Tuesday, March 5, 2024

ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ዕጣ ከወጣባቸው የ20/80 እና 40/60 ጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊና ስምንት የሶፍትዌር ባለሙያዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠየቀባቸው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን የቢሮ ኃላፊውን ሙሉቀን ሀብቱ (ዶ/ር)፣ ሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. እና ሌሎቹን ስምንት ተጠርጣሪዎች ደግሞ ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቅርቧቸዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. የተካሄደው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ሒደት ጥቅም ላይ የዋለው ሲስተም፣ ዓለም አቀፍ የመልማት ስታንዳርዱን ያልጠበቀና የሚና መደበላለቅ የታየበት እንደነበር፣ ሙሉቀን (ዶ/ር) ሲስተሙ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረጋቸውን አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪው ቴክኖሎጂው በኢንፎርሜሽን መረብና ደኅንነት አገልግሎት (INSA) ተፈትሾ ችግር እንደሌለበት ማረጋገጫ የተሰጠበት ብለው የከተማ አስተዳደሩን ማሳሳታቸውንም አክሏል፡፡

ተጠርጣሪው ቴክኖሎጂውን ከልማቱ ጀምሮ እስከ ዕጣ አወጣጡ ድረስ የመከታተል ኃላፊነት እንደነበረባቸው ጠቁሞ፣ ተጠርጣሪው ግን የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ሕዝብና መንግሥትን በማጭበርበር፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲያጣና በተቀናጀ መልኩ ድርጊቱ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ከወንጀሉ ጋር ተያያዥ ጉዳዮችን ለመሥራትና ምርመራውን በሰውና በሰነድ ማስረጃ ለማረጋገጥ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ችሎቱን ጠይቋል። ተጠርጣሪው ሙሉቀን (ዶ/ር)፣ ለፍርድ ቤቱ ባሰሙት የመከራከሪያ ሐሳብ፣ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥደት የተከሰተው ችግር እሳቸውን የማይመለከትና ሊያስጠይቃቸውም እንደማይገባ ተናግረዋል። የማጭበርበር ወንጀል ተፈጽሞበታል የተባለው ሶፍትዌር ‹‹መልማት ከጀመረ በኋላ›› ወደ ሥራ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ በመልማት ላይ የነበረውን ቴክኖሎጂ በተመለከተም ለሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ለኢንሳ ደብዳቤ የጻፉ ቢሆኑም፣ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በታኅሳስ ወር ካገኙት ምክረ ሐሳብ ውጪ ከኢንሳ ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ‹‹ቴክኖሎጂው በኢንሳ የተረጋገጠ ነው፤›› ብለዋል በሚል በመርማሪ ፖሊስ የቀረበባቸውን ውንጀላ ትክክል አለመሆኑንም ተናግረዋል።

ሙሉቀን (ዶ/ር) የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣው ከወጣ በኋላ በተደረገው ኦዲት ላይ አለመሳተፋቸውን ጠቁመው፣ ተከሰተ የተባለው ችግር በሌላ ገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቀዋል። ‹‹እኛን ከብሔራችን ጋር በማያያዝ ለመወንጀል ነው የታሰበው፤›› ያሉት  ሙሉቀን (ዶ/ር) ከእሳቸው እስር ጀርባ ሌላ የተዘጋጀ ነገር አለ የሚል ግምት እንዳላቸው ለችሎቱ አስረድተዋል። ተጠርጣሪው በሁለት ጠበቆች የተወከሉ ሲሆን፣ ጠበቆቹም እንዳስረዱት፣ የደንበኛቸውን የዋስትና መብት እንዲያከብርላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው፣ ፖሊስ ያቀረበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሕግ መሠረት እንደሌለው በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ እንዲያደርገው ጠይቀዋል። ደንበኛቸው በዋስትና ቢወጡ በማስረጃ አሰባሰብ ላይ ሊፈጥሩት ስለሚችሉት እንቅፋት መርማሪ  ቡድን ያለው ነገር እንደሌለ ጠቁመው፣ በእስር ሊያቆያቸው የሚችል ሕጋዊ ምክንያት እንደሌለም ተከራክረዋል።

ሙሉቀን (ዶ/ር) ተጠርጣሪ ለመሆን ብቁ የሚያደርጋቸው ምክንያት እንዳልተጠቀሰ የተናገሩት ጠበቆቹ፣ ፖሊስ ያቀረበው የምርመራ ጊዜ መጠየቂያ በአሳማኝ ምክንያት ተደግፎ የቀረበ ስላልሆነ ውድቅ ተደርጎ ደንበኛቸው በዋስትና እንዲወጡ ችሎቱን ጠይቀዋል።

መርማሪ ቡድኑ፣  ከሲስተሙ ፈጠራ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ድረስ ለተሠራው አሻጥር የተጠርጣሪው እጅ እንዳለበትና ተጠርጣሪው ማስረጃ ለማጥፋት አቅም እንዳላቸው ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል። ፖሊስ ‹‹ምርመራው ጅምር ስለሆነ መስመር እስከሚይዝ ድረስ የዋስትና መብታቸው ታልፎ፣ የጠየቀው የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ፣ የዋስትና ጥያቄውን ባለመቀበል ቀርቷል። መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ለሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በወጣው ጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ላይ ‹‹172 ሺሕ ግለሰቦችን ያላግባብ እንዲካተቱ አድርገዋል፤›› ተብለው የተጠረጠሩት ስምንት  የሶፍትዌር ባለሙያዎችና ኃላፊዎችም ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸወል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መርማሪ ቡድን ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ በኮንዶሚኒየም ዕጣ አወጣጥ ላይ ያልተመዘገቡና ያልቆጠቡ ግለሰቦችን በማካተት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማስገኘት በማሰብና ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ፣ 172 ሺሕ ግለሰቦችን ስም በዳታ ቤዝ እንዲካተቱ ማድረጋቸውን አስረድቷል፡፡ 79 ሺሕ በተገቢው መንገድ የቆጠቡ ግለሰቦች በዕጣው መካተታቸውን ከባንክ መረጃ የቀረበ ሲሆን፣ 172 ሺሕ የሚሆኑት ግን ያልቆጠቡና ያልተመዘገቡ ግለሰቦች መሆናቸው ከባንክ ከቀረበው ሲስተም መረጋገጡን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

‹‹ሒሳባቸውን የዘጉና የወጡ ግለሰቦች ሁሉ እንዲገቡ ተደርጓል፤›› ያለው መርማሪ ፖሊስ፣ በተለይም የ2005 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎችን ወደ 1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች በማስገባት ጭምር ዕጣው እንዲሰረዝና ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስ መደረጉን አብራርቷል።

በተጨማሪም የለማው ሶፍትዌር ከሰው ንክኪ የፀዳ እንዳልነበር አስረድቷል፡፡ ተጨማሪ የምርመራ ለመሥራት፣ ማስረጃ ለመሰብሰብና የምስክር ቃል ለመቀበል ተጨማሪ የ14 ቀናት እንዲሰጠው በጠየቀው መሠረት ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ የጠየቁትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጎ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ በመፍቀድ ለሐምሌ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል ፈቅዷል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -