለንደን ዓለም ሻምፒዮና ማራቶን የብር ሜዳልያን ማጥለቁ ይታወሳል፡፡

ሌላው ኢትዮጵያዊ ሞሰነት ገረመው 2፡06፡44 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ፣ ከሦስት ዓመት በፊት በዶሃ ያገኘውን የብር ሜዳልያ ደግሞታል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሰይፉ ቱራ በ2፡07፡17 በሆነ ጊዜ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡ ከ60 በላይ አገሮች በተሳተፉበት በዚህ ውድድር ከፍተኛ ፉክክር የታየበት በመሆኑ በርካታ አትሌቶች በተቀራረበ ጊዜ ማጠናቀቃቸው ተስተውሏል፡፡

ጎተይቶም ማራቶን ወርቅ

ኢትዮጵያ ሦስተኛው የወርቅ ሜዳልያ ስታሳካ የኢትዮጵያውያን ደስታ ልክ አልነበረውም፡፡ በኦሪጎን የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ በዕንባ ከታጀበ ደስታ ባሻገር፣ በዓለም የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ደስታው ወደር አልነበረውም፡፡ በጎተይቶም ገብረ ሥላሴ፣ አባበል የሻነህና አሸቴ በከሬ የተወከለችው ኢትዮጵያ በጎተይቶም ሦስተኛው የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ አስገኝታለች፡፡

ጎተይቶም 41 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ከኬንያዊቷ ጄፕቱም ኮሪር ጋር ተናንቃ ከሮጠች በኋላ፣ አፈትልካ በመውጣት 2፡18፡11 በመግባት በበላይነት አጠናቃ ድሉን ጨብጣለች፡፡ የገባችበት ሰዓትም እ.ኤ.አ. በ2005 ሄልሲንኪ ላይ ፓውላ ራድክሊፍ ይዛው የነበረውን 2፡20፡57 ክብረ ወሰንን ማሻሻል ችላለች፡፡

እ.ኤ.አ. በ2021 የበርሊን ማራቶን ለመጀመርያ ጊዜ ተካፍላ 2፡20፡09 በማጠናቀቅ የምንጊዜም ምርጥ ስምንተኛ ሰዓት ማስመዝገብ የቻለችው ጎተይቶም፣ በቶኪዮ ማራቶን 2፡18፡18 በመግባት ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት ሁለተኛዋ ማራቶን ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና ማራቶን ወርቅ ያሳካችው በ2015 የቤጂንግ የዓለም ሻምፒዮና በማሬ ዲባባ ነበር፡፡

በርቀቱ በአጭር ጊዜ ስኬታማ መሆን የቻለችው አትሌቷ፣ በቀጣይ ለሚደረጉ ሻምፒዮናዎች ተስፋ የተሰነቀባት አትሌትም ሆናለች፡፡ ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ አስተያየቷን የሰጠችው አትሌቷ በማዕከላዊ መንግሥትና በትግራይ ክልል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከዓመት በፊት መንገድ ክፍት ሲደረግ መውጣቷን ገልጻ፣ ሌሎች ኢትዮጵያውያን የተደሰቱትን ደስታ የእሷም ቤተሰቦች ደስታውን ይጋሩ ዘንድ በአገሪቱ ሰላም እንዲወርድ ምኞቷ እንደሆነ አስረድታለች፡፡

ማክሰኞ ሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ንጋት ላይ በተደረጉ የወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክልና የሴቶች 1,500 ፍፃሜ ሁለት የብር ሜዳልያዎች ተገኝተዋል፡፡ በወንዶች ለሜቻ ግርማ በ3,000 ሜትር መሰናክል የብር ሜዳልያ ሲያገኝ፣ በሴቶች 1,500 ሜትር ጉዳፍ ፀጋይ እንዲሁ የብር ሜዳልያን አግኝታለች፡፡

ሁለቱም አትሌቶች የወርቅ ሜዳልያ የማሳካት ቅድመ ግምት ያገኙ ቢሆንም፣ በ3,000 ሜትር መሰናክል በሞሮኳዊው ሶፊያኒ ኤል ባካሊና በ1,500 ሜትር በኬንያዋ አትሌት ፌይዝ ኪፕዬጎን የበላይነት ተጠናቋል፡፡ በቀሪዎቹ ቀናት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በ800 ሜትር፣ 5,000 ሜትር በሁለቱም ፆታ ማጣሪያ ሲያደርግ በ3,000 ሜትር ሴቶች መሰናክል ፍፃሜ ያደርጋል፡፡

በ5,000 ሜትር ፍፃሜ በወንዶች ሰለሞን ባረጋና በሴቶች ለተሰንበት ግደይ እንዲሁም ጉዳፍ ፀጋይ ይጠበቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -