Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የጎዳና ሕይወትን ለመከላከል የአንበሳውን ድርሻ መያዝ ያለበት ማነው?

ማስተር ኤርሚያስ ገሠሠ የጳጉሜን አምስት ግብረ ሠናይ ድርጅት መሥራች ሥራ አስኪያጅና የማርሻል አርት አሠልጣኝ ናቸው፡፡ የግብረ ሠናይ ድርጅታቸውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የጳጉሜ አምስት ግብረ ሰናይ ድርጅት አመሠራረት፣ የትኩረት አቅጣጫና ዓላማ ምንድነው?

ማስተር ኤርሚያስ፡- ድርጅቱ የተቋቋመው በ1995 ዓ.ም. ሲሆን፣ ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካላት ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ሥራውን ማስፋፋት የጀመረው በ2011 ዓ.ም. ነው፡፡ ዓላማውም በተለያዩ ምክንያት ኑሯቸውን ጎዳና ላይ የመሠረቱትን ወገኖች ከሚኖሩበት የጎዳና ሕይወት ማንሳት፣ ወደየቤተሰቦቻቸው ተመልሰው እንዲቀላቀሉ፣ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ከሱስ እንዲላቀቁና ከተረጂነት ተላቀው ወደ ረጂነት እንዲሸጋገሩ ማድረግ ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርገው የሥራ ክቡርነትን በማስረዳት፣ የሥነ ልቦና ሥልጠና በመስጠት፣ የማረፊያ ቦታ በማዘጋጀት፣ ትምህርት እንዲማሩ በማድረግ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያዘወትሩ በማድረግና ማዕድ በማጋራት ነው፡፡ ድርጅቱ በይፋ መንቀሳቀስ ከጀመረበት አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በጎዳና ሕይወት ውስጥ የነበሩ ወደ 1,000 የሚጠጉ ወገኖችን ከዚህ አስከፊ ሕይወት እንዲላቀቁ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ከጎዳና ሕይወት የተላቀቁት ወገኖች በአሁኑ ጊዜ የት እንደሚገኙና በምን ዓይነት ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ሊገልጹልን ይችላሉ?

ማስተር ኤርሚያስ፡-  ወደ  200 የሚጠጉ የጎዳና ተዳዳሪ የነበሩ ወገኖች በአሁኑ ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እየረዱ ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸውም የሚገኙት አዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች ሲሆን፣ የመቀላቀሉም ሥራ የተከናወነው በቅድሚያ በፍላጎታቸውና ከዚያም በቤተሰቦች ስምምነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አዲስ አበባ የሚገኙ ቤተሰቦች ቅልቅሉን የተቀበሉት በቅድሚያ አንድ አማካይ በሆነ ሥፍራ ተሰባስበው የቡና ማፍላት ሥነ ሥርዓት ተከናውኖ ዕርቅ ከወረደ በኋላ ነው፡፡ በየክልሉ ከሚኖሩት ቤተሰቦች ደግሞ ስምምነት ላይ ሊደረስ የተቻለው በስልክ ግንኙነት በመፍጠር ነው፡፡ ሁሉም ወገኖች ወደየቤተሰቦቻቸው የተሰማሩ ለቤተሰቦቻቸው እጅ መንሻ የሚሆን አልባሳት፣ ጥሬ ቡና፣ ስኳር፣ ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ሸቀጣ ሸቀጦችን በፌስታል ቋጥረው በመያዝ ነው፡፡ ለዚህም የሚያስፈልገውን ወጪና በተለይም ወደ ክልል ለተንቀሳቀሱ ልጆች የትራንስፖርት ወጪያቸውን የሸፈነው ጳጉሜን አምስት ግብር ሠናይ ድርጅታችን ነው፡፡ ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተስፋፋበት ጊዜ ስለነበር፣ በትራንስፖርት ሁለት ሰዎች በሚጠቀሙበት መቀመጫ ላይ አንድ ሰው ብቻ እንዲቀመጥና የባዶውን ወንበር ጨምሮ የራሱንም እንዲከፍል መድረጉም አይዘነጋም፡፡ በዚህም ዓይነት የሒሳብ ሥሌት መሠረት ለአንድ ሰው እስከ 1,400 ብር ድረስ ድርጅቱ ከፍሏል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀሩት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ነው ያሉት?

ማስተር ኤርሚያስ፡- ወደ 30 የሚጠጉ ወገኖች ቤት ተከራይተዋል፡፡ የቀሩት ግን ያመቸናል ብለው በመረጡ ቦታ ኑሯቸውን ተያይዘውታል፡፡

ሪፖርተር፡- ቤት ተከራይተው የሚኖሩ፣ ከቤተሰቦቸው ጋር የተቀላቀሉና በመረጡት ቦታ እየኖሩ ያሉ በምን ዓይነት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል?

ማስተር ኤርሚያስ፡- ቤት ተከራተው የሚኖሩት ወገኖች በኮንስትራክሽንና በመኪና እጥበት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በኮንስትራክሽን ላይ ከተሰማሩትም መካከል አንዳንዶቹ ከረዳትነት ወደ ሙሉ ባለሙያነት ተሸጋግረዋል፡፡ ይህም ማለት የአናፂ ረዳት የነበረው ራሱን ችሎና ሙሉ አናፂ ሆኖ መሥራት ጀምሯል፡፡ ቤት ኪራዩን የሚከፍሉት ራሳቸው ሲሆኑ፣ ድርጅቱ ደግሞ አልፎ አልፎ አስቤዛ ያቀርብላቸዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያት ቤት ኪራይ መክፈል ሲሳናቸው ድርጅቱ ይሸፍንላቸዋል፡፡ ከመሸፈኑ በፊት ግን ገንዘብ ሲያገኙ የሚመልሱለት መሆኑን ቃል ያስገባቸዋል፡፡ በገቡትም ቃለል መሠረት ገንዘቡን ይመልሱለታል፡፡ ድርጅቱም የተመለሰለትን ገንዘብ ለራሱ ሳያውለው በስማቸው የባንክ ሒሳብ ያስከፍትና ገቢ ያደርግላቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ የድጋፍ ፈላጊ ወይም የተረጂነት ስሜት እንዳያድርባቸው ያደርጋል የሚል ድርጅቱ የፀና እምነት አለው፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተቀላቀሉም ልጆች ከጫማ ማፅዳትና ከማስቲካና ከረሜላ ማዞር ጀምሮ ባሉት ጥቃቅን ሥራዎች እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ወይም መነሻ የሚሆናቸውን ገንዘብ ለማግኘት የየወረዳዎቹ ሕፃናትና ለሴቶች ቢሮ በየአካባቢያቸው ያሉትን ባለሀብቶች እንዲያስተባብሩላቸው ስምምነት ተደርጓል፡፡ ባመቻቸው ቦታ ሆነው በተለያዩ የሥራ መስክ ተሰማርተው ከድህነት አረንቋ ለመላቀቅ ደፋ ቀና ለሚሉት ደግሞ ድርጅቱ የአስቤዛ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡    

ሪፖርተር፡- የማዕድ ማጋራቱ የሚደረገው ሁልጊዜ ነው? ወይስ በታላላቅ መንፈሳዊ በዓላት ወቅት?

ማስተር ኤርሚያስ፡- የማዕድ ማጋረቱ ተግባር የሚከናወነው በክርስትናና በእስልምና እምነቶች ዘንድ ተከብረው በሚውሉ የመንፈሳዊ በዓላት ጊዜያት ነው፡፡ ይህንንም የምናደርግበት ምክንያት ብቸኝነት እንዳይሰማቸው ለማድረግና ምን ጊዜም ከጎናቸው የምንቆም መሆኑን እንድንገልጽላቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ለሚያንቀሳቅሰው ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ከየት ነው የሚያገኘው? ሰብዓዊ ድጋፉስ ቀጣይነት አለው?

ማስተር ኤርሚያስ፡- ድርጅቱ እያበረከተ ላለው ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ የሚያገኘው ከአባላት መዋጮና ከአንዳንድ የድርጅቱ ደጋፊ በጎ አድራጊ ግለሰቦች ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የቴአትርና የሥነ ጽሑፍ ምሽት በማዘጋጀት፣ እንዲሁም ከመንግሥት ጋር በመተባበር አማካይ በሆነ ሥፍራ ድንኳን እየተከለ የድርጅቱን ሥራ በማስተዋወቅ የሚያገኘውን መጠነኛ ገቢ ለዚሁ አገልግሎት እንዲውል እያደረገ ይገኛል፡፡ በቀጣይ ግን ሥራውን በእጥፍ ለማሳደግ አቅዶ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ለዚህም የሚውል ቦታ እንዲሰጠው ጉዳዩ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ጥያቄ አቅርቦ መልሱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ ጥያቄውም አዎንታዊ ምላሽ ያገኛል የሚል ተስፋ አሳድሮበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የጎዳና ሕይወትን ለማስቀረት ከመንግሥትና ከማኅበረሰቡ ምን ይጠበቃል ይላሉ?

ማስተር ኤርሚያስ፡- በጎዳና ሕይወት ውስጥ ያሉ ወገኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ አብዛኛዎቹም ከተለያዩ ክልሎች የፈለሱ ናቸው፡፡ ስለሆነም ይህ ዓይነቱን አስከፊ የጎዳና ሕይወት በመከላከሉ ሥራ ላይ የአንበሳውን ድርሻ መያዝ ያለበት መንግሥት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተለይም የየክልሉ ርዕሰ መስተዳድሮች ችግረኛ ልጆችን በከተማ ግብርና፣ በዶሮ ዕርባታ፣ በከብት ማደለብና በሌሎችም ጥቃቅን ሥራዎች በማሰማራት ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህም የአንድ ሰሞን ሥራ ሳይሆን ቀጣይነት ወይም ዘለቄታዊ ያለው አካሄድ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህም የሚሆነው ትምህርታቸውን በማይነካና የረጂነትን መንፈስ በማያበረታታ መልኩ ነው፡፡ ለማኅበረሰቡ በሥነ ተዋልዶ ጤናና በቤተሰብ ዕቅድ ላይ ትኩረት ያደረገ ትምህርት በየጊዜው እንደሚጠው ሁሉ፣ የጎዳና ሕይወትን አስከፊነት የሚገልጽና ወገኖችን ከጎዳና ሕይወት የሚታደግ ትምህርት በየቤቱ፣ በየእምነት ተቋማትና በትምህርት ቤቶች መስጠት ይኖርበታል፡፡ ማኅበረሰቡም የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ መልኩ መንቀሳቀስ ከተቻለ የፍልሰቱን መጠንም መቀነስ ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡     

ሪፖርተር፡- እርስዎ በዚህ ዓይነቱ ሰብዓዊ ሥራ ላይ ለመሰማራት ያነሳሳዎት ምንድነው?

ማስተር ኤርሚያስ፡- ያነሳሱኝ ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛው የጎዳና ሕይወት እየተበራከተ መምጣቱ ሲሆን፣ ይህም እንደ አገር የሚያሳስብ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው የማርሻል አርት አሠልጣኝ/አስተማሪ መሆኔ ነው፡፡ በተለይ የማሠልጠኑ ሥራ በውስጡ ብዙ ሰዎችን ያሰባስባል፡፡ ይህ የተሰባሰበው ኃይል ደግሞ ለአገርና ለዜጋ የሚጠቅም ሥራ ለምን አይሠራም? የሚል ጥያቄ በውስጤ ሠረፀ፡፡ ከማርሻል አርት ትምህርት ውስጥ አንዱና ዋናው ደግሞ ሥነ ምግባር ነው፡፡ የሥነ ምግባር ትምህርትም በተግባር መታየትና መሠራት ይኖርበታል፡፡ ከእነዚህ ሁለት ነገሮች በመነሳት፣ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች በማሰባሰብና በማደራጀት ኢትዮጵያን ካጋጠሟት በርካታ ችግሮች መካከል ቢያንስ አንዱና አነስተኛውን ለማቃለል እየጣርኩ እገኛለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከጎዳና ሕወት ካነሳችኋቸው መካከል በማርሻል አርት ሠልጥነው ለቁም ነገር የደረሱ አሉ?

ማስተር ኤርሚያስ፡- በሥልጠናው የሚሳተፉ ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ሁለቱ ሥልጠናቸውን በብቃት አጠናቀው በመመረቅ፣ በአሁኑ ጊዜ አሠልጣኝ ለመሆን በቅተዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...