መወድስ ለባለድል አትሌቶች
በኦሪገን (አሜሪካ) እየተካሄደ ባለው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ እስከ ማክሰኞ ሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ባገኘቻቸው ሦስት ሦስት ወርቅና ብር ሜዳሊያዎች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ድላቸውን አስመልክቶ በየድላቸው ቀን በዳኒ ገብረመድኅን የቀረቡት ግጥሞች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ለሴቶች 10 ሺሕ
የሞት ሽረት ትግል በሰተመጨረሻ
ይህች ባንዲራ ናት ዕድለኛ
ምን በሐዘን ቢዳምን የሀገሬ ሰማይ
አንዳንዴ ይፈካል በእናንተ ውብ ብቃይ
***
ለወንዶች ማራቶን
እንኳን ደስ አለን
ምን ሐዘን በርክቶ ~ ለዕንባ ብንቀርብም
ሀገር አቀርቅራ ~ ከፍቷት ብታዘግምም
ሳቋ ግን ለሁሌው ~ መቼውም አይከስምም
እንዲህ ጀግኖች አሏት ~ የትም ቢሆን የትም
ስሟን ከከፍታው ~ ከወርቁ ዙፋን ላይ
ለዓለም የሚያሳዩ ~ በአለሙ በአደባባይ
ለሴቶች ማራቶን
እግር በግር ብላ ሆና እንደ ጥላ
እስከ መግቢያው ድረስ አጅባት ከኋላ
እለፊም ብትላት ተይ አይሆንም ብላ
ከመግቢያ ስትደርስ
አሁን ይበቃሻል እይው የእኔን ጀርባ
እኔ ሳየው ቆየሁ የአንቺን በእጀባ
አሁን ተረኛ ነሽ ወጣሁ ከፊት ፊትሽ
ኋላዬን ተከተይ ሌላ እንዳይመጣብሽ
ወርቁ የእኔ ሆኗል ብሩ እንዳያመልጥሽ
ለ1,500 እና 3,000 መሰናክል
ደሞ እንደገና ሌላ የድል ዜና
ከኦሪጎን ሰማይ ከምድሩ ጎዳና
ወርቅ የሆኑት ልጆች ብሩን ዘገኑና
ይኸው ለእምዬ አሏት እንደገና
ሀገሬ ከፍ አለች እንደ አምና ትናንቱ
በሙላት ጉድለት ውስጥ ሁሌ የሚበረቱ
ስለ ክብራ ሲሉ ገጥመው የሚረቱ
ልጆች አሏት ሁሌም ከፊት የሚታዩ
በረገጡት መድረክ በየአደባባዩ
****
ኢትዮጵያ ~ ደራርቱ
እናት ልጇን ከምታይበት የስስት እይታ በምን ይለያል ?! . . . መልካምነት በምስል ቢገለጽ ከዚህ ምስል በላይ የሚገልጸው የለም፡፡ በዚህ ዕይታ ውስጥ ፍቅር እዝነት እርካታ ስስት የኔነት ውዴታ ጥልቅ ስሜት . . . ምን የሌለ ፊሊንግ [ስሜት] አለ?!
- ሰይዶ ጀማል በቡክ ፎር ኦል
***
ውብ ቀለም
የዜግነት ቀለም
በሰው ፊት ላይ ቢሣል፣
ሀገር ከነወዙ
ደራርቱን ይመስላል፡፡
- ኢዛና መስፍን